Saturday, 16 February 2019 14:02

ጓሳና ድንግል ያለአንድ ቀን አይበቅል

Written by 
Rate this item
(15 votes)


         ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ አንዲት ክፉ ሚስት ነበረችው፡፡ በእርሻ ሲደክም ውሎ ሲመጣ፤
“ና ወጥ ስራና ራቴን አብላኝ”
“ና እግሬን እጠበኝ” ትለዋለች፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ፤
“ወገቤን አሞኛል ና እሸኝ” ትለዋለች፡፡
ደሞ ሌላ ጊዜ፤
“ና፤ እግሬን እጠበኝ”
“ና በቅባት እሸኝና አስተኛኝ!” ትለዋለች፡፡
እንዲህ ቁም ስቅሉን ስታሳየው ከርማ፣ የአምላክ ፈቃዱ ሆኖ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡
ከሞተች በኋላ ብዙ ጊዜ በብቸኝነት መኖሩን ያስተዋሉ ሰፈርተኞች መክረው ዘክረው፤ ሌላ ሚስት እንዲያገባ አደረጉት፡፡
አዲሲቱ ሚስት ደግሞ የመጨረሻ ደግ፣ አስተዋይ ሆነችለት፡፡
ጠዋት ከአልጋው ሳይነሳ ቆንጆ ቁርስ ሰርታ እዛው ባፍ-ባፉ አጉርሳው፤ ማታም ከእርሻ ሲመለስ እግሩን አጥባ ወገቡን በቅባት አሽታ፣ ራቱን አጉርሳው አቅፋው ትተኛለች፡፡
ይሄኔ ይህ ባል፤ እንዲህ ብሎ ፀለየ ይባላል፡-
“አምላኬ ሆይ፤ ስላደረክልኝ ሁሉ ምስጋና ይግባህ! አንድ ውለታ እንድትውልልኝ እጠይቅሃለሁ፡፡ ይኸውም ከዚች የተሻለች የምትመጣ ከሆነ እባክህ እቺንም ግደልልኝ!”
***
ዱሮ፤ ዱሮ ዱሮ፤
“ጉዟችን ረዥም
ትግላችን መራራ” ይባል ነበር፡፡
አንድ የደርግ ካድሬ አገሩን ሲያምስ ሲያተራምስ ከርሞ ተረኛ ታካሚ ሆኖ ራሱ ታሰረ፡፡ ከዚያ ሲደጋግመው የኖረውን ያንን መፈክር መጠየቅና መቃወም ጀመረ፡-
“ትግላችን መራራ፣ ጉዟችን ረዥም” ብሎ ነገር ምንድን ነው? መራራ ከሆነ አጠር ይበል፣ ረዥም ከሆነ ጣፈጥ ይበል፡፡ ለምንድን ነው ለህዝባችን ደግ የማንመኘው” አለ። ካልተቀጡ የማይማሩ አያሌ ካድሬዎች ስናፈራ ኖረናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ቤት ያፈራቸው ናቸው!
ዛሬም ሊቀጥል እንደሚችል ጭንቅላትን ይዞ ማሰብ አይጠይቅም፡፡ ዋናው ከሆነውና ከሚሆነው መማር ነው!
“ምንኛ ታድሏል የሰነፍ አዕምሮ
እንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና
አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
ብለዋል ከበደ ሚካኤል፡፡ መስማት ካቃተን ለውጥ አናመጣም፤ ዕውነት ለመናገር ለውጥን ከልብ ካላሰብነው አገር አንለውጥም፡፡ መቼም! መቼም! መቼም!
የመከላከያን መዋቅርና አስተሳሰብ፣ መለወጥ፣ ስለደ ህንነት ያለንን ግንዛቤ ማሻሻል፣ አገርን ከማዳን አኳያ መታደጊያችን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የንቃተ ህሊናችን መበልፀግ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህን የአገር ህልውናዎች በጤናማ መንገድ አለመንከባከብ ቆይቶ ያስከፍለናል፡፡ ወታደራዊና ደህንነታዊውን ኃይል በጤናማ ዐይን ካላየን፣ እንዲሁም የምንመኛትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ካልተዘጋጀን፣ እንደ ልማዳችን ይረፍድብናል፡፡ “ባለበት ሃይ!” የምንባለው ለዚህ ነው!
አንዳንድ ዕድሎች አይደገሙም፡፡ አጋጣሚዎችን ቀልጠፍና መጠቅ ብለን ካልተጠቀምንባቸው ያመልጡናል፡፡ አንዴ ከጠፉ የማይመለሱ ብዙ ናቸውና ይሄንን ቀን አንጣው!
Girl, if you want to
Prove that you are a virgin
Don’t forget, that
 you’ll never prove it again!
ድንግልናሽን ማረጋገጥ ከፈለግሽ ደግመሽ እንደማታረጋግጪው እወቂ፤ እንደማለት ነው፡፡ “ጓሳና ድንግል ያለአንድ ቀን አይበቅል” ማለት ይሄ ነው!!

Read 12594 times