Sunday, 10 March 2019 00:00

በአድማስ አድቨርታይዚንግ ሥራ አስኪያጅ ላይ የተሰጠውን ፍርድ ጠበቃው ተቃወሙ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ላለፉት 20 ዓመታት ገደማ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣን ሲያሳትም የቆየው የ“አድማስ አድቨርታይዚንግ” ዋና ሥራ አስኪያጅ ላይ ፍ/ቤት የሰጠውን ፍርድ የተከሳሽ ጠበቃ “ህጋዊውን ሥርዓት የጣሰ ነው” ሲሉ ተቃወሙ፡፡
ከትላንት በስቲያ፣ የ2005-6 ዓ.ም የሽያጭ ሂሳብ የተሟላ አይደለም በማለት ፍ/ቤት በአድማስ አድቨርታይዚንግ ስራ አስኪያጅ ወ/ት ገነት ጎሳዬ ላይ የአንድ ዓመት ተኩል እስር የወሰነ ሲሆን፣ “የሚያስከስስ ማስረጃ አልቀረበበትም ተብሎ በተተወ ጉዳይ ላይ የተወሰነብን የቅጣት ፍርድ ህግን ያፈርሳል” በማለት የተቃወሙት የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው፤ “ተከላከሉ በተባልንበት ጉዳይ ግን በቂ ማስረጃ በማቅረብ ክሱ ውድቅ እንዲሆን አድርገናል” ብለዋል፡፡
አቃቤ ህግ ያቀረባቸው የክስ ነጥቦች በርካታ እንደነበሩና አብዛኞቹ ማስረጃ ስላልነበራቸው፣ በአንድ የክስ ነጥብ ላይ ብቻ መከላከያ እንድናቀርብ ነበር ፍ/ቤቱ የጠየቀን - ሲሉ አስረድተዋል ጠበቃው፡፡
በየሳምንቱ ሳይሆን የአንድ ዓመት ሂሳብ የሚከፍሉ ቋሚ የጋዜጣ ደንበኞችን በተመለከተ፣ በ2005 እና 2006 ዓ.ም የተሟላ ሂሳብ ባለመመዝገብ፣ የግብር ክፍያ አጓድላችኋል የሚል የክስ ነጥብ ላይ ብቻ መከላከያ ማስረጃ እንድናቀርብ ፍ/ቤቱ በጠየቀን መሰረት፣ በቂ ማስረጃ አቅርበናል ብለዋል - ጠበቃው፡፡
“የዓመት ሂሳብ የሚከፍሉ የጋዜጣ ደንበኞች፣ በአብዛኛው የመንግስትና አለም አቀፍ ተቋማት ትልልቅ ኩባንያዎችና ድርጅቶች መሆናቸውን ጠበቃው ገልፀው፣ ሳይመዘገብ የቀረ ሂሳብ እንደሌለ በበቂ ማስረጃ አስረድተናል፤ ፍ/ቤቱም ይህን በማረጋገጥ ተቀብሎታል” ብለዋል፡፡
“ይህ ከሆነ በኋላ ግን፣ ቀደም ሲል መከላከል ሳያስፈልገን በተተወና፣ ተከላከሉ ባልተባልንበት ሌላ የክስ ነጥብ ላይ ፍ/ቤት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎብናል” ሲሉ ጠበቃው ገልፀው፤ “በህግ የተከለከለና ህጋዊውን ስርዓት የጣሰ ውሳኔ ነው፤ ተከሳሽ ማስረጃ የማቅረብና የመከላከል መብት ተነፍጎ ነው፣ ያለ ዳኝነት ፍርድ የተወሰነብን” ሲሉ ጠበቃው ተቃውመውታል፡፡     

Read 6760 times