Saturday, 16 February 2019 13:56

ምሁራኑ ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ማምጣት አለባቸው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 ፕ/ር መረራ ጉዲና በጐንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል


          የሀገሪቱ ምሁራን ለሀገሪቱ የፌደራሊዝምና የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ማምጣት እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡ የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ማናጅመንት ትምህርት ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የፖለቲካ ውይይት መድረክ ላይ ፕ/ር መረራ ጉዲና፣ የጠ/ሚሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪው ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት  ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ “የምሁራን ሚና እና አስተዋጽኦ በሀገሪቱ ፖለቲካ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ፕ/ር መረራ ባቀረቡት ፅሑፍ “ምሁራን የታሪክ ፈተና አሁንም አለብን፤ ይሄን የታሪክ ፈተና የምንፈታበትን መንገድ እስካሁንም አላገኘነውም” ብለዋል፡፡ የታሪክ ፈተናን ለማለፍና የሀገሪቱን የፖለቲካ ‹ቡዳ› ለይቶ ለማውጣት ምሁራን ተግተው መስራት እንዳለባቸው፣ ሃላፊነትም በጫንቃቸው እንዳረፈ ጠቁመው፤ ለግጭትና መከፋፈል ምክንያት እየሆነ ያለውን የፌደራል ስርአት በተመለከተ ሠፊ ጥናቶችና ምርምሮች ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ባለፉት 27 አመታት ጐንደርን ጐብኝተው እንደማያውቁና ወደ ጐንደር ከሄዱ ረጅም ዘመን እንዳስቆጠሩ የጠቆሙት ፕ/ር መረራ፤ እንዲህ ዝግ ያልሆኑና ሁሉን አቀፍ የምሁራን ውይይት በየአካባቢው ሊከፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ምሁራን እንደከዚህ ቀደሙ ዳር ሆነው ከመመልከት በእውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር ወደ ሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ እንዲመጣ በንቃት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ፕ/ር መረራ አስገንዝበዋል፡፡ የኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክል ከሚለው ጽንፍ መውጣት ያስፈልጋል ያሉት ፕ/ር መረራ፤ አርአያ የሚሆኑን ሰዎች በስፋት ሊኖሩን ይገባል ብለዋል፡፡
ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፤ ጐንደር ድሮ ምሁራን በሃይማኖት፣ በስርአተ መንግስትና መሰል ጉዳዮች ላይ ሲከራከሩ እንደነበር ጠቅሰው፤ እንዲህ ያለው ነፃ ምሁራዊ ውይይት መዘጋጀቱ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል - ምሁራን የሚያሻግር ሃሳብ ማፍለቅ እንዳለባቸው በማስገንዘብ፡፡
ምሁራኑ የሰከኑና ነገሮችን በሚገባ የሚያገናዝቡ፣ በዚህም ለሌላው አርአያ መሆን የሚችሉ መሆን አለባቸው ብለዋል - ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፡፡
አያይዘውም “ምሁራኑ አንድን ህዝብ ከአንድ ህዝብ አቀራራቢ ድልድይ ነው መሆን ያለባቸው እንጂ ልዩነት አራጋቢ መሆን የለባቸውም፡፡ ባለፉት ዘመናት ሀገሪቱን ያከሰሩ እነዚህ አይነት አተያየቶች ናቸው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር አምባቸው መኮንንም ተመሳሳይ ሃሳቦችን አንፀባርቀዋል፡፡ ምሁራን የህዝብ መብራት መሆን አለባቸው ያሉት ዶ/ር አምባቸው፤ የሃሳብ ስፋትና ምልክት ምንጭ መሆን የሚችሉትም ምሁራን ናቸው ብለዋል። ይሄን ከግንዛቤ በማስገባት ምሁራን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ጐንደር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው ይህ የፖለቲካ ውይይት መድረክ ቀጣይነት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡

Read 8878 times