በሙሉ ስሙ ዊልያምስ ጀምስ አዳምስ በሚል የሚታወቀው ዊል አይ አም በሙዚቃው ዝነኛ መሆን ሲጀምር በነበረው ዝቅተኛ የፋይናንስ አስተዳደር የ400ሺ ዶላር ቼክ በመኪናው ኪስ አስቀምጦ ይዞር እንደነበር ናው ከተባለ መፅሄት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ተናግሯል፡፡ ከድሆች መንደር አውጥቶ ለስኬት ያበቃው የሙዚቃ ሙያው ህይወቴን አትርፎልኛል ብሏል፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ባልገባ ኖሮ ይሄኔ በወረበሎች ቡድን ውስጥ እየሰራሁ እሞት ነበር ያለው ዊል አይ አም ስፖርትና ኪነጥበብ ከህገወጥ ተግባራት ለመራቅ ሁነኛ መፍትሄ ናቸው በማለት ለናው መፅሄት ተናግሯል፡፡ በሂፕ ሆፕ፤ አር ኤንድ ቢ እና ኤልክተሮ ዳንስ የሙዚቃ ስልቶች ሲሰራ 10 ዓመታትን ያሳለፈው ዊል አይ አም ብላክ አይድ ፒስ ከተባለው የሙዚቃ ቡድን ጋር 6 አልበሞችን ከመስራቱም በላይ ለብቻው ደግሞ 4 አልበሞችን በመስራት ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ በሎስ አንጀለስ የፋሽን ሙያና ንግድን የተማረው ዊል አይ አም በራሱ የልብስ አምራች ኩባንያም ቀንቶታል፡፡ በቅርብ ጊዜ በወጡ የካርቱን ፊልሞች በድምፅ በመተወንና በማጀቢያ ሙዚቃዎች ስራውም እንደተዋጣለት ይገለፃል፡፡ ከብላክ አይድ ፒስ የሙዚቃ ቡድን ጋር እና ከሌሎች ምርጥ ሙዚቀኞች ጋር በግጥም ደራሲነትና በፕሮዲውሰርነት ተመራጭ ሆኖ በመስራት ላይም ይገኛል፡፡