Sunday, 03 March 2019 00:00

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ካፒታሉን ወደ 3.5 ቢ. ብር ማሳደጉን አስታወቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው


ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ካፒታሉን ወደ 3.5 ቢ. ብር ማሳደጉን የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከትላንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ ከ10 ዓመት በፊት በተፈረመ 279.2 ሚ እና በተከፈለ 91.2 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲሁም በ5 ሺህ ባለ አክሲዮኖች መስከረም 8 ቀን 2001 ዓ.ም መመስረቱን የገለፁት የባንኩ ኃላፊዎች፣ በአገሪቱ አጠቃላይ በባንክ ስራ ላይ የነበሩ እንደ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የዋጋ ግሽበትና መሰል በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጦ በ10 ዓመት ቀርቶ በ50 ዓመት ሊሳካ የማይችል ስራ ሰርቷልብለዋል፡፡ ባንኩ በአሁን ሰዓት 257 ቅርንጫፎች፣ 5775 ሰራተኞች፣ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ ከ300 ሺህ በላይ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ያለው ሲሆን ወደ 15.7 ቢ፣ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለ9ሺህ ተበዳሪዎች ማቅረቡንና 5.9 ቢሊዮን ገደማ የብሔራዊ ባንክ ቦንድ በመግዛት እንዲሁም ባለአክሲዮኖቹን ወደ 12 ሺህ በማሳደግ አንቱ የተሰኙ ስራዎችን መስራቱ ተገልጿል፡፡
ባንኩ የተከፈለ 2.2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያለው ሲሆን በአጠቃላይ ካፒታሉን ወደ 3.5 ቢሊዮን ማሳደጉም የስኬቱ መለኪያ ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበትን፣ የብሔራዊ ባንክ አስቸጋሪ መመሪያዎችን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን፣ የወጪ ንግድ በበቂ ሁኔታ አለመኖርንና እንደ መብራትና የቴሌኮሚዩኒኬሽን መሰረተ ልማት አለመሟላት ፈተናዎች ቢጋረጡበትም ከላይ የተገለፁትን ውጤታማ ስራዎች በመስራት በዘርፉ ተምሳሌት ሆኗል ያሉት ኃላፊዎቹ፣ በዚህም በአገሪቱ ከሚገኙ ባንኮች በተቀማጭ ገንዘብ 7ኛ፣ በቅርንጫፉ ብዛት 6ኛ፣ በትርፍ መጠን 4ኛ በውጭ ምንዛሬ ማስገኘት 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ውጤታማ ባንክ እንደሆነ ተገልጿል፡፡




Read 5031 times