Sunday, 03 March 2019 00:00

ሥነ - ጥበብ የማን ናት?

Written by  በሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(1 Vote)

“መገላልጦች” ስለ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ-ሥላሴ ሐውልት በአፍሪቃ ሕብረት

የሀውልቱን መመረቅ በጉጉት፣ በቸልታም ሆነ በጐሪጥ ይጠባበቁ የነበሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሕብረቱ 32ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት ሐውልቱ ተመርቆ ከተገለጠበት ቅጽበት አንስቶ ለእኔ እንደ እሳተ - ጐመራ ፍንዳታ የሚታየኝ፣ ኋላም እየተጋጋለ፣ እየተፋፋመ፣ ከዚያም ከቅርብ ቀናት ወዲህ እየተቀዛቀዘ የመጣው፤ በመቀጠልም እየተዳፈነና እየተረሳሳ የሚመጣ የሚመስለው የሕዝቡ “ግንፍሌ፤ ግንፍልፍሌ” እና ቀስ በቀስ በየቦታው እየሰረገ ድምጹን እያጠፋ ያለው አፀፋ፤ በተለይ በሃገራችን “ሥነ - ጥበብ የማን ናት?” የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ የተነፈሰ ጐማ እንዳለውና ግዙፍ ዛፍ ስር ተረስቶ ለዘመናት እንደ ከረመ መኪና የተዘነጋ ከሚመስለው (አንዳንዴ ግን በሆኑ ምክንያቶች የሆኑ ሰዎች ሞተሩን ሲያንቀሳቅሱት ብቻ በምንሰማሙ መኪና) እና ዛፉንና የቆመውን መኪና ተገን በማድረግ ጐጆ ቀልሰን፣ መንደር መስርተን፣ ማኅበረሰብ ሆነን ፈርጀ ብዙ መልክ ይዘን፣ እንደ ፍጥርጥራችን፣ በየተለያየ አቅጣጫ ስለምንሮጥላት ሥነ -ጥበብና በተለይም ስለ ሀገራችን ሥነ - ጥበብ በእርጋታ እንዳስብ ካደረጉኝ ታሪካዊ ክስተቶች መሀከል የሃውልቱ መገለጥ አንደኛው ምናልባትም በሙያዊ የግል ጉዞዬ፣ ከፍ ያለ አትኩሮት ልሰጠው የሚገባ ክውናዊ (Performative) ክስተት ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የሃውልቱ መገለጥ በሀገራችን የሥነ -ጥበብ ሂደት አለባብሰን ያለፍናቸው፣ ችላ ያልናቸውና ያላሰብናቸው ወይም ትኩረት ያልሰጠናቸው ጉዳዮችን ገልጠን እንድንመለከታቸው “እድል” የሚከፍት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ አልፎ ተርፎም ሠፊው ማኅበረሰባችንም ሆነ በሙያው ውስጥ ለምንዳክረው፣ ለምንዋኘውም ሆነ ያሉብን ጐታች እውነታዎች ስበው እንዳያሰምጡን ለምንታገለው ለእኛ ለኢትዮጵያ ዘመንኛ የሥነ -ጥበብ ማኅበረሰብ አባላት ( “ታጋዮች” ልንባል እንችላለን) አይነተኛ የአብራሄ -ጥበብ እድልም (Enlightment Opportunity) ሆኖም ይታየኛል፤ የአባባ ጃንሆይ ሀውልት፡፡
ሃውልቱ ከተመረቀ በኋላ በነበሩ ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ በፌስ- ቡክ ገፆች እንዲሁም ሰዎች እርስ-በእርስ ያደርጓቸው የነበሩ የሃሳብ ልውውጦች በአንድ ወቅት በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተጽፎ ያነበብኩት የአለቃ ገብረሃና ተረትን ነበር ያስታወሱኝ፡፡ አለቃ በአንድ መንደር ሲያቋርጡ ሰዎች ተሰብስበው ሲያወኩ ያዩና ቀረብ ይላሉ፡፡ ሁካታው መሃል አንድ የሚያውቁት የሃብትም ሆነ የዕውቀት ባለጠጋ የሆነ ሰው ቆሞ፣ በዙሪያው ያሉት ሰዎች የሚያወርዱበትን መአት በዝምታ ይቀበላል፡፡ አለቃ ትንሽ አሰብ አድርገው ወደ መሃል ዘልቀው እጆቻቸውን ያወናጨፉ ጀመር፡፡ ክዋኔያቸው ግራ የገባቸው፣ ምን እያደረጉ እንደሆን ቢጠይቋቸው፤ “ስድብን ቦታ ቦታ እያስያዝኩ ነው” በማለት ይመልሳሉ፡፡ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ መቋጫ፤ “ሰዎች በደረጃቸው ልክ አውርደው ለግጥሚያ ቢጋብዙህ፣ አቅምህን ወደነሱ ደረጃ አውርደህ አትግጠማቸው፡፡ በቦታቸው ከሆነ የሚያደርጉትን ያውቃሉና” የሚል አንድምታ እንደነበረውም ትዝ ይለኛል፡፡
የሃውልቱ ዋና ቀራጺ በቀለ መኮንን (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፤ አለቃ ገብረሃና ተረት ውስጥ እንዳለው ባለጠጋ፣ ዝምታን አልመረጠም፤ ከጠቢብነቱ ዙፋን ወርዶም ፍልሚያ አልገጠመም፡፡ ሃውልቱ ከተገለጠ በኋላ ባሉት ሌሎች ሃያ አራት ሰአታት ውስጥ አንድ ጽሑፍ በፌስ ቡክ እንዲሁም በቀጣዮቹ ሌሎች ሃያ አራት ሰአታት ውስጥ ደግሞ አንድ የሬዲዮ ቃለ መጠይቅ አድርጐ ነበር፡፡ በዚህም ቀራጺው ወይ ከዝምታው አሊያም ከፍልሚያው ባለመገኘት የሰጣቸው ምላሾችን ከምሉዕነት አንጻር በመመዘን ሳይሆን ከበቂነት አኳያ ለመመልከት መሻት ሌላው ለመጻፍ ያነሳሳኝ ምክንያት ነበር። የዚህ ጽሑፍ አላማም እንደ አለቃ ገብረሃና “ስድብን ቦታ ቦታ ማስያዝ” አሊያም ሰዎችን ወደ ደረጃቸው በመውረድም ሆነ ወደ ደረጃቸው በመውጣት ለመፋለምና ለመነዛነዝ አለመሆኑን ላሳውቅ እወዳለሁ፡፡ ይልቁንስ ያቺን የአብራሄ-ጥበብ የምትገልጠውን ችቦ መለኮሻ ብትሆንልኝ ብዬ ነው ብዕሬን ማንሳቴ፤ አንድ ችቦ ደግሞ በባህሪው የመክሰም አሊያም ነዶ የማለቅ እጣ ፈንታ የተቸረው በመሆኑ፣ ወደ አብራሄ ጥበቡ ሙሉ ለሙሉ ላያደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህም ስለ ሥነ-ጥበብ ያለ ሁሉ የሃገራችን ሥነ-ጥበብ ምህዳርን የሚያሰፋ ጽሑፎችንና አስተያየቶችን ወደ አደባባይ በማውጣት ችቦውን ለኩሶ እንዲቀላቀል ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የሐውልቱን መገለጥ መሰረት በማድረግ “ሥነ-ጥበብ የማን ናት?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ እንድንወያይባቸው ወደ መረጥኳቸው ሃሳቦች ለመሸጋገር ግላዊ ግርምቶቼና ትዝብቶቼን ይፋ ለማውጣት አፍታ በመውሰድ እቀጥላለሁ፡፡ በቀዳሚነትም ግርምት፣ ትዝብት፣ ቁጭትና የሆነ ዓይነት የመቁነጥነጥ ስሜት የፈጠሩብኝና ብሶት የወለዳቸው ጥያቄዎችን ለራሴ እንድጠይቅ ያደረጉኝ፤ ስለ ሐውልቱ ያለ ለከት የተሰነዘሩት የ“ይመጥናል አይመጥንም”፣ የ“ይመስላል አይመስልም” ጉድፍ የሞላባቸው አስተያቶች ናቸው፡፡ የአስተያየቶቹ ፀያፍነት ብቻ ሳይሆን ድፍረታቸውም ጭምር ነበር ያጥወለወለኝ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ግልብነት በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ ወዘተ “ኢትዮጵያዊ ማንነታችን” ተከልሎ ያደፈጠ መሆኑን ብረዳም፣ በሥነ-ጥበብ ማሳያ ቦታዎችና ድግሶች ላይ ዝር ብሎ የማያውቀውና የማይመጥን ሙዚቃና ፊልም ሲጋት በዝምታ የተለጎመ ሁላ፣ ሥነ-ጥበብ/ቅርፅ/ስዕል/ ሲሆን አፉ የሚፍታታለት ማህበረሰብ ውስጥ መገኘታችን አስገርሞኛል፡፡ አንድ ጠበቅ ያለ ወዳጄ፤ “አንድ ሰው ጮኸብህ ማለት እርዳታህን እሻለሁ፤ እርዳኝ ማለቱ ነው” ይላል፡፡ “ሥነ-ጥበብ የእኔም ናት!” በሚል የባለቤትነት ስሜትም ይሁን ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ የመሰለውን የለፈፈ ሁሉ “እርዱኝ!” እያለ ነው ብለን በጥበብ መንገድ ብናስብ ለተሻለ ጉዞ መነሻሻ እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡ (ግብረ-ገብ የጎደላቸውና ድፍረት የሞላባቸው አስተያየቶች በቦታቸው እንዳሉ ሳንዘነጋ) በዚህ መንገድ ትንሽ ለመቀጠል ስሞክር ደግሞ “ማኅበረሰባችን ከሥነ-ጥበብ ጋር ያለው ልምምድና ትውውቅ እንዲዳብር ምን ተሰርቶለት ነው ቢያንስ እርዳታ እንዲጠይቅ የምንጠብቀው” የሚል ጥያቄ ያቆመኛል፡፡ ከስሜት በዘለለ በምክንያት “ሥነ-ጥበብ የእኔም ናት!” እንዲል የሚያስችል መሰረት ሳይሰጠው እንዲህ ባሉ ምክንያቶች የተረሳ የሚመስለው የሥነ-ጥበብ ሞተራችን ሲንቀሳቀስና ድምጹ ሲሰማ በግርምት ሞተሩ ሊነሳ የቻለበትን መንስኤ እንዲሁም የተነሳበትን የቴክኒክና የፍልስፍና መሰረትን ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ (ረስቶት የነበረውና ያልጠበቀው) የሞተሩ ድምጽ አስበርግጎት ወይም አስጠልቶት ብቻ ስድቡን ቢያወርድ የሚጠበቅ ባይሆንም የሚገርም አይመስለኝም፡፡ ይህ ትዝብቴ “ስድብን ቦታ ቦታ ማስያዝ” ተደርጎ እንደማይወሰድብኝ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ስድባቸው ቦታ ቦታ እንዲይዝ (ማለትም ወደ ራሳቸው እንዲመለስ) የሚገባቸው ሰዎች እዚህ ጋዜጣ ሰፈር አይገኙምና እንዴት ብሎ ስድብ ቦታ ቦታውን ይይዛል?
እንደ BBC ያሉ አሁንም ቅኝ ግዛታዊ (Colonial) አተያይና ጎጠኝነት ያልለቀቃቸው የሐውልቱ መቆም መሰረታዊ ምክንያትን ወከባ ውስጥ ለመክተት የሞከሩ፤ በዚህም የሐውልቱ ሥነ-ጥበባዊ ዋጋን ከመጤፍ ያልቆጠሩ መኖራቸው ሌላ ግርምት ውስጥ የከተተኝ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይቅርና በዓለም ታሪክ “እንከን የለሽ” የሚባል መሪ ያለ አይመስለኝም፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ ( ....… ) በመልካም እንደሚነሱ ሁላ በመልካምነት ላይነሱ የሚችሉ ታሪኮች አሏቸው፡፡ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን በተመለከተ ግን የሚያወላዳ ነገር ያለ አይመስለኝም። ለዚህም ነው ሐውልት የቆመላቸው፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ይህን ማየት ማገናዘብ ያልቻለ፣ የሸፈነውን ግርዶሽ ይግለጥ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህ ጩኸት ከላይ ከገለፅኩት ጋር ተደምሮ፣ ለጊዜውም ቢሆን ትንሽ መደናቆር ለመፍጠር መዋሉ ነው፡፡
መረንነት ተከልሎ ካደፈጠበትና በግልብነት ከተጋለጠበት አፀፋው፣ ከወከባው፣ ከመደናቆሩ መሃከል ግራ የተጋባ የሚመስለው የሃገራችን የሥነ-ጥበብ ማኅበረሰብ፣ ሐውልቱን በተመለከተ ያሳየው ያደባባይ ዝምተኝነት አይሉት ጭምተኝነት፤ ሻል ሲልም ቁጥብነት የተሞላው ማንንም ያለማስቀየም አዝማሚያ፣ ሌላው ያስገረመኝ ነገር ነበር፡፡ ፌስ ቡክ ፎቶና የሥዕል ስራን ለመለጠፍና “ላይክ ላይክ” ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ሥነ-ጥበብን ከፍ የማድረግ ሃቲት (Discourse) ለመፍጠርም ማዋል ይችላል’ኮ። ቢያንስ በቡድን ወይም ከግለሰብ ጋር ስለ ሃውልቱ የተነጋገርናቸው ጠቃሚና ሚዛናዊ ነጥቦች ወደ ፌስ ቡክ  ቢወጡ መራኮትን ይቀንሱ ነበር፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታዎች ሃሳባችንን በነጻነት ሳናስተላልፍና ኃላፊነታችንን ሳንወጣ እንዲሁም የሙያው ባለቤት መሆናችንንና ሥነ-ጥበባችን ቢያንስ የሙያ ባለቤት እንዳለው የሚያመላክት ሚዛናዊ ሙያዊ አስተያየትና ማብራሪያ መሥጠት አለመቻሉ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ሃውልቱን ወድደው ድጋፋቸውን የሰጡት ደግሞ ሌላኛው ጽንፍ ያለውን አስተያየት ሚዛን ለማስተካከል እንጂ ሙያዊ መሰረት ለማስረጽ ካለመሆናቸው በዘለለ አትኩሮት ለማሸሽ የተደረጉ ሙከራዎች ሆነው ታይተውኛል፡፡
ሌላው ይቅርና የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ጉዳዬ ነው ብለው ከተቋቋሙ ተቋማትና ከሚሠሩ ባለሙያዎች ምን ይጠበቅ ነበር? አልረፈደምና አሁንስ ምን ይጠበቅ? ሃውልቱን የማቆም ተቋማዊ ኃላፊነት የወሰደው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም (እንደ ተቋም ይፋዊ መግለጫ የመስጠት ሃላፊነት ወይም አስፈላጊነት በት/ቤቱ በኩል የታመነበት አይመስልም)፤ እንደ ፕሮጀክቱ ባለቤትነት ከተሰጡ ምላሾች ውስጥ ሚዛን የሚደፉትን ለይቶና አጥርቶ ለመወያየት እንዲሁም የዚህን ባለውለታ ት/ቤት ተቋማዊ ሉአላዊነትና ልዕልና ለመጠበቅ ሲባል ይፋዊ መግለጫ እስኪሰጥ መጠበቅና በዚያም ላይ መወያየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ በምስረታው የአንበሳውን ድርሻ በሚወስዱት ሠዓሊ አለ ፍለገሰላም ሕሩይ (እ.አ.አ. 1923-2016) የተሠየመው ት/ቤት፤ አፍሪቃ ውስጥ ካሉ የሥነ - ጥበብ ት/ቤቶች አንፃር ከአንጋፋዎቹና ከጠንካራዎቹ አንዱ ከመሆኑ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ካሉ እንደ ንግድ ስራ ት/ቤት (School of commerce) ጋር የሚስተካከል ታሪክና ሃገራዊ ሃላፊነት ያነገበ በመሆኑ እንዲህ አይነት የዘመናት ውዝፍ እዳዎች በሚዘረገፉበት ወቅት ሁኔታዎችን አብራሄ ጥበብ ለመከሰት እንደሚችሉ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የደፈረሰውን ለማጥራት በሚያስችል ተቋማዊ አቀራረብ ይበልጥ አደፍርሶ እንዲጠራ ቢያደርግ፣ የሥነ ጥበብን ዋጋ በማኅበረሰብ ለማስረጽ እንደሚችል እሙን ነው። ት/ቤቱ በሰፊው ከሚታወቅበት ማህበረሰብን ተደራሽ የማድረግ አገልግሎቱ (Community Service) እንደ አንዱ በመውሰድ ሃውልቱን መሰረት ያደረጉ ውይይቶችን እንዲሁም ሌሎች ሥነ-ጥበብን በተመለከተ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ መድረኮችን ማዘጋጀት ቢችል፣ “ሥነ-ጥበብ የማን ናት?” ለሚለው ጥያቄ መልሱን ለማግኘት ከሚቻልባቸው ቦታዎች አንዱና በኢትዮጵያ አውድም ዋነኛው በመሆኑ፣ ት/ቤቱ ባለቤት ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ ውርስ-ቅርሱ (Legacy’ው) ነውና ቀጣይ ስራዎች እንደሚጠበቁበት ግልጽ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የምሁራን ስብስቡ ከበቂ በላይ ነው፡፡
ከት/ቤቱ ባሻገር ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማትና ባለሙያዎች ይኖሩ እንደሆን ለማየት ብንሞክር፣ የኢትዮጵያ ሠዓልያንና ቀራጽያን ማኅበር፣ ብርቅዬ (በጣት የሚቆጠሩና ራሳቸውን የፈጠሩ በመሆናቸው) የሀገራችን የሥነ ጥበብ ታሪክ አጥኚዎችና ተመራማሪዎች   እንዲሁም የሥነ-ጥበብ አጋፋሪዎችን እናገኛለን፡፡ ማሕበሩም ሆነ ባለሙያዎቹ ያገባኛል በማለት በሚኖሩበት የሀገራችን ሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ የኛን ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃን ሥነ-ጥበብ እንድንቃኝ እድል በሚሰጠው የዚህ ሐውልት መቆም ታሪክና ስለ ሃውልቱ ያላቸውን አተያይ ያለማንፀባረቃቸው አንድምታን በበጐነት ለመረዳት ብንሞክር በቀዳሚነት የምናገኘው አመክንዮ ሃውልቱን በአካል የመጐብኘት እድል በማፈላለግ ላይ ሆነው ሊሆን እንደሚችል መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ እድሉን አግኝተውም ቢሆን ጥናት ለማድረግና ሃሳብ ለማደርጀት ተገቢውን ጊዜ በመውሰድ እያከናወኑ ሊሆን ይችላል። የትኛውም ቢሆን ግን የሚረፍድ ጊዜ የለምና ችቦአቸውን ለኩሰው፣ ወደ ብርሃን ለሚደረገው ጉዞ እንደሚመጡ ሁሌም እምነቴ ነው፡፡ ከመረጥነው ሃሳብ፣ መድረክና ስብስብ ውጪ ያለውንና ሌላውን በትልቅ ሚስማር ከንችሮ፣ በየመረጥነው ጥግ ብቻ ማልጐምጐም የትም እንዳላደረሰን፣ ተምረን ብቻ ሳይሆን አስተምረን ማለፍ ያለብን የሥነ - ጥበባችን አጓጊ ዘመን ላይ መሆናችንን ማስታወስ ይገባናል፡፡ ከእነ ዘርፈ ብዙ ልዩነታቸው፣ በአንድነት በመቆም ለሃገራቸው፣ ለሰፊው ማኅበረሰባቸውም ሆነ ለራሳቸው መትረፍ የቻሉት የጋና እና የናይጄሪያ የሥነ-ጥበብ ማህበረሰቦች ያመጡትን ለውጥ  እያወቅን እንዳላወቀ ሆነንና ያልተነካ ሥነ-ጥበባዊ ሃብታችንን ለመዳሰስ ችላ በማለት፤ በቂ ውሃ እያለን ደጃፋችን ላይ ላለው፣ እኛን ለሚመስለን ብቻ ውሃ እያጠጣን ለመኖር የመረጥነው ለምንድነው? ሥነ-ጥበብ የምሁራንና የልሂቃን ብቻ ሳይሆን የማንኛውም ሰው መሆኗንና እንድትሆን መስራት እንደሚገባን የሃውልቱን መቆም መሰረት በማድረግ የተፈጠረው ትርምስ አስረጅ ይመስለኛል፡፡ ምነው “ቄሱም ዝም፣ መጽሃፉም ዝም” ሆንን?
የቀ.ኃ.ሥ መታሰቢያ ድርጅት ተወካይ የሆኑ ግለሰብ የዛሬ ሁለት ሳምንት፣ በዚሁ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ-ምልልስ የታየው ተጣራሽ አስተያየት፣ ሳላነሳ እማልፈው ሌላኛው አስተያየት ነው፡፡ ግለሰቡ የአቶ መለስ ዜናዊ አስተዳደር፣ የጃንሆይን ዐፅም ቀብርና ሌሎች አፄውን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች እንዳይሠሩ የጋረጠባቸውን ያስታውሱና፣ ወረድ ብለው ደግሞ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ጠቀስ ያደርጋሉ፡፡ የሚያስተዛዝበው ንግግራቸው ግን የኢትዮጵያ መንግስት የሃውልቱን ወጪ መሸፈን አለመሸፈኑ “ሌላ ጉዳይ” መሆኑን መግለጻቸው ነው፡፡ ለምንድነው አፋቸውን ሞልተውና በተለይ እንደ ንጉሳዊ ቤተሰብነታቸው፣ የከበረ ምስጋና ያላቀረቡት? ያላሳኩትን ቀብር ለማስፈፀም ያዩትን ፍዳና ውጣ ውረድ ዘክዝከው ተናግረው ማመስገን የሚገባቸው፣ ያውም የኢትዮጵያ መንግስታት አድርገውት የማያውቁትን ሆኖ ባየንበት፣ ይህ ታሪክ አመስግኖ፣ ይበል ይበርታ እንደ ማለት፣ ማክሸፍሸፍ ምን ይሏል? /አልተደመሩም እንዴ?/
በሚቀጥለው ሳምንት፣ሀውልቱን በማቆም ታሪክ ውስጥ ብንመለከታቸው ጠቃሚ ስለሚሆኑ ጉዳዮች፤ ብዙዎችን ስላብሰከሰከውና ስለ ቆመው ሃውልት ምስል መነጋገር ስለምንችላቸው ሃሳቦች፤ ስለ ሃሳቦቹ ጠቀሜታና ለምን ፍጆታ መዋል እንደሚገባቸው፤ የሃውልቱ መቆም ስለሚፈጥራቸው እድሎች እንዲሁም “የብቻዬን ጥግ” አካትቼ እስክመለስ ድረስ የዛሬውን እንደሚከተለው አጠቃልላለሁ፡፡
ስለ ሃውልቱ ከተሠጡ አስተያየቶች መሃል በተደጋጋሚነታቸው ብቻ ሳይሆን በሸዋጅነታቸው (Tricky በመሆናቸው) ከጓደኞቼ ጋር ሲያነጋግሩን የነበሩትን ላንሳ፡፡ አንደኛውና ሁሉም የተቀባበለው ሃውልቱ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን የመምሰል ያለመምሰሉ ጉዳይ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ሃውልቱ የአጼውን ግርማ ሞገስ ማሳየት አልያም ግርማቸውን ማቅለሉ ነው፡፡ እንዲህ ብዬ አሰብኩ “ሃውልቱ አጼነታቸውንና የሆኑትን “ቢመስል” ነው እሚሻለው ወይስ ኃይለ ሥላሴ የሆኑትን ቢሆን?” ይህ ምርጫ ለኛ ቢሆን፣ ከመሆንና ከመምሰል የቱን እንመርጣለን? ስለ መምሰል እንደዚህ የሚያብሰከስከንስ ለምንድነው? ግርማ ሞገስ ያለው ሃሳብ ሳይኖረን፣ ስለ ግርማ ማውራት ቀትረ-ቀላልነት አይሆንም?
የሥነ - ጥበብ ስሱነትና ነኪነት እንዲሁም የሃገራችን ሥነ-ጥበብ ባለቤቷን የምትፈልግበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ መሆኗን ወለል ብሎ እንዲታይ የሚያስችል እድል በመፍጠር፣ የግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሃውልት በአፍሪቃ ሕብረት እንዲቆም ያስቻሉት የቀራፅያን ቡድን አባላት ማለትም ሠዓሊ፣ ቀራጺ፣ ገጣሚና መምህር በቀለ መኮንን (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፤  ሠዓሊ፣ ቀራጺና መምህር ሙዜ አወል፤ ወጣቱና ባለ ብዙ ተስፋው ቀራጺ ሄኖክ አዘነ እንዲሁም ሌላኛው ወጣት ቀራጺ  መስፍን ተስፋዬ፤ የአለ የሥነ - ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ኃላፊዎችና አ.አ.ዩ.፤ ይህ ታሪክ እንዲሰራ በማስቻላችሁና በመስራታችሁ የአደባባይ “እንኳን ደስ ያላችሁ!” በማለት፣ “ሥነ - ጥበብ የማን ናት?” በሚቀጥለው ሳምንት ይቀጥላል፡፡ ቸር እንሰንብት!






Read 858 times