Sunday, 17 March 2019 00:00

ቃለ ምልልስ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በአዲስ አበባ ውዝግብ ላይ ይናገራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

አዲስ አበባ ለምን እንዲህ አወዛጋቢ ሆነች? በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው የኦሮሚያ የልዩ ጥቅም ጉዳይ ለምን ተደነገገ? አዲስ አበባ ለምን የኦሮሚያ ርዕሰ ከተማ ሆነች? በመዲናዋ ላይ የተፈጠረው ውዝግብ እንዴት ሊፈታ ይችላል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ህገ መንግስቱ በ1986/87 ሲረቀቅ፣
ከ29ኙ የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚቴ አባላት አንዱ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

           አዲስ አበባ ለምን እንዲህ አወዛጋቢ ሆነች?
ማንም ይሁን ማንም ስለ አዲስ አበባ ጉዳይ ሲያነሳ፣ ህገ መንግስቱ ላይ ያሉትን ድንጋጌዎች ማስተዋል አለበት፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉት እስካልተቀየረ ድረስ አዲስ አበባ በተቀመጠው መሰረት ነው የምትታየው ማለት ነው፡፡ በህገ መንግስቱ የተቀመጠው ደግሞ የባለቤትነት ጉዳይ ሳይሆን አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት (መሃል) የምትገኝ እንደመሆኗ፣ ኦሮሚያና አዲስ አበባ የሚገናኙበት ብዙ ጉዳይ አለ፡፡ የፀጥታ፣ የማህበራዊ፣ የተፈጥሮ ሃብት ጉዳይ የመሳሰሉት ማለት ነው።  ይሄን በተመለከተ ሁለቱ አካላት የአዲስ አበባ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ተመካክረው መስራት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡ አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሃል የምትገኝ እንደ መሆኗም፣ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል ብለን ነው በወቅቱ በህገ መንግስቱ ያስቀመጥነው፡፡ አሁን በኦሮሞዎች በኩል ይሄ ድንጋጌ አይሆንም፤ ባለቤትነታችን ይረጋገጥልን ካሉ፣ የለም የሁላችንም የኢትዮጵያውያን ናት፤ አዲስ አበባ የአማራ ነበረች የሚሉም ወገኖች አሉ። እነዚህ ሁለቱ አካሄዶች አሁን በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን የሚፃረሩ ናቸው፡፡ ምናልባት በህገ መንግስቱ የተቀመጠው የአዲስ አበባ ጉዳይ ይለወጥ ከሆነ፣ እሱ ራሱን የቻለ አካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በሁለቱም ወገኖች የሚነሳው ነገር ከህገ መንግስቱ ውጪ ነው፡፡ የባለቤትነት ጉዳይን የሚያነሱ ከሆነ፣ መጀመሪያ ህገ መንግስቱ ይሻሻልልን ነው ማለት ያለባቸው፡፡ በሌላ በኩል፣ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች፤ አዲስ አበባ፡፡
ይህም ቢሆን በህገ መንግስቱ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች የሚል አልተቀመጠም፡፡ እንዴት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች ማለት ይቻላል? በየትኛው ህግስ ነው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማነት የተረጋገጠው?
የኦሮሚያ ዋና ከተማ የመሆኗ ጉዳይ ከታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም የሃገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ከመፍታትና ከኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እኛ ያስቀመጥነው አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ነች ብለን ነበር፡፡ ኦሮሚያ ደግሞ ከታሪክ፣ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ አንፃር ነው ዋና ከተማ የሆነችው፡፡ ከታሪክ አንፃር አፄ ምኒልክ አዲስ አበባ ላይ ሲከትሙ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ወደ ባሌ፣ አርሲ በግድ የሄዱ ኦሮሞዎች አሉ፡፡ ይሄ ጉዳይ ደግሞ የአብዛኛው የኦሮሞ ፖለቲከኞች የትግል ማጠንጠኛ ነው፡፡ አካባቢው የኦሮሞዎች ሃገር ነበር። ከዚህ አኳያ እና አዲስ አበባ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧም በኦሮሚያ መሃል (እምብርት) የምትገኝ በመሆኗ፣ ዋና ከተማ ማድረጉ ተመራጭ ሆኗል፡፡ በመሰረቱ የፌደራል መንግስቱም፣ የኦሮሚያ ክልል መስተዳደርም አዲስ አበባን ዋና ከተማቸው ማድረጋቸው ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡
የባለቤትነት ጥያቄው የሚነሳውና ጉዳዩን ያልጠራ የሚያደርገው የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማውን አዲስ አበባ በማድረጉ ነው የሚል ክርክር ይነሳል---
ይሄ እውነታን መካድ ነው፡፡ አፄ ምኒልክ ይሄን አካባቢ ወርረው ነው የያዙት፡፡ አስተዳደራዊ መዋቅራቸውን አፄ ምኒልክ ሲያቋቁሙ፣ ከየአካባቢው ይዘዋቸው የመጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ አብረዋቸው የመጡት እዚህ ያሉ ሰዎች፣ አሁን የሰብአዊ መብታቸውንና የዜግነት መብታቸውን ተጠብቆ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመኖር መብታቸውን መጠበቅ ነው የሚያስፈልገው እንጂ ወደ ባለቤትነት ጥያቄ ከተመጣ ከ150 ዓመት በፊት አካባቢው የኦሮሞዎች ሃገር ነው፡፡ ይሄ በቂ የታሪክ ማስረጃ ያለው ነው፡፡ ያን ያህል አነታራኪ አይደለም። ዋናው የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ዋና ከተማ ነች የሚለውን መያዝና በዚህ መልኩ መሄድ ነው የሚሻለው፡፡ የታሪክ ባለቤትነት ጥያቄ ውስጥ ከተገባ፣ ክርክሩ የታሪክ ማስረጃ ነው የሚሆነው፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሞዎች ሃገር ነበረች፡፡ አሁን ሌላው ባለቤት አይደለም ማለትም ሆነ የኦሮሞ አይደለችም ማለት ተገቢ ክርክር አይሆንም፡፡ ትልቅ ስህተት ያመጣው የኦሮሚያ ዋና ከተማ ማነው የሚለው በግልፅ በህግ አለመደንገጉ ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት ተብሎ የተወሰነ ይመስለኛል፡፡ በኋላ እነ አባዱላ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በነበሩ ጊዜ፣ የክልሉን ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ አድርገዋል፡፡ ይሄ ባይሆን ዛሬ ያን ያህል ውዝግብ ባልተፈጠረ ነበር፤ ዋናው ይሄን ሁሉ ብጥብጥ ያመጣው ግን ህገ መንግስቱ ከወጣ 24 ዓመት ቢሆነውም፣ ስለ አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ግንኙነት በሚደነግገው አንቀፅ 49 ንኡስ አንቀፅ 5 መሰረት፣ የልዩ ጥቅሙ ጉዳይ እስከ ዛሬ በዝርዝር አለመብራራቱ ነው፡፡ እሱ በወቅቱ ጣጣውን ጨርሶ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የሚፈጠረው ውዝግብ ያን ያህል በሆነ ነበር፡፡
በወቅቱ “የልዩ ጥቅም” ጉዳይ በህገ መንግስቱ የተካተተው ምንን ታሳቢ በማድረግ ነበር?
ልዩ ጥቅም የሚለው ጉዳይ የመጣው፣ ኦሮሞዎች በአዲስ አበባ ላይ ያነሱትን ታሪካዊ ጥያቄ በማሰብ ነበር፡፡ የፌደራሉ መንግስት መቀመጫ እንድትሆን የተመረጠችው አዲስ አበባ ይሄ ጥያቄ ያለባት ነበረች፡፡ የፌደራሉ መንግስት መቀመጫ እንዲሆን የተመረጠው መሬት፣ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጣ መሬት ወይም ግዛት አይደለም፡፡ የኦሮሞዎች መሬት ነው፡፡ ታሪካዊ ጥያቄ የሚነሳበት መሬት ነው፡፡ በኦሮሞዎች ሃገር ላይ ነው የፌዴሬሽኑ መቀመጫ ሊከትም የተወሰነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኦሮሞዎች ከተማውን ለፌዴሬሽኑ ዋና ከተማነት ሲሰጡ የከፈሉትን ዋጋ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ኦሮሞዎችም እንደ ማንኛውም ዜጋ በከተማዋ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን የባለቤትነት ጥያቄ አያነሱም፡፡ በዚያው ልክ አዲስ አበባንና ኦሮሚያን የሚያገናኝ በርካታ ማህበራዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ቆሻሻ የሚራገፈው በኦሮሚያ ውስጥ ነው፤ አዲስ አበባ የምትገነባው በአቅራቢያዋ ካለው የኦሮሚያ መሬት በሚመጣ የድንጋይና የተለያዩ የግንባታ ቁሳቁስ ነው፡፡ ስለዚህ የሁሉም የሆነችው አዲስ አበባ፣ የኦሮሚያን ሃብት ስትወስድ፣ በምትኩ ለኦሮሚያ መስጠት ያለባት ጥቅም አለ ከሚል እሳቤ ነው፣ ድንጋጌው የተካተተው፡፡
ከሌሎች አካባቢዎች  ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ጥሬ ዕቃ (ሀብት) አለ፡፡ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ሃይልን  ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህ አካባቢዎችም ልዩ ጥቅም ቢጠይቁ ያስኬዳል?
ይሄን መከራከሪያ እኔም ብዙ ጊዜ እሰማለሁ። ግን ብዙም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ አብዛኛው የአዲስ አበባ የመሰረተ ልማት ግብአት (አሸዋ፣ ጠጠር፣ ድንጋይ) የሚመጣው ከኦሮሚያ ነው እንጂ ከከተማዋ ከ4 መቶ እና 5 መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው ከሚገኙ አካባቢዎች አይደለም፡፡ የውሃ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችም ከኦሮሚያ ነው የሚመጣው፤ በአንፃሩ አዲስ አበባ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዋን የምታራግፈው በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም መታየት ያለበት፡፡
በወቅቱ እርስዎን ጨምሮ  29 አባላት በነበሩበት  የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ አንቀፅ በህገ መንግስቱ እንዲካተት ሃሳብ የቀረበው በማን በኩል ነው? በዋናነት የልዩ ጥቅምን ሃሳብ ያራምድ የነበረው ማን ነው?
ያኔ በህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ እኔና ዳዊት ዮሐንስ ብቻ ነን ከኢህአዴግ የነበርነው። የህውሓት ተወካይ አልነበረም፤ ኦነግ ከእነጭራሹ በሂደቱም አልነበረም፡፡ እነ አቶ ክፍሌ ወዳጆና ሌሎች ከሲቪክ ማህበራትና የተለያዩ አካላት የተወከሉ ናቸው በኮሚሽኑ የነበሩት፡፡ እኛና እነ አቶ ክፍሌ ስንወያይ፣ በዋናነት የብሔር ብሔረሰቦች መብት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይ በጣም የሞቀ ጉዳይ ነበር፤ እነ ኦነግም ይሄን ሃሳብ ይዘው እንገንጠል የሚል ሃሳብ ሲያራምዱ ስለነበር፣ ያንን ለማለዘብ ነው ሃሳቡ የመጣው፤ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባ ስናደርግ፣ በአዲስ አበባ ላይ የሚነሳውን የባለቤትነት ጉዳይ ለማለዘብና አዲስ አበባ የሃገሪቱ ዋና ከተማ እንድትሆን ለማድረግ የመጣ ሃሳብ ነው። ሃሳቡ በኛ መሃል ተነስቶ ውይይት አድርገንበት ነው በአብላጫ ድምፅ ያፀደቅነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሽግግር የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሲቀርብ፣ ህውሓትም ተጨምሮበት ነው፣ እኛ ያዘጋጀነውን ረቂቅ ያፀደቁት፡፡ ይሄ ም/ቤት ካፀደቀው በኋላ፣ 545 ሰዎች ከየወረዳዎች ተወክለው፣ ለ6 ሳምንት ተቀምጠን የተረቀቀውንና በሽግግር ም/ቤቱ የፀደቀው  ረቂቅ ላይ ስንወያይ ነበር፡፡ ከኦሮሚያ 177፣ ከአማራ 137፣ ከትግራይ 37፣ ከደቡብ 123 ተወካዮች፣ ቀሪዎቹ ከሌሎች አካባቢ የተውጣጡ ነበሩ፣ በዚህ ጉባኤ ውስጥ የተወከሉት፡፡ በወቅቱ ከኦሮሚያ ተወካዮች መካከል በውይይቱ ላይ “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ከማለት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች መባል አለበት” የሚሉ ነበሩ፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ሁሉም ውይይት ከተደረገ በኋላ አስታራቂ  ሃሳብ ሆኖ የተገኘው የልዩ ጥቅም ድንጋጌው ነው፡፡
በህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ የነበራችሁት ከየት ከየት የተወከላችሁ ነበራችሁ?
ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰባት፣ ከሰባቱ ውስጥ ኢህአዴግ የሆንነው እኔና ዳዊት ዮሐንስ ብቻ ነበርን። ከፓርላማው ውጪ 7 ሰዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ነበሩ፤ ቀሪዎቹ 15 ሰዎች ከሴቶች፣ ከሠራተኞች፣ ከንግድ ማህበርና ከመሰል ሲቪክ ተቋማት የተውጣጡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ነው የልዩ ጥቅም እሣቤ የመጣው፡፡ በዚህ 29 የኮሚሽኑ አባላት ውስጥ የህወሓት ሰዎች አልነበሩም፡፡
አዲስ አበባ፤ “ፊንፊኔ”፣ “በረራ”፣ “ሸገር” ወዘተ--- የሚሉ ቀደምት ስያሜዎች እንደነበሯት ይነገራል። እነዚህን ስያሜዎች ከባለቤትነት ጋር የሚያገናኙት  ወገኖች አሉ፡፡ ይሄ ከታሪክ አንፃር እንዴት ይታያል?
ይሄ ጉዳይ በብዙ መልኩ መታየት ይችላል። የሰዎች ወዲህና ወዲያ መንቀሳቀስን የአየር ፀባይ ለውጥ፣ ጦርነት፣ ድርቅ የመሳሰሉት ይወስኑታል፡፡ በዚህ ምክንያት የሰዎች ወዲህና ወዲያ መፍለስ አለ። በሚፈልሱበት ወቅት ጊዜያዊ ማረፊያ ያደረጉትን አካባቢ በሰው፣ በተራራ በመሳሰሉት ይሰይሙታል፡፡
በሌላ በኩል፤ ለምሣሌ ከ15ኛው ክ/ዘመን በፊት አሁን አዲስ አበባ አካባቢ ጅዳ የመሳሰሉ የሚባሉ የእስላማዊ ሱልጣኔቶች ነበሩበት፡፡ በታሪክ የምናገኘው ሱልጣኔቶች እንደነበሩበት እንጂ ምን አይነት ህዝብ ወይም የትኛው ጐሣ በአካባቢው እንደነበረ አይታወቅም፡፡ ስለዚህ አንድ ቦታ የዚህን አይነት ስም ነበረውና የእሱ ነው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሣሌ ኤርትራ ውስጥ ባሬንቱ የሚባል ቦታ አለ፡፡ ባሬንቱ አንዱ የኦሮሞ ቅርንጫፍ (ቦረና እና ባሬንቱ)  መጠሪያ ነው፡፡ አሁን ባሬንቱ የሚባል ቦታ ኤርትራ ውስጥ ስላለ ቦታው የኛ ነው ማለት አንችልም፡፡ መረዋ የሚባል የኦሮሞ ጐሣ አለ። እነ ራያ የተወለዱበት ጐሣ ነው፡፡ መረዋ ዛሬ አማራ ክልል ውስጥ አለ፡፡ አሁን ያ ቦታ የኛ ነው ማለት አንችልም። ምናልባት የቀድሞ ነገስታት የተለያዩ ዘመቻዎችን ወደማያውቋቸው አካባቢዎች ያደርጉ ነበር፡፡ ያደሩበት ወይም የከረሙበትን ቦታ የራሳቸውን ስያሜ ይሰጡት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ዛሬ እነዚያን ስያሜዎች ይዞ፣ የኛ ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ስሰማ በጣም ያስቀኛል፡፡ የአፄ ሚኒልክ ሠላይ የነበረ አጽመ ጊዮርጊስ የሚባል ሰው ነበረ፡፡ ይሄ ሰው በየአካባቢው (አዳዲስ አካባቢዎች) እየዞረ የህዝቡን አኗኗር፣ ባህል፣ ጦረኝነት የመሳሰሉትን ያጠና ይሰልል ነበር፡፡ ይሄ ሰው ነው ዛሬ መነታረኪያ የሆነውን በረራ የሚል ነገር የፃፈው፡፡ በግራኝ አህመድ ጦርነት ጊዜ፣ የግራኝ አህመድ ተከታይ የነበረ አንድ ሰው ደብረሊባኖስን እንዳቃጠለ በጽሑፉ ይገልጽና፣ ስለ በረራ ያነሣል፡፡ ይህ ሰው ስለ ደብረ ሊባኖስ ሲናገር፣ ከደብረ ሊባኖስ ትንሽ ዝቅ ብሎ በረራ የሚባል ቦታ ብሎ ይጠቅሣል። ነገር ግን አጽመ ጊዮርጊስ ያንን በመጥቀሱ፣ አዲስ አበባ በረራ ነበረች ወይም በረራ ተብሎ የተጠቀሰው የአማራ አካባቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ለምሣሌ ወለጋ ውስጥ፣ ምስራቅ ሸዋ “ቱሉ አማራ” የሚባሉ ቦታዎች አሉ፡፡ በሌሎች አካባቢም “አማራ ካንቺ” የሚባል ስያሜ ያላቸው የኦሮሞ ጐሣዎች አሉ፡፡ እነሱ አማራ ናቸው ማለት ነው? አማራ ናቸው ማለት እንችላለን? አንችልም፡፡ ዋናው ቁምነገር ሠፊ ማህበራዊ መሠረት ዘርግተው ሲኖሩበት የነበሩት ማህበረሰቦች እነማን ናቸው የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ከኦሮሞ ጋር መያያዝ፣ አፄ ሚኒልክ ወደ ቦታው ሲመጡ፣ ማህበራዊ መሠረት የነበራቸው ኦሮሞዎች ስለነበሩ ነው፡፡
“ፊንፊኔ” እና “ሸገር” የሚሉ ስያሜዎችስ ምንጫቸው ከየት ነው?
በቀደም አንድ ጽሑፍ ሳነብ ነበር፡፡ ሸገርም ፊንፊኔም የኦሮሚኛ ቋንቋ አይደለም ይላል፡፡ እኔ እስከማውቀው የኛ (ወለጋ) አካባቢ ሰዎች፣ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ሸገር ልሄድ ነው ይላሉ፡፡ በኦሮሞ ማህበረሰብ ሸገር ማለት አዲስ አበባ ነው፡፡ ስለ ፊንፊኔ እኔ ብዙ አላውቅም፡፡ የፍልውሃ አካባቢ ስያሜ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በእውነቱ እኔ በዚህ ላይ ጥናት አላደረግሁም፡፡ ሸገር ግን በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ የሚታወቅ ስያሜ ነው፡፡
ድሬደዋ እና አዲስ አበባ እንዴት ራሳቸውን የቻሉ ከተሞች ተደርገው በህገ መንግስቱ ተቀመጡ?
ድሬደዋ ላይ ሶማሌዎችም ኦሮሞዎችም የባለቤትነት ጥያቄ ያነሱበት ነበር፡፡ ስለዚህ አስታራቂ ሆኖ የተገኘው በፌደራል ስር ሆና፣ ራሷን የቻለች ከተማ እንድትሆን የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይም የኦሮሞ ባለቤትነት ጥያቄ የሚነሳበት ስለሆነ፣ አስታራቂው፣ በፌደራል መንግስት ስር እንድትተዳደርና ኦሮሚያ ጥቅሙ እንዲጠበቅለት የሚለው ሃሳብ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚነሱ ውዝግቦች እንዴት  መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል ይላሉ?
እኔ እስከሚገባኝ አስተዳደሩ በፌደራል መንግስት ስር ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ባለው መሠረት አስተዳደሩ በፌደራል መንግስት ስር ቢሆን ማንንም አይጐዳም፡፡ ወይም ደግሞ አስተዳደሩ በኦሮሚያ ክልል ስር ሆኖ፣ የፌደራል መንግስት ዋና ከተማም ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የማየው ከአስተዳደር ጉዳይ አንፃር ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱ አስተዳደር የሚቋቋምበት መሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በውስጡ የሚኖሩ ዜጐች አሉ፡፡ ማንኛውም ዜጋ የመኖር መብት አለው፡፡ እንደ ማንኛውም ዜጋ፣ የራሣቸውን ምክር ቤት አቋቁመው፣ ስለ ራሳቸው ጉዳይ የሚወስኑበት፣ ራሣቸውን የሚያስተዳድሩበት ሁኔታ መፍጠር ይችላሉ፡፡ አስተዳደሩ በፌደራል ስርም ሆነ በኦሮሚያ ይሄን ማድረግና የከተማዋ ዜጐች የራሣቸውን ም/ቤት አቋቁመው፣ የመተዳደር መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አሁን ማን ያስተዳድር ወይም አስተዳደሩ በፌደራል ወይም በኦሮሚያ ይሁን የሚለው መወሰን አለበት፡፡ ይሄ ሁሉ የሚፈፀመው ግን ህገ መንግስቱ ላይ የተደነገጉት ጉዳዮች ከተሻሻሉ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ህገ መንግስቱ ላይ የሠፈረውን ነው ሙሉ ለሙሉ መተግበር የሚገባው፡፡ ህገ መንግስቱ ባልተሻሻለበት ሁኔታ ሌላ ሂደት ውስጥ መግባት አይቻልም፡፡ ህገ መንግስቱ የማይሻሻል ከሆነ ደግሞ የልዩ ጥቅም ጉዳይ ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ 

Read 4842 times