Saturday, 26 May 2012 12:40

የዊል አይ አም ዜማ ከጠፈር ይሰራጫል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ዊል አይ አም አሜሪካ ወደ ማርስ ከምታደርገው ጉዞ በተያያዘ  የማጀቢያ ሙዚቃ እንዲሰራ በናሳ ተጠየቀ፡፡ ሙዚቃው ከጠፈር በሚተላለፍ ሪፖርት አጃቢነት ወደ ምድር የሚሰራጭ ይሆናል፡፡ የብላክ አይድ ፒስ መሪ ድምፃዊ የሆነው ዊል አይ አም ከአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ጋር በቲቪ ፕሮግራም አስተዋዋቂነት መስራቱን የገለፀው የዴይሊ ሜል ዘገባ ልጆች ለጠፈር ሳይንስ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያነቃቃ ዜማም ለናሳ ሰርቶ  እንደነበር አመልክቷል፡፡ በተያያዘም የ37 ዓመቱ ዊል አይ አም ሰሞኑን በእንግሊዟ ከተማ ታውንተን የ2012 ለንደን ኦሎምፒክ ችቦን ይዞ ሮጧል፡፡ የኦሎምፒክ ችቦን ማንገብ ከግራሚ ሽልማት የላቀ ልዩ ክብር ይሰጣል ብሎ የተናገረው ዊል አይ አም ዘ ቮይስ በተባለ የቴሌቭዥን ሾው በዳኝነት እየሰራ በመላው ዩናይትድ ኪንግደም ተወዳጅ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

በሙሉ ስሙ ዊልያምስ ጀምስ አዳምስ በሚል የሚታወቀው ዊል አይ አም  በሙዚቃው ዝነኛ መሆን ሲጀምር በነበረው ዝቅተኛ የፋይናንስ አስተዳደር  የ400ሺ ዶላር  ቼክ በመኪናው ኪስ አስቀምጦ ይዞር እንደነበር ናው ከተባለ መፅሄት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ተናግሯል፡፡ ከድሆች መንደር አውጥቶ ለስኬት ያበቃው የሙዚቃ ሙያው ህይወቴን አትርፎልኛል ብሏል፡፡  ሙዚቃ ውስጥ ባልገባ ኖሮ ይሄኔ በወረበሎች ቡድን ውስጥ እየሰራሁ እሞት ነበር ያለው ዊል አይ አም ስፖርትና ኪነጥበብ ከህገወጥ ተግባራት ለመራቅ ሁነኛ መፍትሄ ናቸው በማለት ለናው መፅሄት ተናግሯል፡፡ በሂፕ ሆፕ፤ አር ኤንድ ቢ እና ኤልክተሮ ዳንስ የሙዚቃ ስልቶች ሲሰራ 10 ዓመታትን ያሳለፈው  ዊል አይ አም ብላክ አይድ ፒስ ከተባለው የሙዚቃ ቡድን ጋር 6 አልበሞችን ከመስራቱም በላይ ለብቻው ደግሞ 4 አልበሞችን በመስራት ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ በሎስ አንጀለስ የፋሽን ሙያና ንግድን የተማረው ዊል አይ አም በራሱ የልብስ አምራች ኩባንያም ቀንቶታል፡፡ በቅርብ ጊዜ በወጡ የካርቱን ፊልሞች በድምፅ በመተወንና በማጀቢያ ሙዚቃዎች ስራውም እንደተዋጣለት ይገለፃል፡፡ ከብላክ አይድ ፒስ የሙዚቃ ቡድን ጋር እና ከሌሎች ምርጥ ሙዚቀኞች ጋር በግጥም ደራሲነትና በፕሮዲውሰርነት ተመራጭ ሆኖ በመስራት ላይም ይገኛል፡፡

 

 

 

Read 907 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:43