Print this page
Sunday, 03 March 2019 00:00

የናይጀሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ምርጫው ተጭበርብሯል አሉ ክስ እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ረቡዕ ይፋ በተደረገው የዘንድሮው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ሙሀመድ ቡሃሪ ማሸነፋቸው መገለጹን ተከትሎ፣ በተፎካካሪነት የቀረቡት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አቲኩ አቡበከር፣ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉ በይፋ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
ረቡዕ ማለዳ ላይ ይፋ በተደረገው የምርጫ ውጤት ሙሃመድ ቡሃሪ 56 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ካስታወቁ ከሰዓታት በኋላ፣ ተሸናፊው አቲኩ አቡበከር በሰጡት መግለጫ፣ ምርጫው በ36 ግዛቶች ተጭበርብሯል፣ ዳግም እንዲካሄድ በፍርድ ቤት ክስ እመሰርታለሁ ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በጤና እክል ሳቢያ አገሪቱን በቅጡ ለመምራት አልቻሉም፤ ሲሾሙ የገቡትን ቃል አክብረው አገሪቱን ከኢኮኖሚ ቀውስና ከሽብርተኞች መናኸሪያነት ማውጣት አልቻሉም በሚል ተቃውሞ በርትቶባቸው የከረሙት የ76 አመቱ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ቡሃሪ፤ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን እንደሚቀጥሉ ያረጋገጠው የምርጫ ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በርካታ የቡሃሪ ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ገልጧል።
በተለያዩ ምክንያቶች ሲራዘም የቆየው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ቅስቀሳ ከተጀመረበት ጥቅምት ወር አንስቶ በተነሱ ግጭቶች ከ260 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ውጤቱን አልቀበልም ማለታቸው ተጨማሪ ግጭት ሊያስከትልና አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ሊያመራት እንደሚችል መሰጋቱንም አክሎ ገልጧል፡፡



Read 860 times
Administrator

Latest from Administrator