Sunday, 10 March 2019 00:00

የእግር ኳስ ማሊያ በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)


      በዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ የስፖርት ትጥቆች አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች የገበያ ድርሻቸውን አስፋፍተዋል፡፡ በተለይ እግር ኳስን  በተለያዩ ውሎች የተሳሰሩ ግዙፍ ኩባንያዎች በዓለም ዙሪያ ለሚያሰራጯቸው ምርቶች ትኩረት ሰጥተው በማራኪ የውል ስምምነቶች እየተንቀሳቀሱ የገበያ አድማሳቸውን በማስፋፋት ገቢያቸውንም በየዓመቱ በ2 እጥፍ  በማሳደግ መስራቱን ቀጥለዋል፡፡ እግር ኳስ ከዓለም ህዝብ ገሚሱን ቀልብ የገዛበት ሁኔታ ትስስሩን አቀላጥፎታል፡፡ በተለይ በኤሽያና አፍሪካ አህጉራት ለዓለም አቀፍ የስፖርት ክንዋኔ የተፈጠረው ጉጉት ለኢንዱስትሪው ምቹ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይ እግር ኳስ በየእንዳንዱ የጨዋታ ቀን የሚያገኘው ትኩረት እና በልዩ ድራማው የሚጨምረው ተወዳጅነት ገበያውን አድርቶታል፡፡ በሌላ በኩል ለእግር ኳስ ስፖርት መላው ዓለም የሚሰጠው ፍቅር ለተለያዩ የስፖርት ትጥቆች ተፈላጊነት መንስኤ ሆኗል፡፡ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የስፖርት ትጥቆችን እንደፋሽን የመከተሉ ባህል እየጨመረ የመጣውም ከስፖርቱ ጋር ተያይዞም  ሳይያያዝም ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድንና የክለብ ማሊያዎች፤ የስፖርት ጫማዎች፤ ቱታዎች እና ሌሎች ተመሳሳይ ምርቶች ገበያ በዓለም ዙርያ ተጧጡፎ እንደቀጠለ ነው፡፡ ለተለያዩ ስፖርቶች በተለይም ለእግር ኳስ ታስበው የተመረቱ የስፖርት ትጥቆች በስፖርቱ ውስጥም ሆነ ከስፖርቱ ውጭ ላሉ የኑሮ ሁኔታዎች የሚያመቹ ፋሽኖች በመሆን ሰፊ ገበያ እያገኙ ናቸው።  ይህም በዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪ “Athleisure” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የፋሽን አቅጣጫ ፈጥሯል፡፡
በዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ በተለይም እጅግ ተወዳጅና ትርፋማ በሆነው እግር ኳስ ከማሊያዎችና ሌሎች የስፖርት ትጥቆች አቅርቦት፤ ሽያጭ እና ስፖንሰርሺፕ ጋር በተያያዘ በመላው ዓለም የሚንቀሳቀሰው መዋዕለንዋይ  ከፍተኛ እድገት እያሳየ ነው፡፡  በዓለም ዙርያ ምርቶቻቸውን በማሰራጨት የሚንቀሳቀሱ የስፖርት ትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች ያላቸው የገበያ ፉክክር ተጠናክሯል፡፡ ኩባንያዎቹ የምርቶቻቸውን የጥራት ደረጃ፤ የአገልግሎት ብቃት እና ቴክኖሎጂ በየጊዜው እየጨመሩ ገበያውን በሚቆጣጠሩበት ውድድር ውስጥ ከቷቸዋል፡፡
ባለፈው ሰሞን የእንግሊዙ የስፖርት ትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያ UMBRO አምብሮ ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ የተቀላቀለው ከላይ ከተዘረዘሩት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር ሊያያዝ የሚችል ነው፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ ልዩ ትንታኔ የተዘጋጀው የእግር ኳስ ማሊያና ሌሎች ትጥቆች በኢትዮጵያ እና በዓለም ዙርያ የደረሱበትን ደረጃ ለማስተዋወቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያን  ኳስ የተቀላቀለው አምብሮ
አምብሮ ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ ያደረገው ግዙፉ የእግር ኳስ ትጥቆች አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን የኢትዮጵያን እግር ኳስ በይፋ ሲቀላቀል ከኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር ለ4 ዓመታት በሚቆይ ውል ለመስራት በመስማማቱ ነው፡፡ በትጥቅ አቅርቦትና ተያያዥ ተግባራት ለመንቀሳቀስ የተደረገው ስምምነት በብዙ መልኩ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከሁለት ሳምንት በፊት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ እንደተገለፀው አስቀድሞ ከጣሊያኑ የትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ኤሪያ ጋር ፌደሬሽኑ የነበረው ውል እንዲቋረጥ ከወሰነ በኋላ በምትክነት የሚሰራውን ኩባንያ ለማግኘት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ስለሆነም የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት በቅድሚያ  በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ስድስት ኩባንያዎችን (በዝርዝር ባይጠቀሱም) በቅርበት በማነጋገር እቅዶቻቸውን አጢነዋል፡፡ አምብሮ ያቀረበው እቅድ ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ መካከል ተመራጭ በፌደሬሽኑ በኩል ተቀባይነት ያገኘው በተለያዩ ሁኔታዎች ነው፡፡ በመጀመርያ ያለምንም ክፍያ በነፃ በጣም ብዙ ምርቶቹን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለያዩ ደረጃዎች እንደሚያቀርብ ማስታወቁ ነው፡፡ በሌላ በኩል አምብሮ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በሚያቀርባቸው የስፖርት ትጥቆች ዲዛይን ላይ የፌደሬሽኑን ሃሳብ መጋበዙ እንዲሁም በናሙና መልክ የሚያቀርባቸውን ምርቶች  በስራ አስፈፃሚዎቹና  የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ማስገምገሙ ስምምነቱን አፋጥኖታል፡፡ አምብሮ ከፌዴሬሽኑ ጋር በሚገባው ውል መሰረት በዓመት ለሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች የሚሆኑ ከ900 በላይ ልዩ ልዩ ትጥቆችን ያለ ምንም ክፍያ ሲያቀርብ፤ ፌዴሬሽኑ አቅርቦቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባበትን  ወጪ ሊሸፍን የስፖርት ኮሚሽን ደግሞ ቀረጡን ሊከፍል ታቅዷል፡፡  በተጨማሪ በሁለቱም ጮታዎች እና በሁሉም የእድሜ ደረጃዎች ኢትዮጵያን ለሚወክሉ ስድስቱም ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ ትጥቅ የሚያቀርብ ይሆናል። ከማሊያዎቹ ባሻገር  ቱታዋች፣ የመመገቢያ ልብሶች፣ ካሶቲኒዎች፣ ቦርሳዎች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የስፖርት ቁሳቁሶችንም አምብሮ ለፌደሬሽኑ  የሚሰጥ ይሆናል፡፡
አምብሮ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ሲቀላቀል ዋናው ትኩረቱ ከአገሪቱ የህዝብ ብዛት አኳያ ተጠቃሚ የሚሆንባቸውን እድሎች በማገናዘብ ይመስላል፡፡ የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በመግለጫቸው እንዳነሱት ዓለም አቀፉ ኩባንያ ለደጋፊዎች በሚሸጡ ማሊያዎች የተወሰነ ገቢ ለማግኘት እቅድ አለው፡፡  ለደጋፊዎች ከሚያቀርባቸው ማሊያዎች ሽያጭ ላይ ተካፋይ ለመሆንም የእግር ኳስ  ፌደሬሽኑ ተደራድሮ የተሳካለት ሲሆን፤ ማሊያው በአገር ውስጥና በየትኛውም የዓለም ክፍል  ሲሸጥ በሚኖረው ድርሻ ስምምነት መኖሩም ተገልጿል፡፡ ስለሆነም የብሄራዊ ቡድን ማሊያዎች ሽያጭ ላይ በአምብሮ ከሚቀርበው ምርት ሽያጭ የፌደሬሽኑ ድርሻ በ3% ዘንድሮ ጀምሮ በየዓመቱ በ1% እጨመረ 2022 ላይ 6% እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡
ባለ ጥምር አልማዝ ብራንድ ያለው አምብሮ በእግር ኳስ ትጥቆች አምራችነትና አቅራቢነት ከ94 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበተ ሲሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለመጀመርያ ጊዜ በይፋ የተዋወቀው  ከ4 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱ የብሄራዊ ቡድን፤ የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለቦች ተጨዋቾች የነበሩትን አዳነ ግርማና አስቻለው ግርማ ስፖንሰር አድርጓቸው  ነበር፡፡ ሁለቱ ተጨዋቾች የአምብሮን ትጥቆችን እንዲያስተዋውቁ ሲመረጡ፤ ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ  የአፍሪካ ዋንጫን በመሳተፋቸውና ከዚያም የቻን ሻምፒዮናዎችን አከታትለው በመጫወት የነበራቸውን አስተዋፅኦ ለማድነቅ ነበር፡፡ ተቀማጭነቱን በማንቸስተር ከተማ  አድርጎ በዓለም ዙርያ የሚንቀሳቀሰው አምብሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የእግር ኳስ የስፖርት ትጥቁን ያመረተው በ1934 እ.ኤ.አ ላይ ለማንቸስተር ሲቲ   ሲሆን ክለቡ በዚሁ ዓመት የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማሸነፉ ከእንግሊዝ እግር ኳስ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ያስተዋወቀው ክስተት ሆኖለታል። ከዚያ ታሪክ በኋላ በ1958 እ.ኤ.አ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን፣ በ1966 እ.ኤ.አ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫዎችን ሲያሸንፉ ያሰለፏቸውን ቡድኖች የአምብሮን የስፖርት ትጥቆች አልብሷቸዋል፡፡ በ1999 እ.ኤ.አ ላይ በሦስት ዋንጫዎች በእንግሊዝና አውሮፓ እግር ኳስ ላይ የነገሰው የማንችስተር ዩናይትድ ቡድን ዋና ትጥቅ አምብሮ ያመረተው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት  ለግብፁ ታላቅ ክለብ አልሃሊ የስፖርት ትጥቆችን የሚያቀርበው ኩባንያው የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከመቀላቀሉ በፊት  ከቦትስዋናና ዚምባቡዌ ጋር የሚሰራባቸውን ስምምነቶች ማድረጉ ታውቋል፡፡ በያዝነው የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ከኤቨርተንና ዌስትሃም እንዲሁም ከሆላንዱ ፒኤስቪ ክለቦች ጋር የሚሰራው ይህ ኩባንያ አስቀድሞ በነበሩት ውሎች ደግሞ የብራዚልና እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም የማንቸስተር ዩናይትድ  ሙሉ የስፖርት ትጥቆችን የሚያቀርብ ነበር፡፡
ከኢትዮጵያ  ኳስ እንዲርቅ ውል የፈረሰበት የጣሊያኑ ኤሪያ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የጣሊያኑ የስፖርት ትጥቆች አምራችና ኩባንያ ኤሪያ  ውላቸውን በስምምነት የፈፀሙት ከ3 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ከኤርያ በፊት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የስፖርት ትጥቆችን በኦሎምፒክ ኮሚቴ በኩል የሚያቀርበው የጀርመኑ አዲዳስ ነበር፡፡ ከአዲዳስ ጋር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የነበረው ግልፅ ያልሆነ ትስስርን በማቋረጥ ያለፉት 2 ዓመታት ከጣልያኑ የትጥቅ አምራች ኩባንያ ኤርያ ጋር እየተሰራ ነበር፡፡ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ  በተለያዩ ምክንያቶች ውሉን ሲያፈርስ ቀሪ የሁለት ዓመት ኮንትራት ከኤርያ ጋር ይቀረዋል፡፡ ፌደሬሽኑ ከኤሪያ ጋር  በነበረው ስምምነት በዓመት 90ሺ ዩሮ ክፍያን ይፈፅም የነበረ ሲሆን፤ የትጥቅ አቅርቦቱ በሁለቱ ሴትና ወንድ ዋና ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ የተወሰነና ለታዳጊና ወጣት ቡድኖች የሚሆኑትን ትጥቆች ፌደሬሽኑ በግዢ ከጣሊያኑ ኩባንያ እንዲቀበል የሚያስገድድ ውል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ፌደሬሽኑ ከኤሪያ ጋር የነበረውን የውል ስምምነት ያቋረጠባቸው የተለያዩ ምክንያቶች በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች ተብራርቷል፡፡ የኤሪያ የስፖርት ትጥቆች በደረጃቸው እየወረዱ መምጣታቸውና የነበሩ ጉድለቶችን ባለመስተካከላቸው፤ አቅርቦቶች በሚያስፈልጉበት ቀነገደብ አለመድረሳቸው እንዲሁም የዲዛይን ጥራታቸውና ውበታቸው የስፖርት ቤተሰቡን አለማስደሰታቸው የውል ስምምነቱን ለማፍረስ አስገዳጅ ምክንያቶች ሆነዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከኤርያ ጋር የነበረውን ውል 2 ዓመታት እየቀሩት በማፍረሱ  የካሳ ክፍያ እንዲከፍል ያደርገዋል፡፡ ኤሪያም ፌደሬሽኑ ውሉን ባለማክበሩ የውል ማፍረሻ ክፍያ እንዲፈፅምለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የስራ አስፈፃሚው አባላት በመግለጫቸው እንዳነሱት በመደበኛው ውል ለሚቀሩት ሁለት ዓመታት እስከ 180ሺ ዩሮ እንዲከፍል ፌደሬሽኑ ቢስማማም በውሉ መሰረት ስምምነት ያለጊዜው ሲፈርስ አፍራሹ ወገን የሚከፍለው 100 ሺ ዩሮ በመሆኑ ይህን ክፍያ ለመፈፀም ወይንም በሚቻለው ድርድር ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የዋልያዎቹ ስኬታማነት ያገዘፈው አረንጓዴና ቢጫ ሸንተረር ማሊያና ሌሎች  መዘበራረቆች
ከስድስት ዓመታት በፊት ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ እንዲሁም በቻን ሻምፒዮናዎች በተከታታይ መሳተፋቸው  ማሊያቸውን ተወዳጅ አድርጎት ነበር፡፡ በወቅቱ ለብሄራዊ ቡድን  የስፖርት ትጥቆች በኦሎምፒክ ኮሚቴ በኩል በአዲዳስ ተመርተው የቀረቡ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን ከዋልያዎቹ አህጉራዊ ስኬት ጋር በተያያዘ ልዩ ገበያ ሊፈጥሩ ችለዋል፡፡ በተለይ  አረንጓዴና ቢጫ  ሸንተረር የነበረውና በሁለት ክንዶች ላይ ቀይ ቀለም ያረፈበት ማሊያቸው ያገኘው ተወዳጅነት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ትህ ማሊያ እና ሌሎች ተለዋጭ ማሊያዎች  ከዋሊያዎቹ ስኬት ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ በቀን እስከ 250 ማሊያዎች መቸብቸባቸው ይታወሳል፡፡ ማሊያዎቹ ዋጋቸውም እንደ የጥራት ደረጃው ከ50-200 ብር ይሸጥ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ የተለያዩ አስመጪና ላኪ ኩባንያዎችም ከቻይና እስከ 10,000 ማሊያዎችን በማስመጣት ትርፋቸውን ዝቀውበታል፡፡ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑም በ75 ብር ሂሳብ ከ15,000 ማሊያዎችን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ስልጣን የተረከቡ አስተዳደሮች  በማሊያው ላይ ምንም አይነት ቋሚ ውሳኔ ማሳለፍ ሳይችሉ ቆይተዋል። ይህን ተከትሎም በተለያዩ ጊዜያት ከሜዳ ውጪና በሜዳ ላይ ቡድኑ በሚታጠቀው ማሊያ መዘበራረቅ ተስተውሏል፡፡  አንዳንድ ጊዜ ታዋቂውን ባለ አረንጓዴ ቢጫ ሸንተረር ማሊያ ሌላ ጊዜ ሙሉ ቢጫ አንዳንዴ ደግሞ ሙሉ አረንጓዴ ማሊያ በመታጠቅ ብሄራዊ ቡድኑ እየተሰለፈ በማየረካ ውጤት ሲዳክር ነበር። ከ4 ዓመታት በፊት ሩዋንዳ ባስተናገደችው 4ኛው የቻን ሻምፒዮና ላይ የነበረውን ክስተት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ያኔ ከካሜሮን ጋር በተደረገው ጨዋታ ዋልያዎቹ የለበሱት ባለ ሙሉ ቢጫ ቀለም ማሊያ ለትችት አጋልጧል።  በዚሁ ማሊያቸው ላይ ያለአግባብ የተለጠፈው የአገር ስም ደንቡን በጣሰበት ምክንያት  አጨቃጫቂ ሁኔታዎች ፈጥሯል፡፡ በወቅቱ ዋልያዎቹ የለበሱት ማሊያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን ደንብ ተጣርሷል ተብሎ  አላግባብ ተለጥፎበት የነበረው የአገር ስም በነጭ ተሰርዞ ግጥሚያው መደረጉ ይታወሳል፡፡ በዚያን ሰሞን ይፋ ካልሆኑ ምንጮች የወጡ ዘገባዎች ይህኑ ችግር ለመቅረፍ የተነሱ ይመስሉ ነበር፡፡ በተለይ በአውስትራሊያ የሚገኝ የትጥቅ አምራች ኩባንያ AMS አማካኝነት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚሆን አዲስ የማሊያ ዲዛይን እንደቀረበ ተዘግቦ ነበር፡፡ የዋሊያዎቹ ቁልፍ ተጨዋች  የነበረው ጋቶች ፓኖም ለብሶት በሶሻል ሚዲያዎች ያስተዋወቀውን ማሊያ አስመልክቶ በወቅቱ ሶካአፍሪካ እንደዘገበው  ማቲው ዎልፍ በተባለ ሰው የቀረበ ዲዛይን እንደሆነ ተጠቅሶ ነበር፡፡ ይሁንና ማሊያው በስፖርት ቤተሰቡ ተቀባይነት እንደማያገኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሰራጩ  በርካታ የተቃውሞ  አስተያየቶች በመረጋገጡ የኢትዮጵያን ኳስ ለመቀላቀል የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡   ዋናው ምክንያት ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑ መደበኛ መለያዎች የሆኑትን የባንዲራ ቀለማት  በሚያረካ ሁኔታ ዲዛይኑ አለመጠቀሙ ነበር፡፡ ኤኤምኤስ የተባለው የአውስትራሊያ ኩባንያ ያቀረበው የአዲስ ማሊያ ፕሮፖዛል  ቡኒ ቀለም ከማብዛቱም በላይ የኢትዮጵያ ባህላዊ ጥለቶች አግንኖ ያቀረበ ስለነበር ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይ በተለያየ የእድሜ ደረጃ እና ሁለቱም ፆታዎች ለሚንቀሳቀሱ ብሔራዊ ቡድኖች የሚሆኑ ማሊያዎች ቋሚ ቀለማት እና መለያ  እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትጥቅ አምራችና አቅራቢ አምብሮ የሰራው ዲዛይን በይፋ አልተዋወቀም፡፡ በፈደሬሽን አስተዳደር በኩል አብዛኛውን የስፖርት ቤተሰብ የሚያረካ የማሊያ ዲዛይን ሊተዋወቅ እንደሚችል በተለያየ መንገድ  ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም አምብሮ በሚያቀርበው ትጥቅ የኢትዮጵያ ልዩ መለያዎች የሆኑ የባንዲራ ቀለማትን በውበት ያዋሀደ ዲዛይን እንደሚያንፀባርቅ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ክለቦች  የስፖርት ትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች፤ የማሊያ ሽያጭና ስፖንሰርሺፕ
በኢትዮጵያ ስፖርት በተለይም በእግር ኳስ ለረጅም የውድድር ዘመናት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የሚታወቀው የጀርመኑ አዲዳስ ኩባንያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለዓመታት ለተለያዩ ክለቦች እና ቡድኖች ትጥቅ በማቅረብ እነማን ይሰሩ እንደነበር ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት የሚከብድ ነው፡፡ ሁለቱ የዓለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች የጀርመኑ አዲዳስ እና የአሜሪካው ናይኪ ከኢትዮጵያ ታላላቅ አትሌቶች ጋር ዛሬም ድረስ በተለያዩ ስምምነቶች እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከሁለቱ ባሻገር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ልዩ ልዩ ትጥቆችን በማቅረብ  የሚጠቀሱ ኩባንያዎች የመጡት ባለፉት 5 የውድድር ዘመናት ነው፡፡ የጣሊያኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ኤርያ፤ የቱርኩ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ማራቶን፤ የአውስትራሊያው ኤኤምኤስ ይገኙበታል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ለሚወዳደሩ ክለቦች ትጥቆችን በማቅረብ ሲሰሩ የቆየቱን ኩባንያዎች በዝርዝር አጥንቶ የሚያቀርብ ሪፖርት መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በስፖርት የተሟላ ትጥቅ አቅርቦት በመስራት አንጋፋዎቹ ክለቦች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በማሊያዎቻቸው ሽያጭ እና ስፖንሰርሺፕ በመስራት ተጠቃሚ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከ84 ዓመታት በላይ እድሜ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሊያው ላይ ስፖንሰሮችን በየጊዜው በመለጠፍ እና አዳዲስ ፋሽኖችን ለደጋፊዎቹ በማቅረብ በአርአያነት የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ ጊዮርጊስ የማሊያ ላይ ስፖንሰር መጠቀም የጀመረው በአዲስ መልክ በተደራጀ ማግስት በ1989 ዓ.ም ነው፡፡ ክለቡ በታሪኩ የመጀመሪያውን የማሊያ ላይ ውል ስምምነት የተፈራረመው ከሞሃ ለስላሳ መጠጥ ኢንዱስትሪ ጋር በሦስት መቶ ሃምሳ ሺ ብር ነው፡፡  በየጊዜው የክፍያ መጠኑን በማሳደግ የፔፕሲ ማስታወቂያን በማሊያው ደረትና ጀርባ ላይ  ከ10 ዓመት በላይ ለጥፎ ተጫውቷል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ደግሞ በማሊያው ደረት ላይ ከአዲስ ኩባንያ ጋር በአዲስ ውል ስምምነት ለመስራት ተፈራርሟል። የፔፕሲን ዓርማ በማሊያው እጅጌ ላይ ለጥፎ በመጫወት ላይ ሲሆን  አዲሱ የማሊያ ስፖንሰር ደርባ ሲሚንቶ ነው።  ከደርባ ሲሚንቶ ጋር በፈፀመው የአምስት ዓመት ኮንትራት ውል መሰረት   በዓመት 5 ሚሊዮን  ብር እንደሚከፈለው ይነገራል፡፡ ከስፖርት ትጥቅ ጋር በተያያዘ የሚጠቀስ ሌላው ፈርቀዳጅ ሁኔታ ባለፈው ዓመት  የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከኤርያ ጋር ያደረገው የሶስት አመታት የውል ስምምነት ነው፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ክለቦች የሚደረጉ ጅምር ጥረቶችንም ማንሳት ይቻላል፡፡ ስሑል ሽረ፤ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከራያ ቢራ ጋር የማሊያ ስፖንሰርሺፕ ስምምነት የተፈራረሙት በዘንድሮው የውድድር ዘመን መግቢያ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ዳሽን ቢራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ ዋልያ ቢራ፣ ሜታ ቢራ፣ ሐረር ቢራ፣ ሐበሻ ቢራ በማሊያ እና በሌሎች በስፖንሰር ስምምነቶች እንዲሁም በክለብ ባለቤትነት በኢትዮጵያ እግርኳስ ሲሳተፉ የቆዩ ናቸው፡፡ በያዝነው የውድድር ዘመን ዳሽን ቢራ የወልዲያ እና ፋሲል ከተማ፣ ሐበሻ ቢራ የኢትዮጵያ ቡና የማሊያ ስፖንሰር እንደሆኑ ሲታወቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አጋሮች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የነበረው የገበያ ፉክክር…
ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለተሳተፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ የስፖርት ትጥቆችን በማቅረብ የሰሩት ስምንት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ኩባንያዎቹ በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ በሚያቀርቧቸው የስፖርት ትጥቆች  ዓለም አቀፍ የገበያ ትኩረት የሚያገኙ ሲሆን ከ12.6 እስከ 14.5 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ የሚያገኙበት ይሆንላቸዋል። በዓለም ዋንጫው የሚሳተፉ ብሄራዊ ቡድኖችን ሙሉ የስፖርት ትጥቆችን በማቅረብ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ደግሞ ሁለቱ ግዙፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች አዲዳስ ከጀርመን እንዲሁም ናይኪ ከአሜሪካ ናቸው፡፡ በ21ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ አዲዳስ የ12 ብሄራዊ ቡድኖችን ናይኪ ደግሞ የ11 ብሄራዊ ቡድኖችን ሙሉ የስፖርት ትጥቅ አቅርበዋል። ከሁለቱ ኩባንያዎች ባሻገር ፑማ፤ አምብሮ፤ ኒው ባላንስ፤ ኤርያ፤ ሃመል እና ኡሁል ስፖርት የተባሉት ትጥቅ አምራች እና አቅራቢያዎች ከገበያው ድርሻ ነበራቸው፡፡ ፑማ ለ4 ብሄራዊ ቡድኖች እንዲሁም ኒውባላንስ ለሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ የስፖርት ትጥቅ ያቀረቡ ሲሆን አምብሮ፤ ሃመል፤ ኢርያ እንዲሁም  ኡሁል ስፖርት በነፍስ ወከፍ አንዳንድ ብሄራዊ ቡድኖችን በመያዝ በዓለም ዋንጫው ሙሉ የስፖርት ትጥቅ በሚያቀርቡበት ውሎች ሰርተዋል። በዓለም ዋንጫው ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገቡት የብሄራዊ ቡድን ማሊያዎች የጀርመን፤ ሜክሲኮ፤ ፔሩ፤ ፈረንሳይ፤ ናይጄርያ፤ ኮሎምቢያ፤ ብራዚል፤ ስፔን፤ ፖላንድና ግብፅ ናቸው፡፡
ታላላቅ የስፖርት ትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎችና የአውሮፓ እግር ኳስ
በአውሮፓ እግር ኳስ ባለፉት 10 ዓመታት የስፖርት ትጥቆች ለኢንዱስትሪው ልዩ የገቢ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ ዋናው ምክንያት ለደጋፊዎች የሚቀርቡ ማሊያዎች ሽያጭ በየጊዜው እድገት ማሳየቱ እና በማሊያዎች ስፖንሰርሺፕ የረጅም ጊዜ ውሎችን በመፈፀም የሚገኙ ገቢዎች ከፍተኛውን ድርሻ በማስመዝገባቸው ነው፡፡ ከአውሮፓ እግር ኳስ በተለይም በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች ከታላላቅ የስፖርት ትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች ምናልባትም ከ80% በላይ የሚሆነው የገበያ ድርሻ የያዙት የጀርመኑ አዲዳስ እና የአሜሪካው ናይኪ ናቸው፡፡  ባለፉት 10 ዓመታት በአውሮፓ የክለብ ውድድሮችና የውስጥ ሊጎች ዋንጫዎችን በመሰብሰብ እና ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ከተሳካላቸው ክለቦች ጋር በመስራትም ሁለቱ ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከአውሮፓ ስኬታማ የእግር ኳስ ክለቦች ጋር በመስራት 51% ድርሻ ያለው ናይኪ ሲሆን የአዲዳስ ድርሻው 28.5% ነው፡፡ እነ አምብሮ እና ፑማ  5.7% ድርሻ ነው ያላቸው፡፡
በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐች ማለትም በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ በስፔን ላሊጋ፤ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ፤ በጣሊያን ሴሪኤ እና በፈረንሳይ ሊግ 1 ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል ከ18 ክለቦች ጋር በመስራት ቀዳሚ የሚሆነው ናይኪ ሲሆን፣ አዲዳስ ከ15 ክለቦች፣ ፑማ ከ10 ክለቦች፣ አምብሮ ከ8 ክለቦች ጋር የስፖርት ትጥቆችን በማቅረብ እየሰሩ ይገኛል፡፡ አዲዳስ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ እና የተለያዩ የውድድር ደረጃዎች ባለው አቅርቦት ሙሉ ሙሉ ገበያውን የተቆጣጠረ ቢሆንም በእንግሊዝ በጣሊያን፣ በስፔንና በፈረንሳይ ሰፊ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ናይኪ ነው፡፡
አምብሮ እና ሌሎች ኩባንያዎች በእንግሊዝ እግር ኳስ
ባለፉት 50 ዓመታት በእንግሊዝ እግር ኳስ በተለያዩ ደረጃዎች ከሚወዳደሩ ከ90 በላይ ክለቦች ጋር በስፖርት ትጥቆች አቅራቢነት ከ200 በላይ ኩባንያዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ይህን የሚያመለክተው የእግር ኳስ ትጥቅ አምራቾች በእንግሊዝ  እግር ኳስ ያላቸውን ተሳትፎ ለማመልከት Football kits Manufacturers Survey 2017 በሚል ርእስ የተዘጋጀ ሪፖርት  ነው፡፡  በሪፖርቱ መሰረት ከዓለማችን ግዙፍ የስፖርት ትጥቅ አምራቾች መካከል  በእንግሊዝ እግር ኳስ ከብዙ ክለቦችና ቡድኖች ጋር በመስራት አምብሮ (UMBRO) ግንባር ቀደም ነው።  ከፕሪሚዬር ሊግ አንስቶ እስከ ታችኛው ዲቪዚዮን ለሚወዳደሩ ከ80 በላይ ክለቦች የስፖርት ትጥቆችን  ላለፉት 50 አመታት ለማቅረብ አምብሮ ቀዳሚው ሲሆን አዲዳስ ከ60 ናይኪ ከ37 እንዲሁም ፑማ ከ35 የእንግሊዝ ክለቦች ጋር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
በእንግሊዝ እግር ኳስ በስፖርት ትጥቆች አቅራቢነት ለ46 የውድድር ዘመናት በመስራት በ1ኛ ደረጃ የሚጠቀሰው አምብሮ ሲሆን አዲዳስ በ42 የውድድር ዘመናት፣ አዲምራል ለ41 የውድድር ዘመናት ፤ ናይኪ ለ28 የውድድር ዘመናት እንዲሁም ፑማ ለ24 የውድድር ዘመናት የስፖርት ትጥቆችን ለማቅረብ ሰርተዋል፡፡   
 የማሊያዎች ስፖንሰርሺፕና ሽያጭ  በዓለም እግር ኳስ
በዓለም እግር ኳስ ላይ የስፖርት ትጥቆች አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች በማሊያዎች ስፖንሰርሺፕ እና ሽያጭ  ከፍተኛ የገቢ መነቃቃት ፈጥረዋል፡፡ በተለይ በማሊያዎች ስፖንሰርሺፕ የሚገኘው ገቢ በየውድድር ዘመኑ በመጨመር ላይ ነው፡፡ የአውቶሞቢል፣ የጐማዎችና መለዋወጫ አምራችና አቅራቢዎች፤ ሎተሪ አወዳዳሪና አቋማሪዎች ፤ የቴሌኮም ኩባንያዎች፣ የጉዞና የቱሪዝም ድርጅቶችና ኩባንያዎች፣ የባንክና የፋይናንስ ተቋማት፣ መኪና አምራቾች፣ አየር መንገዶች የአይቲና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በማሊያዎች ስፖንሰርሺፕ እየሠሩ ከሚገኙት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ባለፉት 10 ዓመታት በአምስቱ  የአውሮፓ ታላላቅ ሊጐች በማሊያ ስፖንሰርሺፕ የተንቀሳቀሰውን መዋዕለ ንዋይ በማስላት በኔልሰን ስፖርትስ የተዘጋጀው ልዩ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፉት 10 ዓመታት የተንቀሳቀሰው ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ በኔልሰን ስፖርትስ በቀረበው ዝርዝር መሰረት በማሊያዎች ስፖንሰርሺፕ ከሚገኘው ገቢ በጉዞ፣ ቱሪዝም እና ሆቴል 1.14 ቢሊዮን ዶላር፤ በባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት 1.312 ቢሊዮን ዶላር፤ በመኪና አምራቾች 797.7 ሚሊዮን ዶላር፣ በአቋማሪና ሎተሪ አወዳዳሪ ኩባንያዎች 633 ሚሊየን ዶላር፤ በኃይል ላይ በሚሰሩ ኩባንያዎች 564 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በቴሌኮም ኩባንያዎች 552 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏል፡፡
በማሊያ ስፖንሰርሺፕ ኢንቨስት ከተደረገው መዋዕለ ንዋይ በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ድርሻ  የጀርመን ኩባንያዎች ያወጡት 1.36 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ኩባንያዎች 1.026 ቢሊዮን ዶላር፣ የእንግሊዝ ኩባንያዎች 844 ሚሊዮን ዶላር፣ የአሜሪካ ኩባንያዎች 668 ሚሊዮን ዶላር፤ የጣሊያን ኩባንያዎች 648 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የሆላንድ ኩባንያዎች 511 ሚሊዮን ዶላር በማሊያ ስፖንሰርሲፕ ወጭ ማድረጋቸውን የኔልሰን ስፖርት ዎርልድ ፉትቦል ሪፖርት አረጋግጧል፡፡
“ብራንድ ፋይናንስ ፉትቦል 50” የተባለ ጥናታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ደግሞ በአውሮፓ እግር ኳስ በከፍተኛ ደረጃ ከሚወዳደሩ ከ40 በላይ ክለቦች ጋር በማሊያ ስፖንሰርሺፕ 6 አየር መንገዶች፣ 6 መኪና አምራቾች፣ 8 የፋይናንስ ተቋማት፣ 7 አቋማሪዎች 6 የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ዓለም አቀፍ ምርቶች፣ 5 የቴክኖሎጂ እና የቴሌኮም ኩባንያዎች እየሰሩ ናቸው፡፡  ኢምሬትስ ከ3 የአውሮፓ ክለቦች ከሪያል ማድሪድ፣ ፒ.ኤስ ጂና አርሰናል ጋር በመስራት በዓመት 158 ሚሊዮን ዶላር፣ ቼቭሮሌት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር 71 ሚሊዮን ዶላር፣ ሬካቶን ከባርሴሎና ጋር 67 ሚሊዮን ዶላር፣ ኢትሃድ ከማን ሲቲ ጋር 59 ሚሊዮን ዶላር፣ ዮካሃማ ከቼልሲ 56 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ በመክፈል በማሊያ ስፖንሰርሺፕ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
በ2019  በማሊያ አቅርቦት ከፍተኛውን ገቢ ከሚያገኙ ክለቦች በተለይ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በፈፀሟቸው ውሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ሪያል ማድሪድ ከጀርመኑ የትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ጋር ለ10 ዓመት የፈፀመው 1.26 ቢሊዮን ዶላር  የውል ግዙፉ ሲሆን በዓመት ከትጥቅ አምራች ኩባንያ ከፍተኛውን ክፍያ በማግኘት ግን የቅርብ ተቀናቃኙ ባርሴሎና የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ ባርሴሎና ከአሜሪካው የትጥቅ አምራች ናይኪ ጋር የሚሰራበት ውል እስከ 2028 እኤአ የሚቆይ ሲሆን በዓመት 140 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያገኝበት ነው፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ ከአዲዳስ ጋር እስከ 2025  እኤአ በሚቆይ ውል በዓመት 75 ሚሊዮን ፓውንድ፤ ቼልሲ ከናይኪ ጋር በዓመት  እስከ 2032 እኤአ በሚቆይ ውል በዓመት 60 ሚሊዮን ፓውንድ  እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ከአዲዳስ ጋር  እስከ 2020 እኤአ በሚቆይ ውል በዓመት 34 ሚሊዮን ፓውንድ እየተከፈላቸው ነው፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው በማሊያ ስፖንሰርሺፕ ከፍተኛ ገቢ በሚያስገኝ ውል የሚንቀሳቀሱ 10 የስፖርት ክለቦች ናቸው፡፡
ሪያል ማድሪድ በኤምሬትስ  — $80 million በዓመት
ማንችስተር ዩናይትድ በቼቭሮሌት — $68 million በዓመት እስከ 2021
ባርሴሎና በራኩቴን — $60 million በዓመት እስከ 2022
አርሰናል በኤምሬትስ  — $56 million በዓመት እስክ 2024
ቼልሲ በዮኮሃማ   — $51 million በዓመት እስከ  2020
ሊቨርፑል በስታንዳርድ ቻርተር — $50 million በዓመት እስከ 2023
ማንችስተር ሲቲ በኢትሃድ — $48 million በዓመት ዘንድሮ የሚያበቃ
ቶትንሃም በኤአይኤ— $45 million በዓመት እስከ 2022
ባየር ሙኒክ በደች ቴሌኮም  — $34 million በዓመት እስከ 2023
ፓሪስ ሴንተዠርመን በኤሚሬትስ  — $32 million በዓመት ዘንድሮ የሚያበቃ
ከማሊያዎች የስፖንሰርሺፕ ገቢ ባሻገር ለደጋፊዎች በሚቀርቡ ማሊያዎች ሽያጭም የዓለም እግር ኳስ ኢንዱስትሪ ተጠቃሚ እየሆነም መጥቷል፡፡ በዓለም እግር ኳስ የስፖርት ተከታታዮችና ደጋፊዎች በውድድር ዘመን መጀመሪያ/አጋማሽ እና መጠናቀቂያ  ማሊያዎችንና ሌሎች የስፖርት ትጥቆችን የሚገዙበት ልዩ ባህል በመላው ዓለም በመስፋፋቱ ነው፡፡  ይህም የስፖርት ትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች በየዓመቱ በተለያየ አዳዲስ ፋሽንና ቴክኖሎጂ ማሊያዎችን በማምረትና በዓለም ዙርያ  አቅርቦቱን በማቀላጠፍ እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፡፡
በዓለም እግር ኳስ በየዓመቱ ከፍተኛ የማሊያ ሽያጮችን በማስመዝገብ ከ1 እስከ 10ኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ክለቦች በአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች የሚወዳደሩት ናቸው፡፡ ታላላቆቹ የስፖርት ትጥቆች አምራች እና አቅራቢ ኩባንያዎች በየዓመቱ ለገበያ የሚያቀርቧቸውን የማሊያዎች ብዛት እና አጠቃላይ ገቢ በግልፅ የሚያሰፍሩት መረጃ ባይኖራቸውም ፤ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሪያልማድሪድ ዓይነት ክለቦች ከ1.2 እስከ 1.5 ሚሊዮን ማሊያዎችን በየዓመቱ እንደሚሸጡ እና በዚህም በየዓመቱ ከ10-18 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ። በማሊያ ሽያጭ ገበያውን የሚመራው በየዓመቱ እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገባው የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ነው፡፡ በማሊያ ሽያጭ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች እስከ 5.14 ሚሊዮን ማሊያዎችን በመሸጥ በ1 ደረጃ የሚጠቀሱ ሲሆን የስፔን ላሊጋ 3.10 ሚሊዮን፣ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 2.02 ሚሊዮን፣ የፈረንሳይ ሊግ 1 1.22 ሚሊዮን እንዲሁም የጣልያን ሴሪኤ ክለቦች 1.18 ሚሊዮን ማሊያዎችን በየዓመቱ እየሸጡ ናቸው፡፡  በ2018 የክለቡን ማሊያ ብብዛት በማሸጥ አንደኛ ደረጃ የተሰጠው የማንችስተር ዩናይትዱ አሌክሲ ሳንቼዝ ሲሆን ፖል ፖግባ፤ ሃሪ ኬን ከቶትንሃም፤ መሀመድ ሳላህ ከሊቨርፑል እንዲሁም ኤዲን ሃዛርድ ከቼልሲ እሰከ አምስት ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው ከአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች መካከል በየዓመቱ ከፍተኛ የማሊያ ገቢ እና ብዛት የሚያስመዘግቡት ክለቦች ናቸው፡፡
በዓመት የሚሸጡ ማሊያዎች ብዛት
ማንችስተር ዩናይትድ  2.5 ሚሊዮን
ሪያል ማድሪድ 2.3 ሚሊዮን
ባርሴሎና 1.98 ሚሊዮን
ቼልሲ 1.65 ሚሊዮን
ባየር ሙኒክ 1.5 ሚሊዮን
አርሰናል 1.23 ሚሊዮን
ጁቬንትስ 850ሺ
ሊቨርፑል 705ሺ
ፓሪስ ሴንትዥርመን 685ሺ
ኤሲ ሚላን 650 ሺ
የመረጃ ምንጮች
Soccerethiopia.com
Mitsui & Co. Global Strategic Studies Institute Monthly Report December 2017
FOOTBALL KIT MANUFACTURERS SURVEY 2017 Chris Oakley
NIELSEN SPORTS WORLD  FOOTBALL REPORT 2018
Kit Manufacturers: The League table
GLOBAL SHIRT SALES LEAGUE

Read 7100 times