Wednesday, 13 February 2019 00:00

የላይቤሪያው መሪ ዜጎች በየቀኑ ለአገራቸው እንዲጸልዩ ጠየቁ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  በወር አንድ ቀን ሙሉ ሌሊት ለመንግስታቸው እንዲጸልዩም ተነግሯቸዋል


     የቀድሞው የአለማችን ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋችና የወቅቱ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ አገሪቱ ከገባችበት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ቀውስ እንድታገግም በቀን ለ2 ሰዓታት ያህል ተግታችሁ ጸልዩ ሲሉ ለዜጎቻቸው ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ላይቤሪያውያን ምዕመናን ለኢኮኖሚው ቀውስ በየቀኑ ከሚያደርጉት የሁለት ሰዓታት ጸሎት በተጨማሪ በየወሩ የመጨረሻው አርብ ለአገራቸው መንግስትና ህዝብ ሙሉ ለሌት ተግተው እንዲጸልዩ በፕሬዚዳንት ዊሃ በአማካሪያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ በጎ አስተያየታቸውን የሚሰጡ በርካታ ላይቤሪያውያን የመኖራቸውን ያህል ብዛት ያላቸው ሌሎች ግን፣ ገዢዎቻችን እርኩሳን ስለሆኑ ጸሎታችን ሰሚ አያገኝም በማለት የመሪያቸውን የጸሎት አማራጭ እንደተቹት ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ታዋቂ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ስልክ በመደወል አስተያየቱን የሰጠ አንድ ላይቤሪያዊ በበኩሉ በየቤተክርስቲያኑና መስጊዱ ደጃፍ ተደፍተን ለመጪዎቹ 100 አመታት ብንጸልይ እንኳን፣ ጠብ የሚልልን ነገር አይኖርም ማለቱም ተነግሯል፡፡
የጆርጅ ዊሃን የጸሎት ጥሪ ያልተቀበሉት ሄንሪ ፒ ኮስታ የተባሉት ታዋቂ የአገሪቱ የሬዲዮ ጋዜጠኛም፣ አሜሪካ፣ ቻይናና ጃፓንን የመሳሰሉ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገራት ወደ እድገት ማማ የወጡት በጸሎት ሳይሆን ጠንክረው በመስራትና ብዙ መስዋዕትነት በመክፈል ነው ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 4395 times