Tuesday, 19 March 2019 00:00

በከፍተኛ ሁኔታ የተበከሉ የአለማችን ከተሞች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በአለማችን  በከፍተኛ ሁኔታ የብክለት ተጠቂ የሆኑ ከተሞች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ክፉኛ ከተጠቁ ቀዳሚዎቹ 30 የአለማችን ከተሞች መካከል 22ቱ በህንድ እንደሚገኙ ለማወቅ መቻሉን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ግሪንፒስና አይኪውኤር ኤርቪዡዋል የተባሉት ሁለት ተቋማት በአለማችን የተለያዩ አገራት ከተሞች ውስጥ በፈረንጆች አመት 2018 የአየር ጥራትን በመገምገም ያወጡትን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በከፍተኛ ሁኔታ በመበከል ከአለማችን ከተሞች በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠቺው የህንዷ ጉሩግራም ናት፡፡ ሌላዋ የህንድ ከተማ ጋዚያባድ በአየር ብክለት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ የፓኪስታኗ ፋይዛላባድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። የህንዶቹ ፋሪዳባድ፣ ባይዋዲ፣ ኖኢዳ እና ሆታና ከተሞች በቅደም ተከተላቸው እስከ ሰባተኛ ሲይዙ፤ የቻይናዋ ሆታን 8ኛ፣ የህንዷ ሉክኖው 9ኛ፣ የፓኪስታኗ ላሆር 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ተቋማቱ ባወጡት ሪፖርት እንዳሉት፤ ጥናቱ ከተሰራባቸው 3 ሺህ የአለማችን ከተሞች መካከል 64 በመቶ ያህሉ ለተለያዩ የጤና ችግሮች በሚያጋልጥ የአየር ብክለት ተጠቂ መሆናቸው ተረጋግጧል። 99 በመቶ የደቡብ እስያ አገራት እንዲሁም በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሁሉም አገራት የአለም የጤና ድርጅት ካስቀመጠው አማካይ የአየር ብክለት መጠን በላይ እንዳላቸውም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ሲኤንኤን በበኩሉ፤ የአየር ንብረት በመጪው አመት ሰባት ሚሊዮን ያህል ሰዎች ያለወቅቱ እንዲሞቱ ሰበብ ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት ዘግቧል፡፡

Read 2440 times