Sunday, 03 March 2019 00:00

ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ዓመት ማጠናቀቂያ በግማሽ ይሸጣል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“የምከተለው የኢኮኖሚ ሞዴል
ካፒታሊዝም ነው” ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

የቴሌ ኮሚኒኬሽን 49 በመቶ ድርሻ ወደ ግል ለማዘዋወር አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንና በዚህ ዓመት መጨረሻ የከፊል ሽያጩ እንደሚከናወን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ማስታወቃቸውን ጠቅሶ ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚከተሉት የኢኮኖሚ ሞዴል ካፒታሊዝም መሆኑን አስታውቀው በዚህም ባለፉት 28 ዓመታት በመንግስት ቁጥጥር ስር ቆዩ ግዙፍ ተቋማትን ወደ ግል ማዘዋወር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚወስዱት የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሚከተሉት የካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ሞዴል እና ተቋማትን ወደ ግል የማዘዋወር ፖሊሲ ከራሳቸው ፓርቲ (ኢህአዴግ) ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር የጠቀሰው ፋይናንሻል ታይምስ ጠ/ሚኒስትሩ በውሳኔያቸው ገፍተውበት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር ዝግጅቶችን ማጠናቀቃቸውን አስታውቋል፡፡
መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 49 በመቶ ድርሻ ወደ ግል እንደሚያዘዋውር ቀሪውን 51 በመቶ በራሱ እያስተዳደረ እንደሚቀጥል ጠ/ሚኒስትሩ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 60 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሲሆን ይህ አመት ከመጠናቀቁ በፊት በከፊል ወደ ግል ይዘዋወራል ተብሏል፡፡
ወደ ግል መዘዋወሩም ለሃገሪቱ በቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝም ጠ/ሚኒስትሩ በቃለ ምልልሳቸው ያስገነዘቡ ሲሆን የአገልግሎት ቅልጥፍና እና ተወዳዳሪነትም ይጨምራል ደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡   



Read 6188 times