Wednesday, 06 March 2019 10:32

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(6 votes)



ደም በቃል አይገባም!



ቀይ ነው አሉ እንጂ ቀይም መልክ የለውም
ቀይ ፅጌ ነው ቢሉም፣ ቀይ ውበት የለውም
ዕውነት እንደቃል ግን መኖሩ ይከብዳል
ስዕልም ሲቀባ ቀላል ነው እንዳበባ፣ ቀላል እንደቀለም
አድዋማ ቀይ ነው ብሎ አይነገርም!
ደም ነው የተኳለው ያማረውም አፅም!
ቀይ ሞትን አያቅም ቀለም የለውም አፅም!
አበውን ነው እንጂ እኛን ገልፆ አይረካም!
ከአድዋ፤ እስከ ኮሚውን ድንበር
ኸማህል እስከ ዳር አገር
ስንቱ ቆስሎ
ስንቱ ሞቶ
እናት አባት ተሰውቶ
“እናትና አባቴን በጊዜ ቀብሬ
መንግስት እጦራለሁ አንጀቱን አስሬ”
ተብሎ ተብሎ ሁሉ መንዝሮ ዘር
በሞተችውማ አገር ትግል ያልነው ግርግር
ህይወት ባወራንበት ሞት - ቀመር
ያፈራን መስሎን ስንቀብር
ስናደነቁር በፍቅር
ስንደነቁር በጦር ጣር
ኖርን ስንል በሞት ዳር
ሞትን ቋምጠን ሳንሞት
ተምታቶ ቀብርና ዕርገት
ያየን መስሎን አለማየት
ዕድገት ብለን አለ - መክሊት
ኑሮን መጮህ እንደዘበት በባዶ አንጀት ፍል መለከት
የለም የዛን ያህል መርገምት!!
መርገምት አልሻሻል አለን
መርገምትን አጉል ለመድን!
ነፃነት አለን እያልን
ባንዲራም አለን እያልን
መንገድም አለን እያልን
ብርሃን አፀናልን እያልን
ፍፃሜው ግን ጨለመብን!!
ይህ ትዝብትም ብርሃን ነው፣ ድንገት ለነገ ቢሆነን!
ማፅንስ እንጂ ጨንግፈን
አልመን፤ መተኮስ እምቢኝ ብሎን
ፍሬ እንዴት እሺ ይበለን?!
ፍቅርም እኛን ባከለ
ፍትህ እኛን በመሰለ
እኩልነትም ከኛ እኩል፣ ስለ እኩልነት ባወቀ
አድናቆት ከራሱ በላይ፣ ድንቅነትን ካሳለቀ
ዕውንም ሞትስ ራሱን እንጂ እኔና አንቺን የት አወቀ፣
ይሄን ያለ በምድር እንጂ፣ በገሃነም መች ፀደቀ?
እስቲ እንንቃ ጎበዝ ለነገዋ ፀሐይ
እንንጋም አንንጋም ትታይም አትታይ!
“ጥንትም ወርቅ በእሳት እኛም በትግላችን
እየተፈተንን”
ወደድሽም
ጠላሽም
ብትመጪም ብትቀሪም
 “እናሸንፋለን
እናቸንፋለን!”
ትላንትም ብለናል    ብለን ተፈጠምን
ዛሬም እንላለን፡-     የፍትጉ እጅ ነን!
“ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ
ከመናገር በፊት የአርምሞ ፀጥታ
ዛሬም ያገሬ ሰው ያንዳፍታ ዝምታ፡፡
ነገ ግን ይዋጋል መታገሉ አይቀርም
ታግሎም ያቸንፋል አንጠራጠርም!!”
ብለን ነበር አሁን ያው ነው ቃሉ ብሂሉ
መቼም መቼም ቢሆን፣ አይቀርም
ትላንት ነገ ያልኩት ለካ ዛሬ ሆነ
ያለፈው በአሁን አፍ ይሄው ተኮነነ
የላዩ ስር ሆኖ የስሩ ተጫነ!
ገዳሙ ዕምነት በቃው ከተማው መነነ
አድዋችን ይሄው ነው
እኛ እሱን ሆነናል እሱም እኛን በሆነ!
የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም     




Read 3253 times