Sunday, 03 March 2019 00:00

ለአንድ እራት 5 ሚሊየን ብር የሚከፈልበት ልዩ ምሽት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)


· ገቢው በ29 ቢ. ብር አዲስ አበባን ለማስዋብ ለተያዘው ፕሮጀክት ይውላል
· ታዳሚዎቹ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር የተናጥል ፎቶ የመነሳት ዕድል አላቸው ተብሏል
· ታላላቅ ባለሀብቶች፣ የዓለም አቀፍና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተጋብዘዋል



የመዲናዋን ገፅታ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚለውጥ የተነገረለትንና በቅርቡ ይፋ የተደረገውን የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸውን የማልማት ስራን ወጪ ይደግፋል የተባለ ለአንድ እራት 5 ሚሊዮን ብር የሚከፈልበት የእራት ምሽት ሊደረግ ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ 5 ሚሊዮን ብር ከፍለው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ለእራት ለሚታደሙ እንግዶች የተለያዩ መታሰቢያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
“እራት ለሸገር” በሚል ስያሜ በተዘጋጀው በዚህ የእራት ግብዣ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለታላላቅ ባለሀብቶች፣ ለዲፕሎማቶችና ለዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጥሪ መተላለፉን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በጣሊኑ ቫርኔሮ ኩባንያ የሚሰራውና በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣል የተባለው የአዲስ አበባ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች የማልማትና የማስዋብ ስራ ሲጠናቀቅ የእራት ምሽቱ ታዳሚዎች ስም በተናጥል ተፅፎ በወንዝ ዳርቻዎቹ ላይ እንደሚቀመጥ ታውቋል፡፡ ታዳሚዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በተናጠል ፎቶ የመነሳት ዕድል የሚያገኙ ሲሆን ይኸው ፎቶግራፎቹ ተሰብስበው የ“አዲስ አበባን ገፅታ የቀየሩ ግለሰቦች” በሚል በአንድ ጥራዝ ላይ እንደሚቀመጡም ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎች ልማት ስራ፣ የአዲስ አበባ ከተማን ለሁለት ከፍለው የሚያልፉ ወንዞችን መሰረት ያደረገ ሲሆን ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ ያለውን 56 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ይሆናል ተብሏል፡፡ ሥራው ሲጠናቀቅ 4ሺ ሄክታር መሬት እንደሚያለማ የተነገረ ሲሆን በውስጡም የመዝናኛ፣ የመጓጓዣ፣ የንግድ ማዕከላትና አረንጓዴ ሥፍራዎች (ፓርኮች) ይኖሩታል ተብሏል፡፡




Read 971 times