Sunday, 17 February 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “ታሪክ እውቀት እንጂ እምነት መሆን የለበትም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 - ባህልና ቋንቋን የሥልጣን መስፈርያ ማድረግ ትልቅ ስህተት ነው
       - የበዳይ ተበዳይ ታሪክ ማራገቡ ጠቃሚ አይደለም
       - ታሪክን እንደ ትዝታ ማየት መልመድ አለብን

            አንዳንድ የኢትዮጵያ ልሂቃን ታሪክን የውዝግብና የግጭት ምንጭ በማድረግ ረገድ ሚናቸው ቀላል አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕ/ር አህመድ ዘካሪያስ፤ ታሪክ እውቀት እንጂ እምነት መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ ምን ማለት ናቸው? ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በታሪክ ዙሪያ ሰፊ ትንተና ሰጥተዋል፡፡ እነሆ፡

           የዛሬው የኢትዮጵያ ቅርፅ እንዴት መጣ?
በአጠቃላይ ዛሬ የምናየው የኢትዮጵያ ቅርፅ እንዴት መጣ የሚለው በአግባቡ መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አፍሪካን ቅኝ ገዥዎች ሲቀራመቷት፣ ድንበር ገፍተው ገፍተው፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ቅርፅ አበጁልን፡፡ ይሄ ውጫዊ ማለትም፣ እኛ  ፈልገን   ያመጣነው   ቅርፅ    አይደለም፡፡ እኛ ያመጣነው ከመንደር ወደ ትልቅ የተጠናከረ ሃገርነት የመለወጥን ቅርጽ ነው፡፡ ትልቅ ኢምፓየር የመሆን ጉዳይ፣ በኛ ህልም የመጣ ነው፡፡ የግዛት መሳሪያ መሬት ነው፡፡ አቅም ያለው በየጊዜው መሬቱን ያሰፋ ነበር፡፡ ጠመንጃን ቀድሞ ያገኘና የሰው ኃይሉ የተደራጀ፣ በየትኛውም ዓለም ከሱ በጉልበት አናሳ የሆነውን ሲያጠቃልል ነው የኖረው፡፡ የአብዛኞቹ የዓለም ሃገራት አመሰራረት ከዚህ እውነት የራቀ አይደለም፡፡ አሁን ምናልባት የመረጃና የስልጣኔ ዘመን ነው፤ ይህ አይነቱ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ቀድሞ ግን ጠመንጃ የያዘ አካል ድምፁም ዝናውም ያስፈራራል፡፡ ዓለም ራሷ የሰፋችው ጠመንጃና ቀድሞ ቴክኖሎጂ በእጃቸው የደረሰ ኃይሎች፤አዲስ አለም ለማሰስ ባደረጉት ጥረት ነው፡፡ ነገሩን ሰፋ አድርገን ማየት አለብን፡፡ ሁሉም ተጣልቶ፣ ተዋግቶ፣ ተላልቆ፣ እርስ በእርሱ ተጨካክኖ ነው የዛሬውን ተወዳጅ ቅርፁን ያገኘው፡፡ የትናንትም ሆነ የዛሬ ታሪክ የሚነግረን፣ አንዴ የሃገርነት ቅርፅ ውስጥ በህግ ከተገባ በኋላ፣ ተከባብሮ የመኖር ልማድን ነው፡፡ ቂም በቀልን መቁጠር ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡ ሌላው የሰለጠነው ዓለም፤ ያለፈውን የመጠፋፋት ታሪክ የሚያነበው ለመማር፣ ለማወቅና ስለ ሃገሩ የእውቀት አድማሱን ለማስፋት ነው፡፡
የስልጣን አካሄዳችን ላይ ችግር አለ፡፡ በተለይ ከ14ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሰሜኑን የሃገራችንን ሁኔታ ስናይ፣ የሳባና የሰለሞን ግንኙነት ተብሎ ነው ለመንግስት ስርአት ስንጠቀምበት የኖርነው። የስልጣን ምንጭ የሳባና የሰለሞን ዝርያ ሆነ፡፡ ሌላው በዚህ መስፈርት ከስልጣን አካባቢ ተገለለ፡፡ እውቀትም፣ ጉልበትም ኖረው አልኖረው፣ በሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ውስጥ መጠመቅ አለበት፡፡ የሰለሞንና የሳባ ደም ነበር ኃይልና አቅም የነበረው። በዚህ ምክንያት የስልጣን ምንጭ እሱ ሆኖ ሌላው ተገለለ፡፡ እነ አፄ ቴዎድሮስም ከመጡ በኋላ ነገሩን ወደ ሳባና ሰለሞን ደም የማቀላቀል ሁኔታ አለ፡፡ ከአፄ ኃይለሥላሴ በኋላም በደርግ ጊዜ ይሄ የሰለሞን ዘርን የማየት ነገር ነበር፡፡ የዚህ ታሪክ ጫና ዛሬም አለ፡፡ ይሄ በእጅጉ በታሪካችን ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ ነው፡፡ በኋላም የማርክሲዝም ዘመን ሲመጣ ራሱ፣ ይሄን የሰለሞን ዘር ሃረግ ጉዳይን ለመጎተት ይሞከር ነበር፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች በሃገሪቱ ታሪክ ጉልህ ቦታ አላቸው፡፡ በማርክሲዝም ትግል ወቅት ሁለት ድምፆች ነበሩ በጉልህ የሚሰሙት፡፡ አንዱ የመደብ ጭቆና ነው፤ ሌላው የብሔር፣ የዘር ጭቆና ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ የስልጣን መንደርደሪያ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ የመደቡ ጉዳይ ተፈልጎ ጠፋና በቀጥታ ወደ ብሔሩ ነው የሄድነው፡፡ የብሔሩ ጉዳይ ግን ሙሉ ለሙሉ ለስልጣን የተደረገ አይመስለኝም። ምክንያቱም ቋንቋ፣ ባህል ሃይማኖት የመሳሰሉት መብቶች ናቸው፤እንጂ ልዩነት መፍጠሪያ መሆን አይችሉም፡፡ እኛ ደግሞ ሁላችን ተዛንቀናል፡፡ መዛነቁ ያለና ለወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ የባህል ልዩነቶች ለወደፊትም ይኖራሉ፡፡ የእኔነት ጥያቄዎች ግን ብዙውን ልንከራከርበት የምንችልበት ነው፡፡ እኔነት አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ እኔነቶች አንድ ግለሰብ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ አንዱን ብቻ የሌለ አቅም ሰጥቶ ማውጠንጠኑ ብዙም የሚጠቅም አይደለም፡፡ እንደ ግለሰብ ብዙ እኔነቶችን እየወረስን፣ እያስተናገድን ነው የምንኖረው፡፡ “እኔ ንፁህ ነኝ” የሚል ካለ ተሳስቷል፡፡ ንፁህ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡
ለእርስዎ ታሪክ ምንድን ነው?
ለኔ ታሪክ ማለት ያለፈ ትዝታ ነው፡፡ መጥፎም ጥሩም ትዝታዎች አሉን፡፡ እነዚህን ትዝታዎች እንዳይኖሩን ማድረግ አንችልም፡፡ የተዛቡ ትዝታዎች በአፃፃፍ፣ በታሪክ አቀራረብ ላይ… አንዱን አጠናክሮ ሌላውን አኮስሶ የሚቀርብበት ሁኔታ ራሱን የቻለ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ የኛ ታሪክ ደግሞ የህዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ስልጣን ታሪክ ነው፡፡ እገሌ ንጉሥ እንዲህ አድርጎ … በዚህ ወጥቶ የሚል ነው። ግኡዝም ቢሆን ታሪኩ ሊዘከር ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአድዋ ተራራ ግኡዝ ነው፡፡ ግን ታሪኩ ትዝታውን ይናገራል። የታሪክ መሳሪያ መገለጫ ነው፡፡ እንግዲህ እኛም ታሪክ ብለን ስንነሳ፣ እነዚህ ትዝታዎች ከግኡዛን ጋር እየተጋራን የምንቋጨው ነው፡፡ ሁሉም ነገር ታሪክ አለው፡፡ ታሪክ የሌለው ነገር የለም። ስለዚህ እኔ ብዙ ጊዜ የምለው፤ ታሪክን እምነት ባናደርገው፣ የእውቀት ብናደርገው የተሻለ ነው፤ እምነት ሲሆን አማኝን በእውቀትም ቢሆን መለወጥ ያስቸግራል። አንዴ ካመነ አለቀ፡፡ ታሪክ ግንዛቤ ነው። ያንን ግንዛቤ ከተለያየ ወገን ማስፋትና በሱ ላይ እውቀት መሰብሰብ ነው የሚያስፈልገው፡፡ መቼም ገዳይ ካለ ሟች ይኖራል፡፡ የተገዳዩም የገዳዩም ታሪክ ትዝታ ነው፡፡ እንዴት? በምን ሞተ? እያልን በጉዳዩ ላይ እውቀት እንሰበስባለን፡፡ ያ እውቀት መማሪያ እንጂ እንደ እምነት ይዘን መጠፋፊያ ወይም ሃሳብ ማወራረጃ ማድረጋችን ከስልጣኔው ብዙ መራቃችንን ከማመላከት የዘለለ ቁም ነገር የለውም፡፡ የሃገሪቱን ታሪክ ከሌላው አለም አንፃር እየተመለከትን፣ አስፍተን ማየት ይኖርብናል፡፡ አሁን የሌሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ነው ከውጭ እዚህ ለማምጣት የምንጥረው፡፡ ብሔር ሲባል ከመሬትና እዚያ ውስጥ ከሚኖር ህዝብ ጋር ነው የሚታየው፡፡ ያኔ የሌለ ብሔር ብሔረሰብ እያልን ነው፣ የፖለቲካ መጫወቻ ያደረግነው፡፡ አሁን ከዚህ ጨዋታ መውጫ ቀዳዳው ነው የቸገረው፡፡ ባህልና ቋንቋን የስልጣን መስፈሪያ ማድረግ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በታሪካችን መግባባት የተሳነን እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚወክል ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ማጣት ደግሞ ሁኔታው ስር እንዲሰድ አድርጓል፡፡ አሁን ይሄን ለማስታረቅ የፖለቲካ ልሂቃኑ ኃላፊነት የጎላ ነው፡፡ ለምሳሌ ትግልን የኢኮኖሚ ጉዳይ ማድረግ፡፡ እንዴት በኢትዮጵያ የሚኖሩ 100 ሚሊዮን ሰዎች በልተው፣ ተዝናንተው ጥሩ መጠለያ አግኝተው መኖር ይችላሉ የሚለውን የሚመለከት ንቅናቄ ያስፈልጋል፡፡ ታሪክን እንደ እምነት ሳይሆን እንደ እውቀት የሚመለከት ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል፡፡ ህብረተሰባችን አንድነትን የሚያገናዝብ መሆን አለበት፡፡ የበዳይ ተበዳይ ታሪክ ማራገቡ ጠቃሚ አይደለም፡፡
መሬትና የአሠፋፈር ጉዳይ  የግጭትና የንትርክ ምንጭ ለምን ሆነ?
አሠፋፈራችንን በተመለከተ እንደገና ረጋ ብለን ማየት ያለብን  ነገር አለ፡፡ መብት ላይ የምንደራደረው ነገር የለም፡፡ የማንኛውም ሰው መብቱ በህገ መንግስት መከበር አለበት፡፡ ለዚህ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ አሁን የአሠፋፈር ጉዳይ የጠብ ምንጭ እየሆነ የመጣው የሰው መብትን በህገ መንግስት ማስጠበቅ የተሣናቸው ተቋማት በመኖራቸው ነው፡፡ ድሮ በመንደር እንኳ ፀብ ሲኖር በህግ ይፈታ ነበር፡፡ አሁን ፈጣሪን የመፍራትም ሆነ ህግን የመፍራት ነገር የለም፡፡ ይሄ አክስሮናል፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት የዛሬ ኢትዮጵያን የፈጠሯት ዳግማዊ ምኒልክም አይደሉም፡፡ የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ግፊት ነው በዋናነት የፈጠራት፡፡ ሁላችንም በበርሊን ኮንፈረንስ (የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ቅርምት ስምምነት) የተፈጠርን ነን፡፡ ቅኝ ገዥዎች ናቸው የዛሬ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካን ቅርጽ ያስያዙት፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩት በኋላ ላይ ነው፡፡ ይሄ ለምን ሆነ የሚለው ሌላ ትንታኔ ያስፈልገዋል፡፡ እንግሊዞች ገብተው ነበር፤ ያልቆዩበት ምክንያት አላቸው፡፡ ወርቅ የለም ዝም ብሎ ተራራ ነው የሚል አመለካከት ስለነበራቸው፣ ኢትዮጵያ ላይ ብዙም ትኩረት አላደረጉም፡፡ በሌላ በኩል የክርስቲያን ደሴት የሚለው የመስቀል ፍቅር ላላቸው አውሮፓውያን ብዙ የጠቀመ ይመስለኛል፡፡ የአድዋ ጦርነት ግን ትልቅ ሃይል ነው፡፡ የጀግንነት ተጋድሎ ውጤት ነው፡፡
የሀገሪቱ የታሪክ ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
ትልቁ የውስጥ ችግራችን ሆኖ የዘለቀው ስልጣን፣ ለኔና እኔ ለምወክለው ይገባል የሚለው አመለካከት ነው፡፡ በሽታው ያለው ፖለቲካው ላይ ነው፡፡ አንዱ ማሳያ ቋንቋን ለስልጣን ማግኛ የመጠቀሙ ጉዳይ ነው፡፡ በመሠረቱ ቋንቋ የስልጣን ምንጭ ወይም የታሪክ ተወቃሽነት ምንጭ መሆን የለበትም፡፡ ቋንቋ የበር ቁልፍ ነው፡፡ ሌላ ትርጉም የለውም። ሁሉንም ቋንቋ መናገር ቢቻል በቀላሉ የሚፈለጉ በሮች ይከፈታሉ ማለት ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ነው መታየት ያለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቋንቋ ነፃ ነው፡፡ እነ ስታሊንም ቢሆኑ ቋንቋን ነፃ ለማድረግ ነበር የሞከሩት፡፡ እኛ ግን የክርክር ነጥባችን ነው ያደረግነው፡፡ ይሄ ትልቁ ስህተት ነው፡፡ እኔ ሁሉንም ቋንቋ  ባውቅ ጥሩ ነው፡፡ አፍሪካን ያቀኑ ተመራማሪዎች፣ 20 እና 30 ቋንቋ ለምደው ነው አፍሪካን የተቆጣጠሯት፡፡ ስለዚህ ቋንቋ የፖለቲካ አጀንዳ መሆን የለበትም፡፡ ቋንቋ የእውቀት ማግኛ ቧንቧ ነው፡፡ በኔ በኩል፤በትናንቱ ትዝታ የነገን ተስፋ ነው የምሰንቀው እንጂ ትዝታን አሁን አላላምጥም፡፡  
በዚህ መንገድ የታሪክ አተያይ ማዕቀፉን ብናሰፋው ለፖለቲካው ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ። አሁን ታሪክ ብለን የምንነታረከው በግለሰብ መሪዎች ገድል ዙሪያ ነው፡፡ ግለሰብ ህዝብ መሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ደግሞ የግለሰቦች ገድል ነው፡፡ ስለዚህ በግለሰቦች የመጣን ጣጣ፣ የህብረተሰብ አድርገን ስናየው ነው ችግር የሚሆነው፡፡ ጦርነት ይኖራል፤ በጦርነት መገዳደል ይኖራል፣ መጋባትም ይኖራል፣ ቤተሰብ መመስረት ይኖራል፡፡ የአለም ታሪክን ብናገላብጠው ከዚህ እውነት ፈቅ አይልም፡፡ ለምሣሌ በኛ ሁኔታ ትናንት የነበረውን የደርግን ብናይ፣ ካድሬው ወንድምህን ገድሎ እህትህን ያገባል፡፡ ያለፈ ታሪካችንም ከዚህ ያለፈ አይደለም፡፡ በአለም ላይ በተለያየ ምክንያት የሀገር ምስረታን ጨምሮ ያልተቋሰለ የለም፡፡ ግን የዚያ ቁስል ማገገሚያ መድሃኒቱ የጊዜ ሂደት ነው። የታሪክ ቁስል የሚያገግመው በጊዜ ሂደት ነው፡፡ ጊዜ ነው የሚያክመን፡፡ ስለዚህ ትዝታን በዚህ መልክ ብናስተናግደው የተሻለ ነው፡፡ ምሁራንም ትዝታን (ታሪክን) አስፍተው ቢያሳዩ የተሻለ ነው፡፡
በተለይ ዘመናዊ ኢትዮጵያን ፈጠሩ የሚባሉት አፄ ቴዎድሮስን፣ አፄ ዮሐንስን አፄ ምኒልክን እንደ ሰው ብናስተናግዳቸው መልካም ነው፡፡ እንደ ህዝብ ወይም እንደ መላዕክ ወይም እንደ ሰይጣን ስናደርጋቸው ነገር ይበላሻል፡፡ መላዕክትና ሠይጣኑን ቴዎድሮስ ሳይሆን ሰውየው ቴዎድሮስን ማየት፣ ዮሐንስንም ምኒልክንም እንደዚያው ማየት ብንችል ጥሩ ነው፡፡ ማጨለም ተገቢ አይደለም፡፡ በጨለመው ውስጥ እውነት ተቀብሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ለምን ብለን ብንጠይቅና ጨለማውን ብንመረምር፣ እውነቱን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ጥፋት መማሪያችን መሆን አለበት እንጂ ያደረ ቂም ማወራረጃ መሆን አይችልም፡፡ በታሪክ ጉዳይ ማጨለምና ማብራት የሚባል ነገር አለ፡፡ በማብራትና በማጨለም መሃል ያለው እውነት ይጠፋል፡፡ እንደ ፈረንጆቹ ታሪክን እንደ ትዝታ ማየት መልመድ አለብን፡፡ የስልጣን ምንጭን በርዕዮተ አለም ላይ መመስረት አለብን፡፡ ወደ ትናንቱ ባህልና ልምድ መመለስ አለብን፡፡ ይሄን ስናደርግ ቀስ በቀስ ችግሩን እየፈታን እንሄዳለን፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ተሟልቶ  ቀርቧል ማለት ይቻላል?
እንደውም ታሪክን ማወቅ ገና አልጀመርንም። ሁሉን አቀፍ የሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ በማወቅ በኩል ገና አልጀመርነውም፡፡ ጅምር የታሪክ ግኝቶች ናቸው አሁን ያሉት፡፡ ሌሎች ጉዳዮች ሰፍተው መምጣትና መቅረብ አለባቸው፡፡ ፈረንጆቹ ጋ ይሄ አካሄድ ሰርቷል፤ውጤት አምጥቷል፡፡ ታሪክን አሟልተው ስለሚያዩ እንደ ትዝታ ለመቁጠር አይቸገሩም። ታሪክን እምነት አያደርጉም፤ እውቀት ነው የሚያደርጉት፡፡ እኛ ነን አሁን እየተቸገርን ያለው፡፡ ታሪክን እንደ አንጐል ማበልፀጊያ አይደለም የምንወስደው፡፡ በነገራችን ላይ እውነት ያለችው ፈጣሪ ጋ ብቻ ነው፡፡ እውነት የት ነው ያለችው? ይባላል፤ እውነት እርግጠኛ ሆኖ አለች የሚባለው ፈጣሪ ጋ ብቻ ነው፡፡ እኛ ወደ እውነት ለመቅረብ ነው የምንሞክረው፡፡ መረጃም ማስረጃም ማቅረብና ወደ እውነታው መጠጋት እንጂ እውነት ተፈልጋ የምትገኘው ከፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ አሁን ታሪክን በመመርመር ሂደት ላይ ነው ያለነው፤ ገና አልጠራም። በሂደት ነው ወደ ጠራ ታሪክ የቀረበ ግኝት ማግኘት የሚቻለው፡፡ ታሪክ የማያልቅ ነገር ነው፡፡ የታሪክ አፃፃፋችን ደግሞ ያለቀ አይደለም፤ በሂደት ያለ ነው። ታሪክ ገና እየተፃፈ ነው ያለቀለት የሚባል ታሪክ የለም፡፡ ስለዚህ ታሪክ መማማሪያ እንጂ መነታረኪያ መፈራረጂያ መጣያ መሆን የለበትም፡፡ ታሪክ እምነት ሳይሆን እውቀት ነው፡፡ እውቀት ደግሞ በየጊዜው አንጐልን ማዳበር ነው፡፡ የታሪክ እውቀት ሙሉ ያደርገናል፡፡ ታሪክ የሌለው ህዝብ የለም፡፡
የቀድሞ መሪዎችን ወይም ጀግኖችን በዘር ማጠር ተገቢ ነው ይላሉ?
ትልቁ ችግራችን ስልጣን እንዴት እንመሠርታለን የሚለው ነው፡፡ ያንን ለማረጋገጥ የምንሄድበት መንገድ ነው ችግር የሆነብን፡፡ ለምሣሌ ራስ አሉላ አንድ ሰው ናቸው፡፡ ከአፍሪካ የጀግና ጀግና ናቸው። ቅኝ ገዢዎችን ያርበደበዱ ጀግና ናቸው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የሚከበሩ ናቸው፤ አይደለም በኢትዮጵያ። ገድላቸውን በወቅቱ ባልዋሉበት መንደርተኝነት፣ ወደ መንደርተኛ አስተሳሰብ ወስዶ ተራ ማድረግ ነውር ነው፡፡ ከመንደር ተወልዶ የአፍሪካ የጀግንነት ተምሣሌት የሆነን ሰው፣ መልሶ ወደ መንደር ለመውሰድ መሞከር ታሪኩን ማኮሰስ ነው፡፡ ለመላ ጥቁር ህዝቦች የሚሆን ሰውን፣ ለመንደር መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ ዘር፣ ደም፣ ዝምድና ሳይሆን መታየት ያለበት፣ ለሀገራቸው ምን አደረጉ የሚለውን ብርሃን ማየት ነው ትልቁ ጉዳይ፡፡ ባልዋሉበት ወስዶ የመንደር ሻማ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡

Read 3586 times