Tuesday, 12 February 2019 00:00

በአመቱ ኢንተርኔት ላይ የሚጠፋው ጊዜ 1.2 ቢሊዮን አመት ይደርሳል ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ፊሊፒንሳውያን በቀን ከ10 ሰዓት በላይ ኢንተርኔት ላይ ያጠፋሉ


    በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2019 በተለያዩ የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በድምሩ 1.2 ቢሊዮን አመት ያህል ጊዜ ኢንተርኔትን በመጠቀም ያጠፋሉ ተብሎ እንደሚገመት ሁትሲዩት የተባለው የጥናት ተቋም ያወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አመለከተ፡፡
ዘ ዲጂታል 2019 የሚል ርዕስ ያለውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በአለማቀፍ ደረጃ በኢንተርኔት የሚጠፋው ጊዜ በእጅጉ እየጨመረ ሲሆን ባለፈው የፈረንጆች አመት ዜጎቿ ረጅም ጊዜን በኢንተርኔት ላይ ያጠፉባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ፊሊፒንስ ናት ተብሏል፡፡
ፊሊፒንሳውያን ባለፈው አመት በየቀኑ በአማካይ 10 ሰዓት ከ2 ደቂቃ የሚሆን ጊዜ ኢንተርኔት በመጠቀም እንዳጠፉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በየቀኑ በአማካይ ዘጠኝ ሰዓት ከ29 ደቂቃ ኢንተርኔት ላይ ያጠፉት ብራዚላውያን የሁለተኛነት ደረጃን ይዘዋል ብሏል፡፡
በየቀኑ በአማካይ ለዘጠኝ ሰዓት ከ11 ደቂቃ ኢንተርኔት ላይ ተጥደው የሚውሉ ዜጎችን ያፈራቺዋ ታይላንድ በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ኮሎምቢያውያን ለዘጠኝ ሰዓታት፣ ኢንዶኔዢያውያን ደግሞ ለስምንት ሰዓታት ከ36 ደቂቃዎች እንደቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ሪፖርቱ ካካተታቸው የአለማችን አገራት መካከል በ2018 ያለፈው የፈረንጆች አመት ዜጎቿ አነስተኛ ጊዜን በኢንተርኔት ላይ ያጠፉባት ቀዳሚዋ አገር ጃፓን ስትሆን፣ ጃፓናውያን በአመቱ በአንድ ቀን ውስጥ ኢንተርኔት ላይ ያጠፉት አማካይ ጊዜ ሶስት ሰዓት ከ45 ደቂቃ ብቻ ነው ተብሏል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ በየቀኑ በኢንተርኔት የሚጠፋው አማካይ ጊዜ ስድስት ሰዓት ከ42 ደቂቃ ያህል እንደሆነ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረገጾች እንደሆነም አመልክቷል። ጃፓናውያን በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የሚያጠፉት ጊዜም በአለማችን አነስተኛው ነው ተብሏል፡፡

Read 2049 times