Saturday, 16 February 2019 14:35

በሃንጋሪ ከ3 በላይ ልጆችን የሚወልዱ እናቶች ከገቢ ግብር ነጻ ሊሆኑ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)


           የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣ ከ3 በላይ ልጆችን የሚወልዱ የአገሪቱ እናቶች ዕድሜ ዘመናቸውን ሙሉ የገቢ ግብር እንዳይከፍሉ እንደሚደረጉ ከሰሞኑ ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡
በሃንጋሪ የወሊድ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱና በቀጣይ አገሪቱን የሚረከብ በቂ የሰው ሃይል ላይገኝ ይችላል የሚል ስጋት የተፈጠረበት የአገሪቱ መንግስት፤ እናቶች ልጆችን እንዲወልዱ ለማበረታታት ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው እሁድ ባደረጉት ንግግር ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
መንግስት ለአዲስ ተጋቢዎች የመቋቋሚያ ብድር ለመስጠትና ጥንዶቹ ሁለት ወይም ሶስት ልጆችን ከወለዱ ዕዳቸውን በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ ለመሰረዝ ማቀዱን ያስታወቁት ቪክቶር ኦርባን፤ ከዚህ በተጨማሪም ቢያንስ ሁለት ልጆች ላሏቸው ቤተሰቦች የቤት መግዣ የብድር አቅርቦት ለማሟላት ማቀዱንም አክለው ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ አብዛኛው የተማረ የሰው ሃይል የተሻለ ስራና ገቢ ፍለጋ ወደ ሌሎች አገራት መሰደዱን የጠቆመው ዘገባው፣ በርካታ እናቶች መውለድ ማቆማቸውንና በዚህም የአገሪቱ የህዝብ ብዛትም እ.ኤ.አ እስከ 2050 ድረስ በ15 በመቶ ሊቀንስ ይችላል መባሉን አመልክቷል፡፡
የወሊድ መጠን መቀነሱ ያሰጋቸው ፖላንድና ሰርቢያ፣ ወሊድን ለማበረታታትና አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በማሰብ በቅርቡ ለእናቶች ተመሳሳይ ማበረታቻዎችን ማድረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1309 times