Saturday, 02 February 2019 15:36

ነቢይ ፍለጋ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

  ‹‹ጽኑ ነቢይ ሲነሣ እንደዚሁ ጽኑ ንጉሥ ያስነሣል፡፡››
            
     አዎን!
ትልቅ ሕዝብ ‹‹ነበርን››!!!
‹‹መቸስ ምን እንላለን›› . . .
.  .  .  .  .  .  .  .  .  .  .
ከማውጋት ያለፈም እስቲ ተስፋ እናብጅ ስለቆዘምንበት
ወደ ኋላ ወደ ፊት መንቀሳቀስ መሄድ ጉዞ አክለንበት
ከትናንት ውብ ድርሣን ለዛሬ እሚበጀን የክብር ትንሣኤ
የቋጥኝ እንጎቻ ገዝፎ ቢታይ ድንገት
ከመሳ መንገዱ ነግ አለም መድረሻ ከምንተምምበት
አንድም በአዲሱ መም ያምናን ክብር አግንነን
ወደፊት መገስገስ አሁን ከቆምንበት፡
‹‹የለም! ተመልሰን እምንዘግነው አለን›› ካልንም
ከአቻምና የአያቶች ቤት
የተውነውን ጥበብ መዶሻ ጨብጠን
መፈልፈያ መሮ ነባሩን ውብ አለት
እንፈልጋ እንግዲህ . . .
. . . የትንቢት ቃልና እውነተኛ በጎ ፍቺውን እየናፈቅን፤ ንግስቲቱ ሕንደኬ፤ በሀብትና በገንዘብዋ ከሾመችው ጃንደረባ እጅ መንሻ ማግኘት ከቶም ትዝ ሳይለው፣ ቅዱስ ግብሩን ፈጽሞ ከዓይን እንደተሰወረውና ጃንደረባው  መንገዱን ደስ ብሎት እንዲሄድ እንዳደረገው፣ ልክ እንደ ሐዋርያው ፊልጶስ ሁሉ እንዲሁ፤ ቃሉም 1ኛ ቆሮ 14፡ 3 ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል። እንዲል የእኛም ዘመን ነቢያት እንዲሁ ጮክ ብለን የምናነበውንና ያልገባንን ቃል ፍቺ ሰጥተው ከመተርጎምና ከመለኮታዊው ጸጋ እኛን ከማገናኘት፣ ደስታን ከማጎናጸፍ፡ የጽድቅን መንገድ ከመጠቆም ቅዱስ ግብር ይልቅ አሉታዊ  ግብር ተጠምደው ስንታዘብ ፤ መቸስ በገባን መጠን እንመላለሳለንና ያጥንት ጥርስ ባናበቅልምና በወተት ጥርሳችንም ያሰብነው ቢሆንም ምናልባት ... በርግጥም ‹‹እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም።›› መባሉን ባንዘነጋም አብሮም ደግሞ ‹‹እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ።›› ተብሏልና (ማቴ 13፡29-30)  የቱንም ያህል እምነት የግል ቢሆንም፤ በተለይ ደግሞ በዚህ ዘመን፡ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ‹‹የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?›› በሚል መሪ ፍለጋ ፡ ጽድቅ እና ንስሀ ለሚቃትቱ ምስኪን ምእመናኑ የማማለል አቀራረብና ታክቲኩ በልዑል ቅዱስ አምላክ ስም የተለበጠ ፋሽን የሆነ ምላሽን በመስጠት ላይ ላሉ አንዳንድ የዘመናችን የኃይማኖት መምህራን (በማወቅም ይሁን ባለማወቅ) ወለፈንዲ ምግባራት፤ እንደ ጥንታዊ ሀገርና እንደ ታላቅ የነበረ/የሆነ ሕዝብ አካል አዲስ ትውልድ፤ . . . እንደ ሰው መገኛ ምድር . . . ወዘተ. ጉዳዩ አካሂያዳችንን ወደ ኋላ አያሽቆለቁለውም ወይ? ተብሎ በግልጽ መጠየቅ አይገባምስን? ትንቢትን ስለ ማክበር የተሰጠችው ትእዛዝም ብትሆን (1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡ 20-21 ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ) ከመፈተንና መገንዘብ ጋር መቆራኘቱንም በማስተዋል፤ ደግሞም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ (ማቴ 24፤3-5) የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች  እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።››
ከፍልስፍናም ገጽ መላምት ክሌዕቱ የፍጥረት አብዮት
ከአዳም የአሜን ሚስት ከሊሊት መከዳ ፍቺ እና መለየት
አክንፎ ካስቀራት አዲስ ህልምን መሻት ሌላ አለምን ማየት
የቅዠቷ ግልድም የጥላዋ ጥለት . . .
ከዓለም የቀደምንባቸውን ክቡር ጸጋዎቻችንን እየተውን ጭራሹኑ ከ‹‹ኋላችን›› በነበሩት ሕዝቦች ግራ የተጋባ (የመጃጃል ወይም ጅራት የመሆን አመል እንበለው ይሆን!) አካሂያድ ተሸብበን ስንረመጥ ሲታይ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪቃዊ የአለም የሥነ ጽሑፍ ኖቤል ሽልማት ተሸላሚው ዎሌ ሶይንካ Wole Soyinka ዛሬ እኛን ለአለሙ ሁሉ ኃይማኖቶች ቀደምት የነበርነውን ኢትዮጵያዊያንን ግራ ለሚያጋባንና በቅኝ ግዛት ውስጥ ሲማቅቁ የኖሩት ናይጄሪያዊያን ገና ያኔ ከግማሽ ምዕተ አመት በፊት ጀምሮ ለተደናበሩበት ለእኒህ የአባይ ነቢያት መበራከት በ1953 እ.ኤ.አ በጻፈው፡ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ለጥፋት በተዳረገው በነቢይ ኢዮሮብዓም Jeroboam በሰየመው ሀሰተኛ ነቢይ ገጸ ባህርይ ስም The Trials of Brother Jero በሚል አርእስት የከተበውን ድንቅ ተውኔቱን እናስታውሳለን፡፡ (ለዎሌ ሶይንካ የክብር ዶክትሬት ባበረከተለት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ተማሪዎች ለመድረክ ቀርቦ የነበረውን ትርጉም ተውኔቱን በቅርቡ በፕሮፌሽናል መድረክ ላይ ልናየው ተስፋ እያደረግን) በሽሙጥ ተውኔቱ ውስጥ፤ ነፍሱ ከንግድ ስራ (ገንዘብ) ጋር ክፉኛ ተጣብቃ ሳለ፣ በጉባኤ መካከል ግን ራሱን ጻድቅ የእግዚአብሔር ሰው አድርጎ በመታበይ በነቢይነት የሚሞናደለው መሪ ገጸ ባሕርይ፤ ስለ ምስኪናን ተከታይ ምእመናኑ በንቀት ተሞልቶ እንዲህ ይላል፡-  «I know they are dissatisfied because i keep them dissatisfied. Once they are full, they won’t come again» ‹‹ምእመናኑ እርካታን ያጡ መሆናቸውን ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ እርካታ ማጣቱንም ያለማሳለስ እማድላቸው እኔው ራሴው ስለሆንኩ፡፡ አንድ ጊዜ እርካታን ካገኙማ ዞር ብለውም አያዩኛ፡፡›› ... እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ  መልስ አለው፤  ‹‹በሐሰትም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው።›› (ኢሳ. 9፡15)
ውቃቢም እንዳለች
ሕዝብ ባንድ ሲቆም እሚያቅበጠብጣት
አዶ ከበሬዋ የሚፈጠፍጣት
ደረት እምትደልቅ እምታወርድ ሙሾ፡
ባሳቻ ሰአት በዱር ለልክፍቷ ወጥመድ ላንዴው ምሷን ሰጥቶ
ፈረሷን አስጓርቶ በአድባሩ ባውጋሩ በዠማ አስደንብሾ፡
ልሳኗን ጠርቅሞ ደረቷን ጀርባ አርጎ ክንዶችዋን ጎንድሾ
በአዳልሞቲ ጠቋር በወሰን በሻህምበሶ
በደጋጎቹ ስም ግዝት አውለሽልሾ
የሀዘን ማቋን ቀድዶ እንዳትኖር ማድረግ ነው
መቃብሯን ሰርቶ በዘላለም ሊሾ
በወጉ በላመ ፡ በወል በተቦካ እፍኝ ያገር እርሾ ፡፡
እምነትን በነፃነት ከማራመድ የሚጋፋንን ክልከላ እንደምናወግዘው ሁሉ፤ ባንጻሩም የእምነት ነጻነትን ለአሉታዊ አላማ የማዋልን ጉዳይ በመንፈሳዊ ሚዛን ለመዳኘት ሥጋዊም መለኮታዊም አቅሙም ፈቃዱም ባይኖረንም እንኳ ከጤናማ ማህበራዊ መስተጋብርና ለሞራላዊ ውድቀት ከመቆርቆር አኳያ በምናገባኝ ልንሸሸው እማንችለው ደረጃ የደረሰ፣ ዘመኑ የደቀነብን ጎትጓች ክፍተት መሆኑ ግን  እሙን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያናት ህብረት ከወራት በፊት ያወጣው የጋራ አቋም መግለጫም፣ የጉዳዩን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስ ጠቋሚ ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፤ ‹‹የእምነት ተቋማት ያላግባብ ገቢ ማጋበሻ መሆን እንደሌለባቸው›› ያሳሰቡትም ያለምክንያት አይደለም፡፡ አርዕስተ ጉዳዩን ለውይይት በማቅረብ ፈር ቀዳጅነቱን ያሳየችን ሶሎሜ፤ በፋና ቴሌቪዥን በሚተላለፈው ዝግጅቷ ላይ የጉዳዩን ባለቤቶች ለአደባባይ ማብቃቷን ማድነቅም ግድ ይላል፡፡ ተወያዮቹ የችግሩ ምንጭ የሆኑትን እንከኖች ሲነቅሱ፤ ማንም ሰው ተነስቶ የራሱን ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት የንግድ ፈቃድ ማውጣት ብቻ ነው የሚጠበቅበት ማለታቸውን ሰምተናል። ‹‹እኛን ይመስላሉ እንጂ እኛን አይደሉም!›› ድንቅ አገላለጻቸውን ጨምሮ፡፡  ‹‹አባይ ነባይ - መፍቀሬ ነቢያትን እንዴት ማከም ይቻላል?›› በሚል አርዕስት መጽሀፍ ያዘጋጁት ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ ፤ ለዛሬው ጽሑፍ የተጠቀምንበትን ስዕል (ቀበሮ?) የፊት ሽፋን ማድረጋቸው፤ በወንጌል ላይ የሰፈረውን አስተምህሮ፣ በስዕል ቋንቋ ግልጥጥ አድርጎ በማሳየት፡ ዘመኑ የደቀነብንን ተጠየቅ በጉልህ የሚያንፀባርቅ ነው - ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ፣ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።›› ማቴ. 7፡15፡፡
ፀሐይ መሳይ ክብር ቀስተ ደመና ሕብር
ሰማይ ያክል ሀገር ሰማይ ያክል ድንበር
ዝሆኑ ድርጭት ሲያክል እያደር አንሶ አንሶ፤
ቢቆዝም አይደንቅም ሀገር ቢትከነከን
ትናንትን ሙጢኝ ቢል ከዛሬው ቀንሶ፤
ተስፋና አመዳዩን ፀጋ እና መርገሙን
በየልኩ ሰፍቶ ከአሁን ተቀንሶ
በውሎ አዳሩ ልክ በኑሮው አስልቶ ዘመኑን ነቃቅሶ፡፡

የምጡቅ ልቡን ኬላ ድንበር እሚያፀና ከሳጉ እሚያጽናና
ያያት ቅድማያቶች ክቡር እምክቡራኑ ድንቅ ስብዕና ረቂቅ ህልውን
በ‹‹ያኔ! ወይኔ!›› ወኔ አላስቆም አላስቀምጥ አላስተኛ ያለ
‹‹ትናንት! ትናንት!›› እሚል ዛሬን አቅል እሚንጥ መቀስቀሻ ደወል
የሆነ እፁብ ‹‹እንትን›› ከጊዜ የገነነ
አሁን ላይ አቻምና ፡ አሁን ላይ አምና አለ፡፡
አባ ጎርጎርዮስ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሮማ ካቶሊክ ኃይማኖት ተከታዮች ጋር በተዋወቀችበት መድረክ በጋራ ለውይይት ተቀምጣ በፍሎሬንስ ጉባኤ  የተስማማችበትን ‹‹በእምነቶች መካከል ያለውን ጥላቻና ክፉ አስተሳሰብ ለመክላት ቤተ ክርስቲያን ‹‹በትክክለኛ አላማው›› ትቀበለዋለች›› የሚሉንን የኢኩሜኒዝምን (Ecumenism) ታሪካዊ ንቅናቄ መሰል፤ ሰላማዊ አላማ ያላቸው ቀና አስተሳሰቦች፤ ከእድገትና ስልጣኔ መሳ ለተጋረጡብን የእለት ተእለት ተግዳሮቶች መፍትኼ ማግኛ ይሆኑ ዘንድ በዘመኑ ጥያቄ ልክ ሰፋ፡ ዳበር ማለት ይችሉ ዘንድ መመኘት ደግ ነው መቸም፡፡ የእድገትና ስልጣኔያችንን ዳና ተከትለን፣ የእውነተኛ ዋጋችንን እስክንረዳ ድረስ ማገገሚያ ቢሆነን፡፡ ነጋ ጠባ በአክሱም ሀውልት፣ ላሊበላ፣ ፋሲለደስ፣ ኮንሶ፣ ሐረር ግምብ፣ ጢያ ትክል ድንጋይ . . . ወዘተ ላይ ዓይናችንን እያንከራተትን . . .
እኛ እስክንጠይቀው ኮራ ደራ ብሎ
ዘመን ድር አድርቶ ለጥ ብሎ ፈርሾ፡
ሳናገኘው አንቀር
መስፈንጠሪያ ደጋን የፈርጥ አክናፍ ሆኖ
ነግ እሚደርሰንን እፍኝ የድንጋይ እርሾ፤
አለት ላይ ከሆነ ታትሞ እሚያደክመን
አስርቦ አስጠምቶ በጠኔ አስጠርቶ
ከንቱ እሚያባዝነን የአዱኛ ቆሌ የሀበሻ ሀብሾ፡፡
ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት በአለማቀፍ ደረጃ በተከበረው የማርቲን ሉተር 500ኛ አመት መታሰቢያ ክብረ በአል ሰሞን ደግሞ ማርቲን ሉተር ከሮማ ካቶሊክ ያፈነገጠበትን (protest) የመጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ እውቀት የቀሰመው፤ በዘመኑ በእንግድነት ወደ ጀርመን ሀገር አቅንቶ ከነበረ ሚካኤል የተባለ ኢትዮጵያዊ ዲያቆን እንደነበር David D, Daniels የተባሉ ጸሀፊ በ religionnews.com.com/ October 28, 2017 ገጽ ላይ Martin Luther’s ‘dream church? It wasn’t in Europe የሚል አዲስ መረጃን የገለጠ ጽሑፍ አስነብበዋል፡፡ ይህንን የጸሐፊውን መላ ምት ከ15 ዓመታት በፊት በ1996 ዓ.ም በሀገረ አሜሪካ Minesota ለንባብ የበቃው የኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ደቂቀ እስጢፋኖስ - በሕግ አምላክ›› ትርጉም መጽሐፍ ይጋራዋል። ‹‹ደቂቀ እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ የተነሱት በአጼ ይሥሀቅ (1406 - 1421) ዘመን ሲሆን ማርቲን ሉተር ጀርመን ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ይዞ ከመነሳቱ ከሰላሣ ዓመት ግድም በፊት ነው፡፡ ይላሉ፡፡ የክርስቶስ ተከታይ የነበረው ሰማዕቱ እስጢፋኖስ ሞት በፈረዱበት ገዢዎች ፊት ቆሞ ‹‹ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው?›› እንዳለው ሁሉ፤ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ  ደግሞ ስለ ኢትዮጵያዊያኑ ደቂቀ እስጢፋኖስ ፈር ቀዳጅ ታሪካዊ እንቅስቃሴ ‹‹አሕይዎና ተሀድሶ (Revival and Renewal or  Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠው ሥርዐት ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥኦ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሐሳቦች ናቸው፡፡›› ይላሉ፡፡ የዚህ ታሪካዊና እንደ ሌሎቹ በርካታ ቅርሶቻችንም ሁሉ በአለም ቀደምት የነበረው እንቅስቃሴ መስራች የሆኑት የአባ እስጢፋኖስ ጥቅስም በመጽሀፉ መክፈቻ ገጽ ላይ ግዘፍ ነስቶ እንዲህ ይላል . . . ‹‹ጽኑ ነቢይ ሲነሣ እንደዚሁ ጽኑ ንጉሥ ያስነሣል፡፡››
The same is true! (ቀሺም ነቢይ (ካለ) ሲነሣስ?!)
እኛ ግን ‹‹አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል እርሱንም ታደምጣለህ።›› የትንቢት ቃል የሙጢኝ ብለን እንደ ትናንቱ ዛሬም ነገም እንላለን ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› . . . አሜን፡፡
ገሀዱን እውነት አንክድ ፡ ማወቁንስ እናውቃለን
በእርግጥም ትልቅ ‹‹ነበርን›› - ካመንንም ነን - እንሆናለን፡፡
አዎ...ን
ትናንት ትዝታን እያንጎራጎርን ከናፈቅነው ብሩህ ዘመን
ከነግ ተስፋ ዓለም እንደርሳለን፤
ግምበኞች የናቁትን ድንጋይ ኗሪውን የማእዘን ራስ
በጽናት ዛሬ እንፈልጋለን፡፡

‹‹መቸስ ምን እንላለን›› . . .                       
 (ስንኞቹ ከ‹‹እፍኝ የድንጋይ እርሾ›› 2005 ዓ.ም- ተራኪ ግጥም የተቀነጫጨቡ ናቸው - የፀሐይ ገበታ - ያልታተመ፡፡) የስዕል ምንጭ

Read 484 times