Sunday, 17 March 2019 00:00

ሚዛናዊነት ለተሸለ ውጤት (BalanceforBetter)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ከላይ በርእስነት የተቀመጠውን አባባል ያገኘነው ባለፈው ሳምንት የተከበረውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሚመለከት እንደመሪ ቃል ከተጠቀሙበት የ March/8/ ድረገጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 29 ቀን 2011/ በውጭው ደግሞ March 8/2019 ዓ.ም ተከብሮ የዋለው የዓለም የሴቶች ቀን በዘንድሮው ትኩረቱ የጾታ እኩልነት እንዲከበር፤ ጾታዊ ጥቃት እንዳ ይፈጸም አስቀድሞ መጠንቀቅ፤ ሴቶች ያደረጉዋቸውን በጎ ነገሮች በሚመለከት እውቅና በመስ ጠት ተገቢው የአድናቆት ዝግጅት እንዲኖር ማስቻል የመሳሰሉትን ነው ከድረገጹ የተገኘው መልእክት የሚያስረዳው፡፡ ይህም በአለምአቀፍ ደረጃ በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን ክፍተት ለመዝጋት ያመቻል። በእርግጥም ሴቶችና ወንዶች እኩል መሆናቸውን ለማረጋገጥና ሴቶችና ወንዶች በኑሮአቸው ወይንም በድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በሚሰሩ ሰራተኞች መካከል …ወዘተ ሚዛናዊነት መኖሩን ለመመልከት ይረዳል፡፡
ይህ የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለእኔ ልዩ ቀን ነው ያሉን የ75/አመት አዛውንት ሴት ወ/ሮ እንግዳሸት አለሙ ይባላሉ፡፡ ወ/ሮ እንግዳሸት ያሳለፉትን ሕይወት እንዲህ በማለት ነበር ለአምዱ ሪፖርተር የገለጹት፡፡     
ወደ ትዳር አለም ስገባ ገና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ በእርግጥ ወንጌልን መላልሼ እንዳነብ እንዲሁም ዳዊት በደንብ እስኪገባት ብለው ስደግም ከመጀመሪያውም ለዘመናዊው ትምህርት ዘግየት ብያለሁ፡፡ ወደ ትዳር አለም ስገባ ግን እድሜዬ ገና አስራ ስድስት ነበር፡፡ባገባሁ በሁለተኛው አመት ጀምሮ ልጅ መውለድ ጀመርኩ፡፡ በማከታተልም ገና ሀያ አምስት አመት እንኩዋን ሳይሞላኝ ነበር አምስተኛ ልጄን የወለድኩት፡፡ በጣም ተቸገርኩ፡፡ አንዱ ተወልዶ ጡት እየጠባ ሌላ ይረገዝ ነበር፡፡ እርጉዝ ሆኜ ሁሉ ልጅ የማጠባበት ወቅት ነበር፡፡ ልጆቹም ህጻናት ስለነበሩ ሁሉም እሹሩሩ ይፈልጋሉ፡፡ በእርግጥ የሚረዳኝ ሰው ቢኖርም እንኩዋን ልጆቹ ግን እናታቸውን ስለሚፈልጉ እኔ ካላባበልኩዋቸው እሺ አይሉም ነበር፡፡ እጅግ በጣም ደከመኝ፡፡ ታዲያ ለባለቤቴ ….
…እባክህን ይህንን ልጅ እንዳይወለድ የሚያደርግ መድሀኒት ከማገኝበት ውሰደኝና እኔም አረፍ ልበል አልኩት፡፡ የእሱም መልስ የሹፈት ሳቅ ነበር፡፡ እኔም መልሼ…ምነው ለምን ሳቅህ አልኩት፡፡ እሱም….ተይኝ እባክሽ…ይህንን ማሾፍ አቁሚ፡፡ ልጅ መውለድ እንደ ሆን የተፈጥሮ ግዴታሽ ነው፡፡ እኔ ማሳደጊያ አላጣሁ፡፡ አንቺ ደግሞ ዘር እንዳገኝ ለማድ ረግ ብዬ አገባሁሽ እንጂ…ሌላማ ምን ታረጊልኛለሽ? አለኝ፡፡ እንዴ…ሚስት የሚገባው ዘርን ለማግኘት ሲባል ብቻ ነው? አልኩ፡፡ እናስ ሌላ ምን ትሰሪያለሽ? ልጅ እየወለድሽ ማሳደግ ነው፡፡ በቃ፡፡ እኔ ከአገር አገር እየሰራሁ ማሳደጊያውን አመጣለሁ፡፡ በቃ፡፡ አለኝ፡፡
ልጆች ሲወለዱ ሲወለዱ…ወደ 9/ ደረሱ፡፡ አስረኛውን ልጅ እርጉዝ ሆኜ ግን እጅግ በጣም ታመምኩኝ። እሱም ምን ሆነሽ ነው? ደሞ እርግዝና ሕመም መሆን ጀመር እንዴ አለኝ፡፡ ልጆቹን ከፍ ከፍ ሲሉ ለመላላክ ካልሆነ በስተቀር ዞር ብሎ አያያቸውም፡፡ እኔ ደግሞ አስረ ኛውን ልጅ ሳረግዝ የመጀመሪያዋ ገና 14/አመትዋ ነበር። ልጅትዋ ግን ካለእድሜዋ እኔን ለማገዝ ከቤት ውስጥ በጣም ትሰራለች። እኔም ሕመሙ እየበረታብኝ ሄደ፡፡ ለሕክምናም የተወሰድኩት ወደ ጋንዲ ሆስፒታል ነበር፡፡ ሐኪሞቹም ጽንሱ ሆዴ ውስጥ መሞቱን ነገር ግን ባይሞትም የተረገዘው ልጅ ችግር ያለበት መሆኑን ለእሱው አስረዱት፡፡ እሱም ምን አለ መሰላችሁ….ስታሟርቺ በራስሽ ላይ ያመጣሽው ጣጣ ነው፡፡ አለኝ፡፡ ሐኪሞቹም ድጋሚ እንዳይረገዝ አስጠንቅቀው አክመው ወደ ቤቴ ሸኙኝ፡፡ እኔም ወደቤቴ የገባሁ እለት በምሽት ጨርቄን ጠቅልዬ ወደ እናቴ ቤት ሄድኩ፡፡ ብለመን ብለመን አሻፈረኝ ብዬ ዘጠኙን ልጆቼን እናቴ ቤት ቁጭ ብዬ ተቆራጭ እየተቀበልኩ አሳደግሁዋቸው፡፡ እሱ እንደኔ ያለችውን አግብቶ ማስወለዱን ቀጠለ፡፡ ይህ በየአመቱ የሚከበረው የሴቶች ቀን እንደዚህ ያለውን ጊዜ ሲያመጣ እጅግ ከሚደሰቱት መካከል ነኝ፡፡ ምክንያቱም በራሴ ሰውነት እና ሕይወት ማዘዝ የእኔ መብቴ መሆኑን ስለሚናገርልኝ ነው፡፡ የዛሬዎቹ ልጆች እኮ እድለኞች ናቸው፡፡ አጥብቀው መብታቸውን ለማስከበር መስራት አለባቸው እላለሁ፡፡ የዚያን ዘመኑን ሚዛን ያጣ አስተሳሰብ ወዲያ ማስወ ገድ ይገባል ብለዋል ወ/ሮ እንግዳሸት፡፡      
አለም አቀፉ የሴቶች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ የተሰማው በውጭው አቆጣጠር በ1909/ ሲሆን በዚህ ጊዜ በግምት /15.000/ የሚሆኑ ሴቶች በኒውዮርክ ጎዳና በሰልፍ በመውጣት ለሚ ሰሩት ስራ የሚከፈላቸው ገንዘብ የልፋታቸውን ያህል እንዲሆንና የሚሰሩት ስራም ተመጣጣኝ እንዲሆን እንዲሁም የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር የመሳሰሉትን ጥያቄ ያቀረቡበት ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ከብዙዎች ልብ በመስረጹም በ1911/ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአሜሪካ፤ በእንግሊዝ፤ አውስትሪያ፤ዴንማርክ፤ጀርመንና ሰዊዝላንድ የሴቶች መብት መከበር እንዳለበት በጎዳና ወጥተው ድምጻቸውን አሰሙ፡፡
ከአመታት በሁዋላም በውጭው አቆጣጠር በ1975/የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በይፋ አመቱ የሴቶች አመት እንዲባልና ማርች 8/ም የአለም የሴቶች ቀን በሚል በየአመቱ እንዲከበር ለመላው አለም ውሳኔውን አሳወቀ፡፡ ይህ ወቅት አለም አቀፉ ህብረተሰብ በሴቶች ዙሪያ ስላሉ ማንኛውንም አይነት የመብት ጥሰት እንዲረዱና በተለይም በእኩልነት ላይ ያለውን ልዩነት ሁሉም እንዲገነዘበው ለማድረግ ያስቻለ ወቅት ነበር ፡፡
የሴቶች መብት መሰረታዊው የሰው ልጅ የሰብአዊ መብት ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምድሪቱ ላይ በሚኖር በማኝኛውም ሰው እውቅና እንዲያገኝ እና እንዲከበር የተላለፈ ድንጋጌ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች ከጥቃት ነጻ የሆነ ሕይወትን፤ ከባርነት ነጻ መውጣትን፤አድሎ የሌለበት፤ ትምህርትን እንዲያገኙ፤ንብረታቸውን እንዲያስተዳድሩ፤ መምረጥ እንዲችሉ እና በተሰማሩበት የስራ መስክ እኩል ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚደነግግ ነው፡፡  
March 8/ አለም አቀፉ የሴቶች ቀን በራሽያም እንደውጭው አቆጣጠር ከ1917/ ጀምሮ የሴቶ ችን ጥያቄ እና የሚደርስባቸውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የተባበሩት መንግስታት በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር እስከወሰነበት ጊዜ ድረስ በየአመቱ ብሔራዊ ቀን ሆኖ ሲከበር ቆይቶአል፡፡
ሁሉም ቀን የሴቶች ቀን ነው ቢባል ሴቶች ይገባቸዋል። እንዲያውም ሴቶች ከዚያ በላይ ይገባቸዋል የሚለው የMarch 8/ ድረገጽ ነው፡፡ ሴቶች የሚገባቸውን ክብር ዛሬም እያገኙ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ቀን ሴቶች ላገኙዋቸው ድሎች ካለምንም መከፋፈል ማለትም በዘር፤ በሀይማኖት ፤በቋንቋ ፤በባህል ፤በኢኮኖሚና ፖለቲካ ልዩነት ሳይኖር ሁሉም እውቅናና ክብር የሚያገኙበት ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው፡፡
አለምአቀፉ የሴቶች ቀን March 8 እንዲሆን የተደረገው በውጭው አቆጣጠር 1913/መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቀኑም በአለምአቀፍ ደረጃ ያሉ ሰዎች ሴቶችን በሚመለከት ከሚያሳዩት ንቀትና ዝቅ አድርጎ መመልከት እንዲታቀቡ ለማድረግ የተለያዩ እውነታዎች የሚታዩበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሴቶች ሙሉ በሙሉ በአለም አቀፉ የልማት ክንውን እኩል ተሳታፊ እንዲ ሆኑ ለማድረግ ነው፡፡
አለም አቀፍ ቀናት ከሴቶች ውጭም የሚከበሩ ወይንም የሚታሰቡ ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መክከል ፡-
October 11/ አለም አቀፍ /የሴት ልጆች/ የልጃገረዶች ቀን አንዱ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ መሰረት መከበር የጀመረው በ2012/ነው፡፡
ሌላው November 19/ ነው፡፡ ይህም አለም አቀፍ የወንዶች ቀን ሲሆን በየአመቱ ይከበራል፡፡

Read 7085 times