Saturday, 09 February 2019 12:32

ቃለ ምልልስ ከአቶ በረከት ስምዖን ባለቤት ጋር

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(9 votes)

  “በህዝብ ጥቅም ላይ አይደራደርም፤ በሙስና ላይ ያለው አቋም ይታወቃል”

     በ13 ዓመት የታዳጊነት ዕድሜ ላይ ነበር ትምህርት አቋርጠው ወደ ትግል የገቡት - ወ/ሮ አሰፋሽ ፈንቴ፡፡ በ1977 ዓ.ም ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር እዚያው በረሃ ትዳር መስርተዋል፡፡ አገሪቱ በአመጽ ስትታመስ በነበረችባቸው ያለፉት ዓመታት፣ ከሥልጣናቸው በፈቃዳቸው የለቀቁት አቶ በረከት ስምኦን፤ የጡረታ ጊዜያቸው የመጀመርያ ሥራ ያደረጉት “ትንሳኤ ዘ ኢትዮጵያ” የተሰኘውን ሁለተኛ መጽሐፋቸውን
ማሳተም ነበር፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ግን (ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ) ድርጅታቸው ብአዴን፣ ከ”ጥረት” የቦርድ አባልነታቸው አገዳቸው፡፡
በመታገድ ብቻ ግን አላበቃም፡፡ ለውጡን በሚመራው የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት ላይ የመረረ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁት የቀድሞው ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣን አቶ በረከት ስምኦን፤ በቅርቡ ደግሞ በሙስና ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ጋዜጠኛ ሠላም ገረመው፣ ከባለቤታቸው ወ/ሮ አሲ ፈንቴ ጋር በአቶ በረከት እስርና ተያያዥ ጎዳዮች ዙርያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ አነሆ


     አቶ በረከት ስምዖን የተያዙት እንዴት ነበር?
አቶ በረከት የተያዘው ከቤቱ ነው፡፡ እኔ ልጄን ት/ቤት ለመውሰድ ከእንቅልፌ ተነስቼአለሁ። እሱ ተኝቶ ነበር፡፡ ጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ገደማ ይሆናል። “አሴ፤ ፖሊሶች ሊወስዱኝ መጡ” አለኝ። ሁሌም ስለሚቀልድ እውነት አልመሠለኝም ነበር። “የእውነትህን ነው?” ብዬ ስጠይቀው፣ ዘና ብሎ ነበር የሚያወራው። በመስኮት ብቅ ብዬ ለማየት ስሞክር፣ ገና አልነጋም ነበር፡፡ ግቢ ውስጥ ዛፍ አለ፤ ከዛፉ ስር ሬንጀር የፌደራል ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ነበሩ፡፡ እውነት መሆኑን ሳይ በጣም ደነገጥኩ። ነገር ግን ብደነግጥም የተሰማኝ ስሜት ለቅሶ ወይም አንገት መድፋት አልነበረም፡፡ ይህንን ንፁህ ሰው እንዲህ አሳዶ መያዝ ምን ማለት ነው? የሚለው ነገር፣ በውስጤ ከፍተኛ የሆነ እልህና ቆራጥነት፣ ከጎኑ የመቆም ነገር ነው የተሰማኝ፡፡ ይሄንን ስንነጋገር ትንሿ ልጄ ሰምታ ነበር፤ 13 አመቷ ነው፡፡ “የእውነት ነው ይዘውህ የሚሄዱት?” ብላ አለቀሰች፤ “አዎ ይዘውኝ ሊሄዱ ነው” አላት “መቼ ትመጣለህ?” አለችው፤ ልክ እሱ እንደሚወስን አድርጋ፡፡  “የት ነው የሚወስዱት?” የሚል ጥያቄ ቀጠለ። እኔም ላስረዳት ሞከርኩ፡፡ “በርቺ አባትሽ ንፁህ ሰው ነው፤ ምንም አይሆንም” አልኳት። ምክንያቱም የፈተና ወቅት ነበር፤ ደግነቱ ልጄ ብዙም አልተቸገረችም፤ ወዲያው “እበረታለሁ!” አለችኝ፡፡ ከዛም ልብሱን ማዘገጃጀት ማገዝ ጀመርኩ፡፡ በዚህ መሀል እሱ ወጣ፡፡ ፖሊሶቹ ወረቀት ይዘው ነበር፤ ሲያነበው የአማራ ክልል ነው ይላል፤ የአማራ ክልል ከዚህ አሳጅቦ ይወስደኛል ብሎ አልጠበቀም፤ ምናልባት በፌደራል መንግስት ልጠራ እችል ይሆናል ብሎ ገምቶ ነበር፡፡ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሊገባ ሲል ግቢ በር ላይ ነበር ወረቀቱን የሰጡት። ፖሊሶቹ የዚህን ጊዜ እጁን ለመያዝ ሞከሩ፤ አትይዙኝም አለ፡፡ በካቴና ሊያስሩትም ሞከሩ፤ አትወስዱኝም አለ፡፡ ምክንያቱም “የክልሉ መንግስት ፍርዱን በሚዲያ ጨርሶታል፤ ሙሰኞች ብሎ አውጆታል፤ ስለዚህ ይህንን አልቀበልም፤ ወደ አማራ ክልል አልሄድም፤ የፌደራል መንግስት ስሜን አላጠፋም፤ ስለዚህ የፌደራል መንግስት ይክሰሰኝ እንጂ አማራ ክልል ባህርዳር ተይዤ አልሄድም” በማለት ከሁለት ሰአት በላይ ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ፣ ፖሊሶቹም እየተጨመሩ ሄዱ፡፡ ከእሱም ጋር እንመካከር ነበር፡፡ “ወደ ክልል ይዞ መሄድ ምን ያህል ህጋዊ ነው? እሱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበረው፣ ከፍተኛ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ ነበር፤ እንዴት ከፌደራል አልፎ ወደ ክልል ይሄዳል?” በማለት ሰዎች ለማማከር ለመደወል ሞክሬ ነበር፤ ምላሽ የሚሰጥ አልነበረም፡፡
ማንን ነበር ለማማከር የሞከሩት? አሁን ስልጣን ላይ ያሉትን ነው?
እነሱን ማወቅ አልችልም፡፡ የቀድሞ ጓደኞቹ፤ አሁን ያሉትን ኃላፊዎች ጠይቀው መልስ እንዲሰጡኝ ነበር፡፡ ይሄ ማለት እምቢተኝነት አይደለም፡፡ ከዛ በኋላ መረጋጋቱ ሲመጣ ፖሊሶቹ የታዘዙ ናቸው፤ እነሱ የፈጠሩት ነገር አይደለም፤ ስለዚህ ትሄዳለህ አትሄድም የሚለው ውጥረት ሲበዛ፣ “እንደውም ስሜን ማጥራት አለብኝ፤ የትም ቦታ ይሁን የትም ፍትህ እንዲኖር ብቻ ነው እምፈልገው፤ ሔጄ ስሜን አፀዳለሁ፤ እራሴን ነፃ አወጣለሁ፤ እንደውም ያጣሁትን እራስን የመግለጽ መድረክ አገኛለሁ። ከዚህም በላይ ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ” በማለት ፍቃደኛ ሆኖ ሄዷል፡፡ አቶ ታደሰ ተይዞ ስለነበር፣ አብረው ነው በአውሮፕላን ወደ ባህርዳር  የወሰዷቸው፡፡
አቶ በረከት የጤና ችግር እንዳለባቸው ይነገራል----ከዚህ አንጻር የማረሚያ ቤት ቆይታቸው እንዴት ነው?
በጤናው በኩል ከፍተኛ የልብ ህመምና ኮሌስትሮል አለበት፡፡ በአብዛኛው በየስድስት ወሩ ውጪ ሀገር እየተመላለሰ ህክምና እንደሚወስድ  ይታወቃል፡፡ የህይወት ዘመን መድሃኒቶችን ይወስዳል፤ በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ ወደ እስር የገባው፡፡ መድሃኒቶቹን ሄዶ ተመርምሮ ነው፣ በየስድስት ወሩ ይዞ የሚመጣው፡፡ መድሀኒቱ ሊጨምርበትም ሊቀንስም ይችላል፤ ይሄ የሚሆነው ተመርምሮ ነው፡፡ ከሁለት ወር በፊትም በደቡብ አፍሪካ ታክሞ፣ ለ4 ጊዜ የሚሆነው በቂ መድሀኒት ይዞ መጥቷል፡፡ እስካሁን የደረሰበት የጤና ችግር የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ህመሙ ቢነሳበት ስድስት ወርም ላይጠብቅ ይችላል፡፡ በመሀከልም ሊነሳበት ይችላል፤ ቢነሳበት ምን ይሆናል የሚለውን የሚመልሰው፣ የክልሉ መንግስት ነው፡፡ ምን ያዘጋጀው ነገር አለ? የሚለውን መመለስ የሚችለው ክልሉ ብቻ ነው፤ እስካሁን ግን ያጋጠመው የጤና ችግር የለም፡፡
ከጤናቸው ውጪ የደህንነታቸው ጉዳይ ያሳስብዎታል?
መጀመሪያ ከዚህ ሲሄድ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ በሚባለው ነበር የታሰረው፡፡ እዛ ሲደርሱ የሆኑ ቡድኖች ተሰባስበው ሌባ፣ ወንጀለኛ፣ ነብሰ ገዳይ ----- ብለው ስም እየጠሩ በስድብ ነበር የተቀበሏቸው። በሃይል ለመውሰድም ያሰቡ ይመስል ነበር፡፡ “ተጠርጣሪ ነው” ሲባሉ ነው የሄዱት፡፡  እስር ቤቱ መሀል ከተማ ላይ ነው ያለው፡፡ የፀጥታው ሁኔታ ማንም ሰው የሚያውቀው ነው፤ አስተማማኝ አይደለም፤ በየቀኑ ይተኮሳል፤ ሰዎች ይሞታሉ፤ የህግ የበላይነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ይሄንን የሚያስተዳድር አካልም ጠንካራ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ ለሱ ህይወት የሚያሰጋው ነበር፡፡ ወደ ፍ/ቤት ሄደው የ14 ቀን ቀጠሮ ከተሰጣቸው በኋላ ግን ወደ ወህኒ ቤት ነው የወሰዷቸው፡፡ ከባህርዳር ከተማ ወጣ ያለ ሲሆን እስካሁን ሠላማዊ ነው። ከከተማ ወጣ ያለም ስለሆነ ለመሠባሰብ እድል የሰጠ አይደለም፡፡ እንደውም ለአቶ ታደሰና ለአቶ በረከት ለብቻቸው አንድ ክፍል ነው የሰጧቸው፤ የተለየ ጥበቃም እየተደረገላቸው ነው ያሉት። በዚህ አጋጣሚ ጠባቂዎቹ፣ ከፍተኛ እንክብካቤ እያደረጉላቸው ስለሆነ፣ በእነሱ ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
ከ25 ዓመት በላይ በሥልጣን ላይ የቆዩትን  አቶ በረከትን፣ ህዝብ ይወዳቸዋል ወይም ይወዳቸው ነበር ብለው ያምናሉ?
የበረከት አስተዋጽኦ በተለያዩ ሰዎች የተለያየ እይታ ይኖረዋል፡፡ ሁሉም ሰው ይወደዋል፤ ሁሉም ሰው ይጠለዋል የምትይው አይደለም፤ የሚያደንቁት በስራው ያደንቁታል፡፡ አንድ የመንግስት ኃላፊ ሁሉንም ማስደሰት አይችልም። ሁሉንም የሚጠቅም ሥራ ሊሠራ አይችልም። ሲሰራ የነበረው ብዙኃኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እስከጠቀመ ድረስ እዛ ላይ ነው እድሜውን የጨረሰው፡፡ ከ19 አመቱ ጀምሮ ለ42 አመታት ያህል ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ የነበረ ሰው ነው፤ ትልቅ አስተዋጽኦና መስዋዕትነት ከፍሏል። ብዙ ጊዜ ከብዙኃኑ ህዝብ ጥቂቶች ሊጐዱ ይችላሉ። የሚጠቅመውን ህዝብ ወክሎ ነው ሲሰራ የነበረው፤ በግሉ ምንም አይነት ጥቅም ሳያገኝ ማለት ነው፡፡ እንደውም ቤተሰቡንና እራሱን አደጋ ላይ በሚጥሉ ነገሮች ላይ ግንባር ቀደም ነበር፡፡ ይሄን ማድረጉ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው ነው የመጣው። ጥቅማቸው የተነካባቸው ደግሞ ደመኛ ጠላቶቹ ሆነው፣ ስሙን ያጠፋሉ። እሱ ደግሞ በእንደዚህ አይነት ነገሮች ላይ ደንዳና ነው፡፡ አብዛኞቹ በሶሻል ሚዲያ ላይ የሚሰጡ የተለያዩ አስተያየቶች፣ የዋህ የሆነውን ህብረተሰብ ጥላቻ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ናቸው፡፡  
መቼም ለመንግስት የሚያቀርቡት ጥያቄ ወይም ቅሬታ ወይም አቤቱታ አሊያም ወቀሳ አይጠፋም----?  
መንግስት ከሁሉም በፊት ይሄ የተደረገው ድርጊት አግባብ ነው ወይ? የሚለውን ምላሽ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ የፌደራል መንግስትን ማለት ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ያንን ድርጊት ፈጽሟል፡፡ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፤ የተሠራው ስራ ግፍ እንጂ ፍፁም ትክክለኛነት የለውም፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ የፌደራል መንግስት ምን አቋም አለው? የሚለውን ማወቅ እፈልጋለሁ። በመጀመሪያ በተጠረጠረበት ክስ እጁ አለበት ወይ? ቢኖርበትስ በምን ህጋዊ መስፈርት ነው የሚለውን ማወቅ እሻለሁ። እጁ ካለበትም በህግ አደባባይ በትክክለኛ ፍትህ፣ ፍርድ እንዲያገኝ ነው የምፈልገው። ከሳሾቹ ባቀረቡት ክስ መሠረት እንኳን ስናየው፣ ሙስና ሊያስብል የሚችል ምንም አይነት ነገር የለውም። እንደውም የአስተዳደር ችግርን የሚያመለክት ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ እሱም ሆነ አቶ ታደሰ፣ ከእስር በዋስም ቢሆን ወጥተው እንዲከራከሩ ነው መደረግ ያለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ ደግሞ በተለይ በረከት ከፍተኛ የፌደራል ባለስልጣን የነበረ ከመሆኑ አንጻር ጉዳያቸው አዲስ አበባ ውስጥ በፌደራል መንግስት የሚታይበት ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም በኢኮኖሚ ደካማ ነን፤ እዚያ ድረስ ተመላልሶ ለመጠየቅ እንቸገራለን፡፡ ባለቤቴ ለመንግስት ሲሰራ እንጂ የግል ጥቅሙን ሲያግበሰብስ አይደለም የኖረው። ከዚህ አንጻር መንግስት ይሄንን  እንዲያደርግልን እንጠይቃለን፡፡
“ክሱ ሙስና የሚባል አይደለም” ለማለት ያበቃዎት ምንድን ነው?
መጀመሪያ በረከት የተከሰሰበት ነገር ሙስና ነው አይደለም ከማለታችን በፊት በረከት በሙስና ላይ ያለው አቋም ምንድነው የሚለውን ማወቅ እንችላለን፡፡ ሙስናን በመጠየፍ የሚያደርገው ትግል ከልክ በላይ ይሄዳል ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ በረከትን ከሙስና ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለውም፤  ከህብረተሰቡም የተደበቀ አይደለም። ይታወቃል፡፡ በሙስና ላይ ትግል ሲያደርግ መኖሩን አብረውት ይሠሩ የነበሩት የድርጅት አባላትና አመራሮች ጭምር ያውቃሉ። መጽሐፉንም ማየት ይቻላል፡፡ “ትንሳኤ ዘ-ኢትዮጵያ” ላይ ያለ ምንም ምህረት ግለሰቦችን እየጠራ፣ ተቋሟትን እየጠቀሰ የሚያውቀውን መረጃ ሁሉ አውጥቷል፡፡ ይሄ ደግሞ በእሱ ላይ ሌሎች እንዲያቄሙበት፣ በጠላትነት እንዲነሱበት ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡ ቤተሰቡ ላይ ሳይቀር ችግር ለሚያስከትሉ ነገሮች ጭምር ምንም አይነት ርህራሄ ሳያደርግ የታገለ ሰው ነው፡፡ “በረከት ሙስናን ይፀየፋል” የሚለው በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ውስጥ ይታወቃል፡፡
እንግዲህ የተከሰሰበትን ጉዳይ በተመለከተ፣ በረከት ረዘም ላለ ጊዜ፣ የጥረት ቦርድ ሊቀመንበር ሆኖ ሠርቷል፡፡ በዚህ ሂደትም ጥረት ከሦስት ወደ 20 በላይ ተቋም እንዲያድግ አድርጓል፡፡ ተቋሙ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብቶችን አፍርቷል፡፡ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙት ድርጅቶች ቀዳሚ እንዲሆን ያበቃው፣ ባደረገው ጥረትና ትግል ነው፡፡ ይሄንን ሲያደርግ ግን የአሠራር ድክመቶች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ ይሄ ሰው የቢዝነስ ማኔጀር አይደለም፤ አላጠናም፣ እየወደቀ እየተነሳ፣ ከልምድ፣ በተለያየ መንገድ እሱም ሆነ አቶ ታደሰ፣ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ፣ የክልሉ መንግስትም የክልሉ ኃላፊዎችም፣ እነሱ እንዲሠሩ ከ20  አመት በላይ እድል ሰጥቷቸው፣ አብረው ተስማምተው እየወሰኑ የቆዩበት ጉዳይ ነው፡፡
ይሄ የሙስና ጉዳይ የመጣው ከለውጡ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ሙስና ለማስመሰል በማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ቅስቀሳ ተደረገ፡፡ ቅድም እንዳልኩት የሚጠሉት አካላት አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ወደ ታች እንድታሽቆለቁል፣ ኢትዮጵያ መኖር የለባትም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ዘመቻ አድርገውበታል፤ ይሄ እንደ ቀላል ሊታይ አይገባም። በረከትን የሚያውቁት ሰዎች እስኪጠራጠሩ፣ መልካም ስሙን እስኪያጐድፍ ድረስ፣ በረከት በሙስና አይታወቅም ሲል የነበረ ሁሉ፣ በደቦ “እሱን ያልተናገረ የማሪያም ጠላት” እስኪመስል ድረስ ስሙ  በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመረዝ ተደርጓል፡፡
የክልሉ መሪዎች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የደቦን ፍርድ እየተከተሉ የሚሄዱ ናቸው። ይሄ ምን ያደርግላቸዋል? ይሄ ዝናቸውን የሚገነባላቸው፣ ምርጫ ካርዳቸውን የሚያበዛላቸው፣ የስልጣን ጊዜያቸውን የሚያራዝምላቸው አድርገው የወሰዱት ነው የሚመስለኝ፡፡ ስለዚህ ያለው ለውጥ የበፊት አመራሮችን ወደ ታች ወደታች የሚያደርግ ሁኔታዎች ሲመጡ ድጋፍ ያስገኝልናል፡፡ በማለት እነሱ ላይ እንደዚህ አይነት ሃሳብ ቀረበ፡፡ ምንም ይሁን ግን የጥረት ድርጅታዊ ስብሰባ አድርጐ በነበረው ውይይት በማስረጃ አቶ በረከትን ጨምሮ አቶ ታደሰም ሆነ ሌሎቹ በጥረት ጉዳይ ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎችን በሙስና የሚያስጠይቃቸው ነገር የለም በማለት ወስኗል።
በረከት በጡረታ ከወጣ በኋላ የሚፈልገው የፖለቲካ ተሳታፊ መሆን አልነበረም፤ በመረጠው መንገድ ዜጋን ማገልገል ነበር፡፡ ዜጋን ለማገልገል መሪ መሆን አይጠይቅም ይል ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሰቆጣ አካባቢ ያለውን ተፈጥሯዊ ግኝት በመጠቀም ለመስራት ያቅድ ነበር፡፡ ምክንያቱም በትግሉ ጊዜ ከፍተኛ የጦርነት ታጣቂ ነበር፡፡ ከ10 ጊዜ በላይ በአውሮፕላን የተደበደበ ህዝብ ነው፡፡ ለዚህ ህዝብ ትግሉ የተጀመረባቸው አካባቢዎችን አይቼ፣ እነሱን በሚያስፈልጋቸው ነገሮች አገለግላለሁ ብሎ በሄደ ጊዜ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደ ሽፍታ ተደርጐ፣ ፎቶ ተነስቶ መለቀቅ ጀመረ፤ ላሊበላ ገባ ተባለ። ብዙ ሰዎች መጡ፡፡ ለእነዚህ ወሬዎች ምላሽ አልሠጠም፤ ከዚያ በኋላ የደብረማርቆሱ ጉዳይ መጣ። ይሄንንም ዝም ብሎ ነው ያለፈው። ሀቅ ስለሌለው አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው በጮኸ ቁጥር፣ የወረደ ነገር ባወራ ቁጥር ለዛ መልስ መስጠት አይመጥነኝም በማለት ነው። በወቅቱ ቦታው ላይም አልነበረም፡፡ አዲስ አበባ ነበር፡፡ እንደውም ደውለው “የት ነህ?” ሲሉት “ደብረማርቆስ” ይል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ዝም ማለቱ ሲበዛባቸው፣ የአመራሮች ስብሰባ ባህርዳር ላይ ነበር፡፡ ሁለቱንም ሲጠሯቸው፣ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ በምን ላይ ይገኛል? የመንቀሳቀስ መብታችን ተረግጧል? ምን ዋስትና አለን? ብለው ጠየቁ፡፡ ምንም ዋስትና የለም ተባሉ፡፡ ሁለቱም በስብሰባው ላይ አልተገኙም፡፡ ያኔ የስብሰባው ውጤት ተብሎ፣ በሰበር ዜና ተለቀቀ፡፡ ስብሰባው ላይ ባልተገኙበት፣ ሊከራከሩ በማይችሉበት ሁኔታ ሙስና የለባቸውም ተባለ፡፡ አንድ ጊዜ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ፣ ለምን ድጋሚ ሊነሳ ቻለ?    
አሁን ልጆችዎ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት?
ሦስት ልጆች ነው ያሉን፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን ከኢትዮጵያ ውጪ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። በደብረማርቆስ  በነበረው ሁኔታ አቋርጦ ነው የመጣው፡፡ እሱን ማውራት ይከብደኛል። ትንሿ ልጃችን የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ በእስሩ ሁኔታ በጣም አዝነዋል፡፡ በእሱ ላይ በሚደረገውን ዘመቻ እሱ ብቻ አይደለም፤ እኛም ነበር የተጐዳነው፡፡ ልጆቻችን ከዚህ በፊት የነበረውን ዘመቻ፣ በተለያየ መንገድ ይሰሙት ነበር፡፡ አሁን ግን በእስር ላይ መሆኑን ማየትና መቋቋም አይደለም ለእነሱ፣ ለእኔም ይከብዳል። እንደ ሀቀኛ ተምሳሌት፣ እንደ ህዝብ ወዳድ የሚያዩትና የሚኮሩበት አባታቸውን፤ ሲታሰር በጣም ተሰምቷቸዋል፡፡
ከአቶ በረከት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቃችሁት እንዴትና የት ነበር?
ከኮረም ስመለስ ሌሎች ታጋዮች ከእናቴ ጋር ይተዋወቁ ነበር፤ እናቴ ለታጋዮች ምግብ በመስጠት ትሳተፍ ነበር፡፡ ስመጣ በረከትን አገኘሁት፤ በወቅቱ የተማረከ የደርግ ወታደር ልብስ ነበር የሚለብሰው። ስለዚህ የደርግ ወታደር መስሎኝ ነበር፡፡ የደርግ ወታደሮች ብዙ መጥፎ ነገሮችን ያደርጉ ስለነበር በጣም ጠላሁት። ነገር ግን እየተቀራረብን ስንመጣ በጣም ተዋደድን፤ ልብሱ የደርግ ወታደር ይሁን እንጂ ውስጡ በጣም ተጫዋች ነበር፤ እየተዋደድን እየተፋቀርን መጣን፡፡ ከእኔ በፊት እህቶቼና ወንድሞቼ በርሃ ወጥተው ነበር። ደርግ መልሶ ሰቆጣን ለመያዝ ሲመጣ፣ የእኛ ድርጅት ኢህዴን ነበር የሚባለው፤ ወደ ኋላ የማፈግፈግ ሁኔታ ስለነበር ሰቆጣን የመልቀቅ ውሳኔ ተወሰነ። በወቅቱ እናቴም ኢህዴንን ታግዝ ስለነበር አብራን እንድትሄድ ተደረገ፤ ምክንያቱም ደርግ ተመልሶ ከመጣ ቤተሰቡ ላይ አደጋ ሊያደርስ ይችላል ተብሎ እኔ፣ ታናናሾቼና እናቴ ወጣን - ወደ ትግል፡፡ ታናናሾቼ ህፃናት ማቆያ ውስጥ ገቡ፡፡ እዛው ት/ቤት አለው፤ ቦታው አርማጮ ይባላል፡፡ ከትግል በፊት የጀመርነው ፍቅር አሁንም እንደቀጠለ ነው። በ1977 ዓ.ም እዛው ትግል ላይ ሆነን ጋብቻ ፈፀምን፤ የመጀመሪያ ልጄንም ትግል ላይ ሆኜ ነው የወለድኩት፡፡ ብዙ ችግሮች ተጋፍጠናል፡፡ የምግብ እጥረት ነበር፡፡ ለህፃናት የሚያስፈልጉ ነገሮች በሌሉበት ነው የወለድኩት፤ ብቻ ብዙ ፈተና ነበር፡፡
ለመሆኑ አቶ በረከት ምን አይነት ባል  ናቸው?
በረከት፤ በውጪ ለሚያየው ሰውና ውስጥ ያለው ነገር የተለያየ ነው፤ በጣም ተጫዋች ነው፡፡ ቤተሰቡን ህይወት እንዲዘራ የሚያደርግ ነው፤ ህፃናት በጣም ይወዳል፤ የእህቶቹ ልጆች ከወላጆቻቸው በላይ በረከትን ነው የሚወዱት፤ ወደ እሱ ነው የሚመጡት። ለቤቱ ትልቅ ፍቅር አለው፡፡ ለስራ ከወጣ ልጆቹን ደጋግሞ ነው የሚደውልላቸው። ለቤተሰቡ ልዩ ፍቅር አለው። ኢህአዴግ ውስጥ በተከሰተው ብልሽት፣ ጭቅጭቁ እየበረታ ሲመጣ እንኳን፣ “ቤቴ ስገባ ነው ሰላም የማገኘው” ይል ነበር፡፡ ትልቅ ሰው ያከብራል፤ ደካሞችን ያግዛል ይንከባከባል፡፡ ይሄ ተግባር ደግሞ የጀግኖች ተግባር ነው፡፡
ህዝቡ ስለ አቶ በረከት መረዳት አለበት የሚሉት ነገር አለ?
አቶ በረከትን የሚጠላውም ሰው ሳይቀር በሙስና ጉዳይ እጁ እንደሌለበት ያውቃል። ይሄንን ሁሉም ይመሰክርለታል፤ በዚህ ላይ ምንም አይነት ማብራሪያ አልሰጥም፡፡ ምናልባት አንድም የሚያልፈው ነገር የለም፤ “ታበዛዋለህ ሁሉን ነገር በአንዴ ልታፀዳ አትሞክር፤ ህብረተሰቡ ውስጥ ያለ የሙስና ቆሻሻ በአንድ ጀንበር አይፀዳም፤ በሌሎች ላይ አተኩረህ ታገል” ሊባል ይችል እንደሆነ እንጂ በዚህ ላይ ምንም አይነት የሚያጠራጥር ነገር የለም። በረከት ለ27 አመታት ኢህአዴግን ግንባሩን ሰጥቶ ሲታገል ነበር፡፡ ግን ውድቀቱን መንገላታቱን፣ ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን የሚፈልጉ፣ ባልዋለበት ባልተሳተፈበት ስሙን ሲያጠፉ የኖሩ ናቸው። ይሄን የሚያደርጉት እንደገና ወደ ስልጣን እንዳይመለስ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከሚሊኒየም በዓል በኋላ “የሚያኩራራ ሥራ ሰርተናል” በሚል ስሜት ውስጥ እንደነበር ሁሌም በረከት ይናገር ነበር፡፡ ትንሿ ስህተት እየሠፋች ትመጣለች፣ ችግሮቻችንን ማጽዳት ላይ እናተኩር ሲላቸው፤ “ችግር ሳይኖር ችግር አለ የምትለው ሟርተኛ ስለሆንክ ነው” ተብሏል። በረከት ዛሬ አይደለም ለመልቀቅ ያሰበው፤ ከአቶ መለስ ሞት በፊት ነበር፡፡
ጥሩ ዜጋ ለመሆን የግዴታ ኢህአዴግ መሆን የለብኝም፤ ከኢህአዴግ ጋር አልቆረብኩም፣ ከኢህአዴግ የተሻለ ድርጅት ከመጣ ጥዬው እወጣለሁ የሚሉ ቃላቶች አሉት፡፡ ቆራጥ አስተሳሰብ ነው ያለው፤ ብዙ መልካም ነገሮች እያሉ ትንሿ ነገር አደጋ ካላት ይታገላል፤ ምክንያቱም ሁሌም ጥሩ ነገር በጃችን ነው፤ መጥፎ ነገር እየሰፋ ነው የሚሄደው ብሎ ስለሚያስብ ነበር፡፡ “እኔ ድርጅት አላመልክም” የሚለው ነገር አለው፡፡ “ከኢህአፓ በላይ የማመልከው አልነበረም፤ እሱ እንኳን ፈርሷል” ይል ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ የሚለው ግን በውስጥ ነው ለውጪ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ይሄ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ አማራጭ የሌለው ድርጅት ነው፤ አማራጭ ያለው ድርጅት ቢመጣ ደስታውን አይችለውም፤ እስኪመጣ ግን በውስጡ ያሉትን ችግሮች እያፀዳ፣ ለውጪ አሳልፎ ሳይሰጥ ሲያድን ነበር፡፡ ይሄ ለራሱ ሲል ያደረገው አይደለም። ኃላፊነት ይሰማዋል በረከት፡፡
ሌላው በረከት የሚከሰስበት ጉዳይ ብሔር ነው - ተወልዶ ያደገው ጐንደር ከተማ ነው። ጐንደር ተወልዶ አድጐ፣ የጐንደርን ባህል የአማራውን ቋንቋ እየተናገረ ነው ያደገው። ቤተሰቦቹ በትውልድ ኤርትራዊ ናቸው። ኤርትራ ማለት ኢትዮጵያ ማለት ነው፡፡ በጐንደርና በኤርትራ መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ከቤተሰቡ ይልቅ የአካባቢው ባህል ቋንቋ፣ ስሜት ነው እሱ ላይ የሠፈረው፡፡ ቤተሰቦቹም ቢሆን በወጣትነት ነው የመጡት። ከጐንደር ማህበረሰብ ጋር የሚጋፉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ያደገበትን ማህበረሰብ፣ ቋንቋና ባህል መርጦ ነው የተቀላቀለው፤ ትግርኛን እንኳን የለመደው በትግል ወቅት ነበር፡፡
አቶ በረከት ከተያዙ በኋላ  ጠ/ ሚኒስትር ዐቢይን ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ አለ?
በረከት ሲያዝ ጠ/ሚኒስትሩ አገር ውስጥ አልነበሩም፡፡ ብዙ የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ እውነቱን ሳላውቅ መናገር አልፈልግም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ሳይሰጡ ፌደራል ፖሊስ ሊተባበር አይችልም የሚሉም አሉ፡፡  እኔ ግን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን ማናገር እፈልጋለሁ። ጉዳዩን አያውቁትም  ወይ? ምንድነው የታሰበው ነገር? የሚለውን ለመጠየቅ፣ እኛ ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለን፣ በሚቀርቧቸው ሰዎች በኩል ጥያቄውን አቅርበናል፡፡ እስካሁን የተሰጠን መልስ የለም፡፡ በትዕግስት እየጠበቅን ነው። ቀላል ነገር አይደለም፤ በረከት ለአገር የከፈለው ዋጋ መታየት አለበት፡፡
አሁን በአገሪቱ ላይ ያለውን ለውጥ በተመለከተ በግልዎ ምን አስተያየት አለዎት?
ቀደም ሲል ጠ/ሚኒስትሩን ማንነታቸውን አላውቅም፡፡ ምን አይነት ሰው ናቸው? ምን አይነት ፖለቲካዊ አቋም አላቸው? የሚለውን እንደ ማንኛውም ሰው በሩቅ ስከታተል ነው የቆየሁት። ለውጥ መጣ ሲባል ምኞቴ የነበረው ምን አለበት ጥሩ አመራር፣ ጥሩ መንግስት ቢኖር የሚል ነበር። ምክንያቱም ባለቤቴ ከዚህ ፖለቲካ እንዲወጣ በጣም ስጐተጉተው ነበር፤ ነፃ የሆነ ቤተሰብ እንዲኖረኝ እመኝ ነበር፡፡ መብቴን  እንኳን በአግባቡ አልተጠቀምኩም። ሁለተኛው፤ ካለው የስርአት ብልሽት ጋርም ተያይዞ፣ “አንተ ተጠያቂ የምትሆንበት ችግር ምንድነው?” እያልኩ ስጠይቀው ነበር፡፡ አሁን ያለው ለውጥ ግልጽ አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ፖሊስ እየተተገበረ ነው ወይስ ተቀይሯል? የሚለውን አይገልጽም፤ ሰዎች እየሞቱ ነው። በ27 አመት ውስጥ ተደምሮ ሞቶ የማያውቅ ሰው እየሞተ ነው ያለው። ግልጽ የመንግስት አካሄድ እየታየ አይደለም። አሁን ለምሳሌ የሥራ ዕድል የለም፡፡ እነዚህ ነገሮች ታዝቤያለሁ፡፡
አቶ በረከት በፈቃዳቸው ሥልጣን ከለቀቁ  በኋላ፣ ቤተሰቡ በምንድን ነው የሚተዳደረው?
በራሴ እንቀሳቀሳለሁ፤ እሠራለሁ፡፡ ከመንግስት ጡረታ ከተወጣ በኋላ ማቋቋሚያ በሚል የሚሰጥ ነገር አለ፤ እሱ ደርሶናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ሸጠን ያገኘነው ነገር አለ። ቢበዛም ቢያንስም፣ እራሳችንን ለማስተዳደር የሚያበቃ ነገር አለን፡፡
አቶ በረከት በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ  ነበሩ ብለው ያምናሉ?
አቶ በረከትን በቅርብ የሚያውቀው በጣም ያከብረዋል፡፡ በረከት ወደ አንድ ቢሮ ሲመደብ ወይም ሠራተኞች ወደሱ ሲመደቡ ይደናገጣሉ። በእሱ ላይ በሚደረገው ዘመቻ ምክንያት ሳይቀርቡት ይፈራሉ፤ ለምሳሌ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ነበር፡፡ ገና ሲሄድ የገጠመው ችግር ይሄ ነበር፡፡ ከተግባባ በኋላ ግን ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ነው ያተረፈው። በዲሞክራሲ ነው የሚመራው፡፡ የሙያ ነፃነትን አይነፍግም፡፡ ትንንሽ ስራዎች ውስጥ አይገባም። ምክንያቱም የፖለቲካ ብስለት አለው፤ አንባቢ ነው። አቶ በረከት በጣም ያነባል፡፡ ጓደኞቹ ከውጪ ምን እናምጣልህ ሲሉት፣ መጽሐፍ ነበር የሚለው፡፡ ወደ ትግል የገባው ሀይስኩል ሳይጨርስ ነው፤ ግን እራሱን እያስተማረ ነው ለዚህ የበቃው፡፡ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም አንብቡ ብሎ የሚመክር ሰው ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በረከትን “ከጀርባ አይዋጋም፣ በፊት ለፊት ነው” እያሉ የሚያደንቁት አሉ፡፡ እንደ ጥሩና የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ የሚያዩት አሉ። በረከት በትችት ያምናል፡፡ በግምገማ ጊዜ በጣም ይናገራል፡፡ ሲናገሩትም ይመልሳል፡፡ ማስተካከል ያለበትን ይቀበላል፤ እንደ በረከት የሚናገር የሚቆጣ ሰው የለም፤ ፊት ለፊት ነው ማስመሰል አያውቅም። በዚህ ይወደዳልም ይጠላልም፡፡ እሱን ከፍ ያደረገው ስልጣን በዝቶለት ሳይሆን በአቋም የተሻለ ስለነበር ነው፡፡
ጐንደር ላይ ኮሎኔል ደመቀ ሲታሰሩ በጣም ተቃውሞ ነበር፤ ህዝቡም ደግፎት ነበር፡፡ ሰውየው ትክክልም ይሥራ መጥፎ የህዝብ ድጋፍ አግኝቷል። ስለዚህ ለህዝቡ ሲባል እናቁም ብሎ ለአቶ ኃይለማርያም ደብዳቤ ጽፎ አዋሳ ድረስ ጠይቋል፡፡ ተገልብጦ ተወቃሽ የሆነው ግን እሱ ነበር፡፡ አሁንም በተጋበዘ ቁጥር እየሄደ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፤ እንደውም አሁን የ27 አመት ታጋዮች “የቀን ጅቦች” በተባሉበት ጊዜ ቢሆን ኖሮ፤ አንገቱን ይደፋ ነበር፡፡ መድረክ ሳይኖር ሚዲያ ሳይኖር ለህዝብ እስከጠቀመ ድረስ ይለፋል፡፡

Read 10686 times