Print this page
Saturday, 02 February 2019 15:26

2 ቢ. ዶላር በሚመነዘርበት ገበያ፣ “10ሺ ዶላር ከየት መጣ?” በሚል ጥያቄ አገር ይወዛገብ?

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

• “እዚህ 10ሺ ዶላር፣ እዚያ 20ሺ ዶላር እየተያዘ ነው። ይሄ ሁሉ ዶላር ከየት ነው የሚመጣው? በምርመራና በሕጋዊ እርምጃ...” ... ይሄ ፓርላማ ውስጥ የተስተጋባ ጥያቄ ነው።
 • እንዴት ነው ነገሩ። ከዳያስፖራ እየተላከ ከሚመጣው ዶላር ውስጥ ግማሹ የሚመነዘረው፣ በባንክ ሳይሆን በጥቁር ገበያ እንደሆነ ጠፍቷቸው ነው?
 • ታዲያ፣ ከዳያስፖራ የተላከ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከበርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኑሮ ጋር የተቆራኘ ነው - ከጥቁር ገበያውም እንዲሁ።
 • በጥቁር ገበያ የሚመነዘረው ምን ያህል ነው? ከ2 ቢሊዮን የሚበልጥ ዶላር በዓመት። ታዲያ፣ “20ሺ... ዶላር ከየት መጣ?” የሚል ጥያቄ፣ ምን የሚሉት ጥያቄ ነው?
 • በየ3ደቂቃው... ዓመቱን ሙሉ፣ በየእለቱ ቀኑን ሙሉ፣ በየ3 ደቂቃው ከ20ሺ ዶላር በላይ የሚመነዘርበት ገበያ ነው - ጥቁር ገበያው።
      ዮሃንስ ሰ


    “ላለማወቅ የመሳከር አዙሪት” ውስጥ እየሰጠምን እስከመቼ መቀጠል እንደምንችል እንጃ! የጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሬ፣ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ የአገሪቱ ነባርና የዘወትር መዋዕል እንደሆነ እየተዘነጋ፣ አንዳች የማይታወቅ እንግዳ የመጣብን፣ ያልተጠበቀ ዱብዳ የወረደብን ማስመሰል፣ በዚህም መወዛገብና የተሳከረውን አገር ወደባሰ ጡዘት ማጣደፍ ምን ይጠቅማል?
ከዳያስፖራ እየተላከ ከሚመጣው ዶላር ውስጥ፣ ምን ያህሉ ነው በባንክ የሚመነዘረው? ገሚሱ፣ በባንኮች አስተላላፊነት እየመጣ ይመነዘራል። ገሚሱ ግን በባንክ የሚመጣና የሚመነዘር አይደለም። አንዳንዴም ከግማሽ በላይ የዳያስፖራ ዶላር፣ በጥቁር ገበያ የሚመነዘር መሆኑ፣ ለበርካታ ዓመታት የሚታወቅ ነባር እውነታ ነው። እና ታዲያ፣ ለምን አንዳች ድብቅ ወንጀል፣ ድንገት የተፈጠረ እናስመስላለን? ከዳያስፖራ፣ ከአሜሪካ ወይም ከአረብ አገራት፣ ዶላር የተላከላቸው ቤተሰቦችና ወዳጆች፣... ማለትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ በጥቁር ገበያ የሚጠቀሙት።
በሌላ አነጋገር፣ በየሱቁ፣ በየቅያሱና በጓዳው እለት በእለት የሚካሄደው የዶላር ምንዛሬ፣ እንደአስተላላፊና እንደአገናኝ ሆነው በሚሰሩ አቀባባዮችና ነጋዴዎች በኩል የሚከናወነው የጥቁር ገበያ ምንዛሬ፣ ለበርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ “ቅንጣት ታክል” እንደ ወንጀል የሚቆጠር ድርጊት አይደለም። የሌላ ሰውን ንብረት ሳይነኩ በፍቃደኝነት የሚገበያዩበት እንጂ፣ ከሰው አታልለውና አጭበርብረው ንብረት ለመውሰድ የሚያሰፈስፉበት ገበያ ሆኖ አይታያቸውም። ለመስረቅ ወይም ለመዝረፍ የሚዘምቱበት የቅሚያ መናሃሪያም አይደለም።
ለሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ የዶላር ምንዛሬ ጥቁር ገበያ ማለት፣ ከሌላው ገበያ ብዙም የተለየ አይደለም - የግዢና የሽያጭ ገበያ ነው። ከዳያስፖራ የተላከላቸው ዶላር፣.... የ”አገር ዶላር” አይደለም። የግላቸው ንብረት፣ የግላቸው ገንዘብ እንዲሆን የተላከ፣.... የጎደለ የወር አስቤዛ የሚያሟሉበት፣ የደከመውን ኑሮ የሚደግፉበት፣ መጦሪያ ወይም የኪስ መደጎሚያ ነው። የእነዚህ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ገበያ ሆኗል - የዶላር ምንዛሬ ጥቁር ገበያ። ይሄ፣ ጥሬ እውነታ ነው - ቢጥመንም ባይጥመንም፣ ብንደግፍም ባንደግፍም። ይልቅስ፣ እውነታውን ተገንዝበንና ምንነቱን አውቀን ልናስብበት እንችላለን። ይሄ የምርጫ ጉዳይ ነው - ለዚያውም የሚበጅ አማራጭ ነው።  አልያም ላለማወቅ በጭፍንነት የምንሳከርበት ሰበብ ሊሆንልን ይችላል። ይሄም የምርጫ ጉዳይ ነው - አጥፊ አማራጭ ቢሆንም። የትኛው የሚበጅ፣ የትኛው የሚያጠፋ እንደሆነ መለየትና መምረጥ ደግሞ፣ የእያንዳንዱ ሰው ሃላፊነት ነው።
ከዳያስፖራ እየተላከ ለቤተሰብና ለወዳጅ ከሚመጣው ዶላር ውስጥ፣ የቱን ያህል ከበርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ጋር እንደተቆራኘ ለመገንዘብ የሚፈልግ ሰው፣ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣውን ዓመታዊ ሪፖርት ማየት ይችላል። በውጭ አገር የሚኖሩ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩት ገንዘብ፣ በየዓመቱ እየጨመረ እንደመጣና  በ2010 ዓ.ም የተላከው ገንዘብ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገልፃል የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት። (በጥር ወር መግቢያ ላይ የወጣው አዲስ ዓመታዊ ሪፖርት ገፅ 63፣ ገፅ 77)።
ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በዓመት! በ2010 ዓ.ም!
በምን ያህል ፍጥነት እየጨመረ እንደመጣ ተመልከቱ።
የዛሬ 15 ዓመት፣ ከውጭ አገር የተላከው ዶላር፣ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በታች ነበረ። በእርግጥ ያኔም እየጨመረ ነበር። ነገር ግን፣ ከውጭ እየተላከ የሚመጣው ዶላር በየዓመቱ ቢጨምርም፣ በ1998 ዓ.ም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በታች እንደነበር የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያመለክታል (በ2000 ዓ.ም የወጣው የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት)።

        ከውጭ አገር የተላከ ገንዘብ
1998    በቢ. ዶላር    0.74
1999    በቢ. ዶላር    1.2
2000    በቢ. ዶላር    1.8
2001    በቢ. ዶላር    1.8
2002    በቢ. ዶላር    1.8
2003    በቢ. ዶላር    1.9
2004    በቢ. ዶላር    1.9
2005    በቢ. ዶላር    2.5
2006    በቢ. ዶላር    3.0
2007    በቢ. ዶላር    3.8
2008    በቢ. ዶላር    4.4
2009    በቢ. ዶላር    4.4
2010    በቢ. ዶላር    5.1
 ከ2005 ወዲህ ብቻ፣ ከውጭ የሚመጣው ገንዘብ ወደ እጥፍ ጨምሯል። ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር ወደ 5.1 ቢሊዮን ዶላር። ከአገሪቱ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት ጋር ሲነፃፀር ወደ 10 በመቶ ይጠጋል። ከአገሪቱ የምርት ኤክስፖርትም እጅጉን በልጦ እጥፍ ለመሆን ተቃርቧል።

ምናለፋችሁ፣ ትልቅ ገንዘብ ነው ከዳያስፖራ እየመጣ ያለው - ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅም ጋር ስናስተያየው ማለቴ ነው።
ታዲያ፣ ይሄ ሁሉ ዶላር፣ መምጫ መንገዱ ይለያያል። መንግስት በሚፈልገው መንገድ በባንክ በኩል ብቻ አይደለም የሚመጣው። ገሚሱ በባንክ በኩል ይመጣል። ገሚሱ ግን፣ በሰው በሰው፣ በጓደኛ በስራ ባልደረባ በኩል፣ አልያም በአቀባባይ በመልእክተኛ በኩል እንደሚመጣ ይታወቃል። እነዚህ የመላኪያ መንገዶች በጭራሽ ሚስጥር አይደሉም። ምግብ የመብላት ውሃ የመጠጣት ያህል የሚታወቁና የተለመዱ የዶላር መተላለፊያዎች ናቸው- ባንክ የማይነካቸው ዶላር የመላኪያ መንገዶች። ለነገሩ፣ በየዓመቱ የሚታተሙት የብሔራዊ ባንክ ሪፖርቶችንም መመልከት ትችላላችሁ። ምን ያህሉ ዶላር በባንክ እና ያለ ባንክ በተለያዩ መንገዶች እንደሚመጣ የሚገልፁ መረጃዎች በብሔራዊ ባንክ በሪፖርቶች ተጠቅሷል (ከ2000 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በወጡ ስምንት ዓመታዊ ሪፖርቶች ውስጥ በዝርዝር በቁጥር ተገልፀዋል። ሚስጥርም ድብቅም እንዳልሆነ ደጋግሞ መናገር ካስፈለገ ማለቴ ነው)።    
የመላኪያ መንገዱ የመለያየቱ ያህል፣ የዶላር አመነዛዘሩም ይለያያል። መንግስት በሚቆጣጠረውና መንግስት በሚተምነው የምንዛሬ መጠን ብቻ አይደለም፣ ዶላሩ የሚመነዘረው።
ከዳያስፖራ የተላከ ዶላር፣ ገሚሱ በባንክ በኩል እየመጣ፣ በመንግስት ተመን ይመነዘራል።
ገሚሱ ደግሞ፣ በጥቁር ገበያ ይመነዘራል። ዛሬ፣ በዓመት ከውጭ እየተላከ ከሚመጣው ዶላር ውስጥ፣ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ፣ በጥቁር ገበያ ይመነዘራል። ይሄ፣ ድብቅ ሚስጥር አይደለም። ምርምር የማያሻው፣ ገና ድሮ ታይቶ፣ ታውቆ፣ ተስፋፍቶ ከአገሪቱ የዘወትር አኗኗር ጋር የተዋሃደ የምንዛሬ ገበያ ነው - ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የሚገበያዩበት።  
በአጭሩ፣ በሰው በሰው፣ በአቀባባይ በመልእክተኛ በኩል ከዳያስፖራ ዶላር የተላከላቸው ኢትዮጵያውያን፣... ግማሽ ያህሉ፣ በጥቁር ገበያ ነው ገንዘባቸውን የሚመነዝሩት።
በተለይ፣ መንግስት አለቅጥ ገንዘብ እያሳተመ ብር በሚረክስበት ወቅት ደግሞ፣ ጥቁር ገበያው ይደራል። በእርግጥ፣ ለከት የለሽ የገንዘብ ሕትመት፣ የዜጎችን ኑሮ በዋጋ ንረት ከማናጋትም አልፎ፣ ኢኮኖሚን እያዛባና እያቃወሰ ለዓመታት የሚዘልቅ መዘዝ ስለሚያስከት ነው፣ መንግስት ከእንደዚህ አይነት አጥፊ የገንዘብ ሕትመት መቆጠብ የሚገባው። አስቀድሞ ከጥፋት መቆጠብ ይሻላል። ገንዘብ ታትሞ ብር ከረከሰ በኋላ ግን፣ በዚህም ሳቢያ የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ከናረ በኋላ፣... የዶላርን የምንዛሬ ዋጋ በድሮው የዋጋ ተመን ጨምድዶ ለማቆየት መንግስት መንገታገቱ፣ ከጉዳት በስተቀር ጥቅም የለውም። እንደሌለውም በተደጋጋሚ ታይቷል።
ብር አለቅጥ እየታተመ ከረከሰ፣ እንደሌላው የግብይት ዋጋ ሁሉ፣ የዶላር ዋጋም ይንራል። የሌሎች ሸቀጦችን ዋጋ ለመቆጣጠርና ጨምድዶ ለማቆየት የሚካሄድ የመንግስት ዘመቻ፣ ወደባሰ የገበያ ግርግርና መናጋት ሲያመራ አይተን የለ? የዶላር የምንዛሬ ዋጋ ላይ የሚደረገው ቁጥጥርም እንዲሁ፣ ችግሮችን ያስከትላል። ሁለት መዘዞችን መጥቀስ ይቻላል።
ባለፉት 6 ዓመታት እንዳየነው፣ ኤክስፖርትን አደንዝዞ የኋሊት እንዲንሸራተት ካደረጉት ዋነኛ መንስኤዎች መካከል፣ “የብር ኖር በገፍ እያተመና እያረከሰ፣ የዶላር የምንዛሬ ዋጋን ግን ጨምድዶ የመቀጠል የመንግስት ምኞት”፣ አንዱ የጥፋት መንስኤ ነው። የዶላር ጥቁር ገበያ የሚስፋፋውም በዚሁ ሰበብ ነው። እንዴት?
መንግስት፣ በአነስተኛ የምንዛሬ ዋጋ፣ ከዜጎች ዶላር ለመግዛት ይመኛል - በገበያ ዋጋ ሳይሆን ራሱ በሚተምነው አነስተኛ ዋጋ። ከዳያስፖራ ገንዘብ የተላከላቸው ዜጎችስ፣ ዶላራቸውን በመንግስት ተመን ለመሸጥ ፈቃደኛ ናቸው?
ዶላር የተላከላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ዶላራቸውን ለመሸጥ እንደማንኛውም ገበያተኛ፣ ደህና ዋጋ ለማግኘት ገበያውን ዞር ዞር ብለው ቢመለከቱና ቢያፈላልጉ ይገርማል? ደህና የገበያ ዋጋ ስለሚያገኙም ነው፣ ግማሹ ያህል የዳያስፖራ ዶላር በጥቁር ገበያ የሚመነዘረው።
የዚህን ያህል ከሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ጋር ለዓመታት የተጋመደ የዶላር ምንዛሬ ገበያ፣ “ማንም ያልደረሰበት ድብቅ ሴራ” የሆነብንና ሚስጥሩ ድንገት የተገለጠልን ይመስል፣ “10ሺ ዶላር.... 20ሺ ዶላር ተያዘ። ከየት መጣ?” እያልን የመወዛገቢያ ርዕስ ልናደርገው አይገባም ነበር። የውዝግብና የውግዘት፣ የውንጀላና የዛቻ ሰበብ ካናፈቀን በቀር፣ ከ20ሺ ዶላር.... “250 እጥፍ” የሚበልጥ ዶላር ነው በየቀኑ በኢትዮጵያ ጥቁር ገበያ የሚመነዘረው።
በየቀኑ.... 5.5 ሚሊዮን ዶላር ይመነዘራል። ከጥዋት እስከ ምሽት፣ በ12 ሰዓታት ውስጥ 5.5 ሚሊዮን የሚመነዘርበት ከሆነ...
በየ3ደቂቃው... ዓመቱን ሙሉ በየእለቱ፣ ቀኑን ሙሉ በየ3 ደቂቃው ከ20ሺ ዶላር በላይ የሚመነዘርበት ገበያ ነው - ከሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኑሮ ጋር የተቆራኘው የምንዛሬ ጥቁር ገበያ። በዚህ መሃል ድንገት ተነስተን፣ “አንድ ሰው 10ሺ ዶላር ይዞ ተገኘ።.... ጉድ!.... ጉድ!” ብለን አገሬውን የምንቀውጥ ከሆነ፣.... ከምር አገሬውን አናውቀውም የሚያስብል ብቻ ሳይሆን፣ ጨርሶስ የማወቅ ፍላጎት ርቆናል ወይ? ወይም ከእውቀት ለመሸሽ እየራቅን ነው ወይ? ያስብላል።


   ከውጭ አገር የተላከ ገንዘብ

1998 በቢ. ዶላር 0.74
1999 በቢ. ዶላር 1.2
2000 በቢ. ዶላር 1.8
2001 በቢ. ዶላር 1.8
2002 በቢ. ዶላር 1.8
2003 በቢ. ዶላር 1.9
2004 በቢ. ዶላር 1.9
2005 በቢ. ዶላር 2.5
2006 በቢ. ዶላር 3.0
2007 በቢ. ዶላር 3.8
2008 በቢ. ዶላር 4.4
2009 በቢ. ዶላር 4.4
2010 በቢ. ዶላር 5.1

Read 2770 times