Saturday, 09 February 2019 12:22

በጐንደር በታጠቁ ሃይሎች ጥቃትና ግጭት በርካቶች ሞተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

 በአማራ ክልል ጐንደር ደንበያ ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃትና በፈጠሩት ግጭት በርካቶች መገደላቸውንና መኖሪያ ቤቶች መቀጠላቸውን ምንጮች ያስታወቁ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በጐንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ ባለፈው ሐሙስ ምሽት በተፈጠረ የእሣት ቃጠሎ እንስሳትን ጨምሮ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸው ታውቋል፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ እንዳለው ከረቡዕ ጥር 29 ቀን ጀምሮ በተለይ በደንቢያ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች “በአማራ እና በቅማንት ብሔረሰቦች” መካከል ግጭት መፈጠሩንና በዚህም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
ግጭቱ በዋናነት የተፈጠረው በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ልዩነትን በመፍጠር አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ አቅደው በሚሠሩ ሃይሎች ነው ያለው የክልሉ መንግስት፣ ግጭት ፈጣሪ ታጣቂ ሃይሎቹ ከቀላል እስከ ከባድ መሣሪያ የታጠቁ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡ ለዚሁ ግጭት ህገወጥ መሣሪያ ወደ አካባቢው ከመግባቱም በተጨማሪ የሚሠለጥኑ ሃይሎች እንዳሉ ያስታወቁ የክልሉ መንግስት፣ በግጭቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የእስር ትዕዛዝ ወጥቶ ፍለጋ እየተከናወነ መሆኑንም አክሎ ገልጿል፡፡
በምዕራብ ጐንደርና ማዕከላዊ ጐንደር ዞኖች እስካሁን በተፈጠሩ ግጭቶች ጥቃቶች ከ39 ሺህ በላይ ዜጐች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውም የአማራ ክልል መንግስት አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በጐንደር ከተማ አዘዞ ልዩ ስሙ ግራር ሠፈር በተባለው አካባቢ ከትናንት በስቲያ ምሽት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ60 በላይ ከብቶችና በርካታ ቤቶች መቃጠላቸው ታውቋል፡፡
ሐሙስ ምሽት ከ4 ሰዓት ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ እስከ ምሽቱ 7 ሰዓት ድረስ መቆየቱን የጠቆሙት የአካባቢው ምንጮች በአካባቢው ማህበረሰብ ርብርብ ሊጠፋ መቻሉንም ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የእሣቱን መነሻ ምክንያት በተመለከተ የከተማው አስተዳደር ፀጥታ ቢሮ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 8498 times