Print this page
Sunday, 10 March 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “ማን ነው የካደው? ማነውስ የተካደው?”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


• የዲሞክራሲ ሂደትን የማይደግፍ ድርጅት፣ በመጨረሻ ራሱን ነው የሚያጠፋው
• ትግራይ ውስጥ ገብተን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከባድ ሆኖብናል
• በትግራይ አደገኛ የፖለቲካ አካሄድና የህዝብ አፈና ነው ያለው

በፖለቲካ የለውጥ ሂደቱ ተማምነው ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነውና ከተቋቋመ ከ24 አመት በላይ ያስቆጠረው “የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር” ምክትል ሊቀ መንበር ኢ/ር ግደይ ዘርአጽዮን፤ በትግራይ ክልል የፖለቲካ አቅጣጫ፣ በህውሓት ወቅታዊ አካሄድ፣ በጎሳ ፖለቲካ እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

ወደ ትግራይ ተንቀሳቅሳችሁ፣ ህዝብን ለማወያየትና ለማደራጀት ሞክራችኋል?
ህውሓት አሁን ያንን አካባቢ ከድሮው በበለጠ ሁኔታ ተቆጣጥሮታል፡፡ ብሄርተኝነትን ባልተገባ መንገድ በመቀስቀስ ህዝቡን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ የወልቃይት የራያ ጥያቄዎች፣ የህዝቡን ቀልብ ለመሳብ ጠቅሟቸዋል፡፡ ከአማራ ክልል ጋር የገቡበት እሰጣገባ ለእነሱ ጠቅሟቸዋል፡፡ ወደዚህ ዓይነት ፍጥጫ መግባቱ ጥቅም የሌለው ከመሆኑም በላይ ለህውሓቶች ጥይት እንደ ማቀበል ነው። አሁን የጦርነት መንፈስ ነው በትግራይ ያለው ማለት ይቻላል፡፡ “በኤርትራ በኩል መጡብህ፣ በዚህ መጡብህ፣ ተከበሃል” እያሉ ነው ህዝቡን አስጨንቀው የያዙት፡፡ ሌላው የሚጠቀሙበት ፕሮፓጋንዳ፣ ህገ መንግስታችን  እየተጣሰ ነው የሚል ነው፡፡ በሶማሌ ክልል አብዲ ኢሌ ሲያዝ፣ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ተገባ የሚል ፕሮፓጋንዳ ነው ይዘው የተነሱት፡፡ በዚህ ህገ ደንባችን፣ ህገ መንግስቱ እየተጣሰ ነው በሚል፣ የህግ ማስከበር እንቅስቃሴው ወደ እነሱ እንዳይደርስ አስቀድመው በፕሮፓጋንዳ ሰርተውበታል፡፡ ለእነሱ በሚጠቅማቸው ጉዳይ ላይ ህዝቡን ያነሳሱታል፡፡ ሰላማዊ ሰልፎቹም የዚህ አካል ናቸው፡፡
የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደር ሰፊ የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው በየሰልፎቹ በሚያደርጓቸው ንግግሮች የሚሰጣቸው ድጋፍ ያመላክታል … ይህስ ከምን የመነጨ ነው?
በትልቁ ይሄ ተከበናል፣ ጠላቶች ከየአቅጣጫው መጥተውብናል የሚለው ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ እሳቸው በየመድረኩ ይሄን ፕሮፓጋንዳ ተጠቅመው፣ የሚመጣብንን ጥቃት እንከላከላለን፣ የሚያጠቃን ከመጣ እናጠቃለን የሚሉ ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችን ነው የሚያደርጉት፡፡ ካለው ሁኔታ ጋር እየነጎዱና ሁኔታውን እየተጠቀሙበት መሆኑ ጊዜያዊ የስሜት ድጋፍ ሊያስገኝላቸው የቻለ ይመስላል፡፡ በተለያየ ቦታ ትግራዋዮች ጥቃት ደርሶባቸው ስለነበረም እሱም አጋዥ ሁኔታ ነው፡፡ እሳቸውም በዚህ ጉዳይ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር ነው የሚያደርጉት፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ትግራዋዮች መፈናቀላቸውን በቁጭት ሲገልፁ ይደመጣል፡፡ ይሄ የፖለቲካ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ትግራዋዮች ከፌደራል መንግስት ስልጣንና ከጸጥታ አካላት መቀናነሳቸው ሌላ የፕሮፓጋንዳ አካል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለውጥ ከተባለ የግድ መሆን የነበረበት ነው፡፡ ትግራይን አላማ አድርጎ የተነሳ መንግስት ነው በሚል ትልቅ ፕሮፓጋንዳ፣ ብዙ ድጋፍ ያሰባሰቡ አካላት ናቸው አሁን በክልሉ ያሉት፡፡ ይሄ ደግሞ ጥሩ ሂደት አይፈጥርም፡፡ እኛን እንደ ጠላት፣ ተላላኪዎችና ጉዳይ አስፈፃሚዎች አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡
የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር  ዶ/ር ደብረፅዮን፣ በለውጡ ማግስት መከተል ከጀመሩት የአመራር ዘይቤ አንጻር “ህዝበኛ” መሪ  ሆነዋል ማለት ይቻላል?
በትክክል፡፡ ህዝበኝነት ባህሪ ነው፤ እኛ ህዝበኝነትን አንከተልም፡፡ ለዚህ ነው እነሱ የህዝብን ስሜት የሚኮረኩሩ ነገሮችን የሚያደርጉት፡፡ ለምሳሌ እኛ የወሰንና የማንነት ኮሚሽንን ተግባር፣ ህዝቡና እነሱ ይቃወማሉ በሚል አንቃወምም፡፡ በእነሱ በኩል፣ አሁን፣ ሁሉንም የፌደራል መንግስቱን አሰራር መቃወም ነው የያዙት፡፡ ይሄን ይዘውም ወደ ህዝቡ በመቅረብ ነው የሚያራግቡት፡፡ አሁን በሚከተሉት አካሄድ ህዝበኝነት ብቻ ሳይሆን በራሳቸውም እየፈጠሩ ያለው ጥላቻ ነው እየጎላ የመጣው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ላይ ጥላቻ ነው ያላቸው። ከመጀመሪያውም ብቃት የለውም፤ አሁን ያለውን የሃገሪቱን ሁኔታ መቆጣጠር አይችልም፣ በትግራይ ላይ ያተኮረ ጥቃት እየፈፀመ ነው የሚሉ ነገሮችን በደንብ እያራገቡ ነበር፡፡ ይሄ ህዝቡ ጋ ደርሶ ስሜታዊ አድርጎታል፡፡ ሁኔታው ከህዝበኝነትም የተሻገረ ነው። እኛ ደግሞ መቼ ነው እንዲህ የሆነው? እያልን፣ ፊት ለፊት ስለምንጋፈጣቸው፣ ግጭት ውስጥ እንገባለን፡፡ ለዚህ ነው ራሳቸውን የትግራይ ህዝብ ጠበቃ፣ እኛን ደግሞ ህዝቡን የካድን አድርገው የሚያቀርቡን፡፡ የትግራይ ህዝብ ጠላት ከነበሩት ደርግ፣ ኢህአፓና የመሳሰሉት ጋር አብረው እየሰሩ ነው የሚል ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተውብናል፡፡ እኛም እነሱን በመረጃ ለመሞገት እንሞክራለን፡፡ ነገር ግን እነሱ ሚዲያ አላቸው፤ በፍጥነት እየበለጡን ነው፡፡ አሁን ትግራይ ውስጥ ገብተን ለመንቀሳቀስ ለኛ ከባድ ነው፡፡ ግን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ደብዳቤም ለዶ/ር ደብረፅዮን ፅፈንላቸዋል፡፡
ሃገር ቤት ከገባችሁ ወዲህ  ወደ ትግራይ አልሄዳችሁም እንዴ?
መጀመሪያ ስንመጣ አንድ ጊዜ ብቻ ሄደናል፤ ከዚያ በኋላ ግን ነገሮች ጥሩ አልሆኑም፤ አልሄድንም።
ለምን? የደህንነት ስጋት አለባችሁ?
በመጀመሪያ ለመተባበር ዝግጁ ነበሩ፡፡ ማንኛውንም ነገር ከመወሰናችሁ በፊት ትግራይን ተዘዋውራችሁ ተመልከቱ ብለውን ሰፊ ትብብር ለማድረግ ሞክረው፣ እነ ዶ/ር አረጋዊ በርሄም ተዘዋውረው ለማየት ሞክረዋል፡፡ ግን ከዚያ በኋላ ብዙ ነገር ነው የተቀየረው፡፡ የደህንነቱን ሁኔታ ገና አላወቅነውም፤ ነገር ግን በኛ ላይ የሚነዛውን ሁኔታ ስናገናዝብ፣ የደህንነት ጉዳይም ችግር እንዳለው እንገምታለን፡፡ ነገር ግን እኛ ገፍተንም ቢሆን እንገባለን፡፡
አብዛኛው የህውሓት አመራር መቐሌ ነው የከተመው፡፡ በዚህ የተነሳ ህውሓት ተገፍቷል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በእርግጥ ተገፍቷል ወይስ?
ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ያስገደዳቸው ሁኔታ አልነበረም፡፡ በሰሩት ስራ የሚጠየቁ ስለሆነ ምናልባት ፈርተው ሸሽተው ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሰናበቱም ንፁህ ከሆኑ እዚህ መቆየት ማን ይከለክላቸው ነበር? እንደነ ጌታቸው አሰፋ አይነቶቹ ደግሞ ስራቸውንም በአግባቡ አስረክበው አይደለም የሄዱት፡፡ ስለዚህ ተገፍተው ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንጠየቃለን የሚል ፍራቻ ነው ያሸሻቸው፡፡ ትግራይን እንደ መጨረሻ ምሽግ ነው የተጠቀሙት፡፡
በአንድ በኩል፤ ህውሓት “ተክደናል” የሚል ስሜት ያንፀባርቃል፤ በሌላ በኩል “ህውሓት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መቆየት የሌለበት ድርጅት ነው” የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ እነዚህን ሁለት አቋሞች እርስዎ እንዴት ይመለከቷቸዋል?
በእርግጥ የተለያየ ደረጃ ሊኖር ይችላል እንጂ ባለፉት 27 ዓመታት ለደረሰ ጥፋት ህውሓት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተጠያቂ ናቸው፡፡ ህውሓት ዋነኛው፣ በብዙ ነገሮች ወሳኝ የነበረ ፓርቲ እንደመሆኑ፣ በብዙ ወንጀሎች ሊጠየቅ ይችላል። እንደ መንግስት ሲመራ የነበረው ግን ኢህአዴግ ነው፤ ስለዚህ ሁሉም በየደረጃው ሊጠየቅ ይገባል፡፡ እንደ ፓርቲ መቀጠል የለበትም የሚለውም ተገቢ አይደለም፡፡ እኛ በአዋጅ ልናጠፋው አይገባም፡፡ ምናልባት ራሱን ሊያጠፋ ይቻላል፡፡ ህውሓት፣ አሁን ባለው ሂደት ራሱን ያጠፋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ የዲሞክራሲ ሂደትን የማይደግፍ ድርጅት፣ በመጨረሻ ራሱን ነው የሚያጠፋው፡፡ ለአጭር ጊዜ ህዝብን አፍኖ መንገዳገድ ይቻል ይሆናል ግን ዘላቂ አይሆንም።
“ተክደናል” የሚሉት ግን ማን ነው የተካደው? ማን ነው የካደው? የሚል ጥያቄን የሚፈጥር ነው፡፡ እነሱ ናቸው ዲሞክራሲውን የካዱት፡፡ እነሱ በምን ላይ ነው የተካዱት? የለውጥ ሂደቱን የካዱትና ዳር ተመልካች የሆኑት ራሳቸው ናቸው፡፡ በመጀመሪያው የለውጥ ሂደት እነሱ ቢኖሩበትም እንኳ ባመኑበት መንገድ ለውጡን ወደፊት ለመውሰድ አልሞከሩም። ያለ አግባብ ብዙ ሰዎችን አስረናል፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥበናል ሲል ቆይተው፣ ተግባራዊ እርምጃ  ሲመጣ ግን ቀጥ ብለው ነው የቆሙት፤ በፍጥነትና በሙሉ ልብ መጓዝ አልቻሉም፡፡ እነሱ ናቸው ወደ ኋላ የሄዱት እንጂ እነ ዶ/ር ዐቢይ አይደሉም የካዷቸው፡፡ ለምን የተናገሩትን ለመተግበር ወደ ኋላ አመነቱ? በማመንታታቸው እነሱ ናቸው ለውጡን የካዱት፡፡ እስካሁን እኮ ትግራይ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች አሉ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠብቦ ያለው በትግራይ ነው፡፡ እዚህማ በማንኛውም ጉዳይ፣ህገ ደንቦችን በመቀየርና በማሻሻል ሂደት ጭምር በሚገባ እየተሳተፍን ነው፡፡ ይሄ በትግራይ የለም፤ ታዲያ  ማን ነው ትግሉን የካደው? እነሱ ናቸው መስመሩን ስተው ለውጡን የካዱት፡፡
የለውጥ ሂደቱ “የባለ ተራነት አስተሳሰብ” እያስተናገደ ነው፤ አሁንም ከዘር የበላይነት አልወጣም የሚል አመለካከት እየተንጸባረቀ ነው፡፡ እርስዎ በአዲሱ አመራር ምን ታዘቡ?
አሁን የመጀመሪያ ጥያቄ መሆን ያለበት የዲሞክራሲ መዋቅርን መዘርጋትና ማጠናከር ነው። ይሄ ዓይነቱ ግምገማ አሁን መነሳቱ ያን ያህል አያስኬድም፡፡ ገና በለውጥ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በሽግግር ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሁሉን አሳታፊ ምርጫ ተደርጎ፣ ህጋዊ የሆነ፣ ሁሉም ያመነበት ፓርላማ ተመስርቶ ካበቃ በኋላ፣ ይሄን ጉዳይ አበጥረን ማየት እንችላለን፡፡ ጥናትና ውይይቶች እየተደረጉ፣ መፍትሄዎች  ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ያለውን ስትራክቸር ከነችግሩ ይዘን፣ እንደ ሽግግር ጊዜ ተመልክተን፣ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ የማድረግ ሂደት ላይ ትኩረት ብናደርግ ይመረጣል፡፡ ዲሞክራሲን በትክክል ማዋቀር ላይ ነው አሁን ትኩረት ማድረግ ያለብን፡፡
የሃገሪቱ ፖለቲካ ይበልጥ እየተወሳሰበ፣ በዘርና በጎሳ መቧደኑ እየተጠናከረ ሄዷል በሚባልበት በአሁኑ ወቅት አገራዊ ምርጫ ቢደረግ፣ ትልቅ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚወክል ፓርቲ መንግስት የሚመሰርትበትን ስርአት ከመፍጠር የዘለለ ውጤት አያመጣም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ  ምን አቋም አለዎት?
እርግጥ ነው፤ ሁሉም ማንነቱን የሚያጎላበት ሁኔታ ነበር ያሳለፍነው፡፡ እንዲያውም አሁን የአንድነት ጥያቄ እየመጣ ነው እንጂ ቀድሞ የሃገሪቱን አንድነት በእጅጉ አላልተውት ነበር። አሁንም ያለውን የፌደራል ስርአት አወቃቀር መጣስ አይገባም፡፡ አሁን የኢትዮጵያን ህዝብ ብዛት በቀዳሚነት የሚመራው የኦሮሞ ህዝብ ነው። ተከታዩ  አማራ ነው፡፡ ሁለቱ ኃይሎች ጥምረት ከፈጠሩ፣ ሌላው መዋጡ አይቀርም። ይሄን አሁን ባለው ሁኔታ ከመቀጠል ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ነገር ግን አንድ ብሄር ለብቻው የፌደራል መንግስት ስልጣንን የሚቆጣጠርበት ሁኔታ የመምጣት እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ እኛ ራሳችን የፓርላማ አወቃቀሩ እንዲቀየር የምንፈልገው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ አሁን አብላጫ የህዝብ ቁጥር ያለው፣ አብላጫ የፓርላማ ወንበር ተደልድሎለታል፡፡ እኛ የምንለው ግን ሁሉም ክልሎች እኩል መቀመጫ ይኑራቸው ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ኦሮሞያ ትልቅ ኮታ አለው። ቀጥሎ አማራ ክልል ነው፡፡ ይሄ ቀርቶ ሁሉም እኩል የመቀመጫ ኮታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄ የሚቀጥል ከሆነ ግን የህዝብ ብዛት፣ የመንግስትን ስልጣን እየወሰነ ይሄዳል ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ ኢህአዴግ እና አጋሮቹ፣ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመሆን አቅደዋል፡፡ ይሄስ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል?
ይሄ የቆየ እቅድ እንደሆነ ይታወቃል፤ ነገር ግን ብዙ ያልበሰሉ ሁኔታዎች ባሉበት፣ አንድ ውህድ ፓርቲ ሆኖ ይወጣል የሚለውን እጠራጠራለሁ። ግንባር ሆኖ ወይም የግንባሩን አባላት አብዝቶ ሊሄድ ይችላል እንጂ ውህድ ፓርቲ ይሆናል የሚለው፣ ለኔ አስቸጋሪ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡
ምንድን ነው አስቸጋሪ የሚያደርገው?
የዚህ የዘርና የብሔር ጉዳይ ገና አልለየለትም። አልረገበም፡፡ በርካታ የዘር አስተሳሰቦች አሉ። ይሄ ባለበት መተማመን የሰፈነበት፣ የዳበረ ውህድ ድርጅት መፍጠር፣ እንዲህ በቀላሉ የሚቻል አይሆንም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከሰሞኑ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን ያካለለ ፈጣን ጉብኝት አድርገዋል። የዚህ ጉብኝትና ባለፉት ወራት የተካሄዱ አንድምታቸው ምንድን ነው?
ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ግልፅና በፅሁፍ በተቀመጡ ስምምነቶች መታሰር አለበት፡፡ ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው፣ በውል ማሰሩ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ በትክክል የሁለት ሃገሮች ግንኙነት መሆኑን ማስረገጥ ያስፈልጋል፡፡ ህዝብ ማወቅ ያለበትንም ማወቅ አለበት፡፡ ውሎቹም አለማቀፍ ደረጃ ያላቸው መሆን አለባቸው። ጠ/ሚኒስትሩ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እኛን በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚጎዳ መሆኑን በሚገባ የተረዱ ይመስለኛል። ለዚህ ነው ከኬንያ ጋር ስምምነት ያደረጉት፣ ከሱዳንና ከሶማሊያ ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት ማድረጋቸው፣ ይበልጥ ለውስጥ ደህንነታችን ነው ጥቅሙ፡፡ መተማመንን ይፈጠራል፡፡ በጉርብትና ዲፕሎማሲ ውስጥ ደግሞ የእርስ በእርስ መተማመን በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡
በሃገር ውስጥ ያለውን በዘርና በጎሳ የመከፋፈልና መቋሰል ችግር ሳይቀርፉ፣ ምስራቅ አፍሪካን በአንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለማስተባበር መሞከር፣ የሃገር ውስጥ ችግርን ሽሽት ነው፣ የሚል ትችት የሚሰነዝሩ አሉ ----
እንዳልኩት የአካባቢው ጉዳይ እኛ ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ይሄን ማስተካከል የውስጥ ችግርን ተረጋግቶ ለማስተካከል ጠቃሚ ነው። ከዚያ በመለስ ምሳሌነትም አለው፡፡ እሳቸው ማሰብ ያለብን ጠብን ሳይሆን እንዲህ ሰፍተን ነው የሚል መልዕክትም ነው እያስተላለፉ ያሉት፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ብጥብጥ ያልተነሳበት አካባቢ የለም።  አሁን ግን ሁኔታው እየቀነሰ ነው፡፡ ይሄ የትዕግስትና የበሳል አርቆ አሳቢነት አመራር ውጤት ነው፡፡ ሁሉም ችግር ጦር በመላክ፣ በኃይል አልተፈታም፡፡ በሽምግልና በትዕግስት ነው የተፈታው፡፡ ይሄ ተደርጎ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያለያየን ነገር የለም፤ እንኳን እኛ የምስራቅ አፍሪካንም የሚለያይ ነገር የለም፣ የሚል መልዕክት ነው እየተላለፈ ያለው። ይሄን አስተሳሰብ በሚገባ ለማስረፅ ሰፊ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ትዕግስት ይፈልጋል፡፡ እኔ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የመጣው ለውጥ ያስደንቀኛል፤ለውጡ ደግሞ በዋናነት ጨለማ የነበረ የፖለቲካ ድባብ ወደ ብሩህ ተስፈኝነት መቀየር መቻል ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ በቀጣይ የዲሞክራሲ ስርአትን ተቋማዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በትግራይ ያለው ሁኔታ ግን ወዴት እንደሚሄድ ያልለየ ነው፤ አቅጣጫው አይታወቅም፡፡ የህወሓት የፖለቲካ አቅጣጫ አይታወቅም፡፡ ህዝቡን በተለያየ መንገድ አፍነው ይዘውታል፡፡ የመንግስት ሠራተኛውን በስራ ዋስትና፣ ገበሬውን በመሬትና በግብርና ግብአት ዋስትና ጠፍረው ይዘውታል። በትግራይ ያለው የፖለቲካ አቅጣጫ ከዚህ አንፃር አይታወቅም። ህዝቡ በህወኃት ተወጥሮ ነው ያለው። ራሱን ታግሎ እንዴት ነፃ ያወጣል? ራሱን እንኳ ነፃ እንዳያወጣ፣ እንዳይታገል መንገዱን በሙሉ ነው የዘጋጉበት፡፡ አደገኛ የፖለቲካ አካሄድና የህዝብ አፈና ነው በትግራይ ያለው፡፡ የትግራይ ህዝብ ችግር ውስጥ የገባው ደግሞ በማንም ሳይሆን በራሱ ድርጅት ነው፡፡
ሌላው አካባቢ ለህወሓት ጥይት እንደ ማቀበል ከሚቆጠረው ትግራይዋትን የማግለል ሁኔታ ቢያቆም ጥሩ ነው፡፡ የህዝቡን ስቃይ ለማሳጠር አንዱ የፖለቲካ ትግል ይሄ መንገድ ነው፡፡  

Read 1132 times