Print this page
Sunday, 03 March 2019 00:00

ምንሊክ ሆስፒታል አቋርጦት የነበረውን የኩላሊት እጥበት እንደገና አስጀመረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ምንሊክ ሆስፒታል ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮት የነበረውንና ከውጭ አገር በሚገቡ ግብአቶች እጥረት የተነሳ ከ6 ወራት በላይ አቋርጦት የነበረውን የኩላት እጥበት አገልግሎት ባለፈው ረቡዕ እንደገና አስጀመረ፡፡
18 የኩላሊት ሕመምተኞች ወደ ዘውዲቱና ወደ ጳውሎስ ሆስፒታሎች አከፋፍሎ እንደነበረ የተናገሩት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ሜሊ ሆስፒታሎቹ ለራሳቸው ህሙማንም ህክምና ይሰጡ ስለነበረ ጫና ስለነበረባቸው የእኛዎቹን በሦስት ፈረቃ ሌሊት አገልግሎት ይሰጡ ነበር፤ የሌሊት አገልግሎት ደግሞ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ ብለዋል፡፡
አሁን ህክምናውን ያስቀጠለው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ የ6ወር ፓኬጅ ገዝተን ነው ያሉት ዶ/ር ዮሐንስ፣ በቅርቡ ዘውዲቱ ሆስፒታል 32 ማሽኖች ይሰጣሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ 8ቱ ለምኒሊክ ሆስፒታልም ስለሚሰጡ ያኔ ትልቅ አቅም ይኖረናል ብለዋል፡፡
አሁን አገልግሎቱ ሊጀመር የቻለው 50 በመቶውን ክፍያ አስተዳደሩ ችሎ፣ 50 በመቶውን የኩላሊት በጎ አድራጎት ድርጅት ችሎ ሲሆን ሕሙማን የሚከፍሉት ¼ ወይም 500 ብር ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እየተካሄደ ያለው በዘውዲቱ በቅዱስ ጳውሎስና በምኒልክ ሆስፒታሎች ሲሆን ወደፊት አገልግሎቱን በየካቲት ሆስፒታል ለመጀመር እቅድ እንዳለ ዶ/ር ዮሐንስ ሜሊ ገልፀዋል፡፡  

Read 4120 times