Saturday, 16 February 2019 14:28

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)


             ትንሽ ትንሽ የማስታውሳት አጭር ልብወለድ ታሪክ ነበረች - በእንግሊዝኛ የተፃፈች፡፡ … “absurd” የምትባል ዓይነት፡፡ …
ሰውየው ሃብታም ነው፡፡ ጊዜና ጉልበት የተቸረው፡፡ አንድ ሰው እንዲሞት ፈለገና ነፍሰ ገዳይ ገዛ፡፡ የሟቹን ፎቶግራፍ፣ ባህሪውን፣ ስራውንና መውጪያ መግቢያውን አስጠንቶ፣ ቀብድ ከፍሎ ከጨረሰ በኋላ “አደራ ፍንጭ የሚሰጥ ነገር እንዳይኖር” በማለት ደጋግሞ አስጠንቅቆ አሰናበተው፡፡ ከቀናት በኋላ ነፍሰ ገዳዩ ተመልሶ መጣ፡፡
“እህሳ?”
“ተጠናቋል”
“ማንም አላየህም?”
“በጭራሽ”
“በአካባቢው ሰዎች አልነበሩም?”
“አንዲት ሴት አብራው ነበረች”
“እና?”
“እሷንም ጨርሻታለሁ”
ሰውየው “ብራቮ!” ለማለት አፉን ከከፈተ በኋላ ሃሳቡን ቀይሮ ትንሽ አሰብ አደረገና …
“ምን ዓይነት ሴት?” ሲል ጠየቀ፡፡
መልኳን፣ ቁመናዋን፣ የለበሰችውን ልብስ ነገረው፡፡ ለትንሽ ጊዜ ዝም ብሎ ሲያስብ ከቆየ በኋላ ዕንባው ጠብ አለ፡፡ እራሱን እየነቀነቀ እጁን ወደ ኮት ኪሱ ሰደደው፡፡ ያወጣው ግን ቀሪውን ገንዘብ ሳይሆን ሽጉጥ ነበር፡፡ ገዳዩንም ራሱንም ገደለ፡፡ … ለምን?
***
 ወዳጄ፡- የሌሎችን ሰዎች ደስታ ነጥቀን፣ የሌሎችን ሰዎች ሳቅ ቀምተን፣ የሌሎችን ዕድል ተጠቅመን ‹ኖሬያለሁ› ማለት ህመም ነው። ድምፅ የሌላቸው (Voiceless)፣ ኔት ዎርክ የሌላቸው፣ የፖለቲካና የዘር ድርጅት የሌላቸው፣ በገዛ አገራቸው ባዕድ የሆኑ፣ መብራት ሲጠፋባቸው፣ ውሃ ሲቋረጥባቸው፣ ጉዳይ ለማስፈፀም ቀበሌ ሲሄዱ “እሱ የኛ ነው፣ እሷ የኛ ናት” የሚል የሌላቸው፤ ማንም ጉልበተኛ አጥራቸውን የሚያፈርስባቸው፤ ‹አቤት› ማት የሚፈሩ፣ እነሱ ማን አላቸው? … እንባቸውን ከመርጨት በስተቀር!! … “እንባ የነፍስ ቋንቋ ነው” ይላሉ አዋቂዎች፡፡ የነፍስ ለቅሶ፤ የነፍስ ሳቅ፡፡
በሃዘን በምሬት
ሲከፋኝ ስተክዝ፣
በሳቅ በፍስሃ፣
ደልቶኝ ስፈነጥዝ፣
ጠብ አደርጋታለሁ
    ካንጀቴ ጨምቄ
ትናገርልኝ ዘንድ
    የስሜቴን አመፅ
ቃል እየመከነ
    እንቢ ሲለኝ መግለፅ
ፀሐፊው፡- “እንባ ውስጣዊ ጉልበትና ቅድስና እንጂ ደካማነት አይደለም፡፡ ደስታና ሃዘን፣ ፍቅርና ምሬት ከሚሊዮን ቃላትና አንድ ሺ ቋንቋዎች የበለጠ በአንዲት ጠብታ ዕንባ ይገልፃል “There is a sacredness in tears, it is not a sign of weakness, but of power. A drop of a tear could better explain love and sorrow, happiness and stress better than millions of words, thousands of languages” ይለናል፡፡
ወዳጄ፡- ታላቁ ፓይታጎረስ “ህይወት የኦሎምፒክ ጨዋታና ውድድር እንደሚካሄድበት መንደር ነው፡፡ አንዳንዶች ሜዳሊያ ለመውሰድ ይፎካከራሉ፣ አንዳንዶች ለሚሰበሰበው ተመልካች የሚፈልገውን ሸቀጥና ምግብ በማቅረብ ለማትረፍ ይተጋሉ፣ ብዙዎች ግን የሚመጡት ለማየት ነው” በማለት የፃፈልን በተለያየ ቦታና በተለያየ ጊዜ የሁሉም ጥሪና ክወና ህይወት በምታዘጋጅለት መድረክ እንደሚለያይ ለማሳየት ነው፡፡ ኦሎምፒክ ላይ ተመልካች የነበረው በሌላ መድረክ ዋና አክተር ሆኖ ሌሎች ሊመለከቱት ይሄዳሉ፡፡ ኦፔራ፣ ሙዚቃ ኮንሰርት፣ የንግድ ባዛር፣ ፓርላማ፣ ቤተ እምነት ወዘተ ሊሆን ይችላል ወይም ደራሲና ገጣሚ ሆኖ ያነቡታል፡፡ ሃዘንና ደስታም እንደዛው ነው። ቋሚ ደስታ፣ ቋሚ ሃዘን የለም፡፡ ጥላሁን ገሠሠ እንደዘፈነው፡- “ያለቀሰም ሲስቅ፣ የሳቀም ያለቅሳል”። ኋላ ቀር የፖለቲካ ግብር ባለበት ደግሞ አይቀርም፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በራሳችንና በጎረቤታችን፣ ራቅ ስንል በሊቢያ፣ በኢራቅና በመሳሰሉት ቦታዎች የነበረው እንዳልነበረ፣ ያልነበረው እንደነበረ ሆኖ አይተናል፡፡
በታሪክ ፍልስፍና ወይም በተፈጥሮ ዑደት ውስጥ ግን ቦታ የመቀያር ነገር ሳይንስ ወይም ተፈጥሯዊ ሕገ ሥርዓት አይደለም፡፡ ቢሆን ኖሮ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በለመለመባቸው የአውሮፓ ሃገራትና አሜሪካ ይከሰት ነበር። የችግሩ ምንጭ በትክክል ማሰብ መቻልና አለመቻል ነው፡፡ ... የአስተሳስ ድህነት!!
ወዳጄ፡- አርቆ አለማሰብ ማለት እኔ እንደሚገባኝ ይቺን ቅጽበት አለመኖር፣ ይቺን ቅጽበት ለህሊና አለመገዛት ነው፡፡ በዚች ቅጽበት መልካም የሆነ በሚቀጥለው ሚሊዮን ዓመታትም መልካም ነው። የእውነት ገፅታ እንጂ essence አይቀርም። የቅድሙና የበኋላው፣ የትላንትናውና የነገው፣ የአልፋ ኦሜጋው እንብርት የተቋጠረው በዚች ቅጽበት ላይ ነው። … ዘለዓለማዊነት!!
“አሁን ያለሁት ‹እኔ›፣ ትላንት ያልነበርኩ ‹እኔ›፣ ወደፊት የማልኖረው ‹እኔ› ነኝ” ብለን ማሰብ ሲገባን፤ “አሁን ያለሁት ‹እኔ›፣ ትናንት የነበርኩት ‹እኔ›፣ ነገ የምኖረውም ‹እኔ› ነኝ” ብለን እናስባለን፡፡ … ጊዜ ሃሳብ መሆኑን ዘንግተን፡፡ ጊዜን የምንለካው ከፀጉራችን መሸበት፣ ከመንጋጋችን መነቀል ወይም ከቆዳችን መሸብሸብ አንፃር ከሆነ የምናወራው ስለ ጊዜ essence ሳይሆን ስለግለሰብ concept ነው፡፡ “ትዝታ በፖስታ” ሲባል የኖርነውን ሃሳብ ነው የምናስታውሰው እንጂ አሁን የምናስበውን አይደለም፡፡
ወዳጄ፡- ህይወት በጥበብ፣ ህይወት በታሪክ፣ በትራጀዲና ኮሜዲ ገጠመኞች፣ በጤናና በህመም ስሜት፣ በፍላጎትና ጉጉት፣ በአድቬንቸርና ጀብዱ፣ በስልጣንና ትምህርት፣ በቅድስናና እምነት፣ በእንግልትና መከራ፣ በጥረትና ድካም፣ በፍቅርና ወዳጅነት ልትመዘን የምትችለው ሃሳብ በዚች ቅጽበት ሲተረጎም ነው፡፡ ይህን ማድረግ ሲያቅተን አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ የህይወት ትርጉም absured ይሆናል፡፡
“የሚሰማንን በመኖር፣ ኢ-ፍትሃዊነት ላይ በማመፅ ቅዠቱን ሰባብረን ትርጉም ለሌለው ህይወት ትርጉም ልናበጅለት ይገባል (… by rebelling against absurdity, by refusing to participate in the injustice of the world and by living to the fullest we have to make life worth) የሚለን አልበርት ካሙ ነው፡፡
***
ወደ ታሪካችን እንመለስ፡- ሃብታሙ ሰው ጣለበትና በድንገት ካያት ቆንጆ ጋር ድብን ባደረገው የዓይን ፍቅር ወደቀ፡፡ አድራሻዋን ተከታትሎ ሲያጠና ባለትዳር ሆነችበት፡፡ ባለቤቷን አስገድሎ የራሱ ሊያደርጋት ስለከጀለ ነበር ነፍሰ ገዳይ የቀጠረው፡፡ ሟች ከሚስቱ ጋር ጭር ባለ ካፌ ውስጥ በሚዝናናበት ጊዜ ነበር ነፍሰ ገዳዩ ከች ያለው፡፡
ሠላም!!

Read 1166 times