Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 May 2012 13:03

አቦል… ቶና… በረካ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ቅድመ ታሪክ

ከተሞችን ወንዶች ይሠሯቸዋል (ይመሠርቷቸዋል) ሴቶች ይነግሱባቸዋል … አልያም ይገዙባቸዋል፡፡ ወንዶች ቤቶችን ይሠራሉ፤ በድንጋይ… በጠጠር… በሾህ… በአሸዋ… ሴቶች ያስውቡታል…ቤቶች በሴቶች ይደምቃሉ፤ ቤቶች በሴቶች ይዋባሉ፤ በሸክላ… በሰፌድ… ወንዶች ብረትን ይገዛሉ፤ ሴቶች ብልሃትን ያመጣሉ፤ አንዳንዴ ግን (ለምን አንዳንዴ አብዛኛውን ጊዜ ግን) እንዲህ ይሆናል፡፡ አማራጭ ከጠፋ በኋላ… እንደ እናቷ ከሚወዷት… እንደ እናቷ ከምትወዳቸው ከአክስቷ ጋር በአካለ ሥጋ ከተለያየች በኋላ… ተስፋዋ ከተገደለ በኋላ… ተስፋ የለኝም ስትል… ከሞተው ተስፋዋ በኋላ… ወደ ኋላ ተመልሳ እናቷን ይቅርታ እንዳትጠይቅ… ምን ብላ? ለማያውቁት ላላዩት…የሕይወት ታሪኳ ምን ብለው ይቅርታ ይሏታል… ማንን ጐዳች? መጓዝ የነበረባትን መንገድ ቸል ብላ… ለወንዶች ወሬ… ለፍቅር ስሟ የጠፋ… ማንነቷን እንዴት ማሳየት ትችላለች?

ከሐገሯ ስትወጣ አደራሽን ነበር ያልዋት… አደራሽን እሺ የኔ ልጅ?

“ምንም አታስቢ” ነበር ያለችው… ምንም አታስቢ እሺ እማ!

ምን ሊሏት እንደሚፈልጉ ገብቷት ነበር፡፡ እናቷም አምነው ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳሏት አልሆነችም፤ እንዳለችው አልታየችም፡፡

ሃያ አንድ ዓመቷ ላይ  አክስቷን ቀበረች፡፡ ከገጠር ከመጣች ከሁለት ዓመት በኋላ…

ሕይወቷ ተለውጧል… እናቷን ባሰበች ቁጥር ትናደዳለች፤ ትበሳጭባቸዋለች… ምን አለበት በሞተች… ትላለች እናቷን!

ከብዷታል… የእናቷ ይቅር …ያማታል፡፡ የእናቷን ቃል ባለመጠበቋ ከእናቷ ተለይታ በርቀት ተቀምጣ… አዲስ አበባ ሆና ብስጩ አደረጋት…የእናቷ ፍቅር፡፡

አንዳንዴ ታለቅሳለች… ለብቻዋ ትበሳጫለች፡፡ ለልጅነቷ… ለአላዋቂነቷ… እንደተሰበረች ይሰማታል፡፡ ከአዲስ አበባ ርቃ በመወለዷ ከህይወት የራቀች መስሏት ነበር፡፡ ብዙ ነገር ያመለጣት… አስመሰሏትና የመሰላትን ተቀበለች… የተቀበለችውን አመነች፡፡ በወንዶች ከተማ ላይ… ወደዚያ የሚሄደውን ልታደማው… ወደዚህ የሚመጣውን ጠልፋ ልትጥለው! በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች መካከል አንዷ ሆነች፡፡

ውብና መልከ መልካም… ማናቸውም ወንዶች የሚፈልጓት ሴት!  ከራሷ በስተቀር የትኛውም የአዳም ዘር ግድ የማይሰጣት… ቀፋፊና አሰልቺ ሕይወት የምትገፋ ውብ… ነገር ግን ተራ ሴት ሆነች! (ተደርጋ ተሰራች) ዘወትር አመሻሽ ላይ… በራፏ ላይ ቆማ እንዲህ የምትል ሴት ሆነች፡፡

“በቤቴ ውስጥ የወይን ጠጅ አለ፡፡ ከወይን ጠጅ ዋጋ ባልተናነሰ ሁኔታ ደግሞ እኔ አለሁ… ወንዶች የተበሳጩባትን ሴት ሊበቀሉ ወይም ሊረሱ ከፈለጉ አለኹላቸው! (አለሁላችሁ) ኑ ተመልከቱ ጭኖቼን… ጡቶቼን… ልጅነቴን… ኑና ተመልከቱ!

“ከርቤዋን የታጠነች… ሽቶዋን የረጨች… በሮቿን ከፍታ… ማንም የተጠማ ሲኖር ወደኔ ይምጣ” የምትል ሴት ሆነች፡፡

እንዴት?

ከአራት ዓመት ኋላ… ዛሬ

ርጥብ አረንጓዴ ሳር መሃሉ ላይ የአደይ አበባ የበዛበት ይዛለች፡፡ በየሰው ፊት ላይ ፈገግታ አለ፡፡ ሐዘንተኛ ነፍስ አይታይም፡፡ ከዝናብ በኋላ የፈካ የአስራ አንድ ሰዓት ሰማይ ይታያል፡፡ የነጣ የፈካ ከወትሮው ከፍ ያለ የሚመስል፡፡ የከተማው ጠረን ተስፋን የተሞላ ነው፡፡ ከየቤቱ ጣሪያ በላይ እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ የነበሩ የነፍሳት ሀዘኖች በኩበት ጭስ ተጠቅልለው ወደ ሠማያት የሚያርጉ ይመስላል፡፡ በየቦታው ጭስ… በየሰው ተስፋና ደስታ… በየቤቱ ጣሪያው የሚመጥነው ተድላ አለ፡፡ ምክንያቱም ነገ ዐውደ ዓመት ነው፡፡

ቤቷ አዲስ የተሠራ እንጂ የተፀዳ አልመስልሽ አላት፡፡ ሁሉም ጽዱና ዕፁብ  ነበር፡፡ ቄጤማውን አስቀምጣ ሰአቷን ተመለከተች፡፡ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ይላል፡፡

በአደይ አበባ የታጀበውን ርጥብ አረንጓዴ ሣር አስተዋለችው “የታሰረው ይፈታል - የተፈታው ይበተናል- የተበተነው ውበት ሆኖ ለዓመታት ይቆይና… እንደገና የተበተነው ይረገጣል… የተረገጠው ይጨቀያል… እስከ ተነገ ወድያ ጠዋት ድረስ አረንጓዴውና ጭቃው በአንድነት ይደርቃሉ”

የገዛችው ሣር አሳዘናት… ያሳዘናት ግን መረገጡ አልነበረም፡፡ መድረቁም አይደለም፡፡ ርጥብ ለምለም መሆኑ ብቻ ነበር፡፡ በሣሩ ላይ የነበረውን ተመስጦዋን ትታ በቁመቷ ልክ ወደ ሆነው መስታወት ተጠጋች፡፡ መዳፎቿ ጡቶቿ ላይ አረፉ… ዐይኗ ሁለመናዋ ላይ ተንከራተተ “የሆነ ሰው ይመጣል… ውበቴን ይገላምጣል… ቀሚሴን አወልቅለታለሁ… ካልጋዬ ላይ ይወረውረኛል… ዓይኖቼን ጨፍኜ ጭኔን እከፍትለታለሁ… ያልመከኑ ጡቶቼን ያሻቸዋል፡፡ በጣቶቹ ያረጋግጣቸዋል… ለውበት አይሳሳም… በማግስቱም እንዲሁ …በሦስተኛው ቀን ግን እግሮቹ በበሬ አያልፉም፡፡ ለበአል ተበትኖ ማለዳ እንደሚጠርጉት ቅጠል… የኔም ዕጣ ፈንታ እንዲያ ነው” አለች፡፡

ርጥብ… አረንጓዴውን… ለምለም ሳር በተነች፡፡ የአደይ አበባዎቹንም በየሥፍራው ለአይን ማረፍያ ያህል በተነች… አበባ ስትበትን አበባ እየረገጠች ነበር… አረንጓዴውን ስትጥል አረንጓዴውን እየሰበረች ነበር… ዐይኖቿ እግሮቿን አላስተዋሉም፡፡ ጥቂት ሳር እንደያዘች… የቤቷ የወለሉ መሃል ላይ እንደቆመች… ወደ ሩቅ ተጓዘች… ከአራት ዓመት በፊት…

እጇ ላይ ያለውን ጥቂት ሣር አየች፡፡ በእጇ ላይ የቀረው ትንሽ ነበር፡፡ የተበተነውን ርጥብ ለምለም… አረንጓዴውን ቅጠል አስተዋለች “አራት ዓመት ሙሉ የገዛት ወዳሻው የሚበትናት ሳር” አለች፡፡ ራሷን፡፡ “እድሜ ላንተ” አለች… ማንነቱን የማናውቀውን የሆነውን ሰውዬ እያስታወሰች፡፡ “እድሜ ላንተ… ተለምኜ የምታቀፍ ተከብሬ የምሳም… የቁንጅና ልዕልት ነበርኩ… አሁን ግን ተገፍቼ የምወድቅ… ተረግጬ የሚተኙኝ.... ርካሽ ሆኛለሁ” ዕድሜ ላንተ!

ዕንባ በዓይኖቿ ተፀነሰ፡፡

የበተነችው ሣር… ውበቱ… ልምላሜው… ርጥበቱ… ልቧን በሐዘን ሞላው፡፡ “የዚህ ውበት የመጀመሪያ ጠላት ግን እኔው ነኝ፡፡ ራሴው፡፡ ምክንያቱም የበዓል ቡና ሊጠጡ ከሚመጡ ሰዎች አስቀድሜ የረገጥኩት እኔ ስለሆንኩ… ማንም ይረግጠው ዘንድ መንገድ ከፍቻለሁና” አለች፡፡

በራሷ የመፀፀት ስሜት ተሰማት፡፡ በበተነችው ሳር ውስጥ ራሷን የምታይ መሰላት… ሐዘኑም ልቧን የበላው የተበተነው ሳር የርሷ ፍፃሜ ነቢይ ስለመሰላት ነበር፡፡

በቤቷ ውስጥ በብቸኝነት ከሚገኘው ከበሯ ትይዩ ካለው የሶፋ ወንበር ላይ ለዕረፍት አረፍ አለች - እግሮቿን ወደ ፊት ዘርግታ… ሁለት እጆቿን በጭኖቿ መሃል አሣርፋ… ወደ ኋላ ተበተነች… በአካልም በሃሳብም…

ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡ እግሮቿ የደሴን ትቢያ አራግፈው የአዲስ አበባን ድንጋዮች ሲረግጡ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነበር፡፡ እንግዳ ወደ ሆነ ባህል… ነውርን ወደማይፈራ ሕብረተሰብ… አንደበትና ሕይወት ቀለበት ወዳላሠሩበት የማስመሰል ዓለም ስትቀላቀል የመጀመሪያ ጊዜዋ ነበር… ከአምስት ዓመት በፊት!

የአዲስ አበባ ጐበዞች በይን… የዚህችን ሕልመ ሙሉ ሴት ውበት ቀረደደው፡፡ የሸገር ጐበዞች አንደበት… ራሷን ከራሷ አፋታት፡፡ የፒያሳ ወንዶች ስለ ራሷ በምስጢር የምታውቀውን በአደባባይ ሰበኩላት፡፡ “ቁርጥ የድሮ ጓደኛዬን… ፀጉርሽ ብትዬ ከንፈርሽ” በቀኝ መዳፋቸው መዳፏን እያጋጩ፡፡ “ታውቂያለሽ…በቃ ካንቺ ጋር መተኛት ከሁሉም ሴት ጋር የመተኛት ያህል ነው… በናትሽ እሺ በይኝ… በአንቺ ውበት በኩል ከሁሉም ሴት ጋር የተኛሁ ከሆነ ለምን አመነዝራለሁ? ለምን ሌላ እመኛለሁ… እ?” አሏት፡፡

ሠከረች!!

አክስቷ ቤት እየኖረች… በአዲስ አበባ ካሉ የሕክምና ኮሌጆች ተምራ እንደማናቸውም ሰዎች ጠዋት ሥራ ማታ ቤት እያለች… ታልም የነበረችው ውብ ሴት… ለእናቷ ነጭና ሰማያዊ ሕልም የነበረችው ሴት… እነሆ በሸገር ጐበዞች አንደበት… እነሆ ግራጫ ብቻ ሆነች… የእናቷ ሕልም የነበረች ያገር ቅዠት ሆነች፡፡ ወርቅ በሙዳዩ ሳለ እንደሚከበር… የምንጭ ውሃ… በኮረብቶች ማህፀን ሳይለቀቅ ደስ እንዲል… የርሷም ውበት በመሠወሩ የከበረ ነበር፡፡

ወደቀች!!

ዐይነ ርግቧን ቀደዱት፡፡ ነጭ ረዥም ጥለት ቀሚሷን ከጉልበቷ በላይ ቆረጡት፡፡ እናም እንዲህ አሏት… አገጯን በአራት ጣቶቻቸው ይዘው… ቀና እያደረጓት… “እኔ ምልሽ” አሏት

እ? አለች

እ… ለምን ፊልም አትሠሪም?

አስቤበት አላውቅም… ግን ደሴ እያለሁ ትንሽ ግጥም ምናምን እሞክር ነበር… ፊልም ግን? ችግር የለም አሏት፡፡ ትንሽ ሒንቱ ካለሽ በቂ ነው፡፡ ከናቱ ሆድ የተማረ የለ… ደግሞ ውብ ነሽ… ይህን ውበት ይዘሽ… የማንንም ቁስል ምናምን ልትጠርጊ...  ነው? ኧረ ሼ በይ አሏት…

ሼ… አለች፡፡

ሼ!!

ጠዋት ወደ ሦስት ሰዓት ተኩል አካባቢ… የአክስቷ የቁም ሳጥን መስታወት ፊት ለፊት ለ45 ደቂቃዎች ያህል አትጠፋም፡፡ ጥለቷን ጥላ… ጥቁር ታይት… ቢጫ ታይት… ቀይ… ቢጫ ቶፕ… በብሉ ጂንስ… ጭንቅ ሆነባት… የማያሳስበው አሳሰባት፡፡ ባደገችበት አፈረች… ገጠር በመኖርዋ ተማረረች… አሁን ማንም ለምዷታል… ግን አንድ ክፍተት አለ… አንድ ቅሬታ… ፊልም ትችላለች ወይ? ብዙዎች ተኝተዋታል፡፡ ለውጥ ግን የለም… የሕክምና መማሪያ ገንዘቧ በአልባሳትና በመዋቢያ ቀለሞች ነዷል፡፡ ፊልም ልትሠራ መረጧትና… ሕይወቷን ወደ ፊልም ለወጡት፡፡

ከዕንቅልፏ ነቃች!!

የት ሄደ አለች… ያ የመጀመሪያውን የፒያሳውን ልጅ “ቁርጥ ኤክስ ፍሬንዴን… ፀጉሩሽ ብትይ… ከንፈርሽ…” ያላትን…

የት ሄደ አለች …ያ “ካንቺ ጋር መተኛት… ከሁሉም ሴቶች ጋር የመተኛት ያህል ነው” ያላትን…

የት ሄደ አለች… ያ “ፊልም ለምን አትሠሪም… ይሄንን የመሰለ ውበት ይዘሽ… የማንም በሽተኛ ለሃጭ ልትጠርጊ ነው” ያላትን ለሃጫም የካሳንችስ ወሮበላ…

ሕክምናዋን ሳትማር… ፊልም ሳትሠራ… ጊዜው ሄዷል፡፡ ከእናቷ እህት ጋር የምትኖር ብቸኛ ናት… እናቷ እንደማናቸውም ኢትዮጵያውያን እናቶች የዋሕ እና ምስኪን ነበረች… ትዳሯንና ክብሯን ልጇ ላይ የጣለች፡፡ እናቷ እርሷ ላይ የነበራትን ህልም ማን ሠረቃት? ጨነቃት… ጠበባት… የወንዶች አድናቆት… የወንዶች አንደበት ጐዳናዋን አጨለመው… ወደ ግራ ዞረች… ምንም  ወዳለማየት… ወዴትም… ወዳለመጓዝ ተመለሰች…

ተፈፀመች!!

ከተቀመጠችበት ተነሳች… በረዥሙ ተነፈሰች፡፡ ወደ በሩ ተጠግታ ደጇን አስተዋለች፡፡

ልብሷን ቀይራ ረከቦቷን አወጣች…

ቡና የምታፈላበት ቦታ በቤቷ በር ትይዩ ነው፡፡ ነጭ ሥኒ… ከነጭ ረከቦት በላይ ተደርድሯል፡፡ በበሯ የሚያልፍ ሁሉ ረከቦቷን ዘርግታ ሥኒ መደረደሯን ሲመለከቱ ምን እንደሚያስቡ አሰበች… “ቡና” አለች፡፡

በዚህ አንድ ሲኒ አለች… የመጀመሪያውን ስኒ እያጠበች፡፡ ስንት ሰው ጠጥቶበታል? አንዳንዴ በአንድ ጊዜ… በአንድ ስኒ ስንት ሰው ጠጥቶበታል? (ስኒ ሲጠፋ ባንድ ሲኒ ለሦስት) ቡና ይፈራረቃል፡፡

ቡናው ይጠጣል፡፡ “አቦል” - ወፍራም ትኩስ ቡና… ከነሙሉ ጣዕሙ፡፡

“ቶና” - ከሦስተኛው የሚወፍር… ከአቦሉ የሚቀጥን፡፡

“በረካ” - የቀጭን ቀጭን… ጣዕም አልባ… እንኳን ለጠጪው አፍ… በሥኒው የማይሞላ ውሃ… አተላ… የቡና ዕድፍ፡፡

ቡና ከሚያጣጧት ውስጥ “አቦል በቃኝ” የሚሏትን ወፍራም… ድምፀ ቀጭን የሆኑ ጐረቤቷን አስታወሰች፡፡

አሁንም ከሰባት ዓመት በፊት… ቆመች፡፡

የረጠበ እጇን አደራርቃ… ከሳጥኗ ውስጥ ፎቶ አወጣች፡፡ አቦል እያለች ምን ትመስል እንደነበር የሚያስታውሳትን ፎቶ መርጣ ተመለከተች፡፡ የእርሷ አልመስልሽ አላት፡፡ ከራሷ ምስል አጠገብ ሌላ ጉርድ ፎቶ አለ፡፡ “አቦል በቃኝ” ብሎ የፈላው ላይ ለመድረስ… ሌላ አቦል ፍለጋ በመሄዱ እርሷን “ጭላጭ” ያደረገ ሰው ምስል! ሞቅ ያለ ዕንባ ባልተለመደ ዝግታ ወደ ከናፍሯ ወረደ፡፡ ጨው ጨው አላት፡፡ ራሷን ጠየቀች… “ይህን ያህል ዘመን ፎቶውን ለምን ያዝኩት?” ወደ መሬት አየች… እንደገና ወደ ፎቶው… የሆነ ምክንያት አገኘች፡፡ ርጥብ ለምለም… አረንጓዴውን ሣር ቀድሜ የረገጥኩት እኔ ብሆንም… ያጨደው ግን… ተቀዳሚው ጥፋተኛ ራሱ ነው… አለች፡፡

አዎ… ይህ ሰው ልቤን የሰበረው… ሕልሜን ያሳጠረው… ተስፋዬን የገደለው… ሰድቦኝ አይደለም… ከድቶኝ አይደለም… ይህ ወንድ የሰበረኝ… እንዴት ታምሪያለሽ ብሎ ነበር… አዎ… በጣም… ውበትሽ… ታውቂያለሽ ግን… ነበር ያለኝ፡፡ የመጀመሪያው የወንዶች የልብ መክተፍያ መጋዝ… ሌላ ምንም አይደለም… ቆንጆ ነሽ ሲሉ ነው የምንሞተው፡፡

አልገባኝም እንጂ ዐይኖቼ የተጨፈኑት… ጥበቤን አውልቄ… እግሮቼ እንደሚያምሩ ለማስመስከር… መድከም ስጀምር ነው፡፡ ድሪያዬን ጥዬ… የመንታ ጡቶቼን ምንነት… ለአደባባይ ሳሰጣው… ያኔ ነበር የወደቅኩት… ያኔ ነበር… የተሰወረውን ስገልጥ… ሌላ የሚፈለግ ከኔ የጠፋው… ያኔ  ነበር… ይሄ ፎቶውን እስከዛሬ የያዝኩት ልጅ… “ስታምሪ” ብሎ ጉድጓዴን የቆፈረው፡፡  “ከአንቺ ጋር መተኛት እኮ ከሴቶች ሁሉ ጋር መሆን ነው… እንዴት ውብ ነሽ” ሲለኝ… ተሰበርኩ… ታወርኩ፡፡ ስነቃ… እኔ ከኔ ጠፍቼ ነበር፡፡ ዓይኔን ወድቆ አገኘሁት፡፡

ዕንባዋን ጠረገች፡፡

አሁን…

ምድጃው ላይ ያለው ከሰል ጥቁር አይታይበትም፡፡ ጨረቃ ቀለም… እሳት መስሏል፡፡ እጣኗን ጨመረችበት፡፡ ቡናዋን ማፍላት ጀመረች፡፡ ቤቱ በሙቀት ነደደ፡፡

 

 

 

 

 

Read 8848 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 13:10