Saturday, 09 February 2019 13:17

“እህ’ናት” ረጅም ልቦለድ

Written by  (ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ )
Rate this item
(4 votes)

  
           (የዘመናችን መራር እውነት!)
            
 
ርዕስ፡- እህ’ናት
ደራሲ፡- ደሳለኝ ስዩም
የገፅ ብዛት፡- 196
የመሸጫ ዋጋ፡- 61:00(ብር)
የህትመት ዘመን፡- 2010 ዓ.ም.
አታሚ፡- ተፈራ ማተሚያ ቤት
ዘውግ፡- ረጅም ልቦለድ

“ልቦለድ የህይወት ስዕል ነው” ይለናል፤ ፐርሲ ሉቦክ፡፡ በቃላት አማካኝነት በምናብ የሚታይ የሠው ልጅ መልክ ነው፡፡ በድርጊቶቹ ዘመን (ጊዜ)  ይሰፈራል፡፡ የሠው ልጅ ቦታ ዘርፈ ብዙ በሆኑ አተያዮች ይዳኛል፡፡ በጥቅል ስንመለከተው፣ ልቦለድ (በተለያየ ቅርፅ) ኑሮውንና ህይወቱን (እጣፈንታ) ማሳያ ብርቱ ጥበብ ነው፤ ለሰው፡፡ ረጅም ትረካ በአዲስ ቅርፅ (በፅሁፍ) ከተዋወቀ እነሆ አራት ክፍለ ዘመን አስቆጠረ፡፡ በሀገራችን ደግሞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አሀዱ እንዳለ ይነገርለታል። በርካታ ዘውጎችንም ተዋውቀናል፡፡
“እህ’ናት” ረጅም ልቦለድ በስነ-ፅሁፋችን በቅርፅ ደረጃ የራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍ እምነቴ ነው፡፡ ጉዟችን በደረቁ እንዳይሆን ለአእምሮ ማሟሻ፣ ለልብ ማረፊያ ከቀማመስን ወደ ዋናው ጉዳይ እንገስግስ፡፡
«ደሳለኝ ስዩም፤ ውልደቱ ጎዣም አቸፈር ነው፤ይስማላ ጊዮርጊስ! የቴያትር ጥበባት፣ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለማቀፍ ግንኙነት፣ ሶስዮሎጂና ፍልስፍና ተምሯል፡፡ በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ከአምደኝነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፤በተጨማሪም የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና የረቂቅ ድርሰቶች አርታኢ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ይኸ አራተኛ የፈጠራ መጽሐፉ መኾኑ ነው፡፡ «( ከሽፉን ገፅ የተወሰደ)
“እህ’ናት” (የኀፍረት ቁልፍ)  በሚል ርዕስ የቀረበው የረጅም ልቦለድ መጽሐፉ፤ በሦስት ዓብይ ክፍሎችና  በሀያ ስምንት ንዑስ ክፍሎች የተዋቀረ ነው፡፡ በተጨማሪም አስራ አራት የግርጌ ማስታወሻዎች ያካተተ ነው፡፡ ልቦለዱ በኢህአዴግ ዘመን በቅሎ፣ በኢህአዴግ ዘመን የሚዳፈን ህይወት የተሸከመ ነው፤ የዘመናችን ገመና እውነት የተገመደበት አስደናቂ ትረካ ነው፡፡ የአተራረኩ ስልትና የአደረጃጀቱ መንገድ ልብ አንጠልጣይ ነው፡፡ ታሪኩ ገና ከልጅነት (6 ዓመት) እድሜ ጀምሮ በተገፋ ህፃንና በተጎሳቆለ ቤተሰብ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን ህፃኑ «በረከት»፣ በብቸኝነት የሚጋፈጠውን የዘመናችንን እውነታዎች ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ እንደኔ እምነት፤ ህፃኑ በረከት ከልጅነት እስከ አፍላ ወጣትነት ዕድሜው ድረስ ለ 21 ዓመታት፣ በድምሩ 27 ዓመታትን ያለፈባቸው መንገዶች፣ በአጠቃላይ የሀገሪቱን ወጣቶች የሚወክል ይመስለኛል፡፡ በተለይ የተወለደበትን የጎዣም ማህበረሰብ አልፎም አማራውን ይወክላል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነንን ከታሪኩ እንመልከት፡- [መንግስት ጥሩ ደግሶላችኋል፤ እንኳንስ አማራ ሆነሽ? በየደረጃው ትጣሪ ትንገዋለያለሽ? ... አራተኛ ክፍል የወደቀ ግብርናውን ይገባል፤ ስምንተኛ የወደቀ ያው ግብርናውን! ተዚያም ቢዘል ውሃ ሻጭ ነው የሚሆነው፤ አስረኛ የወደቀ ጣውላ ፈቅፋቂነት ቢያገኝ ነው፡፡ ምንም እኮ ተስፋ የላችሁም...] ገፅ 130፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ዘወትር ከሠንደቅ ዓላማ ሰልፍ እየነጠሉ ለተወሰኑ ተማሪዎች የሚነግሯቸውን «ምክር አይሉት ግሳፄ»ን ነው የሚተርክልን፤ በረከት፡፡
በልቦለዱ ውስጥ በርካታ ማህበራዊ ጣጣዎች (መልኮች) ለማሳያነት ቀርበዋል፡፡ ከላይ እንዳየነው በትምህርት ስርዓቱ ላይ ከመነሻው ተቃውሞ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ ትውልዱን ለመበቀል (ተስፋ ለማስቆረጥ) ማለፊያ በሮችን ማጥበብ፣ የትምህርት ስርዓቱ ግብ እስኪመስል ድረስ ተጠቁሟል፤ በርዕሰ መምህሩ አማካኝነት፡፡ «በአማራ ክልል ብቻ የተተገበረው የስምንተኛ ክፍል አጠናቀቀ !» ለዚህ ማሳያ ይሆን? በህይወት ዘመናችን በተደጋጋሚ የታዘብናቸው ጉዳዮች ናቸውና፤ «ሀቅ ነው!» ፤ሳናመነታ እንድንቀበለው ያስገድደናል፡፡ ሌላው በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሰው ማህበራዊ ጣጣ ሙስና (ማጭበርበር) ነው፡፡ [...ታውቃለህ? ችግር ከልክ ሲያልፍ የማትፈልገውን ሁሉ ያስሞክርሃል፡፡ የትኋን ፋብሪካ ውስጥ መተኛት፣ የበሰበሰ ቲማቲም ቁርጥ በደረቅ ዳቦ መብላት፣ የበሰበሰ ሙዝ ከዳቦ ጋር አጨማልቆ መብላት አይሰለችም? ሰለቸኝ! ያኔ ነው ይሉኝታዬን የተውኩትና ህሊናዬን ያባረርኩት... አምስተኛ መንጃ ፈቃድና የሶስት አመት ልምድ ፎርጅድ ያሰራሁት...አየህ ከአበል ውጭ የሶስት ሺህ ብር ደሞዝተኛ ነኝ፡፡ ... ስላጭበረበርኩ መኖር ጀመርኩ.....] ገፅ 143፡፡
ይህን ያህል የህሊና ዝቅጠት ውስጥ የዘፈቀን ምን ይሆን? እንድትመልሱልኝ አይደለም። መልሱ እዚሁ ታሪኩ ውስጥ አለ፡፡ ይኸው፤ [«ተጫወት ጎረምሳው» አለኝ፡፡ አግራሞቴን ደብቄ ለወሬ ተሰናዳሁ፡፡ አየህ አብሬህ ስጠጣ ደስታ ይሰማኛል፤የኢትዮጵያ አዛውንትና ወጣት የሚጋራው የጋራ እሴት ቢኖር ተስፋ ቆራጭነትና ሱስ ነው... እርግጠኛ ነኝ አንተም ተስፋ ቢስ ነህ.. ልክ እንደኔ ....ቂቂቂቂቂ  ሰባ አመት አልሞላኝም ብለህ ነው? ሁላችሁንም አውቃችኋለሁ.....] ገፅ 191፡፡
አዛውንቱ ሦስቱንም መንግስታት አውቃቸዋለሁ ያሉ ይመስለኛል፡፡ ኑሯቸውን በብቸኝነት የሚገፉ፣ የኢህአፓ አባል የነበሩና ብልታቸውን የተሰለቡ ናቸው፡፡ ርዕያቸውን የተነጠቁና  ግፍ የተቀበሉ የዘመናችን ባይተዋር አዛውንት ናቸው፡፡ ያ ትውልድ፤ በዚህ ትውልድ ላይ ያደረሰውን ግፍ በምሬት ይገልፃሉ፡፡ ይህ ትውልድም ርዕዩ የተነጠቀ መሆኑን ይጠቁማሉ። «ሁላችሁንም አውቃችኋለሁ» በማለት አስረግጠው ይነግሩታል፤ ለበረከት፡፡ [ ...አርባ ዓመት ሙሉ ቂም ስንገነባ የኖርን ዜጎች ለናንተ ምን ልንሰጣችሁ እንችላለን...ከሲጋራና ከመጠጥ ውጪ?.... ሌባ ነህ? የግድ መሆን አለብህ ... ካልሰረቅህ አትኖርም... ( ፊት ለፊት የቆመውን ጅምር ህንፃ እያሳየኝ ) አየህ ስትሰርቅ ብቻ ነው መኖር የምትችለው...ስትሰርቅ ብቻ ሳይሆን ከሌቦች ጋር በምስጢር ስትሰራ... ያለበለዚያማ ቂቂቂቀ] ገፅ 192፡፡ የወቅቱን ተጨባጭ ሁነት ልብ በሚሰብር አገላለፅና በእልህ ይነግሩታል -- ለተራኪው፡፡
ልቦለዱ ትውፊታዊ ጉዳዮችንም ዳሷል። ለአብነት ያህል የዳኝነት ስርዓቱን የሚጠቁም ትረካ አለ፡፡ ገበሬዎች በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ምዕመን «ታቦት ሰረቀ» ያሉትን ሌባ ሲያስተዋውቁ፣ የህዝቡ ቁጣ የተገለፀባቸው መንገዶች «በኦሪት ዘመን «እንጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የሚፈፀም አይመስልም። ህዝቡ [...ብረት ምጣድ አግለን ቂጡን ነው እምንተኩሰው.... ገደል ውስጥ ከቶ በገለባ መለብለብ ነበር....እሳት ውስጥ ከተን እንሙቀው....]ገፅ 116፣ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ዘመናዊነትን አስፋፍቻለሁ፣ የፍትህ ስርዓት ዘርግቻለሁ ለሚለው የኢህአዴግ መንግስት ውጤቱ የታለ?  ያሰኛል፡፡ ምንም እንኳ ልቦለድ ቢሆንም የማህበረሰቡ ማህበራዊ ጣጣዎች፣ በቅጡ እንዳልተቃኙ የሚጠቁሙ በመሆናቸው ቅቡል ናቸው፡፡
ልቦለዱ «ማነው ምንትስ?» በፀጋዬ ገብረ መድን ግጥም ጀምሮ፣ ትውልዱን የሚሞግት ነው፡፡ ማነህ ምንትስ?...... የሰቆቃ ድምፁ ያይላል፡፡ ታሪኩ ልብ ይሰብራል፡፡ ሰው የመሆንን እጣ ከማህበራዊ ጉድ ጋር አስተሳስሯል፡፡
 ታሪኩ በ”በረከት” ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ዋናው ገፀ-ባህሪ፣ ዘላቂ የህይወት አጋር የሌለው ባይተዋር ነው፡፡ በተቃርኖ የቆሙ የህይወት ዘመን ተቀናቃኞች ስለሌሉት ሴራው ልል ነው፡፡ በታሪኩ ውስጥ ተራኪውም ፣የታሪኩ ፀኃፊም፣ የታሪኩ ባለቤትም እራሱ በረከት በመሆኑ ውስንነቶች አሉበት፡፡ በባህሪው እኔ ባይ ተራኪ ምልከታው ሙሉ አይሆንም። ልቦለዱ ውስጥ ለሚፈጠሩ ኢ-ሚዛናዊ ገለፃዎችም ሀላፊነት የሚወስደው ተራኪው ይሆናል፤የራሱ ስሜቶች ስለሚጎሉ፡፡
 ጭብጦቹ፤ ሙስና፣ ድህነት (ኢኮኖሚ) እና ስነ- ምግባር  ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ  ማጭበርበር ፣ስንፍና፣ ስግብግብነት፣ ፍትህ፣ የተዝረከረከ አሰራርና በመጥፎ ልማድ መተብተብ ተጠቃሽ ንዑስ ማህበራዊ ጭብጦች ናቸው፡፡  በአጠቃላይ «እህ›ናት» ረጅም ልቦለድ፣ የዘመናችን መራር እውነታዎች  ማንፀሪያ ነው፡፡ ለሰብዕና መላሸቅ «ተመስጌን» ማሳያ ሲሆን ለባይተዋርነት ደግሞ «በረከት» ልከኛ ነው፡፡ ለርህራሄ «የአዳም እናት» ሁነኛ ነች፡፡ መጽሐፉን ኤዞፕ መጻሕፍት መደብር ያከፋፍለዋል፡፡ መልካም ንባብ!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል
አድራሻው ፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1643 times