Sunday, 24 February 2019 00:00

እየቻሉ አለመቻል!!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)


ደርግ ከሥልጣን ወረደ፤ ሕውሓት/ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን ያዘ፡፡ ሥልጣን በያዘ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከሶስቱ የእስልምና እምነት ብሔራዊ በአላት አንዱ የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ። የሃይማኖቱ ተከታዮች ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉን በአዲስ አበባ ስቴዲየም እንዲያከብሩ ተደረገ፡፡ በስቴዲየሙ የስግደት ሥነ ስርዓት ላይ ከተገኙት ሰዎች አንዱ፣ የመገናኛና ትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር አብዱል መጂድ (አፈሩን ያቅልልላቸውና) ነበሩ፡፡ በዓሉ በዚያ መንገድ በመከበሩ የተሰማቸውን ደስታ እየተፍለቀለቁ ገለጹልኝ፡፡
ከእስልምና እምነት ውስጥ የረመዳንን ፆም ፍች ጨምሮ ሦስቱ  ብሔራዊ በዓል ሆነው እንዲከበሩ በአዋጅ ያፀደቀው ደርግ ነው፡፡ እነዚያ በዓላት በሰፊ ሜዳ በስቴዲየም እንዲከበሩ ማድረግ፣ ለደርግ የሚከብደው አልነበረም ግን አላደረገውም፡፡ ምስጋናውን ሕውሓት/ኢህአዴግ ወሰደው፡፡ ማድረግ ሲችል ባለማድረጉ፣ ክብርም ሞገስም፣ መወደድንም ደርግ አጣ፡፡
ሲቻል አለማድረግን የሕውሓት/ኢሕአዴግ ትልቁ ሰው አቶ መለስም (አፈሩን ያቅልልላቸውና)  ደገሙት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስሙን ወደ አፍሪካ ኅብረት በለወጠበት ጊዜ የድርጅቱን ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ ለማንሳት ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡ ያንን ክርክር “የኢትዮጵያ መንግሥታት እኛን በደሉ እንጂ እናንተ ምን ጎደለባችሁ” በሚል መንፈስ ተሟግተው  ጽ/ቤቱ በአዲስ አበባ  እንዲቀጥል ማድረጋቸው አይዘነጋም። በዚህም አቶ መለስን አከብራቸዋለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት ግቢ የጋናው ፕሬዚዳንት የክዋሜ ንኩሩማህ ሐውልት እንዲቆምለት በአደረጉት ክርክር ደግሞ አብዝቼ የማዝንባቸው ሰው ናቸው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጡት ከጋናው ክዋሚ ንክሩማህ በላይ ንጉሠ ነገሥቱ ናቸው፡፡ ከአሁን አሁን ሳይስማሙ ቻርተሩን ሳይፈርሙ መሪዎች ሊወጡ ነው እየተባለ ሲጠበቁ የነበሩት የግብፁ ገማል አብድል ናስርና ሌሎች እንዲፈርሙ የተገደዱት በንጉሡ ግፊትና ተፅዕኖ ነው፡፡ ይህን ቻርተር ሳንፈርም ከዚህ አዳራሽ አንወጣም በማለት የወሰዱት አቋም የሚያስመሰግናቸው መሆኑም አይካድም፡፡
ሌላው ሊታወስላቸው የሚገባው አዲሱ የድርጅቱ ሕንፃ በቻይና እርዳታ ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት እስከ ጀመረባት ጊዜ ድረስ አሁንም እየተገለገለበት ያለውን የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት የነበረውን ሕንፃ ለድርጅቱ የሰጡት ንጉሠ ነገሥቱ ናቸው፡፡ ሕንፃው ለአባዲና፣ ለአሁኑ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ የተሠራ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ የናይጄሪያን የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የጊኒንና የሴኔጋልን አለመግባባት ለማስወገድ ላደረጉት ጥረት፣ እንዲሁም አሁን በመነጣጠል ሊያበቃ የሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም ባደረጉት ሽምግልና የአፍሪካ አባት እስከመባልም ደርሰው ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሰማኒያኛ የልደት በዓላቸው በመላ አፍሪካ እንዲከበር መደረጉም አይዘነጋም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የንጉሡን አስተዋፅኦ በንፁህ ኅሊና አይተውላቸው ቢሆን ኖሮ፣ በድርጅቱ ቅፅር ግቢ ከሚቆሙ የመሪዎች ሐውልቶች የመጀመሪያው የንጉሡ ነበር የሚሆነው። ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እያገኘ ያለውን ምስጋና፣ መለስ ለእራሳቸው ሊያደርጉት ሲችሉ ያመለጣቸው ዕድል ነው። ዶክተር ዐቢይና መንግሥታቸው በወሰዱት እርምጃም ምስጋና እንደሚገባቸው አምናለሁ፡፡  
በንጉሡ ዘመን ከነበሩት ዲፕሎማቶች አንዱ የሆኑት አቶ አስፋው ተፈራ እንዲህ ይላሉ፤ “ምን አልባት ለዛሬውና ለመጪው ትውልድ ይጠቅም እንደሁ አንድ ነገር ለማለት እወዳለሁ። ግርማዊነታቸው እንዲያደርጉልን የምንሻውን ነገር ሁሉ አላደረጉልንም ከማለት ይልቅ በሀገር ውስጥና ከውጪ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አኳያ ተጨባጭ ሁኔታውን መመርመርና ሚዛናዊ የሆነ ነፃ ፍርድ መስጠት ተገቢ ይመስለኛል”
ይህ የአቶ አስፋው ተፈራ ሀሳብ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመንግሥታቸው ዘንድ ዋጋ እንዳገኘ እገነዘባለሁ፡፡ ሶስት ሚሊየን ብር ወጪ አድርጎ የመታሰቢያ ሐውልታቸውን በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ እንዲቆም ያደረገው ንጉሡን የሚቃወምና የሚወቅስ ጠፍቶ አይደለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው ሥራቸውን ከጊዜው ጋር አገናዝበውና መዝነው ያደረጉት ነው፡፡
በገበጣ ጨዋታ እጅ በንክ የሚባል ሕግ አለ። በያዝከው ቀጥል ብሎ የሚያስገድድ ሕግ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና መንግሥታቸው፤ ስለ ንጉሡ ሊወስዷቸው የሚገቡ ተጨማሪ እርምጃዎች አሉ፡፡ ከእነሱም አንዱ፣ ንጉሡ በግል ገንዘባቸው ያቋቋሙት የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጉዳይ ነው። መንግሥት እንጦጦ አጠቃላይ እያለ ቢጠራውም፣ ሕዝብ ተፈሪ መኮንን በሚለው ቀጥሏል፡፡ የመንግሥትን እርምጃ አልወደደውም። ለንጉሡ ይህ ስም ሊመለስላቸው ይገባል። ከስምንት ዓመት በፊት ይህን ጥያቄ አቅርቦ የነበረው የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር፣ ያልተሳካለት በጊዜው የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መንግሥት የንጉሡ የሆነውን ነገር ሁሉ ስለሚያጣጥለው እንጂ የማይገባቸው ሆኖ አይደለም፡፡ ዳግም የሚገባቸውን እንዳያጡ ማድረግ ይገባል፤ ትልቅ የአስተዋይነት ተግባርም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከ1600 ዓመታት የግብፅ ተገዥነት ነጻ ያወጧት ንጉሠ ነገሥቱ ናቸው፡፡ ሐውልቱ በተመረቀ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ አልተገኙም፡፡ ምነው? አሰኝቶኛል፡፡ የቅዱስ ፓትርያሪኩ የፕሮቶኮል ሹም መምህር ሙሴ ኃይሉ በሥነ - ሥርዓቱ እንዲገኙ የቀረበላቸው ግብዣ ዘግይቶ በመድረሱና ለመኪናቸው የይለፍ ፈቃድ ባለመገኘቱ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ እሱስ ቢሆን ለምን ማለት አለብኝ፡፡  
ከዚህ ቀደም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጃንሆይን ነገር አደራ ብያቸው ነበር፡፡ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሌላውም አደራ ነበርና ጥያቄው  መልስ እያገኘ ነው፡፡ ዛሬም አንድ አደራ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አለኝ፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የንጉሡን ሐውልት ብሔራዊ ቤተ መንግሥት አጠገብ ለማቆም እየጣሩ ነበር፡፡ የእሱንም ነገር አደራ ለማለት ነው፡፡  

Read 611 times