Print this page
Monday, 04 February 2019 00:00

የቀሺም ጫማ ጦስ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንድ ወዳጃችን፤ በኑሮ መሰላል ላይ የተሰቀለ ጓደኛውን ከረጅም ጊዜ በኋላ መንገድ ላይ ያገኘዋል፡፡ ወዳጃችን ሆዬ፤ አይደለም በመሰላል ሊወጣ፣ መሰላሉ አጠገብ ገና አልደረሰም፡፡ እና ጓደኝው… “ከስንት ጊዜ በኋላ ተገናኝተንማ ምሳ ሳንበላ አንለያይም፣” ብሎ ሸላይ ሬስቱራንት ይዞት ይገባል፡፡ ይሄ ሰዋችን አጋጣሚ ሆኖ አለባበሱ እንደነገሩ ነበር፡፡ ታዲያላችሁ፣ ሁለቱ ሲገቡ የተወሰኑ አስተናጋጆች፣ “ያዩኝ አስተያየት ሞራሌን ነካው…” ብሏል፡፡ አለ አይደል…“ምስኪን! መንገድ ጠፍቶት ይሆናል እዚህ የገባው!” አይነት አስተያየት፡፡ ምግቡ ከቀረበ በኋላም ቢሆን በሚታወቁ ተጠቃሚዎችና እግር በጣላቸው ተጠቃሚዎች መሀል የመስተንግዶ መድልዎ ነበር…” ብሏል ወዳጃችን፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት እኮ ኪስ ሳስቶ የሆነች ጥብስ ቢጤ ሲያምረን የወዳጅ ጋባዥ ፍለጋ እንሄድ ነበር፡፡ ደግሞም ይሳካልም… እናማ፣ እጩ ጋባዣችሁን ስታገኙት ምን ትሉት መሰላችሁ… “የሚገርምህ ነገር በቀደም ሰዎች ስለ አንተ ሲያወሩ ሰምቼ…” ብላችሁ ‘ማስተር ኪይ’ ትጠቀማላችሁ። እሱም… “ለምን ምሳ እየበላን አናወራም…” ይላል። ‘ስትራቴጂው’ ሠራ ማለት አይደል!
ልጄ ዘንድሮ፤ ያቺ ‘ማስተር ኪይ’ ከአገልግሎት ውጪ ሆናለች፡፡ ታዲያላችሁ… “የሚገርምህ ነገር በቀደም ሰዎች ስለ አንተ ሲያወሩ ሰምቼ…” ብትሉት… “አንተም ፌስቡክ ላይ ተጥደህ መዋል ጀመርክ እንዴ!” ቢላችሁ ነው፡፡ አዎ፣ ብዙ ነገር ተለዋውጧል፡፡
የምር ግን… ይሄ የመስተንግዶ ነገር ወዳጃችን እንዳለው፣ አንዳንድ ደህና የሚባሉ ቦታዎች ሁሉ ትንሽ ፕሮፌሽናሊዝም የሚጎድለው ይመስላል፡፡ እንበልና ከሰማይ ዱብ ያለ የሚመስል… “እስቲ ዛሬ ምሳ ልጋብዘህ…” የሚል ወዳጅ ይገኛል። እናላችሁ…አሪፍ የሆነ ሬስቱራንት ይዟችሁ ይገባል፡፡ አለ አይደል… “የትረምፕ ብርድ ልብስ እንኳን እንዲህ አይመችም…” የሚሉት አይነት ምንጣፍ፡፡ ገና ስትገቡ መጀመሪያ ምናችሁ ቢታይ ጥሩ ነው…ምስኪን ጫማችሁ! በፊት እኮ ብራስሌት፣ ጎልድ ቼይን ምናምን ነበር የሚታየው፡፡ ደግነቱ ያኔ መዋዋስ ይቻል ነበር። ዘንድሮ ቀሺም ጫማ አንለዋወጥ ነገር ሆኖብን ተቸግረናል፡፡ እናማ፣ የአስተናጋጆቹ አስተያየት… “ፋራ እዚህ ከሚገባ ይቺ ምስጥ ሊበላት ጀምሮ የተጠየፋት የምትመስል ጫማውን አይቀይርም ነበር!” አይነት ነው፡፡ “ጫማ አይቀይርም ሲሉ የአምስት መቶ ብር ጫማ ከሚያደርግ መቶ ሀምሳ ብር ጨምሮ የተሻለ ጫማ አይገዛም ነበር?” ማለታቸው አይደለም፡፡ “ይሄንን ወንዝ ወስዶ ጥሎ ለምን የፋይቭ ታውዘንዱን አይገዛም?” ማለታቸው ነው፡፡ (የምር ግን ሀሳብ አለን….የእኔ አይነቱ ምስኪን፣ ምንጊዜም ከኪሱ የማትጠፋ ማሳሰቢያ ጽፎ ቢይዝ አሪፍ ነው… “የኢመርጀንሲ ማሰሳቢያ፣ ድንገት ዝቀተኛው የጫማ ዋጋ አምስት ሺህ ብር የሆነበት ሱቅ ስገባ ከታየሁ፣ በአፋጣኝ የሀኪም ምክር ወደ ማገኝበት እንድወሰድ፣” የሚል ጽሁፍ ያስፈልገናል፡፡ አሁን፣ አሁን አይደለም ሱቆቹ ውስጥ መግባት በመስኮታቸው ስናልፍ፤ “ቺስታዎች! በ24 ሰዓት ካሜራ አይታ ውስጥ ናቸው” የሚባልብን ይመስለናል፡፡) ያፈጠጡባችሁን አስተናጋጆች በሆዳችሁ... “የጫማዬን ቀን ይስጣችሁ!” እያላችሁ ትቀመጣላችሁ። መቀመጫ እንዲህ ይመቻል! “ወንበራቸው እንዲህ የተመቸ፣ አልጋቸው ምን ሊሆን ነው?” (ከርሞም ቢሆን ከአልጋ ጋር የተያያዘችው ጥያቄ ብቅ ማለቷ አይቀርም ብለን ነው!) እናማ...አስተናጋጅ አጠገባችሁ መጥቶ ይገተራል፡፡ አይቆምም...ይልቁንም ያላወራረደው ግዝት ያለበት ይመስል ይገተርና ዝም ብሎ ያያችኋል፡፡ “እንኳን ደህና መጣችሁ” “ሬስቱራንታችን በመምጣታችሁ ደስተኞች ነን” ብሎ የ‘ሴልስ ትህትና’ የለ! አኮሰታተሩ… ምን አለፋችሁ በመስከረም ጠፍቶ በነሀሴ ጓሮ የተገኘ የጨርቅ ኳስ ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡ ጠረዼዛው ላይ ያለው ሜኑም ያፈጥባችኋል፡፡ “ምን፣ ምን አለ?” ስንል፤ አስተናጋጇ አስራ አምስት አይነት ምግብ ትዘረዝርና “ለጊዜው ግን ቀይ ወጥና በየአይነቱ ብቻ ነው፣” መባልን ለምደን ሜኑ መኖሩን ምነዋ አንረሳ!
አስተናጋጁ እንደተገተረ ሁለት ጠረዼዛዎች ራቅ ብሎ ሌሎች አራት ያህል ሰዎች ይቀመጣሉ። ምን አለፋችሁ… ሦስት አስተናጋጆች ሪባን ሊበጥሱ የተቃረቡ የመቶ ሜትር ሯጮች ይመስል ወደዛው ጠረዼዛ ይንደረደራሉ። (እናንተ አኮ ፈጥኖ የሚታዘዛችሁ ጠፍቶ፣ ታይላንድ ‘ለእንትን ቱሪዝም’ ለሄዱት ባለቤትየው ቴክስት ምሴጅ ልትልኩ ምንም አልቀራችሁ!) የተገተረው አስተናጋጅም ወደዛው አየት ያደርግና ፊቱ ይቀጭማል፡፡ አሁን ጨርቅ ኳስ ብቻ ሳይሆን በአሮጌ ካልሲ የተሠራ ጨርቅ ኳስ መሆኑ ያስነቃበታል፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) ምን ያድርግ! ኪሳችሁ በብር እጥረት ወና ከሆነው ከእናንተ ጋር ሆኖ ወፍራም ቲፕ ሲያመልጠው… አለ አይደል… ቢሆንለት “ወይ እድሌ!” ብሎ ስቅስቅ ብሎ ቢያለቅስ አይገርምም፡፡ የቀሺም ጫማ ጦስ!
“ምን ልታዘዝ?” ብራቮ! ለካስ አሰተናገጁ ድምጽ አለውሳ!
“በል እዘዝ…” ይላችኋል…ያለ ‘ነጻ አውጪ ድርጅት’ ነጻ ያወጣችሁ ጋባዣችሁ፡፡
መቼም ጊዜው ከፍቷል፡፡ ገንዘብ አለው ይባል የነበረው ሰው ሁሉ ከቡና ቤት ወደ ጠላ ቤት ‘ኤክሶደስ’ አይነት ነገር ላይ ባለበት ሰዓት፣ ጋባዣችሁን መጉዳት አትፈልጉም፡፡ ምን በወጣው! ግማሽ ሻይ በሎሚ ቢያዝላችሁ እንኳን እዛ አይነት ሬስቱራንት ይዞ መግባቱ በራሱ ግብዣ ነው፡፡  
“ለአኔ ቦዘና ሹሮ፣” ትላላችሁ፣ በጣም ትህትና በሞላው አነጋገር፡፡ (የቀሺም ጫማ ጦስ!) አይፈረድባችሁም፣ ሹሮ እንደ ድሮው መስሏችሁ ነው፡፡ “እስቲ እዛች አሮጌዋ ድስት ውስጥ የተረፈች ሹሮ እንዳለች እዪልኝ፣” ይባልላት የነበረችው እንደ ሜሲ ፎቶ፣ ከሰፊው ህዝብ ቤት የማትጠፋው ‘ዘ ሴም ኦልድ ሹሮ’ መስሏችሁ ነው፡፡ ማለትም እንኳና ቦዘና ሆና ስጋ ጣል፣ ጣል ሊደረግባት፣ ሽንኩርት እንዳለባት ለማወቅ እንኳን ኸብል የሚያስፈልጋት የምትመስል፡፡
“ኋት!” ሦስት ወር ‘ሴቭ’ አድርጎ የጠረዼዛው ‘ጥዳት’ ጢም የሚያስላጭ ቤት ያመጣችሁ…ለሹሮ! “ስማ ነፍስ ያለው ምግብ እዘዝ አንጂ!”
ነፍስ ያለው! ይሄም በዛ…ሹሮ ከዘጠኝ ነፍስ ሰባቱን ይዛም እንዲህ ማጣጣል ውለታ መርሳት ይሆናል፡፡ የአስተናጋጁን አስተያየትማ መተዉ ይሻላል፡፡ ቢችል ኖሮ በሬስቱራንቱ በር ላይ የሚተላለፉ ደንብ ማስከበሮች ቢጠራ በወደደ፡፡
“ደንብ ማስከበር፣ እባካችሁ ሬስቱራንቱ ውስጥ ችግር ገጥሞናል፡፡”
“ምን ሆናችሁ? የሚረብሽ ሰው አለ እንዴ!”
“መረበሽ ሳይሆን ይሄ ግለሰብ ቦዘና ሹሮ አቅርቡልኝ በማለት በሬስቱራንታችን ስምና ዝና ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡” የቀሺም ጫማ ጦስ!
አሁንም ሜኑው ትዝ ስለማይላችሁ ምን እንደምታዙ ማሰላሰል ትቀጥላላችሁ፡፡ በገባችሁባቸው ምግብ ቤቶች ከአምስት አይነት በላይ ምግብ ያለበት ገጥሟችሁ አያውቅማ! ይሄኔ ጋባዥ ጣልቃ ይገባል…
“ለምን ከሜኑው ላይ አትመርጥም!  ደግሞ ምስር አልጫ ብለህ እንዳታዝ…” ይስቃል፡፡
“እሺ፣ ፒፐር ስቴክ ይሁንልኝ፡፡” ፒፐር ስቴክ እኮ ለመጨረሻ ጊዜ ከቀመሳችሁ አስራ አንድ ዓመት ሊሞላ አስራ አንድ ቀን ነው የቀረው፡፡ ጋባዣችሁ አተረፋችሁ! እሱም የእናንተ ቢጤ ያዛል፡፡
“የሚጠጣ…” ይላል አሳላፊው፡፡ ትእዛዝ እየጠየቀ ሳይሆን… “የሚጠጣ ለሚለው ቃል ሦስት ተመሳሳይ ቃላትን ስጥ…” የሚል  የጠመኔ ብናኝ ያሰለቸው አስተማሪ ይመስላል፡፡
እናላችሁ…ምንም እንኳን ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ደረጃቸው ዝቅተኛ በማይባሉ ሬስቱራንቶች ሁሉ በአስተናጋጆች በኩል የፕሮፌሽናሊዝም ችግር ይታያል፡፡ የምር እኮ… በአንዳንድ ስፍራዎች…ሳትጋበዙ የማታወቁት ሰው መኖሪያ ቤት የዘመድ ጉባኤ እንደተሰበሰበ ‘ድንኳን ሰብራችሁ’ የገባችሁ ነው የሚመስላችሁ። የአንተ ፒፐር ስቴክ ገና ሳይደርስ እነኛዎቹ ጠረዼዛ ላይ ግን… ምን አለፋችሁ…ሙሉ ኪችኑ የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ የቀሺም ጫማ ጦስ!
እናላችሁ… ፒፐር ስቴካችሁን ቀመስ ታድርጉና ከእርግብገቢታችሁ እስከ ምናችሁ ይነዝራችኋል፡፡ ፒፐር ስቴክ ስላላችሁ አንደኛውን ቃሪያውን ጠብሰው አመጡት እንዴ!
“በዓመት አንድ ጊዜም ቢሆን እንዲህ ዘና እንበል እንጂ” ይላል ጋባዥ፡፡ ደግነቱ ወዳጃችሁ ከገርልፍሬንዱ ጋር በሳምንት አንድ ቀን፣ አንድ ፍርፍር ለሁለት እየበላ፣ እናንተ ፊት “ቺክን ብሬስትና አሮስቶ እንደሰለቸኝ!” አይነት አሳታሚ ያጣ ፊክሺን ነገር አያደርግባችሁም፡፡
“በዓመት አንዴ ነው የምትመጣው ማለት ነው?” ትላላችሁ ጨዋታ ለማሳመር፡፡
“ያውም እድለኛ ከሆንኩ…አንተስ?”
“እኔ…ቆይ እስቲ፣ ታስባላችሁ፣ ደቡብ አፍሪካ መክፈቻ ጨዋታ መች ነበር!” መጥናችሁ ትስቃላችሁ፡፡ ከዛኛው ቡድን ግን ሳህኖችን የሚያንቀጠቅጥ የጋራ ሳቅ ኤሩን ይሞላዋል። የምር ግን እንደ ምግብ ቤት ባሉ የህዝብ መገልገያዎች የአንዳንዶቻችን ባህሪይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አለ አይደል…ብሄራዊ ቲያትር ኋላ ወንበር ላይ የተቀመጥን ነው የሚመስለው፡፡ እናላችሁ… በሬስቱራንቶች፣ በምግብ ቤቶችና በመሳሰሉት የተሻለ ሙያዊ አገልግሎት ያስፈልገናል… በቀሺም ጫማ ጦስ አታዳሉብንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!  

Read 7130 times