Saturday, 09 February 2019 12:23

ሞኝ የዕለቱን ብልህ የዓመቱን

Written by 
Rate this item
(7 votes)


    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዳኝ በሙሉ ወኔ፣ ዛሬስ ታሪክ እሠራለሁ፣ ብሎ ጠመንጃውን ይዞ፣ ጥይቱን አጉርሶ፣ ወደ አንድ ጫካ ሲሄድ፣ አንድ ሰው መንገድ ላይ ያገኘዋል፡፡
መንገደኛው፤
ሰላም ወዳጄ፣ ወዴት ትሄዳለህ?
አዳኝ፤
    ወደ አደን
መንገደኛ፤
ምን ልታድን?
አዳኝ፤
ዝንጀሮ
መንገደኛ፤
    ስንት ዝንጀሮ?
አዳኝ፤
ብዙ ዝንጀሮ
    መንገደኛ፤
በቁጥር ንገረኝ?
አዳኝ
    ከአሥራ ስድስት እስከ ሃያ
መንገደኛ፤
“ኣ!? ከአሥራ ስድስት እስከ ሃያ?”
አዳኝ፤
“አዎ!”
መንገደኛ፤
“ስንት ጥይት ይዘሃል?”
አዳኝ፤
“አንድ!!”
መንገደኛ (በመደነቅ)
“አንድ?”
አዳኝ፤
“አዎ፡፡ አንድ ጥይት ነው የያዝኩት፡፡ ምነው ተደነቅህ እንዴ?”
መንገደኛ፤
“እንዴ እንዴት አይደንቀኝ?! ለመሆኑ እንዴት ብታነጣጥር ነው አሥራ ስድስት ዝንጀሮ ባንድ ጥይት የምትመታው?”
አዳኝ፤
እሱማ በጣም ቀላል ነው፤ ዝንጀሮዎቹ ባንድ መስመር ሲገቡልኝ ጠብቄ ቃታዬን መሳብ ነው፡፡
አሥራ ስድስቱንም ባንድ ጥይት እሰፋቸዋለሁ፡፡
መንገደኛ፤
ለምን እንደተደነቅሁኝ አሁን ገባኝ፡፡
አዳኝ፤
ምኔ አስደነቀህ?
መንገደኛ፤
ባንተ ዒላማ ችሎታ ሳይሆን፣ ባንተ አገር ዝንጀሮዎች አሰላለፍ ነው!
***
በሀገራችን ያልታቀደ ዓይነት ዕቅድ የለም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ዕቅዶች ይጀመራሉ እንጂ ተከናውነው አያበቁም፡፡ አንድም የዕቅዶቹ በአግባቡና በቅጡ አለመጠናት ነው፡፡ ሁለትም በዘመቻ መልክ የመታሰባቸው አባዜ ነው፡፡ ሶስትም የፈፃሚዎቹ ቸልተኝነት ነው፡፡ የአፈፃፀሙን ችግር ስናወራ ዓመታት አልፈዋል፡፡ የተሾመ ባለሥልጣን ያቀደውን ነገር በውል ሳይተገብር ይነሳና ሌላ ቦታ ይሾማል፡፡ አሮጌውን አዲስ ሹም ይተካውና ሀ ተብሎ ሥራው ይጀምራል፡፡ አዲሱ ከአሮጌው ለመለየት የራሱን ዕቅድ ያወጣል፡፡ በዚህ ዓይነት የድግግሞሽ መላምት ውስጥ ነው ሀገራችን እየኖረች ያለችው፡፡
ዛሬም፤
“ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ” ከማለት አንቦዝንም፡፡ ገና ያልሠራነው ብዙ ሥራ ከፊታችን ስለሚጠብቀን ነው!
የፖለቲካ ችግራችንን በምናየው የለውጥ ፍንጥቅታ የረታነው ከመሰለን ተሳስተናል፡፡
የኢኮኖሚ ችግራችንንም በምናየው የለውጥ ፍንጥቅታ የተፈታ ከመሰለን ተሳስተናል፡፡ የማህበራዊ ቀውሳችን ከሁለቱም የባሰ ውስብስብ ባህሪ አለው፡፡ ብዙ ነገር ተለውጧል ብለን አንሞኝ፡፡
ለውጥን ባንድ ጀምበር ማሰብ ከዕሙናዊው ዓለም (Realistic world) እና ነባራዊው ሥርዓት (Objective System) ውጪ ለውጥን መመኘት ነው፡፡
አሁን ወጣትና ወጣት እየተገናኘ ስለ ችግሩ ይወያይ፡፡ የነገዋን ኢትዮጵያ ይቅረፅ፡፡ ለሀገሩ መፍትሔ ያብጅ! የሰርክ የሰርኩን በማውራት የሀገርን ችግር-ፈቺ መሆን ከቶውንም ዘላቂ መንገድ አይደለም! ሞኝ የዕለቱን ብልህ የዓመቱን የሚባለው በዚህ አግባብ ነው!  

Read 9525 times