Saturday, 02 February 2019 15:34

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(0 votes)

 ክፍል- ፰ ፍልስፍናዊ ትችት- ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት
           
     በክፍል-7 ፅሁፌ ላይ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ትችቶች እንደመጡበትና ትችቶቹም በዋነኛነት የተሰነዘሩት ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች፣ የታሪክ ፀሐፊያንና የዘመናዊነት አቀንቃኝ ምሁራን እንደነበረ ተመልክተናል፡፡ ከእነዚህ ትችቶች ውስጥም፣ ከኢትዮጵያውያን ፈላስፎች የመጣው ትችት በዋነኛነት ዘርዓያዕቆብን፣ ወልደ ህይወትን፣ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስንና ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን ያካተተ ነው፡፡ የእጓለንና የዳኛቸውን ሐሳቦች ለቀጣዩ ጊዜ እናቆያቸውና፣ በዛሬው ፅሁፌ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ የሰነዘሩትን ትችት እንመለከታለን፡፡
ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት በ17ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በፃፏቸው ሁለት ሐተታዎች ውስጥ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተዋል፤ ለምሳሌ፣ ስለ ሴቶች እኩልነትና ስለ ባርነት፣ ስለ እውነትና አመክንዮ፣ ስለ ምንኩስናና ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር፣ ስለ ተአምራትና ስለ ተረት የመሳሰሉትን፡፡ ሐሳቦቻቸው ፍልስፍናዊ እንደመሆናቸው መጠን፣ የፅሁፎቻቸው አቀራረብ ሙሉ በሙሉ ማህበራዊ ሒስ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከእነዚህ ማህበራዊ ሒሶች ውስጥ የያሬዳዊው ሥልጣኔ ዋነኛ ምሰሶ የሆኑት ተአምራዊነትና ምንኩስና (ብህትውና) ላይ የሰነዘሩት ትችት ግን ከሁሉም ጠንከር ያለና ምህረት የለሽ ነው፡፡
ተአምራዊነትና ብህትውና በውስጡ ሥነ ዓለማዊ (metaphysical)፣ ሥነ ዕውቀታዊ፣ ሥነ ምግባራዊና ኪነ ጥበባዊ አስተምህሮዎችን አካትቶ የያዘ፣ ራሱን የቻለ የተሟላ ንፅረተ ዓለም ነው፡፡ በመሆኑም፣ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተመሰረተበትን ይሄንን የተአምራዊነትና የብህትውና ንፅረተ ዓለም ሲተቹ፣ ንፅረተ ዓለሙ በሥነ ዓለማዊ (metaphysical)፣ በሥነ ዕውቀታዊና በሥነ ምግባር የተደገፋቸውን አስተምህሮቶች ነው የተቹት፡፡ እስቲ ትችቶቹን ለየብቻ እንመልከታቸው፡፡
ተአምራዊነት (ሚስጢራዊነት)
ላይ የሰነዘሩት ትችት
ማንኛውም ማህበረሰብ የሚመሰረተው ‹‹እውነት›› ነው ብሎ በሚያምንበት ነገር ነው፡፡ ይሄም ‹‹እውነት›› ሁለት ዓይነት ነው - አመክኖያዊ እና ተአምራዊ (የመገለጥ) እውነት (Rational and Mystical Truth)፡፡ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ተአምራዊው (የመገለጥ) እውነት ላይ የተመሰረተው ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብ ደግሞ በተቃራኒው የሚደግፈው ‹‹አመክኖያዊውን እውነት›› ነው፡፡
በመሆኑም፣ ዘርዓያዕቆብ ከያሬዳዊው ሥልጣኔ ጋር የፈጠረው የመጀመሪያው ግጭት የሚነሳው ከዚህ ‹‹ተአምራዊ (የመገለጥ) እውነት›› ከሚባለው ነገር ጋር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በዘርዓያዕቆብና በያሬዳዊው ሥልጣኔ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ዲበ አካላዊ (metaphysical) ነው፡፡
እንደ ዘርዓያዕቆብ አመለካከት፤ ህዝብ ‹‹አመክኖያዊውን እውነት›› ከመፈለግ ይልቅ ‹‹ተአምራዊውን እውነት›› ወደ መቀበል ያዘነብላል፤ ምክንያቱ ደግሞ አመክኖያዊ እውነት ድካም አለው፡፡ እናም ማንኛውም ህዝብ በእንደዚህ ዓይነት ድካም ውስጥ ማለፍ አይፈልግም (ሐተታ፣ ምዕራፍ 4)፡፡ ተመሳሳይ ሐሳብ ገብረ ህይወት ባይከዳኝም በ‹‹አፄ ምኒሊክና ኢትዮጵያ›› መፅሐፉ ላይ አንስቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከዚህ ‹‹የተአምራዊነት እውነት›› ጋር ለዘመናት ስለኖሩ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመናት ላይ ከዘመናዊነት ጋር አብሮ ወደ ሀገራችን የገባውን ‹‹አመክኖያዊ እውነት ለመረዳት ሲቸገሩ ታይተዋል›› (ገብረ ህይወት 2002)፡፡ የአፄ ምኒልክ የዘመናዊነት ፕሮጀክት፣ ከኢትዮጵያውያን የገጠመው ዋነኛ ተግዳሮትም ህዝቡ የአውሮፓ ቴክኖሎጂ የሚሰራበትን ‹‹አመክኖያዊ እውነት›› መረዳት አለመቻሉ ነው።
ሆኖም ግን፣ እንደ ዘርዓያዕቆብ አመለካከት ድካምን ጠልቶ ‹‹ተአምራዊ (የመገለጥ) እውነት›› ላይ ብቻ የተመሰረተ ህዝብ ለሁለት ዓይነት ዘላቂ ችግሮች የተጋለጠ ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ እንደዚህ ዓይነት ህዝብ በድብቅ ገንዘብን፣ ሥልጣንና ክብርን ዓላማ አድርገው ለሚንቀሳቀሱ ‹‹የሐሰተኛ መምህራን›› ወጥመድ ጥሩ ታዳኝ ይሆናል (ሐተታ፣ ምዕራፍ 4)፡፡
ሁለተኛ ደግሞ፣ ይሄንን ‹‹የሐሰተኛ መምህራንን›› ትምህርት ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፉትና በስተመጨረሻ የማይነቃነቅና የማይተች እምነት ይሆናል። በሂደትም ‹‹የአባቶቻችን እምነት›› እያሉ እውነተኛነቱን ለማሳየት ምልክቶችን፣ ታሪኮችንና ተአምራትን እየጨመሩ ይባስ ያፀኑታል (ሐተታ፣ ምዕራፍ 4)። እናም ህዝቡ ከእንደዚህ ዓይነት አደጋ ሊድን የሚችለው እያንዳንዱ ሰው ‹‹እውነትን›› በልቦናው ሲመረምርና ‹‹አመክኖያዊ እውነትን›› ብቻ ሲከተል ነው (ሐተታ፣ ምዕራፍ 4)፡፡
እዚህ ላይ ዘርዓያዕቆብ የእውነትን ሚዛን ከሃይማኖታዊ መፃህፍት ይነጥቅና ለእያንዳንዱ ‹‹ግለሰብ›› ያድለዋል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ዘርዓያዕቆብ ‹‹ግለሰብን›› በሥነ ምግባር፣ በእውነትና በዕውቀት ጉዳዮች ላይ የመጨረሻው ዳኛና ባለ ሥልጣን አድርጎ ይሾመዋል፡፡ ይሄ የዘርዓያዕቆብ አመለካከት፣ ከአውሮፓ የ18ኛው ክፍለ ዘመናት አብርሆት (Enlightenment) ዘመን ፍልስፍና ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፤ ሥነ ምግባርን፣ እውነትንና ዕውቀትን በሞግዚት ሲያስተዳድር ለነበረው ለያሬዳዊው ሥልጣኔ ግን ዱብዕዳ ነው፡፡
ሌላው፣ ይሄ ‹‹የእውነት ጥያቄ›› (question of Truth) በጣም ወሳኝ የሚሆነው በራሱ አምሳል የታሪክ ፀሐፊዎችን መፍጠር መቻሉ ነው፡፡ ‹‹አመክኖያዊ እውነትን›› የሚከተሉ ህዝቦች፤ ‹‹በገለልተኛነት›› ሙያዊ ሥነ ምግባር መርህ የሚመሩ የታሪክ ፀሐፊዎችን ሲፈጥሩ፤ ‹‹‹‹ተአምራዊ እውነትን›› የሚከተሉ ህዝቦች ግን በምንም ዓይነት መርህ የማይመሩ ‹‹የተአምራት ፀሐፊዎችን›› ፈጥረዋል›› (ሐተታ፣ ምዕራፍ 5)። ያሬዳዊው ሥልጣኔ፤ በ20ኛው ክፍለ ዘመናት ከተሰነዘረበት ትችቶች አንደኛው ‹‹አድሎአዊ የታሪክ አተራረክ›› ላይ እንደሆነ አለቃ አፅመ ጊዮርጊስንና ገብረ ህይወት ባይከዳኝን በመጥቀስ በክፍል-7 ፅሁፌ ላይ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡
ብህትውና ላይ የሰነዘሩት ትችት
ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከተመሰረተባቸው ሦስት አምዶች ውስጥ በዘርዓያዕቆብና በወልደ ህይወት ምህረት የለሽ ትችት የደረሰበት ‹‹ብህትውና›› ነው፡፡ ትችቶቻቸውንም፣ ዘርዓያዕቆብ በሐተታው ምዕራፍ 5፣7 እና 8 ላይ ያሰፈረ ሲሆን፣ ወልደ ህይወት ደግሞ በሐተታው ምዕራፍ 13 እና 24 ሰፋና ጠንከር አድርጎ ፅፎታል፡፡
ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት በ17ኛው ክፍለ ዘመናት ሲነሱ፣ ብህትውና እንደ ባህል፣ በያሬዳዊው ሥልጣኔ ውስጥ የ1100 ዓመታት ዕድሜ ነበረው፡፡ በዚህም የተነሳ የብህትውና አሻራ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ጠንካራ ሃይማኖታዊ፣ ኪነ ጥበባዊ፣ ባህላዊና ተቋማዊ መሰረትን ይዞ ነበር፡፡
ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ‹‹የተፈጥሮን ህግ›› ምርኩዝ ፣ ብህትውና የትውልድ ቀጣይነት ላይ፣ የግለሰብ ደስታና ጤና ላይ፣ እንዲሁም የህዝቦች ብልፅግናና ዓለማዊ ህይወት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ክፉኛ የተቹት ሲሆን፤ ትችታቸውም ‹‹የብህትውና አስተምህሮ ምንጭ›› የሚሉት ‹‹የማቴዎስ ወንጌል›› ድረስ ይሄዳል፡፡ በዚህም ‹‹ብህትውና ይበልጥ ያፀድቃል›› የሚለውን አባባል፤ ‹‹ከተፈጥሮ ህግ ጋር ቅራኔ ስላለው፣ ትዕዛዙ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሊሆን አይችልም›› በማለት በሐተታቸው ውስጥ ብህትውናን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ውጭ አድርገውታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ሐሳብ ማንበብ የሚፈልግ ካለ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› የሚለውን መፅሐፌን ይመልከት፡፡
ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት፤ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ላይ የሰነዘሩትን ትችት አልጨረስንም። በክፍል-9 ፅሁፌ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት በስነ ምግባርና በመንፈሳዊ ህይወት አስተምህሮ እንዴት ከያሬዳዊው ሥልጣኔ አስተምህሮ ሊነጠሉ ቻሉ? የትችታቸውስ ዲበ አካላዊ (metaphysical) መነሻ ምንድን ነው? የሚሉትን ሐሳቦች እንመለከታለን፡፡
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

Read 1077 times