Print this page
Sunday, 03 March 2019 00:00

ሞኙን ላኩትና ሞኞች ሞኞች አገር ሞኙም አልጠየቃት ሞኟም አትናገር

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ሶስት ወንጀለኞች ላይ ሞት ፈረዱ፡፡ ከተፈረደባቸው አንዱ፤
“ንጉሥ ሆይ! አንድ ዕድል ቢሰጡኝ ፈረስዎትን ቋንቋ አስተምሬው እሞት ነበር፡፡” አላቸው፡፡
“በምን ያህል ጊዜ ልታስተምርልኝ ትችላለህ?”
“በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ” ሲል መለሰ፡፡
“ጥሩ፣ አንድ ዓመት እሰጥሃለሁ”
“እኔም በአንድ ዓመት ተዓምር አሳይዎታለሁ!” አላቸው፡፡
አብሮት የታሰረው ሰው፤
“እንዲህ ያለ ቃል ለምን ገባህ? ለምንስ ይጠቅምሃል? በትክክል ምክንያታዊስ ነህ ወይ?”
“አዎን”
“እንዴት?”
“ምክንያቱ ምን መሰለህ?”
አየህ 1ኛ ወይ ንጉሡ ይሞታሉ
     2ኛ ወይ እኛ ማምለጫ እናገኛለን
     3ኛ ወይ ፈረሱ ይማራል
ማን ያውቃል?”
“ለካ ይሄ ሁሉ ዕድል አለ”?!
*   *   *
ብዙ ዕድል እያለን የማንጠቀም እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን፡፡ ምክንያቱን በአጭሩ መንቆጥ ይቻላል፡፡
አንሄድም፣ አንንቀሳቀስም!
ከሄድንበት አንማርም!
የተማርነውን አናሻሽልም!
የተሻሻልነውን ለማንም አናካፍልም! አናስተላልፍም፡፡ መቼም እንዴትም እኒህን ነጥቦች ውል እንደምናስይዛቸው አይታወቅም፡፡ ከጥንቱ ከጠዋቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ጥያቄዎች አሉን፡-
“መቼ ነው ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ የሚገባው?”
“መቼ ነው ፍትህ የሚሰፍነው?”
“መቼ ነው ነገን የምናምነው?”
ሳይመለሱ የቆዩ ጥያቄዎቻችን ዕጣ ፈንታቸው ምንድን ነው? የት ይደርሳሉ? ዛሬስ ምን ያህል ዕድሜ አላቸው?
መሪዎቻችን ህዝባቸውን አያስቡም፡፡ ህዝቦች መሪዎቻቸውን ያለምክንያት ይጠምዷቸዋል፡፡ ጊዜ አይሰጡም፡፡ ቦታ አይሰጡም፡፡ ተስፋ አይሰጡም፡፡ ሀሳባቸውን አይገልጡም! ሀሳባቸውን አያገናኙም!
አንድ አሳቢ፤
“The whole theory of development is knowing what change is all about” የዕድገት ምስጢሩ ለውጥ ምንድን ነው ማለት ላይ ነው እንደማለት ነው፡፡
ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፣ “በባለካባና ባለዳባ” ቴያትር፣
“አንድ ዓለም ተሰጠ ለአዳም ለሄዋን
ለሁለቱ፣ ተረቱ፣ እንደሚነግረን
ምንስ ልጆቻቸው ቢረቡስ ቢራቡ
ጥቂቶቹ ጠግበው ብዙዎች ይራቡ?
ጥቂቶች ሲያምራቸው ያንሱ ጦርነት
ብዙዎችም ይሂዱ ለመሞት ለእልቂት፣”
የአገራችን ዕውነት ይሄው ነው! ጥቂቶች ይኖራሉ፤ ብዙዎች ይሞታሉ! ማንም ምንም ሳይጠይቅ መንገዳችንን እንቀጥላለን፡፡ የሞኞቹን አገር ምሳሌ ሆነን መጓዛችን መሆኑ ነው!
“ሞኙን ላኩትና ሞኞች ሞኞች አገር
ሞኙም አልጠየቃት
ሞኟም አትናገር!”  
የሚለው ተረት የሚመለከተን እዚህ ጋ ነው፡፡ እንጠይቅ! እንጠይቅ! እንጠይቅ!

Read 7941 times
Administrator

Latest from Administrator