Saturday, 16 February 2019 14:26

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

 ክፍል-፲ ፍልስፍናዊ ትችት - እጓለ፣ ዳኛቸውና መስፍን
                                                   
          ከክፍል 7-9 ድረስ ባሉት ፅሁፎቼ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከ17ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች (ማለትም - ከዘርዓያዕቆብ፣ ከወልደ ህይወት፣ ከዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስ እና ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ) በተለያየ ቅላፄ ትችቶች እንደተሰነዘሩበት ተመልክተናል። ከእነዚህ ፈላስፎች ውስጥም በክፍል 8 እና 9 የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ህይወትን ትችቶች ሰፋ አድርገን የተመለከትን ሲሆን ዛሬ ደግሞ የእጓለንና የዳኛቸውን ሐሳቦች እንመለከታለን፡፡
ምንም እንኳ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም በሙያቸው የፍልስፍና መምህር ባይሆኑም ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› (2005) በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ያሬዳዊውን ሥልጣኔን ሸንቆጥ ያደረጉበት ነገር በጣም መሰረታዊ የሆነ ፍልስፍናዊ ይዘት ያለው ስለሆነ፣ በዛሬው ክፍል ላይ የእሳቸውንም ሐሳብ በየመሐሉ እያካተትን እንመለከታለን፡፡
ከ17ኛው ክ/ዘ ጀምሮ የበቀለው የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ አንድ የጋራ ባህሪ አለው - ይሄውም ‹‹ብህትውና››ን ዋነኛ ርዕሰ ጉዳዩ አድርጎ መነሳቱ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ ነባራዊ ሁኔታ መነሳትና እሱንም መገዳደር የፍልስፍና ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የጥንታዊ ግሪክ ፍልስፍና የተነሳው በወቅቱ ገዥ የነበረውንና በእነ ሆሜር ተረኮች የተገነባውን ማህበራዊ ስነ ልቦና አስተሳሰብ በመገዳደር ነው፡፡
ከዚህ እውነታ አንፃር የኢትዮጵያ ፍልስፍናም ለዘመናት ገዥ የነበረውን የብህትውና ባህል ዋነኛ ርዕሰ ጉዳዩ አድርጎ መነሳቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ገና ከጥንስሱ ሲያልም የነበረው የብህትውና አስተሳሰብ ከፈጠረብን የቅራኔ ህይወት መሻገር ነው፡፡ ይሄንን ሐሳብ ደግሞ በዘርዓያዕቆብና በወልደ ህይወት ‹‹የነፍስና ስጋ እርቅ›› ላይ፣ በእጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ላይ፣ በዳኛቸው ‹‹አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት›› ላይ፣ እንዲሁም በመስፍን የ‹‹ብህትውና›› ሐሳብ ላይ እናገኘዋለን። ከዚህ አንፃር የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ህይወትን ሐሳቦች ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተመለከትነው ስለሆነ፣ ዛሬ የቀሪዎቹን ፈላስፎች በየተራ እንመለከታለን፡፡
እጓለ ገብረ ዮሐንስ (1924-1983)
በ17ኛውና በ18ኛው ክ/ዘ ከተፃፉት ሁለት የፍልስፍና ሐተታዎች በመቀጠል ለኢትዮጵያ ፍልስፍና በጣም ወሳኝ የሆነውን ሥራ ያገኘነው ከእጓለ ነው - በ1956 - ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ››፡፡ ምንም እንኳ መፅሐፉ በገፅ ብዛቱ ልክ እንደነ ዘርዓያዕቆብ ሐተታ አነስተኛ ቢሆንም፣ በያዘው ርዕሰ ጉዳይ ግን ዋጋው እጅግ ውድና በዘመኑ ከተሰሩ ስራዎች ሁሉ በጣም የላቀ ነው።
‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› ውስጥ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ገዥ ሐሳቦች ሆነው ወጥተዋል - ትምህርትና ሥልጣኔ፡፡ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ ለዘመናት ገዥ የነበረውን አመለካከትና የሥልጣኔያችንን ልዩ ባህሪ ፈልፍሎ ያገኘልን እጓለ ነው፡፡ ዘመናትን አስሶ ለሥልጣኔው ሁነኛ የሆነ ወኪል በመፈለግም ‹‹ያሬዳዊ ሥልጣኔ›› በማለት የሰየመውም እጓለ ነው፡፡
እጓለ በግልፅ እንደነገረን፣ ‹‹ያሬዳዊ ሥልጣኔ›› ዓለምንና የዓለም የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በመናቅ ሃይማኖትንና እግዚአብሔርን ብቻ ማዕከል አድርጎ በምስራቅ አፍሪካ የበቀለ ሥልጣኔ ነው፡፡ ይሄንን ሐሳብ ደግሞ ፕ/ር መስፍንም ‹‹ኢትዮጵያ ከየት? ወዴት?›› (1986)፣ ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› (2005) እና ‹‹አዳፍኔ›› (2007) መፅሐፋቸው ውስጥ ደግመውታል፡፡ ሐሳቡንም ‹‹ብህትውና›› በማለት ጠርተውታል (2005፡ 12-13)፡፡ በመሆኑም፣ የእጓለንና የመስፍንን ሐሳብ ስናጣምራቸው ያሬዳዊው ሥልጣኔ ‹‹ብህትውና››ን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ፕ/ር መስፍን ከዚህም አልፈው ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ብህትውናን ተጠያቂ እስከማድረግ ድረስ ይሄዳሉ፡፡
ሆኖም ግን፣ ይሄ ብህትውናዊው (መንፈሳዊው) መንገድ ለሰው ልጅ ብቸኛው አይደለም፡፡ እጓለ እንደነገረን፤ ‹‹የሰው ልጅ ህይወት ሁለት መንገዶች አሉት - የመንፈስና የህሊና፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የመንፈስን መንገድ ሲከተል፣ ፋውስታዊው (አውሮፓዊው) ሥልጣኔ ደግሞ የህሊናን መንገድ የተከተለ ነው›› (2003፡ 63-64)፡፡
ምንም እንኳ፣ እጓለ እነዚህን ሁለት ሥልጣኔዎች ‹‹አቻና ተስተካካይ›› ቢያደርጋቸውም፣ ወደ ንፅፅር ሲገባ ግን ያሬዳዊው ሥልጣኔ አንድ ጉድለት እንዳለበት ደርሶበታል - ይሄውም ‹‹የተጠቃሚነት እሴት›› ማጣት ነው፡፡ ሁለቱ ሥልጣኔዎች ባፈለቁት የሥነ ምግባር፣ የኪነ ጥበብና የቅድስና እሴቶች ተስተካካይ ቢሆኑም፣ ከተጠቃሚነት አንፃር ግን አውሮፓውያን ልቀው በመሄድ ሳይንስና ቴክኖሎጂን መፍጠራቸውን እጓለ በግልፅ ያምናል፡፡
በርግጥ፣ አሁን ላይ በተገለጠውና ሰውን እንደ ብሉይ ዘመን በአደባባይ ሰቅሎና በዲንጋይ ወግሮ የመግደል ‹‹የመንጋ ፍትህ›› ጊዜ ላይ መድረሳችንን ስናየው፣ በርግጥ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ‹‹በሥነ ምግባር፣ በኪነ ጥበብና በቅድስና እሴቶች›› ከአውሮፓውያን ጋር ተስተካካይ ነው›› የሚለውን የእጓለን ሐሳብ እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡
‹‹በተዋህዶ ከበረ!!›› - ፖለቲካዊ ወይስ ፍልስፍናዊ መፍትሄ?
ማንኛውም ሥልጣኔ የተመሰረተበት የራሱ የሆነ ዲበ አካላዊ፣ ሥነ ዕውቀታዊ፣ ሥነ ምግባራዊና ኪነ ጥበባዊ ምሰሶዎች አሉት። ሥልጣኔው ጉድለት ሲኖረውም ችግሩ የሚገኘው እነዚህ ምሰሶዎች ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ እጓለም የያሬዳዊው ሥልጣኔ ኪነ ጥበባዊ መሰረት ከቅዱስ ያሬድ እንደሚጀምር አስረድቷል፡፡ ሆኖም ግን፣ እጓለ ለያሬዳዊው ሥልጣኔ ባለው ስስ ስሜት የተነሳ የሥልጣኔውን ኪነ ጥበባዊ መሰረት ከማሳየት ባሻገር ሄዶ፣ የሥልጣኔውን ጉድለት ከዲበ አካላዊ፣ ሥነ ዕውቀታዊና ሥነ ምግባራዊ መሰረቱ አንፃር እንዳይፈትሽ አድርጎታል፡፡ ይሄንን ማድረግ እሱ የደረሰበትን ‹‹የሥልጣኔውን ጉድለት›› ያገዝፍበታል፡፡
በዚህም የተነሳ፣ የሥልጣኔውን ጉድለት ለመሙላት ሥልጣኔው በዘመናዊው ዓለም ውስጥ አላራምድ ያሉትን የብህትውናና የተአምራዊነት አስተሳሰቦች አንቅሶ ከማውጣት ይልቅ፣ ሥልጣኔው ከእነ ችግሮቹ ከአውሮፓዊው ሥልጣኔ ጋር የሚዋኻድበትን ‹‹ፖለቲካዊ ሐሳብ›› አመጣ፡፡ ይሄም፣ አስቀድሞ ያመጣውን ትልቅ ‹‹ፍልስፍናዊ ሐሳብ›› ጎዶሎ አደረገበት፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ከእጓለ ይልቅ ዘርዓያዕቆብ በተሻለ ደረጃ የባህል ችግራችንን አሳይቶናል፡፡
እጓለ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የጥቅምን ነገር ችላ ብሏል›› ያለው ነገር ትክክለኛ ግምገማ ቢሆንም፣ ለዚህ ችግር መፍትሔ ብሎ ያመጣው ‹‹ከአውሮፓ የመዋስ›› ሐሳብ  ግን  ከፖለቲካ አንፃር ካልሆነ በስተቀር፣ ከፍልስፍና አንፃር ትክክል አይደለም። ምክንያቱም፣ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የባህል ችግር ሲኖር፣ ችግሩ የሚቀረፍበትን አፋጣኝ መፍትሔ ማቅረብ የፖለቲካ ጉዳይ ሲሆን (ልክ ነገስታቱ እንዳደረጉት)፣ የችግሩን ስረ መሰረት ፈልፍሎ ማግኘት ግን የፍልስፍና ተግባር ነው፡፡
ከዚህ አንፃር፣ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› የሚለው የእጓለ ሐሳብ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንጂ ፍልስፍናዊ ሥረ መሰረት ያለው አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተጠቃሚነት እሴት ይጎድለዋል›› የሚለው የእጓለ መደምደሚያ ፖለቲከኞችን በቀጥታ የሚወስዳቸው ‹‹ታዲያ ምን ይሻላል?›› ወደ ሚል አፋጣኝ የመፍትሄ ሐሳብ ሲሆን፣ ፈላስፋዎችን የሚወስዳቸው ግን ‹‹የችግሩ ሥረ መሰረት ምንድን ነው? ሥልጣኔያችን እንዴትና ከመቼ ጀምሮ እዚህ ችግር ላይ ሊወድቅ ቻለ?›› ወደ ሚል ትልቅ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የሥነ ማህበረሰብና የፍልስፍና ሐሰሳ ነው፡፡
ፈላስፋዎች ለአንድ የባህል ችግር መፍትሄ የሚያቀርቡት፣ በመጀመሪያ የችግሩን ሥረ መሰረት ካገኙት በኋላ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ እጓለ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› ያለበትን ጉድለት ያሳየን ቢሆንም፣ የችግሩን ሥረ መሰረት ግን ከሥልጣኔው ምሰሶዎቹ ላይ ሳያስስ ነው የሄደው፡፡ ይሄም ለሚቀጥሉት ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች የቤት ስራ ሆኖ አልፏል፡፡
ዳኛቸው አሰፋ
ዘርዓያዕቆብና እጓለ፤ ያሬዳዊው ሥልጣኔ በእነሱ ዘመን የገጠመውን ችግር በተለያየ መንገድና ደረጃ ያሳዩን ቢሆንም፣ በፍልስፍናቸው ውስጥ ግን አንድ ወሳኝ የሆነ ነገር ረስተዋል - የታሪክን አስፈላጊነት፡፡ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ጥናት ውስጥ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› ወሳኝ ግብአት አድርጎ ያሳየን ዳኛቸው አሰፋ ነው - ‹‹አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት›› (2002) በሚለው ትምህርቱ፡፡
በዚህ ትምህርቱ፣ ዳኛቸው ለኢትዮጵያ ፍልስፍና ሁለት አበርክቶዎችን አድርጓል፤ አንደኛው ታሪክን ወሳኝ የፍልስፍና ግብአት አድርጎ ማሳየቱ ነው፡፡
ዘርዓያዕቆብና እጓለ፤ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ያለበትን ጉድለት በትክክል ያሳዩን ቢሆንም፣ ‹‹የችግሩ ሥረ መሰረት ምንድን ነው? ሥልጣኔያችን እንዴትና ከመቼ ጀምሮ እዚህ ችግር ላይ ሊወድቅ ቻለ?›› ወደሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች እንዳይሄዱ ያደረጋቸው በፍልስፍናቸው ውስጥ ‹‹የኢትዮጵያን ታሪክ›› መለንቆጥ አለመቻላቸው ነው፡፡ በዚህም ጉድለት የተነሳ፣ ዘርዓያዕቆብም ሆነ እጓለ ሲያተኩሩ የነበረው በራሳቸው ዘመን ላይ አፍጥጦ የታየው የባህል ችግር ላይ እንጂ የችግሩን ሥረ መሰረት ወደ ማሰስ አልነበረም፡፡
በመሆኑም፣ ዘርዓያዕቆብና እጓለ የኢትዮጵያን ፍልስፍና የቀመሩት በዘመናቸው የነበረውን የባህል ችግር ምንነት በመተንተን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ፍልስፍናቸው ‹‹ወቅታዊነት›› ያመዝንበታል፡፡ ‹‹የወቅታዊነት›› ዋነኛ ችግሩ ደግሞ ወደ ኋላ ሄዶ ከታሪክ ጋር የሐሳብና የመንፈስ ትስስር መፍጠር አለመቻሉ ነው። ‹‹ወቅታዊው የባህል ችግር›› ካሳለፍነው የባህል ታሪክ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለውና የኢትዮጵያም ፍልስፍና የሚቀመረው ይሄንን ያሳለፍነውን የባህል ታሪክ በማጥናትና በመተንተን መሆኑን ያሳየን ዳኛቸው ነው፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው፣ ኢትዮጵያውያን ‹‹በምድራዊ የሰው ልጅ የበላይነት›› መርህ ላይ ከተመሰረተው አክሱማዊ እሴት ወደ ‹‹መለኮታዊ የበላይነትና የሰው ልጅ የበታችነት›› መርህ ወደ ሚመራው ላሊበላዊ እሴት ያደረግነውን ማህበረሰባዊ ሽግግርና የእሴት ለውጥ ወሳኝ የታሪክ ክስተት አድርጎ ይወስደዋል፡፡ ይሄንንም ‹‹የትህትና፣ የጭምትነት፣ ራስን ዝቅ የማድረግ፣ ክብር አለመፈለግ፣ ምድራዊ ጥቅምን የመናቅ›› ላሊበላዊ እሴቶች ኪነ ህንፃዎቻችን ላይ ሳይቀር ታትሞ እንደሚገኝ የነገረን ዳኛቸው ነው፡፡ ይሄም ዳኛቸው ለኢትዮጵያ ፍልስፍና ያስተዋወቀው ሁለተኛው አበርክቶት ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ ‹‹በታሪክ ውስጥ ያሳለፍነውን የባህል እሴቶች አሻራቸውን ኪነ ህንፃዎቻችን ላይ እናገኘዋለን›› የሚለው የዳኛቸው ሐሳብ፤ ሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎችን ባለማካተቱ ቢያንስ ቅዱስ ያሬድን (የኢትዮጵያን ሙዚቃ) የኢትዮጵያ ፍልስፍና ርዕሰ ጉዳይ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ ይሄንን ጉድለት ለመሙላት እየሰራ ነው፡፡
በክፍል-11 ፅሁፌ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› ከኢትዮጵያውያን የታሪክ ፀሐፊዎችና የዘመናዊነት አቀንቃኝ ምሁራን የተሰነዘረበትን ትችቶች እንመለከታለን፡፡

Read 1700 times