Sunday, 17 February 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “እርቅና ሠላም ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም፤ ጣሊያንን ይቅር ያልን ህዝቦች ነን”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

 የእርቅና ሰላሙን ጉዞ የሚጓዘው 100 ሚ. ህዝብ ነው

         ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢነት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌልን እንዲሁም በምክትል ሰብሳቢነት ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴን መሾማቸው ይታወሳል፡፡ በሹመቱ ዙሪያ ከብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢዋ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ጋር ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡

         ፖለቲከኛ መሆን አልፈልግም ስትይ ሰምቻለሁ ሹመቱን እንዴት ተቀበልሽው?
የእርቀ ሠላም ስራ የሁሉም ሰው ስራ ነው። እኔ ሁልጊዜም ፖለቲካ ውስጥ መግባት አልፈልግም እላለሁ፡፡ ወይም ባልገባ ደስ ይለኛል፡፡ ይህ ግን የፖለቲከኞች ሥራ አይደለም። እርቀ ሰላም ለፖለቲከኞች ብቻ የሚተው ስራ አይደለም፡፡ በእርቅና ሰላም ስራ ውስጥ ለመግባት የፖለቲካ ሥራ ውስጥ መግባት ግድ አይሆንም - ስለ እውነት፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ እኩልነት የምትቆረቆሪና በዚህ የምታምኚ ከሆነ፣ የእርቀ ሰላም ጉዳይ ያገባሻል፡፡
እመረጣለሁ ብለሽ ጠብቀሽ ነበር?
ስለ እውነት ለመናገር እርግጠኛ አይደለሁም። አዋጁ ከፀደቀ ሰነባብቶ ስለነበር ሰዎች የተሾሙ መስሎኝም ነበር፡፡ አንዳንዴ ሳትሰሚው የሚያልፍሽ መረጃ አለ አይደል እንደዛ ሊሆን እንደሚችል ነበረ ያሰብኩት፡፡ ነገሩ ሲነገረኝ እንደ ትልቅ መታደል ነው የቆጠርኩት። ምክንያቱም በዚህ አንገብጋቢ በሆነ ጉዳይ ላይ እንድናገለግል ከዚህ ሁሉ ሕዝብ መሀል 42 ሰዎች መመረጣችን ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ከ42 ጠንካራ ስብስብ መካከል ደግሞ ለምክትል ሰብሳቢነት ወይንም ለምክትል ኮሚሽነርነት መመረጥ ሌላ መታደል ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ 42 ሰዎች እያንዳንዳቸው ከአንድ መጽሐፍ በላይ ታሪክ ያላቸው፣ ትልልቅ ነገር ለአገራቸው የሰሩ፣ እነ ዶክተር በላይ አበጋዝ፣ እነ ደራርቱ … በጣም ብዙ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱን ለመወከልና የነሱ ምልክት ለመሆን መመረጤ ለኔ ትልቅ መታደል ነው፡፡ የእግዚብሔር ስጦታ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከእነሱ ጋር በራሱ አብሮ ለመስራት መመረጥ ትልቅ ዕድል ነው። እነዚህ 42 ሰዎች እኮ 42 አገራትን መምራት የሚችሉ … 42 ትላልቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መምራት የሚችሉ … ትልልቅ አቅሞች ናቸው፡፡ ከነዚህ አቅሞች ጋር መሆን በራሱ ለኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ የተዋረድ ሥራ አይደለም ሌሎቹ አንሰው እኔ የተሻለ ሆኜ አይደለም። ምክትል ሰብሳቢ የሆንኩት፡፡ ለዚህ ቅዱስ ስራ፣ ለዚህ ትልቅ ሥራ፣ በጋራ አንድ ላይ ሆነን ለምንሰራው ስራ ምልክት እንደመሆን ነው፡፡
የተሰጠሽን ኃላፊነት እወጣዋለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?
በሚገባ እወጣዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን እኮ እርቀ ሰላም የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ ይቅር ማለት ለኛ አዲስ አይደለም። ጣሊያንን ይቅር ብለን እኮ ኤምባሲውን በአገራችን እንዲከፍት አድርገናል፡፡ በጣም ብዙ ጠላቶቻችን፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዳትቀጥል በጣም ብዙ ነገር ያደረጉንን ሰዎችና አገራት ሁሉ ይቅር ብለን እዚህ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ አርባ ሁለታችን አብረን መንገድ የምንጠርግ ሰዎች ነን፡፡ ግን ትልቁ እወጣዋለሁ ብዬ እንዳስብ የሚያደርገኝ የኢትዮጵያዊነት አሻራችን፣ ትላንት ያለፍንበት ዳራችን፣ ስለ ሰላም፣ ስለ እርቅ፣ ስለ አንድነት፣ ለመስበክ ከቀድሞ ነገስታት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለን የህዝብ መንፈስ … በጣም ጠንካራ ነውና እንደሚሳካልን እምነት አለኝ። 100 ሚሊዮን ህዝብ እንደ ችግር ሳይሆን እንደ ሃብት ነው እኔ የማየው፡፡ እርቅና ሠላም የሚፈልግ መቶ ሚሊዮን ህዝብ እንዳለው አገር፣ ሃብታም በዚህች ምድር ላይ አለ ብዬ አላምንም። እኛ ቅድም እንደነገርኩሽ መንገድ ጠራጊና አስተካካዮች ነን፡፡ ተራማጁ ማለት የእርቅና ሰላሙን ጉዞ የሚጓዘው ይኸው 100 ሚሊዮን ህዝብ ነው፡፡ ይህንን ህዝብ ይዘን እንደሚሳካልን አምናለሁ፡፡ እግዚአብሔርም ይረዳናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክትል ኮሚሽነርነቱ ባጩሽ ጊዜ ለኖቤል የሰላም ሽልማት ብናዘጋጃት የሚል ነገር ተናግረዋል፡፡ ይህንን አባባል አንቺ እንዴት ታይዋለሽ? ለኖቤል የሰላም ሽልማት እበቃለሁ የሚል ሃሳብስ አለሽ?
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህርይ ይታወቃል፡፡ ሰው በጣም ያከብራሉ፡፡ ሁሉንም ሰው ይወዳሉ፣ ብዙዎች ያላያቸውን ጥቃቅን ሰዎች አግዝፈውና ትልቅ አድርገው ማየት የሚችሉ ትልቅ ዓይን ነው ያላቸው፡፡ ለመልካም ምኞታቸው ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ እኔ ግን በዚህ ዓለም ላይ እኔ ብቻ ሳልሆን በጣም በርካታ የዓለም ሰዎች፣ በምጓዝበት ሁሉ እንደታዘብኩት፣ የዓለም የሰላም የኖቤል ሽልማት ይገባቸዋል ብለው የሚያስቡት እሳቸውን ነው፡፡ ያው እሳቸው ሁልጊዜም ለሌሎች በመስጠት ላይ የተመሰረተ አኗኗር ስለሚከተሉ የመስጠታቸው አንዱ አካል ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ በእኔ እምነት ግን ሁላችንም በጋራ ልንቆምበት የሚገባ፣ ወደፊት አገራችንን የዓለም የኖቤል የሰላም ሽልማት መዝገብ ውስጥ ሊያፅፍልን የሚችል ታላቅ ስም፣ ዶ/ር አብይ አህመድ የሚለው ስም ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡   

Read 3118 times