Sunday, 10 March 2019 00:00

አማራን ከቅማንት ያጋጩ አካላት ለህግ ይቀርባሉ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የትግራይ አመራሮች ከጦርነት ዝግጅት እንዲታቀቡ ተጠየቀ

በአማራና በቅማንት ህዝብ መካከል ግጭት የፈጠሩና በወንጀል የተሳተፉ ኃይሎች በሙሉ ለህግ እንደሚቀርቡ የአማራ ክልል ምክር ቤት ያስታወቀ ሲሆን የትግራይ አመራሮች የሚያደርጉትን የጦርነት ቅስቀሳና የሰራዊት ዝግጅት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አሳስቧል፡፡
ምክር ቤቱ ከየካቲት 26 እስከ 29 ለሦስት ቀናት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በዋናነት በክልሉ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መምከሩ ታውቋል። በአሁኑ ወቅት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱን የተመለከተው የክልሉ ም/ቤት፤ በጎንደር በተለይ ከቅማንት ህዝብ የአስተዳደር ጥያቄ ጋር በተገናኘ በተፈጠረው ግጭት የተሳተፉ ወንጀለኞች በሙሉ ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡
በግጭቱ የስነ ልቦና እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችና ተፈናቃዮች በፍጥነት እንዲረዱም ም/ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጡን እንዲሁም በአማራና በቅማንት ህዝብ መካከል ዘላቂ መቃቃር እንዳይኖር፣ እርቀ ሰላም እንደሚካሄድ የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አሰማማኝ አስረስ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘም በአማራና በትግራይ ክልል መካከል እየተፈጠረ ያለውን ግጭት በዝርዝር የገመገመው ም/ቤቱ ፤የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያለው መሆኑን በማውሳት፣ አሁንም የመሪዎች ችግር እንጂ በህዝቡ መካከል ምንም ችግር እንደሌለ መገምገሙን አስታውቋል፡፡
ከትግራይ ክልል አመራሮች በኩል፣ የጦርነት ቅስቀሳዎችና፣ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት እንዲሁም ወደ አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ሰራዊት የማስጠጋትና ጠብ አጫሪ አካሄዶች መኖራቸውን የገመገመው ም/ቤቱ፤ አመራሮቹ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
የትግራይ ህዝብም ለዚህ የአመራሩ የጦርነት ቅስቀሳ ባለመተባበር ሰላም ወዳድነቱን በተግባር እንዲያረጋግጥ የጠየቀው የአማራ ክልል ም/ቤት፤ በአማራ ክልል በኩልም ግጭት ከሚፈጥሩ ትንኮሳዎች፣ የትግራይን ህዝብ ስጋት ላይ ከሚጥሉ ጠብ አጫሪ ንግግሮች ማንኛውም አካል እንዲቆጠብ፣ ከዚህ በተቃራኒው የሚንቀሳቀሱ ካሉ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ ም/ቤቱ አስገንዝቧል፡፡


Read 1286 times