Saturday, 09 February 2019 12:47

ሃዋይ 100 አመት ያልሞላው ሲጋራ እንዳያጨስ ልትከለከል ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአሜሪካዋ የሃዋይ ግዛት ሲጋራ ማጨስ የሚፈቀድበትን ዝቅተኛ እድሜ በየአመቱ እያሳደገች በመሄድ በ2024 የፈረንጆች አመት 100 አመት ለማድረስ ማቀዷንና ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ህግ ለግዛቲቱ ምክር ቤት መቅረቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በዲሞክራቱ ሪቻርድ ክሬጋን ለግዛቲቱ ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ህግ ሲጋራ ማጨስ የሚፈቀድበትን ዝቅተኛ ዕድሜ በየአመቱ ከፍ በማድረግ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ 100 አመት ለማድረስ ያለመ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ ህግ ሲጋራ ማጨስ የሚፈቀድበትን ዝቅተኛ እድሜ በመጪው አመት ወደ 30 አመት ከፍ ለማድረግ ማቀዱን የጠቆመው ዘገባው፣ በ2021 ወደ 40 አመት፣ በ2023 ወደ 60 አመት በ2024 ደግሞ ወደ 100 አመት ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ከአምስት አመታት በኋላ በሃዋይ ግዛት ውስጥ ከ100 አመት ዕድሜ በታች ያሉ ሰዎች ሲጋራ ሲያጨሱ ከተገኙ እንደሚቀጡ የሚደነግገው ይህ ለየት ያለ ረቂቅ ህግ በተለይ ከትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ከፍተና ተቃውሞ ይገጥመዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
አዲሱ ህግ የሲጋራ አጫሾች የእድሜ ገደብ ህግ ኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎችን የሚያጨሱትንና የትምባሆ ቅጠል የሚያኝኩ ሱሰኞችን አይመለከትም መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ሃዋይ በ2017 አመት መጀመሪያ ላይ ሲጋራ ማጨስ የሚቻልበትን ዝቅተኛ እድሜ ወደ 21 አመት ከፍ ማድረጓን አስታውሷል፡፡
ሃዋይ የሲጋራ አጫሾችን የእድሜ ገደብ ወደ 21 አመት ከፍ በማድረግ በአሜሪካ የመጀመሪያዋ ግዛት ናት ያለው ዘገባው፣ በሌሎቹ የአሜሪካ ግዛቶች ሲጋራ ማጨስ የሚፈቀድበት እድሜ 18 ወይም 19 አመት እንደሆነም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2977 times