Saturday, 16 February 2019 13:49

100 የአሊያንስ ትራንስፖርት አውቶቢሶች ከስራ ታገዱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


                                    አውቶብሶቹን ያሳገዳቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው


        አንድ መቶ ያህል የአሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ንብረት የሆኑ የከተማ አውቶቡሶች ከስራ ታገዱ፡፡ አውቶቡሶቹ የታገዱት በባንክ የብድር አከፋፈል ስርዓት ላይ በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነም ታውቋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የአሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢና አባላት በጌትፋም ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አክሲዮን ማህበሩ በገባው ውል መሰረት ብድሩን በየወሩ ለመክፈል በአገሪቱ ላይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ አውቶቡሶቹ የሚያስፈልጋቸውን የመለዋወጫ እቃ ከውጭ ለማስመጣት በነበረ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ተያያዥ ችግሮች እንቅፋት በመሆናቸው በውል መሰረት መክፈል አለመቻላቸውንና በዚህም ምክንያት አበዳሪያቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቶዎቹ አውቶቡሶች ስምሪት ላይ እንዳይውል ከጥር 28 ጀምሮ እግድ ማውጣቱን ተናግረዋል፡፡
ከ2500 በላይ ባለ አክሲዮኖች እና ከ600 በላይ ሰራተኞች ያሉት አሊያንስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር፤ በ2005 ዓ.ም 25 ያህል አውቶቡሶችን በመግዛት የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለፁት የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር አዲል አብደላ፣ መንግሥት በ2008 ዓ.ም 500 ያህል የከተማ አውቶቡሶች በግል አንቀሳቃሾች ወደ አዲስ አበባ ገብተው በአዲስ አበባና በዙሪያው ላሉ ከተሞች አገልግሎት እንዲሰጡ የቀረጥ ነፃና የብድር አቅርቦት ባመቻቸበት ወቅት 300 ያህል አውቶቡሶች እንዲገዙ ከመንግስት ፈቃድ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበራቸው አቅም ከ100 አውቶቡሶች በላይ ማስመጣት ባለመቻሉ መቶዎቹን ብቻ በብድር ገዝተው ወደስራ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልፀው ባንኩ የ6 ወር የእፎይታ ጊዜ ቢሰጣቸውም አውቶቡሶቹ ወደ አገር ገብተው ከማለቃቸው በፊት የእፎይታ ጊዜው እንዳለቀና አውቶቡሶቹ በቅጡ ስራ ሳይጀምሩ ባንኩ ብድር ክፈሉ በማለቱ ከሌሎች በጀቶችም ከሌላም እያመጡ መክፈል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
“መቶዎቹ አውቶቡሶች የመንግስት ፕሮጀክቶችና ራሱ መንግስት ታሪፍ ያወጣላቸው እንጂ በንግድ ታሪፍ የሚሰሩ አይደሉም” ያሉት የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ አባላት በአሁን ጊዜ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ለባንኩ ደብዳቤ በመፃፍ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ በማቋቋምና ራሳቸውም ከባንኩ ጋር በመወያየት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Read 2004 times