Sunday, 10 March 2019 00:00

በ600ሚ. ብር የተገነባው “ጋስት” የመዝናኛ ሞል ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

12ቱም ፎቅ ለመዝናኛነት ይውላል ተብሏል
                                           
          በ600 ሚሊዮን ብር የተገነባውና ሲኤምሲ ሚካኤል ፊት ለፊት የሚገኘው ጋስት የመዝናኛ ሞል ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው 12ቱም ወለል ለመዝናኛና ለጤንነት የዋለ ሞል እንደሆነ የጋስት መዝናኛ ሞል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ተ/ሃይማኖት ተናረዋል፡፡
ተገንብቶ ለመጠናቀቅ አምስት ዓመት ገደማ የፈጀበት ሞሉ፤ የአገራችንን የመዝናኛ ክፍተት ለመሙላት ጥናት ተደርጐ መሰራቱን አቶ ዳዊት ገልፀዋል፡፡ ሞሉ በውስጡ 4 ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶች፣ የወንዶችና የሴቶች አጠቃላይ የውበትና የቆዳ መጠበቂያ፣ የውበት ሳሎኖች፣ ስቲም፣ ሳውና፣ ፉድኮርት፣ የተሟላ ጂም፣ ሙሉ የልጆች መጫወቻና ለስኳር፣ ለደም ብዛትና ለመሰል ህመምተኞች የተዘጋጁ ምግቦችና በርካታ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በተለይ የልጆቹ መጫወቻ ከአካል እንቅስቃሴና መዝናኛ በተጨማሪ አዕምሮን የሚያሰሩና የሚያመራምሩ የጨዋታና የስሌት መሳሪያዎችን በማስመጣት በአካልና በአዕምሮ ብቁ ለማድረግ ታስቦበት የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል፡፡
ከአራቱ ሲኒማ ቤቶች በተለይ ሁለቱ እጅግ ቅንጡና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ መሳሪያዎች የተደራጁ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ሁለቱም ደረጃቸውን የጠበቁና ለከተማችን አማራጭ የመዝናኛ ማዕከል ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ሞሉ ከ200 በላይ ለሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ተጨማሪ ሰራተኞች እንደሚያስፈልጉትም ስራ አስኪያጁ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ቤተሰብን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን መጫወቻ ቦታ አስገብተው ጂም መስራት፣ በቢዝነስ ጉዳይ መወያየት፣ ስቲምና ሳውና መግባት፣ ማሳጅ መደረግና የውበት ሳሎን መግባት የሚችሉበት - ሁሉን በአንድ የያዘ ነው የተባለለት ሞሉ፤ ዋጋውም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደየአቅሙ ሊጠቀምበት የሚችልና አቅምን ያገናዘበ ነው ተብሏል፡፡
ጋስት የመዝናኛ ሞል፤ የጋስት ኤሌክትሮ ሜካኒካል እህት ኩባንያ ሲሆን፤ ጋስት ኤሌክትሮ ሜካኒክ ከ16 ዓመታት በፊት በትንሽ የመበየጃ ማሽን 4በ4 በምትሆን የኪራይ ቤት የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የሶላር ስራ መጀመሩን የተናገሩት አቶ ዳዊት በአሁኑ ሰዓት ጋስት በኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ዘርፍ ቁጥር 1 ተቋራጭ በመሆን የተለያዩ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን፣ የኢንስታሌሽን፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራና ተያያዥ ተግባራትን ከማከናወኑም በላይ የህክምና መሳሪያዎችን በማቅረብ፣ በመቀሌና በአዲስ አበባ የኦክስጅን ፋብሪካ ከፍቶ ለህሙማን የሚቀርበውን ኦክስጅን ለሆስፒታሎች እንደሚያከፋፍል እንዲሁም ጂኤስኤም ቀለምና ለኮንስትራክሽን ስራ የሚውሉ የኬሚካል ውጤቶችን እንደሚያመርት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 4149 times