Saturday, 16 February 2019 13:49

የህጻናት ወታደሮች ቁጥር በ5 አመታት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአለማችን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ወታደሮች እንደሚገኙ ተነግሯል
                       በየአመቱ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በተበከለ ምግብ ለሞት ይዳረጋሉ

          በአለማችን በለጋ ዕድሜያቸው ወደ ውትድርና የሚገቡ ህጻናት ወታደሮች ቁጥር ባለፉት አምስት አመታት ከእጥፍ በላይ መጨመሩንና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በ17 አገራት ብቻ ከ29 ሺህ በላይ ህጻናት ወደ ውትድርና መግባታቸውን አንድ ጥናት አስታውቋል፡፡
በአለማችን የተለያዩ አገራት በጦር መሳሪያ የታገዙ ግጭቶች መስፋፋታቸውን ተከትሎ ወደ ውትድርና የሚገቡ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ ያስታወቀው ቻይልድ ሶልጀርስ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም፣ በመላው አለም በውትድርና ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ቁጥር በመቶ ሺህዎች  ሊቆጠር እንደሚችል መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገው ተቋሙ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፤ በ2017 የፈረንጆች አመት በአለማችን 15 አገራት ውስጥ ብቻ 8 ሺህ ያህል ህጻናት ወደ ውትድርና እንዲገቡ የተደረጉ ሲሆን፣ በታጣቂ ቡድኖች ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ ልጃገረዶች ቁጥርም ባለፈው አመት ከነበረበት በአራት እጥፍ ያህል ጨምሯል፡፡
በተለያዩ አገራት የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖችና አማጽያን፣ ህጻናትን በመመልመል በተዋጊነት፣ በመረጃ አስተላላፊነት፣ በስለላ፣ በጉልበት ስራና በወሲብ ባርነት እንደሚያሰማሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በከፍተኛ ደረጃ የችግሩ ሰለባ የሆኑትም የመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ የደቡብ ሱዳን፣ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ህጻናት መሆናቸውንና በደቡብ ሱዳን ከ19 ሺህ በላይ ህጻናት በታጣቂ ቡድኖች ተመልምለው እያገለገሉ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአለማችን በየአመቱ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በተበከለ ምግብ ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉና ተጨማሪ 600 ሺህ ያህል ሰዎችም ለህመም እንደሚጋለጡ ተመድ አስታውቋል፡፡
በባክቴሪያ፣ በቫይረስ፣ በጥገኛ ህዋሳትና በኬሚካሎች የተበከሉ ምግቦች በአለማችን የተለያዩ አገራት በርካታ ሰዎችን ለሞትና ለከፋ የጤና ችግር እየዳረጉ እንደሚገኙ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅትና የጤና ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ ተጠቁሟል፡፡

Read 1274 times