Saturday, 09 February 2019 12:26

ኢህአዴግ እና የሰብዓዊ መብት ነገር

Written by  መስከረም አበራ
Rate this item
(3 votes)


     አሮጌው ህወሃት መራሽ ኢህአዴግ፤ ከአዕላፍ ነቀፌታዎቹ አንዱ በሰብዓዊ መብት ላይ ያለው እንደ ዱር አውሬ የሚቃጣው አቋሙ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በራሱ ህዝብ ላይ ያደረሰው አረመኔያዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዓለም ላይ በእርኩስነታቸው ከሚታወቁ መንግስታት ተርታ ሳያደርገው አይቀርም፡፡ ቀዳሚ የሚሆንበት አበይት ምክንያት በዓለም ታሪክ ብቅ ብለው የነበሩ እንደ ናዚ ያሉ ጨካኝ መንግስታት፣ የጭካኔ በትራቸው ያረፈው በራሳቸው ህዝብ ላይ ሳይሆን “ሌላ” በሚሉት ህዝብ ላይ ስለነበረ ነው፡፡ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ግን ለመናገር እንኳን  በሚያሳቅቅ፣ የመከራ ድስት ውስጥ ከድኖ ሲቀቅል የኖረው  የራሱን ህዝብ ነበር፡፡
“በአምባገነኑ ደርግ በመጨቆኔ አዝኜ ጫካ ገብቼ፣ ተራራ ቧጥጬ ታገልኩለት” የሚለውን ህዝብ፣ መፈጠርን በሚያስረግም ግርፋት፣ ቁም-ስቅል፣ እስራት፣ ስደትና መከራ ያሳለፈ ነፃ አውጭ ነኝ ባይ፣ ህወሃት/ኢህዴግ ብቻ ነው። በኢህአዴግ እስር ቤቶች፣ የአጋንንት ሰራዊት እንኳን ተመካክረው ሊፈጥሩት የማይችሉት የጭካኔ ትዕይንት፣ በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ ተፈፅሟል፡፡ የሰው ልጅ ጀርባ በኤሌክትሪክ ገመድ ተተልትሏል፣ ሰው ከነነፍሱ እባብ ባለበት በጉድጓድ ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል፣ ሴት ወንዱ ተገዶ ተደፍሯል፡፡ ባጠቃላይ በነፃ አውጭ ነኝ ባዩ አሮጌው ኢህአዴግ ዘመን፤ ስልጣን፣ ድንቁርናና ብልግና ሲቆራኙ የሚፈጠረው ጥፋት ሁሉ ደርሷል። የሰው ልጅ ክቡርነት ተረስቶ፣ ሰው ምናምንቴ፣ ስልጣን ደግሞ ክቡር ሆኖ ኖሯል፡፡
ከእስር ቤት ውጭ ያለው ዜጋም ቢሆን በመፍራት በመንቀጥቀጥ የኖረ፣ ካድሬ ደስ ባለው ቀን ያሰረበትን ዘመዱን መጠየቅ እንደ ሰማይ ርቆት፣ ጭቆናው ገላጋይ የሌለው መርገም መስሎት፣ እስር ቤት ባይገባም ቤቱን እስር ቤት አድርጎ በስነልቦና መረበሽ የሚማቅቅ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ያሰረውን አስሮ ያላሰረውን የታሳሪ ቤተሰብ፣ ስልጣኑ በፈቀደለት መጠን ሁሉ የሚያንገላታ፣ መንግስትነትን የማይመጥን፣ እኩይ ማንነት ባለቤት ነበር፡፡ አረመኔው ኢህአዴግ፤ በጭቃ ጅራፉ ገርፎ፣ ስሙን አክፍቶ ላሰረው ዜጋ፣ ስንቅ እንዲያቀብል የሚፈቅደው፣ ከቤተሰቡ በእድሜው የገፋውን ሰው መርጦ ነበር፡፡
ይሄኔ በልጆቻቸው መጦር የሚገባቸው፣ ለራሳቸው ያለ ድጋፍ መንቀሳቀስ የማይችሉ አቅመ ደካማ አዛውንት የታሳሪ ወላጆች፣ ስንቅ ተሸክመው፣ ከከተማ ዳር ባሉ እስር ቤቶች ይንከራተታሉ፡፡ እነዚህ አዛውንቶች  በዚህ መንከራተታቸው ጊዜ ሁሉ ከእብሪተኞቹ ነገስታት አልፈው እነዚህን እርኩሶች በላይዋ ላይ የሾመችውን ሃገር ጭምር የሚረግሙ ይመስለኛል! በህይወቴ የኢህአዴግ እርኩሰት ጎልቶ እንዲታየኝ  ካደረጉኝ ምክንያቶች አንዱ፣ ይህ አዛውንቶችን በማንከራተቱ፣ ራሱን ጎበዝ አድርጎ የማየቱ ነገር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ተስማምቶ አመታትን ያስቆጠረ ሰው ሁሉ እስከ ዛሬ ይሸክከኛል፡፡ የኢህአዴግ ካድሬነት ከመሰረታዊ የሰውነት ባህሪ ጋር የሚጋጭ የሚመስለኝም ለዚህ ነው፡፡
መሰረታዊ የሰብዓዊነትን መርህ ችላ ብሎ ለስልጣን መደራደር፣ ኢህአዴግን ኢህአዴግ ያደረገው ዋና ማንነቱ ነው፡፡ ተለወጥኩም ተለነቀጥኩም ቢል ኢህአዴግ ከዚህ ማንነቱ ፈቅ ነቅነቅ አይልም፡፡ ተለወጥኩ ያለው የዶ/ር ዐቢይ ኢህአዴግ፤ በሰብዓዊ መብት ላይ አለቅጥ ሲያሾፉ የኖሩትን ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄርን አምባሳደር አድርጎ፣ ሾሞ ሸልሞ አሳይቷል። 77 ሺህ አማሮችን ስንት አመት ከኖሩበት ጉራፈርዳ ወረዳ በአንድ ሌሊት ነቅለው፣ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ዜጎችን ለመከራ የዳረጉትን፤ በዚሁ ዝናቸው ባዕዳን እንኳን አምባሳደርነቱን አንቀበልም ያሏቸውን አቶ ሽፈራው ሽጉጤን፤ ሃገር እየቀያየረ የሚሾመው አወዳሹ የበዛው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት፤ ስለ ሰብዓዊነት ግድ ይለዋል ብሎ ምክንያታዊ ሰሚን ሊያሳምን የሚችል ሰው የለም፡፡ በሱማሌ ክልል ከአብዲ ኢሌ ጋር ያደረጉት እኩይ ስራ አልበቃ ብሏቸው አቶ ሙስጠፋን አላሰራ ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ፤ በተለይ በኋለኛው ሙከራቸው የተነሳ በፊት ላደረጉት፣ በሱማሌ ክልል ለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉ፣ ተጠያቂ ሊሆኑ ሲገባ፣ አሁንም በንጉስ እልፍኝ ይሽሞነሞናሉ፡፡
መቼም ለዶ/ር ዐቢይ መንግስት ጠበቃው ብዙ ነውና፣ እነዚህን በሰብዓዊ መብት ላይ ጉልህ ወንጀል የሰሩ ሰዎች መሾሙ ሃገር ለማረጋጋት ብሎ ነው፣ ሁሉም በአንዴ አይሆንም፣ አንዳንዱን ጥፋት መተው ነው የሚል አይጠፋም። በበኩሌ፤ በሰው ልጅ ክቡርነት አጥብቄ የማምን ነኝና፣ ገንዘብ ከዘረፈው ይልቅ የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብት የረገጠው ሰው ይበልጥ ወንጀለኛ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ አንድ ቀን እንኳን ከተጠያቂነት ነፃ ሆኖ ሲንጎራደድ ማየት አልሻም፡፡ ሲቀጥል በኢህአዴግ እልፍኝ የሰብዓዊ መብት ነገር እጣ ፋንታ የሌለው ጉዳይ ስለሆነ መጠየቁ ቀርቶባቸው፣ እነዚህ ሰዎች ከእነ ክፉ ወንጀላቸው እንደ ማንኛውም ሰው እየወጡ እየገቡ መኖሩ አንሷቸው፣ ስለ መሾማቸው፣ ሿሚው ጠ/ሚኒስትር  ዐቢይ ራሳቸው፣ ከተራ ካድሬያዊ ሽኩቻ ባለፈ፣ ሰው ፊት የሚያቀርቡት ምክንያት ያላቸው አይመስለኝም፡፡
ምናልባት ሃገራችን ካለችበት ክፉ የዘረኝነት ፖለቲካዊ አየር የተነሳ እነዚህን ሰዎች ተጠያቂ ማድረጉ የመጡበትን ዘር የሚያስቆጣ ሆኖ የሚያመጣው ችግር እንዳይኖር ተፈርቶ ነው የተሾሙት የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ በነዚህ ሰዎች ሁኔታ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ህወሃት ከሌላው ፓርቲ በተለየ ሁኔታ  ወከልኩት በሚለው ህዝብ ዘንድ ጥብቅና የሚቆምለት ስለሆነ፣ በአቶ አዲሱ ገ/እግዚአብሄር ተጠያቂነት ምክንያት የሚነሳ ዘረኝነት ወለድ ጉም ጉም ባይጠፋም፣ ሌሎቹ ሰዎች በስልጣን ዘመናቸው ባደረጉበት ማስመረር ምክንያት  የወጡበት ህዝብ ራሱ ለፍርድ የሚፈልጋቸው ናቸው። የጄል ኡጋዴን መከራ ናፍቆት፣ ለአህመድ ሽዴ ጥብቅና የሚቆም ሱማሌ አይገኝም፡፡ አቶ ሽፈራው ሽጉጤም ቢሆኑ በወጡበት ህዝብ ዘንድ ወድቀህ ተነሳ የማይባሉ  ናቸው፡፡  
የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር ዐቢይም እንደ ማንኛውም ኢህአዴግ ቅም የማይላቸው ሰው እንደሆኑ ማሳያው ከላይ የተጠቀሰው ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ  በተደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ በዳኛ ፍሬህይወት ሳሙኤል ሰብሳቢነት በተቋቋመ ገለልተኛ ኮሚሽን የተደረገውን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ሪፖርት ተቀብለው፣ በሃሰተኛው ቦታ እንዲተኩ በተደጋጋሚ ከኮሚሽኑ አባላት የሚቀርብላቸውን ጉትጎታ ችላ ማለታቸው ነው። እነዚህ የኮሚሽኑ አባላት አሁን የለውጥ ሃይል ነኝ የሚለው የእነ ዶ/ር ዐቢይ ቡድን፤ አንገቱን ደፍቶ፣ ከግፈኛው የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ጋር አብሮ፣ ግፍን ሁሉ አሜን አሜን በሚልበት በዛ አስፈሪ ዘመን፣ አንገታቸው ላይ የተሳለ ቢላዋ ሊያርፍ እንደሚችል እያወቁ፣ ከእውነት ጋር ብቻ ያበሩ፣ በሞራል ልዕልና የለውጥ ሃይል የተባለውን ጭምር የሚያስከነዱ ሰዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ያለ ጊዜው ጭምር የፀኑ ሰዎች፣ የኢህአዴግ ካድሬ ሁሉ ምስል ቀርፆ ሊያመልካቸው የደረሰው መለስ ዜናዊ፣ በመንበሩ ቁጭ ብለው እያለ ነው፣ ነፍሳቸውን ሸጠው፣ የህዝብን አደራ ብቻ አንግበው ከሞት ጋር የሚፋጠጡበትን አስፈሪ መንገድ የተጓዙት። በዚህ ጉዟቸው ውስጥ የተረጋጋው ኑሯቸው ተናግቷል፣ ለዱብዳ ስደት በመዳረጋቸው ቤተሰባቸው ተበትኗል፣ ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል። ለህዝብ ሲሉ ይህን ሁሉ ስላደረጉ ሊመሰገኑ ሲገባ፣ ሊሞቱለት የቆረጡትን፣ ብዙ የለፉበትን ነገር ተራ ጥቆማ አድርጎ  ማቃለል ራስን ማስገመት ነው፡፡ በርግጥ በሃሰት ፖለቲካ፣ በጌታ ፈቃድ እያደረ የኖረ የኢህአዴግ ባለስልጣን፤ ለእውነት ሲባል የሚከፈልን መሰዕዋትነት ለመረዳትና ተገቢውን ክብር ለመስጠት ሊቸግረው ይችላል፡፡ ይህን መሰረታዊ ኢህአዴጋዊ ባህሪ እንደተሸከሙ፣ የለውጥ መሪ ነኝ ማለቱ ግን የሚገጥም ነገር አይደለም፡፡
የኮሚሽኑ አባላት መለስ ዜናዊ ያቀረቡላቸውን፣ የኢህአዴግ ካድሬ የእለት ተዕለት ኑሮው አካል የሆነውን የሃሰት ግብዣ እምቢ ብለው ከሃገር የወጡበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ነገሩ የሰዎቹን የእውነት ሰውነት የሚያሳይ፣ ሌላ ሃገር ቢሆን ትልቅ ሽልማት የሚያሰጣቸው፣ ለትውልድ ትምህርት የሚሆን ስራ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዳኛ ፍሬ ህይወት፤ በተበደለው ህዝባቸው ላይ ሌላ ሃሰት ጨምሮ፣ በህዝብ ቁስል እንጨት ላለመስደድ ሲሉ በቦሌ በኩል የወጡበትን መንገድ ለኢሳት ቀርበው ሲያስረዱ፣ በበኩሌ ነገሩ ማለፉን ሁሉ ረስቼ፣ በትልቅ ጭንቀት ተወጥሬ ነበር ያዳመጥኳቸው። በዛች ቅፅበት ያቀዱት አንዱ ነገር ውልፊት ብሎ በመንግስት እጅ ቢወድቁ፣ ሊደርስባቸው የሚችለውን ነገር ማሰቡ የሰውየውን የፍትህ ሰውነት ለመረዳት ያግዛል። ከዚህ የምንረዳው ለዳኛ ፍሬህይወት ፍትህ፣ በደማቸው ውስጥ የሚዞር ነገር እንጂ  ለእንጀራ ሲሉ ብቻ የያዙት ጉዳይ እንዳልሆነ ነው፡፡ እስከ ዛሬ ለፍትህ የሚሞግቱት ሌሎቹ የኮሚሽኑ አባላት እነ አቶ ምትኩ ተሾመ፣ ዳኛ ወ/ሚካኤል መሸሻ፣ አባ ቲዎፍሊዎስ  ሁሉ የህዝብን አደራ ከመብላት፣ ራሳቸውን ለመስዋዕት ያቀረቡ ድንቅ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
በጣም የሚያሳዝነውና የሚገርመው ተለውጫለሁ የሚለው መንግስት፤ እነዚህን ሰዎች በክብር ጠርቶ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ ሲገባው፣ በህይወታቸው የተደራደሩበትን ሪፖርት እያቃለለ መሆኑ ነው። ይህ የሚያሳየው ለዶ/ር ዐቢይ መንግስት ከየአቅጣጫው እየወረደ ያለው የበዛ የውዳሴው ድቤ አቅሉን እንዲስት እንዳያደርገው ነው። ይህ ደግሞ ለማንም አይበጅም! ይብስ የሚገርመው ደግሞ ለወትሮው ለፍትህ እቆማለሁ የሚለው ተቃዋሚ ሃይልም ሆነ ህወሃትን ለማብጠልጠል ምክንያት የማይፈልገው ጋዜጠኛ ሁሉ ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ አለማለቱ ነው፡፡ ጭራሽ ለፍትህ እሟገታለሁ ሲል የኖረው ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ፤ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት በስራው ሁሉ ትክክል ነው እንደ ማለት የሚሞክረው የፖለቲካ አዝማሪነት ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ስለማያዋጣ የአጣሪ ኮሚሽኑን ተገቢ ጥያቄ ዳር ለማድረስ ሰብዓዊነት ይሰማኛል ባይ ሁሉ፣ በሃቅ ላይ ፊቱን ባዞረው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር አለበት፡፡ ይህን ስለተባለ የዐቢይ መንግስት አይሟሟም!
አሁን የለውጥ ሃይል የሚባለው የኢህአዴግ ቡድን፣ በ1997 ለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢያንስ በዝምታ ድጋፍ የሰጠ ነው፡፡ በአንፃሩ ዛሬ ስለ እውነት የሚማፀኑት የኮሚሽኑ አባላት በህዝብ ላይ የደረሰውን በደል ለማጋለጥ በነፍሳቸው የተደራደሩ ሰዎች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የህዝብን ትግል ተተግነው፣ የለውጥ አራማጅ ነን ያሉትን የዛሬዎችን ገዥዎች ሳይቀር የሚልቅ የሞራል ልዕልና ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ስልጣን ላይ የወጣው ቡድን፣ የኮሚሽኑን ሪፖርት በመቀበል  የትናንት ጥፋቱን የማረም ግዴታ አለበት፡፡ የኮሚሽኑ አባላት የተመሰከረለት ለእውነት የመቆም ፅናት ደግሞ ጉዳዩን የትም ድረስ የመውሰድ ብርታት እንዳለው ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ነገሩ ተጓትቶ ባዕዳን ደጃፍ ከመድረሱ በፊት የለውጥ አመራር ነኝ ባዩ የሃገራችን መንግስት፤ ህይወት የተገበረበትን፣ ቤተሰብ የተበተነበተን  ትልቅ ጉዳይ ማቃለሉን ትቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ባይወድም፣ ግዴታው እንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡

Read 1543 times