Sunday, 24 February 2019 00:00

“ከህውሓት ጋር አሁንም ግልፅ የፖለቲካ ልዩነት አለን”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

“በትግራይ ምንም የተቀመጠ አዲስ አቅጣጫ የለም”

  የቀድሞ የህውሓት አንጋፋ ታጋይ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የአረና ትግራይ አባል የሆኑት ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፤ ከሰሞኑ
44ኛው የህውሓት ምስረታ በዓል በመቐለ ሲከበር ተጋባዥ ከነበሩ እንግዶች አንዷ ነበሩ፡፡
ከ18 ዓመታት መለያየት በኋላ ከህውሓት አመራሮች ጋር በዓሉን ያከበሩት ወ/ሮ አረጋሽ አጋጣሚው እንዴት እንደተፈጠረ፣ ከህውሓት ጋር ያላቸው
አንድነትና ልዩነት እንዲሁም በትግራይ የፖለቲካ አካሄድ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


ህውሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበት 44ኛ ዓመት በመቀሌ ሲከበር ተሳታፊ ነበሩ፤ እንዴት በመድረኩ ተሳታፊ ሆኑ? ጥሪውንስ ማን ነው ያቀረበላችሁ?
የትግራይ የንግድና አነስተኛ ማህበር ነው ለኛ ግብዣ ያቀረበልን፤ ህውሓት አይደለም በፕሮገራሙ ላይ እንድንገኝ የጋበዘን፡፡ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው በንግድ ማህበሩ በኩል ነው፡፡ ለኛ ጥሪ ሲያቀርቡ ያሉት፣ “በህውሓት መካከል ክፍፍሉ ካጋጠመበት 1993 ወዲህ ለእናንተ መስዋዕትነት ዋጋ የሰጠ የለም፤ ይሄ ተገቢ አይደለም፤ እውቅና ሊሰጣችሁ ይገባል” ለከፈላችሁት ዋጋና መስዋዕትነት ምስጋናችንን ማቅረብ እንፈልጋለን በሚል ነው፡፡
በሃገሪቱ ከተጀመረው ለውጥ ጋር ተያይዞ ይሆን የጋበዟችሁ?
እነሱ ያሉት “ይሄን ለማድረግ ካሰብን ቆይተናል፤ ነገር ግን በተለያየ ጊዜ ሃሳቡን አንስተነው ሁኔታው አመቺ ስላልነበረ ተግባር ላይ ልናውለው አልቻልንም ነበር፤ አሁን ግን ሁኔታው የተሻለ ስለሆነ ይሄን በአል ምክንያት በማድረግ፣ በራሳችን ተነሳሽነትና በራሳችን ዝግጅት ነው አሁን ያሰባሰብናችሁ” ከ1993 በኋላ ከድርጅቱ የወጣችሁ፣ ከመከላከያ የወጡ ጀነራሎች እንዲሁም በስልጣን ላይ ያሉትን ጨምረን እስካሁን ላደረጋችሁትና ለከፈላችሁት መስዋዕትነት እውቅና ለመስጠት በመፈለግ ነው የጋበዝናችሁ ነው ያሉት። ጥሪው የህውሓት አልነበረም፡፡ ነገር ግን እነሱም እኛም በዚያ መድረክ አንድ ላይ ተገናኝተናል፡፡
ህዝቡ እናንተ በወቅቱ ከድርጅቱ የተለያችሁበትን ምክንያት ምን ያህል ተረድቷል?
እኛ በወቅቱ ከህውሓት የተባረርነው ሙስና ሰርተን ወይም በተለየ ወንጀል ሳይሆን ለፍትህ ስለጮህን እንደሆነ ህዝቡ ያውቃል፡፡ ሃቁን አልረሳም፡፡ ህዝቡ በወቅቱ የተደረገው ነገር ሁሉ ትክክል እንዳልነበር ያውቃል፤ ለዚህም ነው ዛሬ ጊዜ ጠብቀው እውቅና የሰጡን፡፡
በዚህ መንገድ ተሰባስባችሁ ስትገናኙ እርስዎ በግልዎ ምን ተሰማዎት?
በእርግጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች እርስ በእርስ እንገናኝ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በስብሰባዎችም መገናኘት ጀምረናል፡፡ እኔ በዚህ ወቅት የተሰማኝ ስሜት የህውሓት ኢ-ፍትሃዊ የሆነ አሰራርና አካሄድ እየተናደ መምጣቱን ነው፡፡ ህዝቡ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት መብቱ ታግዶ የቆየ ከመሆኑ አንፃር፣ አሁን በትንሽ ድርጅትን ቢሆን ህዝቡ የተሰማውን ለመግለፅ በመቻሉ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከዚህ በላይ እየሰፋ መሄድ አለበት። ይሄ እንዲሆን እኛም ስራችንን መስራት አለብን። በሃገሪቱ በመጣው ለውጥ ምክንያት ህዝቡ ይሄን ዓይነት ክፍተት ማግኘቱን ተገንዝቤያለሁ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፡፡ እንዳልኩት በፕሮግራሙ ላይ እንድንገኝ የጋበዙንም ህውሓቶች ሳይሆኑ ማህበራቱ ናቸው፡፡ ይሄ በራሱ አንድ አመላካች ነገር ነው፡፡ አሁን በተደረገው ነገር ህዝቡ ሃቁን በራሱ ጊዜ ነው ያወጣው፡፡ ያ ሁሉ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ድብደባ ሲደርስብን የነበረው ገደል ነው የገባው፡፡ ህዝቡ ማንን እንደሚያከብር አሳይቷል፡፡ የኛን ማንነት ህዝቡ ጠንቅቆ እንዲያውቅ መልዕክት የተላለፈበት አስደሳች መድረክ ነው፡፡ እውነቱ እየተገለፀ የመጣበት ጊዜ ነው፡፡ ህዝቡን ለእውነት ዋጋ ሰጥቷል፡፡ በፊት እነሱ ፀረ ህዝብ ናቸው፣ ፀረ ሰላም ናቸው እየተባልን ነበር ስንገለጽ የነበረው፡፡
በዚህ መድረክ ላይ ለዚህ ለተፈፀመባችሁ በደል ይቅርታ ተጠይቃችኋል?
እንዲህ ዓይነት ነገር የለም፡፡ ከእነሱ ጋር አሁንም ልዩነታችን እንደፀና ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ንግግር አላደረግንም፡፡ ፕሮግራሙ የንግድ ማህበራቱ ፕሮግራም ነው፤ ከዚያ ያለፈ ነገር የለም፡፡ ከእነሱ ጋር ምንም ያደረግነው ንግግር የለም፡፡ ይቅርታ ደግሞ ዝም ብሎ አይሆንም፡፡ ዝም ብሎ ይቅርታ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ዋናው መፍትሄ የህዝቡን ችግር መፍታት ነው፡፡ በምን መንገድ ነው የህዝቡን ችግር መፍታት የሚቻለው? ከአሁንስ በኋላ እንዴት ነው መጓዝ የሚቻለው? የህዝብ መብት እንዴት ነው የሚከበረው? የሚለው ላይ ገና ስምምነት የለንም። በእነዚህ ላይ መስማማት ሳይኖር እርቅ ምንድን ነው? ብዙ መስማማት ያለብን ነገር አለ፡፡ ዝም ብሎ በደፈናው “ይቅር በቃ፤ ያለፈውን በድለናችኋል” ቢሉንም መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖለቲካ ልዩነት ነው ያለን፡፡ ከውህሓት ጋር ግልፅ የፖለቲካ ልዩነት አለን፡፡ ስለ ህዝቡ ችግር ተነጋግረን፣ ችግሮችን መቅረፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ መስራት ይቻል ይሆናል፡፡
ህውሓት አሁንም ፀረ - ለውጥ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
የኔ አቋም ከዚህ ብዙ የራቀ አይደለም፡፡ የለውጥ ኃይሉም ቢሆን ገና የለውጡን ፍኖተ ካርታ አላስቀመጠም፡፡ ለኢትዮጵያ ተስፋያለው የመናገር የመፃፍ፣ የመደራጀት ነፃነት ትግራይ ውስጥ የለም፡፡ አሁንም በጣም የጠነከረ የካድሬ አደረጃጀት መዋቅር ነው፡፡ የእነዚህን ካድሬዎች አስተሳሰብ የሚቀይር ስራ አልተሰራም፡፡
በትግራይ ምንም አይነት የተቀመጠ አዲስ አቅጣጫ የለም፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አብሮ መኖር እየተሸረሸረ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ በሰሜንም በደቡብም “ጠላት አሉብህ እየመጡብህ ነው፤ አንድ መሆን አለብህ፤ አንድ ሆነህ መመከት አለብህ፤ ነው እየተባለ ያለው፡፡ ይሄ ሁኔታ ደግሞ ለኢህአዴግም ለህወኃትም የእድሜ ማራዘሚያ መንገድ ነው፡፡
ስለዚህ በትግራይ ግልጽ የሆነ የለውጥ አቅጣጫዎች አልታዩም፡፡ በአጠቃላይ ለውጥ የሚባለውም ግልጽ አቅጣጫ አላስቀመጠም፡፡ ግልጽ ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንዲኖር አሁንም ግፊት ያስፈልጋል፡፡ ህወኃት ላይ ይህ አይነቱን ግፊት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በትግራይ ፀረ ዲሞክራሲነት ወደባሰበት ደረጃ እየሄደ ነው ማለት ይቻላል። ህወኃት እስካሁን ምንም አልተሻሻለም ማለት ይቻላል፡፡
ቢያንስ እናንተን አካቶ ውይይት እያደረገ መሆኑን እንደመሻሻል የሚመለቱት አሉ …
መሠረታዊ ለውጥ አላደረገም፡፡ ለትግራይ ህዝብ የመጣ ምንም ለውጥ የለም፡፡ ህዝቡ እኛን ከእነሱ ጋር ለማየት የፈለገው፣ እናንተ ብትኖሩ ትግራይ እንዲህ አትሆንም ነበር የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ አቅም ሳይኖራቸው በስልጣን ቆይተዋል፤ ትግራይንም ወደ ውድቀት ወስደዋታል የሚል አመለካከት ነው ህዝቡ ያለው፡፡ ህወኃት ውስጥ በ1993 የተለዩ ሃይሎች ቢኖሩ ኖሮ፣ ዛሬ ያጋጠመው ፀረ ዲሞክራሲያዊነትና አምባገነንነት አያጋጥምም ነበር ነው የሚለው ህዝቡ፡፡ አሁንም አንድ ላይ ካልሆናችሁ መፍትሔ አይመጣም እየተባለ ነው፡፡
ተባረው የወጡት ናቸው የትጥቅ ትግሉ መሃንዲሶች፤ አሁንም ምህንድስናው ያለው እነሱ ጋ ነው እያለ ነው ህዝቡ፡፡ እናንተ ናችሁ የገፋችኋቸው የሚል ጫና ህዝቡ እያደረገባቸው ነው፡፡ ከዚህ ጫና ለማምለጥ፣ አብረን ነን ለማለት፣ በስብሰባ እየጋበዙን ነው፡፡ ጫናውን ለማርገብ ይሄን እያደረጉ ነው፡፡ በመግለጫቸውም ትግራይ ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በሚያግባባን ጉዳይ አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ ምናልባት ህዝቡ በሚያሳድረባቸው ተጽእኖ ምክንያት ይሄን ሃሳብ አጠናክረው ሊሠሩበት ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ይሄ ነው የሚባል አብሮ ለመስራት የሚያስችል እርምጃ የወሰዱት ነገር የለም። ትናንት ከእነሱ ጋር ተደባልቀን 44ኛ የህወኃት ምስረታን ስላከበርን ሙሉ ደስተኞች ነን ማለት አይደለም፡፡ እኛ ህዝቡን ለማክበር ነው በፕሮግራሙ የተገኘ ነው እንጂ ህወሓትን ደግፈን ወይም የአላማ አንድነት ፈጥረን አይደለም፡፡ እኛ ትክክለኛ ነው ብለን የያዝነውን የፖለቲካ ትግል መንገድ ጀምረናል፤ በሱ እንጓዛለን፡፡
“ህወሓት የትግራይ ህዝብን ወደ ጽንፈኛነት እየመራ ነው” የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎ ሃሳብ ምንድን ነው?
አሁን በአጠቃላይ በሀገሪቱ የተካረረ ፖለቲካ ነው ያለው፡፡ ጽንፈኛነት ነው በሀገሪቱ ፖለቲካ ትልቁን ቦታ የያዘው፡፡ ያ ጽንፈኝነት ደግሞ በህወሓት ብቻ ሳይሆን በትግራይ ህዝብ ላይ እንደመጣ አድርጐ የመደምደም ሁኔታ አለ፡፡ ይሄ ሁኔታ በትግራይ ህዝብ ላይ የራሱን ስጋት ይፈጥርበታል፡፡ ባልበላንበት ባልጠጣንበት ባላለፈልን ሁኔታ እንዳለፈልን ተደርጐ የምንፈረጀው ለምንድነው የሚል ሃሳብ አለ። የትግራይ ህዝብ በህወሓትም የተጐዳ፣ አሁንም ባለው ሁኔታ የተጐዳ ነው፡፡ የመሬት ግዛት ይገባኛል ጉዳይም አንዱ ነው፡፡ ይሄን ሁኔታ ደግሞ ህወሓት እንደ ፖለቲካ መሸሸጊያ ነው የሚጠቀምበት፡፡ እኛ ከሌለን ሊያጠፉህ ይችላሉ ያጠፉሃል፡፡ በማለት ከፍተኛ ስጋት ነው የፈጠረው፡፡ ህዝቡ የመረጃ አማራጭ የለውም፡፡ ሁሉም ፕሮፓጋንዳ ተመሳሳይ ሆኖ ነው የሚቀርብለት፡፡ ስለዚህ አቅጣጫው ሙሉ ለሙሉ ነው መስተካከል ያለበት፡፡ ለጊዜው በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ ስልጣን እስኪይዝ ድረስ ያለውን ህገ መንግስት ማክበር፣ ያለውን ፌደራል ስርአት መሰረት አድርጎ መቆም አለበት፡፡ ሃገሪቱ ተረጋግታ ምርጫ ከተደረገ በኋላ ቀሪው ስራ የአዲሱ መንግስት እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለውን ህግና ህገ መንግስት አክብሮ መጓዝ ነው የሚያዋጣው። የትግራይ ህዝብ ከሌላው ወንድም ህዝብ ጋር መጋጨት አይፈልግም፡፡ በቃን የሚል ጩኸት እያሰማ ነው፡፡ ከአሁን ወዲያ ወደ እሳትና ጦርነት መግባት አይፈልግም፤ ህውሓት ግን ይሄን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ ሊጠቀምበት እየፈለገ ነው፤ ነገር ግን ሃገሪቱ አጠቃላይ አቅጣጫዋን ስታስተካክል ነገሩ ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ያ መጋለጥ ደግሞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ለትግራይ ብቻ ተብሎ ሳይሆን ለሃገሪቱ ጠቅላላ ተብሎ አጠቃላይ ፖለቲካው መስተካከል አለበት፡፡
በክልሉ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን የማወደስ ተግባር ይታያል፡፡ ይህ ትርጉሙ ምንድን ነው?
እኔ እንደማውቀው፤ የትግራይ ህዝብ ሌብነትን፣ ጉቦን፣ ኢ-ፍትሃዊነትን የሚፀየፍ ነው፡፡ በትግሉ ወቅትም ይሄ ጉቦ፣ ሌብነት፣ ወገንተኝነት ይቀራል፤ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ ልማት፣ ይሰፍናል በሚል ተስፋ ነው የተንቀሳቀሰው፡፡ እኛም ስንታገል ቁርጠኝነታችን ለእነዚህ አላማዎች ነበር፡፡ በዚህ ህዝብ ብዙ ውጣ ውረድ አልፏል፡፡ በዚህ አላማ ያለፈና እንደዚህ አይነት አላማ ይዞ የታገለ ህዝብ፤ አሁን ተመልሶ ሌብነትን ሊሸከም አይችልም። ሌባንም አይሸከምም፡፡ እንዲያውም ትናንሽ ሌቦች ሲያገኝ ህዝ አይታገስም፤ ህዝቡ ለፍትህ የቆመ ነው፤ ሌባን አያቅፍም፡፡ ሌባ ይቀጣ የሚል ቁርጠኝነት ነው ያለው፡፡ ይሄ እምነቱ እያለ በመሃል ግን ወያኔን ማጥቃት በሚል ሰበብ የጦሩ አቅጣጫ ያጠፋን ሳይሆን ካጠፋ ጋር ያለን ሁሉ የሚያጠቃ ነው ሲባል፣ ህዝቡ አይሆንም የሚል ተቃውሞ ነው ያሳየው፡፡ በሌላ በኩል፤ የሙስና ትግሉ ፍኖተ ካርታ የለውም፡፡ የተፈለገ ሰው ብቻ ነው የሚታሰረው። ይሄ አሰራር ለ“መጡብህ ሊያጠፉህ ነው” ባዮች እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ መንግስት ተገቢውን አካሄድ አለመከተሉ የፈጠረው ነገር ነው እንጂ የትግራይ ህዝብ ሌባ ደባቂ ሆኖ አይደለም፡፡
ይሄ መስረር እና ፅንፈኝነት በቀጣይ የትግራይ ፖለቲካን ወዴት ሊወስደው ይችላል?
እርግጥ ነው አንዳንድ አስተሳሰቦች እየተፈጠሩ ነው፡፡ አንዳንዱ ለምንድን ነው ትግራየ ኢትዮጶያ … ኢትዮጵያ የምትለው?
አያስፈልግም፡፡ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ እያለች መቆየቷ ጥቅም አላመጣም፤ ስለዚህ ራሳችንን እናልማ የሚል ሃሳብ አለ፡፡ በሌላ በኩል ትግራይ ትግራይ በሚል ንቅናቄ፣ ኤርትራን ጨምሮ ሃገር መመስረት የሚያስቡ አሉ፡፡ እነዚህ እንግዲህ በጭንቅ ጊዜ የሚመጡ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ እኔ ባለሁበት ድርጅት አመለካከት ግን ያልተረጋጋ ፖለቲካ በሚኖርበት ጊዜ ከጭንቀት የተነሳ ብዙ መፍጨርጨሮች ቢኖሩም፣ በጊዜ ሂደት ይረግባሉ የሚል እምነት አለን፡፡ እነዚህ የተካረሩ የፖለቲካ መስመሮች መርገብ አለባቸው፡፡ አጠቃላይ የሃገሪቱ ፖለቲካን የማረጋጋት ስራ መስራት በኛ በኩል ማሰቡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይታሰብ ቢባልም ትግራይ ብቻዋን ሆና ሰላም አታገኝም፡፡ ይሄ የጭንቅ ሃሳብ ትክክል አይደለም፤ አሁን የጭንቀት ሃሳቦች እንዲወገዱ ማዕከላዊ መንግስቱ ከህዝቡ በላይ በሆነ መንገድ ስለ ሀገሪቷ የወደፊት እጣ ፈንታ ማሰብ አለበት፡፡ የተካረረው ፖለቲካ ለሃገሪቱ ዘላቂ ፖለቲካ አደገኛ ስለሚሆን ከፍተኛ ስትራቴጂ ቀርፆ ከህዝብ ጋር መወያየት አለበት፡፡ እንደኔ ኢህአዴግ ብቻውን ይሄን ማድረግ ይችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሌሎችም በዚህ አካሄድ ውስጥ መሳተፍ አለባቸው። እነዚህ አካላት ግልፅ የሃገሪቱን የአካሄድ ፍኖተ ካርታ ማውጣት አለባቸው፡፡ በዚያ ፍኖተ ካርታ መሰረት ስንጓዝ ነው የተረጋጋ ፖለቲካ እየፈጠርን የምንሄደው፡፡ አሁን ለምሳሌ የድንበርና ማንነት አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሟል፤ ይሄ ኮሚሽን ወደ አካባቢዎቹ ሄዶ ማጣራት ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? አካባቢዎቹ ባልተረጋጉበት ማንን ነው የሚያነጋግሩት? እንዴት ነው የሚያጣሩት? ለዚህ ሁሉ ስክነት ያስፈልጋል፡፡ ባልሰከነ ስነ አዕምሮ የሚደረግ ጥናት ምንም ውጤት የለውም፡፡ አሁን ትልቁ አጀንዳ መሆን ያለበት መካረሮች እንዲረግቡ፣ ህዝቡን ማረጋጋት፣ የእርስ በርስ መተማመን መፍጠር ነው፣ ትልቁ ስራ መሆን ያለበት፡፡  

Read 1288 times