Saturday, 16 February 2019 14:09

አፍሪካን በኢትዮጵያ ውስጥ

Written by  በጌታቸው በለጠ
Rate this item
(1 Vote)

 ለምክርም ሆነ ለአዳዲስ የዕውቀት ሸመታ የልብ ወዳጅነት ያልተዘመረለት ት/ቤት ነው። “አልተዘመረላቸውም” ካልኳቸው የቅርብ ወዳጆቼ አንዱ፤ “ከእንዴት ሰነባበትን” የዘወትር ወጋችን አስከትሎ የወረወረብኝ የጥያቄ ናዳ፣ የሦስት ዓሥርት ተኩል ዓመታት አቋሜን መፈታተን ብቻ ሳይሆን፤ መቶ ሰማኒያ ዲግሪ የአመለካከት ለውጥ እንዳደርግ ጭምር ያስገደደኝ ነበር፡፡
ርዕሰ ጭውውታችን ወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታ መነሻ ከማድረግ ተስፈንጥሮ ማረፊያ ያደረገው በእኔው በራሴ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ ይህ ወዳጄ፤ የጨዋታ ደርዙ የማይዛነፍ፣ የንግግር ፍሰቱ የማይነጥፍ ጨዋና “ነገር ዐዋቂ” ይሉት ብጤ መልካም ሰው ነው፡፡
“እንዴት ነህ?” - “ደህና ነኝ፡፡” - “ሀገር በጤና ውላም አላደረች?” - “እርሱን አንተ ንገረኝ?” የጭውውታችን የፍጥነት እርምጃ የተጀመረው በእነዚህ መሰል ዘወትራዊ የወግ መቆስቆሻ ጥያቄዎች ነበር፡፡
ይህ ወዳጄ በሰላ ጣፋጭ ምላሱ ያዥጎደጎደብኝ የሃሳብ ውርጅብኞች የሚከተሉት ነበሩ፡፡ “በረኸኛ የፖለቲካ ጎምቱዎች” ወደ ሀገር ከገቡ ጊዜ ጀምሮ ምን እየፈየዱ እንዳሉ እያደመጥንም፣ እያስተዋልንም፣ እየታዘብንም ነው፡፡ ባህር ማዶኛ አክቲቪስቶችና ወጥቶ አደር የፖለቲካ አበጋዞችም “ጦርና ጋሻቸውን” መሬት ላይ በመጣል ዳግም አቧራውን አራግፈው “ባትዋጋ እንኳ በል እንገፍ እንገፍ!” በማለት ሲዘምሩለት የኖሩትን ልማድ እርግፍ አድርገው በመተው፣ ወደ ቀድሞ መጠለያቸውና የበረሃ ቤታቸው ላይመለሱ በመሃላ ጭምር ቃላቸውን ሰጥተውመ ከለውጡ ነፋስ ጋር ለመንፈስ በሀገር ጣራ ሥር ተጠልለዋል፡፡ በሥርዓቱ የተወገዙና በተገኙበት ተይዘው “ይሙቱ በቃ ፍርድ” የተበየነባቸው የባህር ማዶ ሚዲያዎችና ብዕረኞችም፣ የሀገራቸውን የተነቃነቀ ምሰሶ ሊደግፉ ቤት ሀገር ገብተዋል። “አንተ ግን...” በማለት ይሄው ወዳጄ በወሬ ጉልጓሏችን መሃል በፍፁም ያልጠበቅሁትን የጥያቄ መብረቅ ወርውሮ፣ አርፎ የተኛውን “አቋሜን” አባነነብኝ።
“ትራንስፎርሜሽን አቀንቃኙ መንግሥታችን በነፃነት ጻፉ፣ ያለመሳቀቅ ሃሳባችሁን ለአደባባይ አብቁ ብሎ ዋስትና ሰጥቷል፡፡ ከሀገሩ ሸሽቶ የኖረ ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስት፣ የሶሻል ሚዲያ ዘውገኞችና ሌሎችም፤ ‹ገቡ፣ ገቡ መጡልሽ! ሀገሬ!› እየተባለ ሲዘመርላቸው አንተ ዳግላስ ጴጥሮስ ግን ከየትኛውም ጎራ ወግነህ ሳትቀላቀል፣ እውነተኛ ስምህንና ማንነትህን በብዕር ስምህ ሸፍነህ፣ ለሦስት ተኩል አሥርት ዓመታት በተሸሸግህበት የብዕር ስም ቁጥቋጦ ውስጥ እንዳደፈጥህ፣ በሃሳብ እየተታኮስክ፣ የአንድ ጎልማሳ ሰው ዕድሜ አስቆጥረሃል፡፡ የደርግ መንግሥት እንደ ቀድሞ በምትጽፈው ሃሳብ አያስደነብርህ፣ ፀረ ብዕር አቋም የነበረው የቂሊንጦ ወህኒም እንኳን አንተንና ያገታቸውን ጦማሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የህሊና እስረኞች በሙሉ በሩን ወለል አድርጎ ለቋቸዋል፤ እኮ የአንተ በብዕር ስም የመጠለል ምሥጢር  ምን የተለየ ምክንያት አለው?
“ስደተኛውና በረኸኛው ፖለቲከኛ በድርጊቱና በስሙ ሳያፍር ወደ ሰላማዊ ትግል ተመልሻላሁ ብሎ በአደባባይ ሲንጎማለል፣ አክቲቪስት ነኝ ባዩ “እንኪያ ስላንተኛ” በሰዎች ጭንቅላት ላይ በእንኮኮ ሸክም ከፍ ብሎ ሰንደቁን እያውለበለበ፣ “የሆዱን ባናውቅም የአንደበቱን ማር ሲያንጠባጥብ” እያስተዋልን፤ አንተ ወዳጄ ምን ገዶህ ነው ዛሬም እንደ ትናንቱ በብዕር ስምህ የምትጽፈውን አንብቡልኝ እያልክ የምትማፀነው?”
ወዳጄን ልረታው ከማልችልበት ተጠየቁ ጋር ሙግት ለመግጠምና በጎ ሃሳቡን ለመገፍተር ብርታቱ አልነበረኝም፡፡ የነበረኝ ምርጫ አንድና አንድ ብቻ ነበር፡፡ በወዳጄ አሳማኝ ምክር መሠረት፣ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ከሕዝብ ጋር የተዋወቅሁበትንና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ባሉ መገናኛ ብዙኃን፣ ለብዙዎች ቤትኛ የሆነውን፣ በአንዱ መጽሐፌ ላይም በደራሲነት የተዋወቀውን ዳግላስ ጴጥሮስ የሚለውን የብዕር ስሜን ለታሪክ አደራ በመስጠት “ደህና ሁን ልበልህ በእንባ እየታጠብቁኝ!”ን እያንጎራጎርኩ፣ በሚሊዮን ዜጎች መካከል ከልደት እስከ ሞት ወደምጠራበት መደበኛ ስሜ መመለስ ግድ ሆኖብኛል፡፡
እነሆ ግላዊ ተጠቃሽ ትርጉም የነበረውንና የመኖሪያዬን አካባቢ ስም አጣምሮ የተሰየመውን  የብዕር ስሜን ዳግላስ ጴጥሮስን በመደበኛ ስሜ ተክቼ፣ ይህንን መጣጥፍ  በዳቦ ተምሳሌትነት በመቁረስ ከእዚህ ዕትም ጀምሮ በመደበኛው ስሜ ብቅ ብያለሁ፡፡ እናም፤ “ዳግላስ ጴጥሮስ”ን በክብር እንዲሰናበቱልኝና በመደበኛው ስሜ አንባቢያን “ቤት ለእምቦሳ” ብለው እንዲቀበሉኝ በአክብሮት እየጠየቅሁ ወደ ዕለቱ ብዕረ መንገዴ አቀናለሁ፡፡
የዛሬውንና የነገውን መጻኢ የአፍሪካዊያንን እና የአፍሪካን እድል ፈንታ የሚወስኑት የአህጉራችን መሪዎችና ዲፕሎማቶች ሰሞኑን በፖለቲካ መዲናቸው በአዲስ አበባ ሲመክሩ መሰንበታቸው ይታወሳል፡፡ የሀገራቸው ሕዝብ በአገዛዛቸው ተማሮ እንባውን ወደ ሰማያት የሚረጭባቸው ዓይነት መሪዎች ከደጃፋችን ሲደርሱ፣ ለንግሥነታቸው ክብር የአበባ ጉንጉን አጥልቀን በወታደራዊ ሰላምታ መቀበሉ ዲፕሎማሲ የተባለው አርቲፊሻል ቀኖና ግድ ስለሚል መሪዎቻችን፣ ይህንኑ ዓለም አቀፍ ሕግ ተከትለው፣ ጉንጭ ለጉንጭ በመሳሳም አቅፈው ተቀብለዋቸዋል፡፡ ምን ይደረግ? በአንጻሩ የመሪነትን ወንበር አንለቅም ብለው ለአራትና ለሦስት ዓሥርት ዓመታት በዙፋናቸው የሙጥኝ ብለው የተጣበቁ “መሪዎችንም” እንዲሁ ልብ ለልብ ተቃቅፈን፣ ነዎሩ ብለን ተቀብለናቸዋል፡፡ ወደን ነው፡፡  ረ ብዙ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ዳሩ “በለፈለፉ ባፍ ይጠፉ” ወይንም “በሞጫጨሩ በመከራ ይመከሩ” እንዳይሆንብን እንጂ ብዙ ማለት ይቻል ነበር፡፡
ከአፍሪካ መሪዎች ጋር የተያያዘ ተጓዳኝ ጉዳይ ላነሳ ፈልጌ በማያገባኝ ገብቼ ብዕሬን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ መራሁት፡፡ ይቅርታ፡፡ ዳሰሳዬ የሚያተኩረው በመንግሥታቱ መሪዎች ስብሰባ ዋዜማ የሚካሄደውንና መገናኛ ብዙኃን እጅግም የማይዘግቡትን፣ አንድ የተመሠገነ ዓመታዊ አፍሪካዊ ጉባዔ ለማስታወስ ፈልጌ ነው፡፡
ይህ ጉባዔ በኢትዮጵያ ምድር መካሄድ ከጀመረ ዓሥር ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አዘጋጁ ደግሞ በዶ/ር ቤተ መንግሥቱ የሚመራው ቤዛ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪስ የተባለ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ሀገር በቀል ተቋም ነው፡፡
“አፍሪካ ተነሽ!” በሚል ቋሚ ርዕስና በየዓመቱ በሚለዋወጥ የጉባዔ መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ ጉባዔ፤ ለዚህ ዓመት የመረጠው ዋና ጭብጥ “ጊዜው አሁን ነው!” የሚል ነበር፡፡ ከመላው አፍሪካና ከበርካታ የዓለማችን ሀገራት የሚጋበዙ ታላላቅና የተከበሩ የአፍሪካ ምሁራን በወረቀት አቅራቢነትና በተሳታፊነት የሚታደሙበት ይህ ጉባዔ፤ የምርምርና የሕይወት ተመክሮዎች ተጋምደው የሚቀርቡበት በዓይነቱ የተለየ ባህርይ ያለው ነው፡፡ በጉባዔው ላይ የሚቀርቡት ጥናቶችና የምርምር ውጤቶች፣ አህጉራዊና ሀገራዊ በሆኑ ቁጭቶች ውስጥ የሚከቱ፣ የዜግነት ኃላፊነትን የሚሞግቱና ለተግባር የሚያነሳሱ መልዕክቶች የሚተላለፉባቸውም ጭምር ናቸው። የጉባዔው መዝጊያ የተጠናቀቀውም ክብርት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና የቤተ እምነት ዋና ዋና መሪዎች፣ የተወሰኑ የአፍሪካ መሪዎችና በርካታ ዲፕሎማቶች በተገኙበት ለመሪዎቹ ስብሰባ መሳካት በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ውስጥ የቁርስ ላይ ጸሎት ከተደረገ በኋላ ነበር፡፡
አፍሪካ በአለኝታነት የምትኮራባቸው እነዚህ ጎምቱ ልጆቿ፣ በዚህ ለአንድ ሳምንት በተካሄደ ጉባዔ ላይ ስለ አህጉራችን ሁለንተናዊ አቋም ያቀረቧቸውን እጅግ መሳጭ ጥናቶች፣ ለጊዜው በይደር አስተላልፌ ስለ ሀገራችን ስለ ኢትዮጵያ የጠቃቀሷቸውን አንዳንድ ሃሳቦች ብቻ ለመፈነጣጠቅ እሞክራለሁ። በስሱ የምነካካው የጋዜጣው ውሱን አምድ ስለማይፈቅድልኝ ብቻ ነው፡፡
አንደኛው ታዋቂ አፍሪካዊ ምሁር ስለ ሀገራችን በገለፁት በአንድ መንደርደሪያ ዘለላ ሃሳብ ልንደርደር። ምሁሩ አበክረው የተነተኑት ሃሳብ እንዲህ የሚል ይዘት ይዟል፡፡
“--ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን የሚያዩት ከሃምሳ በላይ ቁጥር ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት እንደ አንዱ በማሰብ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ እንደ የትኞቹም አፍሪካዊ ሀገራት ሉዓላዊና ዓለም አቀፍ ድንበሯ የተከበረላት ሀገር ናት፡፡ እውነታው በዚህ ውሱን ሃሳብ ላይ ብቻ የሚሽከረከር ከሆነ ግን ሊታረም ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም የሚወክለው በድንበር ክልል የተወሰነውን የምሥራቅ አፍሪካ አንድ ንዑስ ክፍል ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ከሀገር መታወቂያነት ከፍ ያለና በዋነኛነትም የጥቁር አፍሪካዊያን ሕዝቦች መለያ ጭምር ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና ጠቦና ተሸብሽቦ፣ የአሁኑን ጂኦግራፊያዊ ቅርፅ ከመያዙ አስቀድሞ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥም ሆነ በጥንታዊያን ሰነዶች ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም የሚጠቀልለው በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በተዘረጋው ሰፊ መልክዓ ምድር ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም ጥቁር ሕዝቦች ነው። ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊለውጥ አይችልም እንዲሉ ማለት ነው።”
ዝርዝሩን ጥናት ከሰማሁ በኋላ በግሌ ኢትዮጵያን መመልከት ያለብን በአፍሪካ ውስጥ ሳይሆን፤ አፍሪካን መመልከት ያለብን በኢትዮጵያ ውስጥ ሊሆን ይገባል ብያለሁ። ይህንን እውነታ የተረዳሁት አንድን ምሁር ለማንቆለጳጰስ ወይንም የፓን አፍሪካን ንቅናቄን ለማራገብ ፈልጌ ሳይሆን እርግጥ ነው ብዬ በማመን ነው፡፡
እንደ ጥናት አቅራቢው እምነት፤ የብዙ ሀገራት የረዥም ዘመናት ታሪክ ተፈልፍሎ ወይንም ተቆፍሮ የሚወጣው በአንትሮፖሎጂ ወይንም በአርኪዮሎጂ የሳይንስ ዘርፎች እየታገዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ማግኘት የሚቻለው ግን በቁፋሮ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች ማንነት ውስጥ በመቅዳት ጭምር ነው። ኢትዮጵያም ሆነ ኩሽ የሚሉት አገላለጾች፣ ከመልክዓ ምድራዊ የችካል ክልል የሰፋ ጥንታዊ የሕዝብነት ማስረጃና ትርጉም አላቸው፡፡
ብዙ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ገናናነትና ትልቅነት የምንተርከው፣ የምንከራከረውና የምናስተዋውቀው ጥንታዊ ባህላችንንና ቋንቋችንን፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ታሪካዊ ቅርሶቻችንን፣ ጀግንነታችንንና ለወራሪ ጠላቶቻችን ያለመበገራችንን ወዘተ. እየተረክን ነው፡፡ የባህልና ቱሪዝም መሥሪያ ቤታችን እንዳይቀየመን ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሁሉ የምንኮራባቸው ታሪኮቻችን መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ በተጨባጭ ጥናት ምሁራኑ ያቀረቧቸው ዝርዝር መረጃዎች የሚያመላክቱት ግን ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ የኢትዮጵያዊነት መሠረታዊ አስኳል የሚገኘው በመላው አፍሪካና ከአህጉሪቱ ውጭ በተለያዩ ዓለማት ውስጥ በተበተኑ የአህጉራችን ጥቁር ሕዝቦች ማንነት ውስጥ ነው፡፡
ነገር አዋቂ አዛውንቶች ሲተርቱ፤ “የባተሌን ስጥ የጎረቤት ዶሮዎች ጭረው ይበትኑታል፤ የሰነፍን ሰው ስጥ ጭረው የሚበትኑት ግን የራሱ የቤት ውላጅ ዶሮዎች ናቸው” የሚሉት አባባል አላቸው፡፡ እውነት ነው፤ ባዕዳን ባተሌ የውጭ ሀገር ምሁራን ከበተኑትና ካውገረገሩት ታሪካችን በማይተናነስ መልኩ እኛው በእኛው ጭረን እንዳልባሌ የበተንናቸውና ያጣጣልናቸው ታሪኮቻችን ብዙዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ከጥቁር ሕዝቦች መገለጫነት አፋትተን በራሳችን ዐውድ ልክ ያጠበብናቸው፣ ዝቅ አድርገንም በክልል በመሸንሸን ያሳነስናቸው፣ ሲከፋም በጎጥ ደረጃ አውርደን ግዙፉን ታሪካችንን እንደ ድንክ ያኮሰመንነው “በቤት ውላጅ ዶሮዎች” የምንመሰለው፣ እኛው የሀገር ውላጅ ልሂቃን ተብዬ ልጆቿ መሆናችንን፣ ስድስተኛው ስሜቴ ወቅሶኛልም፤ ገስጾኛልም፡፡
ሌላኛው ጥናት አቅራቢ አፍሪካዊ ምሁር በተደጋጋፊ አቋም ያቀረቡትን፣ በግሌ ዘርዘር አድርጌ የተነተንኩትን አንድ ርዕሰ ጉዳይ ልጥቀስ፡፡ እንደ ጥናት አቅራቢው አገላለጽ፤ የጊዜን ፅንሰ ሃሳብ በተሻለ ሁኔታ የሚገልጹት ክሮኖስና ካይሮስ የተባሉ ሁለት የግሪክ ቃላት ናቸው፡፡ ክሮኖስ ተፈጥሯዊውን የጊዜ ሦስት አቅጣጫዎች የሚወክል ነው፡፡ ትናንት፣ ዛሬና ነገን፡፡ ስንት ሰዓት ነው? ወሩ ማነው? ታህሳስ ሰባት ቀን የሚውለው ምን ቀን ነው? ወዘተ. እያልን ስለ ዓመት፣ ወራት፣ ሣምንታት፣ ቀናት ወይንም ሰዓትና ደቂቃ ጠይቀን የምናገኘው መልስ የሚጠቃለለው በክሮኖስ ውስጥ ነው፡፡ ካቻምና፣ አምና፣ ለክርሞ እያልን የምንናገረውም ክሮኖስን ለማመልክት ነው፡፡
ካይሮስ የሚወክለው ግን የተለመደውን የጊዜ ቀመርና ካሌንደር ብቻ አይደለም፡፡ ትርጉሙ ረቀቅ ይላል፡፡ ካይሮስ፤ ዕድልና ጊዜ አመቻችቶ የሚሰጠን ዕድሜው አጭር የሆነ፣ የማይተካና የማይደገም ወርቃማ ጊዜና አጋጣሚ ነው፡፡ ካይሮስ ለነገ ይደር ብለን የምናቆየውና የምንዘናጋበትም ዕድል አይደለም፡፡
ይህንን ጽንሰ ሃሳብ ከወታደራዊ የጦርነት ስልት ጋር ማዛመድ ይቻላል፡፡ በአንድ የጦርነት ግንባር ላይ አብሪ ጥይት የሚባል አለ፡፡ የአብሪ ጥይት ግልጋሎት በጭለማ የሚደረግን ጦርነት ለማገዝ የሚረዳ ነው፡፡ ሁለት የተፋጠጡ ተፈላሚ ግንባሮች ባሉበት ዐውድ ላይ ጊዜው ጨለማ ከሆነና አንደኛው ወገን የጠላቱን አሰፋፈር ለመቃኘትና ጦርነት ለመጀመር ሲፈልግ፣ የግዳይ ወረዳውን በቅፅበት አሳይታ እልም የምትል አንዲት አብሪ ጥይት ይተኩሳል፡፡ አብሪዋ ጥይት የጦርነቱን ቀጣና ለቅፅበት ወለል አድርጋ ካሳየች በኋላ ትመክናለች፡፡ አብሪዋን ጥይት የተኮሰው ኃይል፣ በዚያ ብርሃናማ ቅጽበት የተኩስ እሩምታ ከፍቶ ጠላቱን ካላስጨነቀ በስተቀር ተዘናግቶ ካመነታ፣ ራሱን ለጠላት አሳልፎ ስለሚሰጥ፣ አጥቂ መሆኑ ቀርቶ ተጠቂ ይሆናል፡፡
“ብረትን እንደጋለ” እንዲሉ የካይሮስ ዕድል በእጃችን በወደቀ ጊዜ በጥበብ፣ በጥንቃቄና በማስተዋል ተጠቅመንበት ውጤት ካላስገኘን በስተቀር፣ ዳተኛ ሆነን በቆይ ብቻ ፉከራ የምናላዝን ከሆነ፣ ዕድሉ ከእጃችን መውጣቱ አይቀርም፡፡ አፍሪካዊው ምሁር እነዚህን ሁለት መሠረታዊ ቃላት በመጠቀም በእጅጉ ሞግተውናል፡፡ ከተለመደው የክሮኖስ የጊዜ አቆጣጠር ተላቀን ዕድልና ጊዜ ባመቻቸልንና ለአጭር ጊዜ በእጃችን ላይ ሊቆይ በሚችለው ሀገራዊ የካይሮስ ዕድል እንድንጠቀምም መክረውናል፡፡
በክሮኖስ ስሌት መሠረት ወደ ኋላ ዞር ብለን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሆነ መሰል ሌሎች ታሪኮቻችንን ብንመረምር በርካታ ካይሮሶችን በከንቱ እንዳመከንን ለመገንዘብ አይገድም፡፡ ዝርዝሩን ለጊዜው ብናቆይም፡፡ ራሳችንን እንደ አፍሪካዊ ባለመቁጠራችን፣ ጥቁር ሕዝቦችን ከሚወክለው ኢትዮጵያዊነት በገዛ ፈቃዳችን ማራቃችን አንደኛውና ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ የታቀፉትን አፍሪካዊያን እህቶቻችንንና ወንድሞቻችንን በማግለላችንም ብዙ እንደተጎዳን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ከተጠለለው ጥቁር አፍሪካዊነት ይልቅ የቆዳ ቀለሙ ለፈገገው ቅድሚያ መስጠታችንም እውነት ነው፡፡ ምንም እንኳ ሰው ሁሉ እኩል ቢሆንም፡፡
ለምሳሌ፤ ባለፉት ዘመናት እንደ ሕዝብ መልካም አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱን መሪዎችንና ልሂቃንን አጥተን ምን ያህል የተመቻቹ የፖለቲካ ካይሮሶችን በሀገራችን አመከንን? የገዘፈውን የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ችላ ብለን ዘውግና ጎጥ ወለድ በሆኑ ትርክቶች እየማለልንስ በማንወጣው አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን አልኖርንም? እየኖርንስ አይደለም? እርግጡን እንናገር ብለን ችግሮቻችንን “በሆድ ይፍጀው ፍልስፍና” እያመካኘን፣ ምን ያህል መልካም ካይሮሶች አልፈውብናል፡፡
በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን በኩል ሊተላለፍ የሚገባውን የአፍሪካ የበረከት በር ጥርቅም አድርገን ዘግተን የሀገራችንን የራስ ምታት ዕድሜ ያራዘምነው እኛው ራሳችን ሳንሆን እንቀራለን፡፡ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ፤ ይህንን መሰል አባባል በዚሁ የአፍሪካ ምሁራን መድረክ ላይ ደጋግመው ሲናገሩ አድምጫለሁ፡፡
ለመሆኑ እኛው ኢትዮጵያዊያን ተብዬዎች ባለታሪክ ነን እያልን ታሪክ ስናፈርስ፣ በአፍሪካ ውስጥ እየኖርን ራሳችንን ከእውነታ ስናፋታ፣ ጀግንነት ክብራችን ስለመሆኑ ዓለም ቢመሰክርልንም ከናካቴው በጋራ ያፀደቅነው ብሔራዊ ጀግና አጥተን አልተቸገርንም፡፡ ኢትዮጵያዊነት አፍሪካዊነት መሆኑን ረስተን፣ በዘራችን ጠባብ ጎሬ ውስጥ ተሸሽገን ባለፉ ታሪኮቻችን እየተጨናበስን፣ በህሊናችን ላይ አቧራ እየበተንን መዋላችን ሃሰት ነው፡፡ ዘራችንን እንካድ ማለት እንዳይደለ ግን ልብ ይሏል፡፡
ጽሑፌን የምቋጨው በግሌ በሚያብከነክኑኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አፅንኦት በመስጠት ነው። ዕድልና ጊዜ እንበለው ወይንም ግፍና ትግል ብቻ የሆነው ቢሆንም፣ የካይሮስ ወርቃማ ዕድል በሀገራችንና በሕዝባችን እጅ ላይ ስለመውደቁ ሁላችንንም የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ በስተቀር አይደለም አፍሪካን በኢትዮጵያ ውስጥ እያዩ በጉጉት ለሚጠብቁን ሕዝቦች ቀርቶ ለራሳችንም ቢሆን መትረፋችንን በግሌ እጠራጠራለሁ። የካይሮስን ዕድል አሁን ካመከንነው፣ ልጆቻችን ታሪካችንን የሚተርኩት ነበር በሚል ኃላፊ ክሮኖስን እየጠቀሱ እንደሚሆን ስጋቴን በድፍረት መግለጽ እፈልጋለሁ። ስጋት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካዊያን ልብ ውስጥ የጎላ ስፍራ ያላት ይህቺ መልካም ሀገር፣ የአንበሳነት አቅሟ ተዋርዶ ወደ ጎጥና ጉሮኖ ደረጃ ማዘቅዘቋም አይቀሬ ይሆናል፡፡
በሀገራችን ቀደምት ታሪክ የአገዛዙን ፍልስፍና በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በመደመር፣ በምህረት ላይ ቃኝቶ የገዛን መሪ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። ኖሮ ከሆነም ከዘርፉ ልሂቃን ለመማር ዝግጁ ነኝ። በእኔ የግል መረዳት፤ ምናልባትም ብዙሃኑ እንደሚተባበሩኝ በማመን፤ የካይሮስ ዕድል ከንግሥና ጋር አገጣጥሟቸው ለመንበረ ሥልጣን የበቁ የሀገራችን መሪዎች በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ (“ጀግናው ኢህአዴግንም ጨምሮ”) ሲገዙን የኖሩት ፀጥና ለጥ አድርገው ነው፡፡ ፀጥታውና ለጡ በአግባቡ መተርጎሙን ሲያረጋግጡ ደግሞ ወቃሻቸውንና መካሪያቸውን “ይለፍልፍ” ወይንም “ይጻፍ ምን እንዳያመጣ ነው” እያሉ ሲያሾፉብን ኖረዋል ወይንም ተሳልቀውብናል፡፡
“ንጉሥ አይከሰስ፤ ሰማይ አይታረስ” የሚለው ብሂል፣ የዘመነ ፊውዳሎቹ መሪዎች አባባል ብቻ ሳይሆን የተከታዮቹም መሪዎች መመሪያ ነበር ቢባል ሃሰት አይሆንም፡፡ ዜጎችም እንደ ንጉሡ እያጎነበሱ ዕድሜያቸውን ሲገፉ ኖረዋል ቢባልም አያስቀይምም፡፡ ካቻምና፣ አምናም ሆነ ዘንድሮ ቃሉና አባባሉ ይለያይ እንጂ ግብሩና ውጤቱ ተመሳሳይ ስለመሆኑም ለንትርክ አይጋብዝም፡፡
“ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” እያልን የዘመርንለትም ደርግ ቢሆን ታሪኩ የተደመደመው ሕዝብን ደም እያስነባና በደም ተጨማልቆና አጨማልቆ ነው። በዲሞክራሲና በፍትሕ ስም እየማለና እየተገዘተ ከበረሃ ተነስቶ ቤተመንግስት ያረፈው ጦረኛው ነጋሲም፣ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በግፍና በኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በሕዝብ ላይ የመከራ ዶፍ ሲያዘንብ አሜን ብለን ገብረናል። እልል ብለንም አዳምቀናል፡፡
በተያያዝነው በዚህ በዘመነ ካይሮስ ግን መሪዎቻችን ካይሮሳዊ አመለካከት እንዳላቸው ብዙዎቻችን በአሜንታና በዕልልታ ተቀብለናል። የካይሮስ እድሉን ወደ ተለመደው የታሪክ ክሮኖስ ለመለወጥ የማይውጠነጠን ሤራ አለመኖሩን ሳንዘነጋ፡፡ ሀገሪቱ በትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ መሆኗን መግለጥ ጅል ማሰኘት ብቻ ሳይሆን “የአዋጁን በጓዳ” ተረት እንዳያስተርትብኝ ስጋት አለኝ፡፡ የትራንስፎርሜሽን ክፋቱ “አረሙና ሰብሉ አብሮ እንዲያድግ” መፍቀዱ ነው። በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የለውጥ ጅማሮ፣ ሪቮሉሽን ቢሆን ኖሮ “በእንትን መቃብር ላይ የእንትንን ባንዲራ እናውለበልባለን!” የሚል መርህ ስለሚተገበር፣ የነገሮች ሁሉ ጅማሬ “በአሮጌው ሟች መቃብር ላይ” ይሆን ነበር፡፡ ደግነቱ ለውጡ ሪፎርም (ተሃድሶ) መሆኑ በጀ፡፡ በውጤቱ ላይ ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች ስለሚነሱ ጠልቄ መግባቱን አልወደድኩትም፡፡
አሁን ያሉት የሀገሪቱ ቁንጮ መሪዎች የካይሮስ ምሥጢር የገባቸው ስለመሆኑ ከተግባራቸው እያየን ነው። ምናልባትም አላዩት ከሆነ፤ ወይንም አይተውም ለጊዜ ጊዜ እንስጥ የሚል መርህ እያራመዱ ከሆነ፣ አንዳንድ ጉዳዮችን በድፍረት መጠቃቀሱ አግባብ ይሆናል። ከዓመት በፊት በአንድ ጡንቻቸው ያስገብሩ የነበሩ የመንግሥት ሹሞች፣ የትራንስፎርሜሽኑን ካባ ከደረቡ በኋላ በሁለት ጡንቻቸው ማስገበር ጀምረዋል፡፡ አንድም የደማቸውን ዲ.ኤን.ኤ እያገዘፉ አለያም በደረቡት ካባ ክብደት እየተመኩ፡፡ የእኒህን ዘመን ወለድ የከባድ ሚዛን ቦክሰኞች የተዘወተረ ድርጊት፣ የካይሮስ ጥበብ የተገለጠላቸው ተወዳሹ መሪያችን ይጠፋቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ እርግጥ እኒሁ ካይሮሳዊ መገለጥ የታደሉት መሪያችን፣ የበቁና የላቁ ኮስታራ አማካሪዎች በዙሪያቸው ስለማሰባሰባቸው ብዙ ዜጎች “እንጠራጠራለን” እያሉ ሲያሟቸው ይደመጣል፡፡ እኔም ብሆን አንዳንድ ሀገራዊ ጉዳዮች ሲጎረብጡን እንደ አንድ ዜጋ ንስሃ ልግባና ደጋግሜ አምቻቸዋለሁ፡፡
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ የካይሮስ ጊዜ በተመለከተ ዓለም እያጨበጨበልን፣ መንግሥታትም በነቂስ ውዳሴ እያዥጎደጎዱልን፣ መገናኛ ብዙሃንም መልሰው እያናኙልን መሆኑ እውነት ነው፡፡ እኛስ ብንሆን ፎቶግራፋቸውን ለመቃብራቸው ሃውልት እንደምንመኝላቸው ቀደምት መሪዎቻችን ሳይሆን ዛሬ ዛሬ የካይሮስ መሪዎቻችንን ፎቶግራፎች፤ በየመኪኖቻችንና በየስልክ እንጨቶች ላይ እየለጠፍን በማጨብጨብ እያስጨበጨብንላቸውም አይደል፡፡ የእኛ ጭብጨባ ባይደመጥ ኖሮ የዓለም ሀገራት ሹማምንት መች ፊት ይሰጧቸው ነበር። ዞሮ ዞሮ መረጃውን የሚሰበስቡት ከእኛው ከሕዝብ ተብዬዎች አስተያየቶች ተነስተውስ አይደለም፡፡ ለማንኛውም በጭብጨባ መካከል ስንቆም፣ ይህንን አባባል ማስታወሱ ክፋት የለውም። “ስትስቅ/ቂ ዓለም ሁሉ አብሮህ/ሽ ይንከተከታል፤ ስትቆዝም/ሚ እና ስታለቅስ/ሺ ግን በርህን/ሽ ዘግተህ/ሽ ለብቻህ/ሽ እንባህን/ሽን እያበስክ ነው።” “አደራ! አደራ! የአፍሪካዊያን መስታወትነታችንን ዘንግተን በጎጥ አጥር ውስጥ እንዳናድር” እያልኩ የመነሻዬን ሃሳብ አግዝፌ ብዕሬን አሳርፋለሁ፡፡
ውጤታማ የካይሮስ ጊዜ ይሁንልን - ሰላም!!!    

Read 454 times