Sunday, 03 March 2019 00:00

“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ ግራ ገብቶታል፣ በጣም ግራ ገብቶታል፡፡ ሲውል ሲያድር የሚሰማቸውና የሚያያቸው ነገሮች ምክንያትና ማብራሪያ እያጣላቸው ግራ ገብቶታል፡፡ ግራ መጋባት ብቻ ሳይሆን ደስ የማይሉ ሃሳቦች ሁሉ እያለፉ፣ እያገደሙ ይመላለሱበት ጀምረዋል፡፡ ቢቸግረው ወደ አንድዬ ሄደ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኸረ አንድዬ!
(መልስ የለም፡፡)
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምስኪኑ ፍጥረትህ በርህ ላይ ቆሜያለሁ!
አንድዬ፡— እናንተ ሰዎች፤ ትንሽ እንኳን ማረፍ አልችልም ማለት ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይቅርታ አንድዬ፣ ግን… አንተም እረፍት ታደርጋለህ እንዴ?
አንድዬ፡— እረፍት ታደርጋለህ ወይ ብሎ ነገር ምንድነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን መሰለህ አንድዬ፣ አንተ እኮ ለደቂቃ እንኳን ዓይኖችህ ዘወር ካሉ ያልቅልናል ብዬ ነው፡፡ መላ ቅጣችን ጠፍቶ ነገሩ ሁሉ ብልሽትሽቱ ይወጣል ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— አሁንማ እንዴት አምሮባችኋል! ስማ… እኔ እኮ አንዳንድ ጊዜ ለብዙ ሰዓታት ሳያችሁ እቆይና… ፊቴን ዘወር አደርጋለሁ፡፡ ‘ለምን ፊትህን ታዞራለህ’  ብለህ ጠይቀኛ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፤ ለምን ፊትህን ታዞራለህ? ይሄን ያህል አስጠልተንሀል እንዴ!
አንድዬ፡— ምን መሰለህ ምስኪኑ ሀበሻ… እንዳንድ ሰሞን ይሄ ለስንት ክፍለ ዘመን ሊለቃችሁ ያልቻለውን በትንሽ ትልቁ መናቆራችሁን ትታችሁ ስትሳሳቁ፣ ስትተቃቀፉ፣ “በአንድ እንትን እንትን እንበል» ስትሉ ሳያችሁ፣ ደስ ይለኝና፣ “ጎሽ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እኔም አረፍኩ፣” እልና… ከዛ ምን ይሆናል በለኛ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ከዛስ ምን ይሆናል?
አንድዬ፡— ከዛማ የተተቃቀፋችሁትን በቅጡ እንኳን ሳትላቀቁ፣ እንደ ጀግኖች መሳሳማችሁ ቀርቶ፣ ጉሮሮ ለጉሮሮ ትተናነቁልኛላችሁ፡፡ እና አሁን እኔ፣ እናንተን በተመለከተ አላየሁም፣ አልሰማሁም ብል ይፈረድብኛል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ከአንተ በላይ ማና አለና ነው የሚፈረድብህ?
አንድዬ፡— እንደ ዘንድሮ አያያዛችሁ፣ እንደ ዘንድሮ ትከሻ ማስፋታችሁ፣ እንደ ዘንድሮ “ከእኛ በላይ ላሳር፣” አባባላችሁ…የእኔን መንበር ላለመፈለጋችሁ ማረጋገጫ የለኝም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኸረ እንደሱ አትበል! አሁን እንደው የፈለገውን ያህል መስመር ብናልፍ የአንተን መንበር እንመኛለን!
አንድዬ፡— ስማ፣ እኔ ከእነ መፈጠራችሁ የማላውቃችሁ ሁሉ “እሱ ልኮኝ ነው፣” እያላችሁ አዳራሹን ሙሉ ስታስጨበጭቡ አይደል እንዴ የምትውሉት! በል ንገረኛ…ይሄን ሁሉ ሰው የምልከው ይሄን ያህል አርጅቻለሁ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኸረ እንደሱ አትበል፣ አንተ ለተናገርከው እኔ እየደነገጥኩ፣ ሥጋዬ እርግፍ ያለ ነው የሚመስለኝ፡፡
አንድዬ፡— ይልቁንም…ምን እናድርግ መሰለህ፣ ጉዳያችሁን ስትጨርሱ፣ ወደ እኔ ኑና፣ እስቲ ያለፈው እንዳይደገም ምን ማድረግ እንደሚሻል እንመካከራለን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ የእኛ ጉዳይ እኮ አይደለም ሊያልቅ፣ ሳይጋመስ አንኳን ግራ እየገባን፣ ይኸው አንደርድሮ አንተ ዘንድ አመጣኝ፡፡
አንድዬ፡— ምስኪኑ ሀበሻ… ምስኪኑ ሀበሻ ስልህ እዚህ ነኝ በለኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እዚህ ነኝ አንድዬ፣ እዚህ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— እስቲ እናንተ ግራ ሳትጋቡ የኖራችሁበትን ዘመን ንገረኝ፡፡ በላ…እናንተም፣ እኔም አፎይ ያልንበትን ጊዜ ንገረኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ…እሱማ አንድዬ፣ እሱማ…
አንድዬ፡— እኔ እስከማውቀው ድረስ አናንተ ምንም ግራ የማይገባችሁ ነገር የለም፡፡ እንደው ብቻ አሁንስ ሻል አላቸው ስል፣ ነገራችሁ ሁሉ እንደተበላሸ አምፖል ብልጭ ድርግም ሆኖብኛል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አኛስ ምን እናድርግ አንድዬ! እንደው ምን አባታችን ብናደርግ ይሻለናል! ደስ ብሎን እስክስታ ስንወርድ እናረፍድና፣ ገና ቀኑ ሳያጋመስ ደግሞ ወገባችንን ቅንጥስ የሚያደርግ ችግር ይመጣብናል፡፡
አንድዬ፡— እኮ ችግር መጣ ባላችሁ ቁጥር የእኔን በር የምትቆረቆሩት፣ አኔ ነኝ ችግሩን  ያመጣሁባችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደሱ አትበላ፣ አንድዬ እንዴት እንደዚህ ትጠረጥረኛለህ፡፡
አንድዬ፡— ይልቅ ግራ የገባኝ እኔ!…እኔ ዘንድ ከመመላለስ ለምን ችግራችሁን በራሳችሁ አትጨርሱትም! ዘላለማችሁን በትንሽ ትልቁ፣ ሞግዚት፣ እሹሩሩ ካላላችሁ አይሆንም ማለት ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን መሰለህ አንድዬ፤ በራሳችን ለመፍታትማ መሞከራችን መች ቀረ…እዚህ ያለውን እንዱን ችግር ፈታነው ስንል፣ እዛ ሌላ ችግር ተቋጥሮ ይጠብቀናል፡፡ እዚህ የተንጋደደውን ቀና አደረግነው ስንል፣ እዛ ደግሞ ቀጥ ብሎ የቆየው፣ መሬት ላይ ይጋደማል… አንድዬ እውነቴን ነው የምልሀ በጣም ግራ ነው የገባን፡፡
አንድዬ፡— እኮ አሁን እኔን ምን ሁን እያልከኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ጣል፣ ጣል አታድርገና! ምን መሰለህ አንድዬ፣ እስቲ ትንሽ ለውጥ ቢጤ እናካሂድ ብለን፣ ጎንበስ ቀና ማለት ከጀመርን፣ ዓመት ልንደፍን ምንም አልቀረን፡፡ የሚገርምህ አንድዬ፤ መቼም የዛ ሰሞን ደስታችንን፣ ይህ ነው ብዬ ልነግርህ አልችልም፡፡
አንድዬ፡— ምኑን ትነግረኛለህ፣ ስንት ወር ሙሉ የእናንተ ሆታና ጭፈራ ድምጽ፣ እኔንም እረፍት ነስቶኝ አይደል እንዴ የከረመው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደሱ ስትል ሆዴ ይባባል! እኛ ደስ እንዲለን ትፈልግ የለም እንዴ!
አንድዬ፡— አሱ በማን እድሌ፣ እኔም እረፍት አገኘሁ ማለት ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ታዲያ የእኛ ሆታና ጭፈራ ለምንድነው ሲረብሽህ የከረመው!
አንድዬ፡— እንግዲህ እውነቱን ንገረኝ ካልክ፣ የሚያስደስቱ ነገሮች ያልካቸውና ጭፈራችሁ አልተመጣጠነም፡፡  ሆታው ትንሽ የበዛ አይመስላችሁም! የሚገርም እኮ ነው፣… እኔማ እነኚህ ሰዎች ትንፋሻቸውን ከአሁኑ ጨርሰው፣ ተስፋ ካደረጓቸው ነገሮች ግማሹን ያህል ቢፈጸምላቸው ምን ሊሆኑ ነው እል ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንጨፍራለና! አንድዬ፣ ወገባችን እስኪቀጭ ነዋ የምንጨፍረው!
አንድዬ፡— ለዛ ያብቃችሁ!…ምንም እንኳን አሁን፣ አሁን ብዙዎቻችሁ ላይ የማየው የግልግል ጉልበተኛነት ባህሪይ ጥርጣሬ ላይ ቢጥለኝም፣ የአንዳንዶቻችሁ ልብ ምን ምስጢር እንደደበቀ ግራ ቢገባኝም…ተስፋችሁ ሞልቶላችሁ ወገባችሁ እስኪቀጭ ለመጨፈር ያብቃችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አየህ አንድዬ፣ አየህልኝ አይደል አንድዬ… እንዲህ ስትል ልቤ ይሞላል፡፡ በቃ፣ አንድዬ ትቶ አልተወንም እላለሁ፡፡
አንድዬ፡— አንድ ነገር አስታወስከኝ… አንድ ነገር በገጠማችሁ ቁጥር ሽቅብ እያንጋጠጣችሁ፣ “ምን አደረግንህ፣ ምን በደልንህ እያላችሁ የምታማርሩኝ፣ እኔም ልጠይቃችሁ…ምን አደረግኋቸው! ራቅ ስላልኩባችሁ ነው እንጂ እነኚህ ደንብ ማስከበር የሚሏቸውን ትጠሩብኝ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!…. ተው እዚህ በቆምኩበት ሀውልት ሆኜ እንዳልቀር!?
አንድዬ፡— አይዞህ፣ ሀውልትማ  አትሆንም፡፡ ለነገሩ እኮ በዙሪያህ የሚንቀሳቀሱ ሀውልቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንድ አንተ ብትጨመር፣ ክፋት የለውም ለማለት ነው፡፡ በል ደህና ሁን!
ምስኪን ሀበሻ፡— ደህና ሁን አንድዬ፣ ደህን ሁን!
ምስኪን ሀበሻ አሁንም ግራ ገብቶታል፣ በጣም ግራ ገብቶታል! ምናልባትም… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ…” እያለም ይሆናል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!
Read 1647 times