Saturday, 02 February 2019 14:45

ኦነግ ሼኔ- “የንጉስ ልጅ”

Written by  መስከረም አበራ
Rate this item
(2 votes)

የተቀየረውን ኢህአዴግ፣ ከከራሚው ኢህአዴግ የሚለየው አንድ ቁም-ነገር፣ ለተቀናቃኞቹ የሚያሳየው ሆደ-ሰፊነት ነው፡፡ ይህ አካሄዱ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የሚሰበስብበት አዋጭ መንገድ ነው፡፡ አዲሱ ኢህአዴግ ሊመሰርተው እንደሚሞክረው አካታች ፖለቲካዊ ንፍቀ-ክበብ፤ አማራጭ ፖሊሲ ይዞ መጥቶ፣ ሰርቶ ለማሸነፍ ለተፈጠረ የፖለቲካ ሃይል ብቻ የሚመች ነው፡፡ የወትሮው ኢህአዴግ ችኩልና ጠላት ያለ መናቅ አባዜ ትንሹንም ትልቁንም ጠላቱን ሲያስር ሲፈታ፣ ሳያውቀው ለትንንሽ ጠላቶቹ የፖለቲካ ኪሎ ሲጨምር፣ የራሱን ኪሎ ደግሞ ሲያመናምን ኖሯል፡፡ ራቅ አድርጎ የማያየው የአቶ መለስ ኢህአዴግ፤ ዶሮም ነብርም የሚያክለውን ጠላቱን እኩል ሲያሳድድ፣ እራሱን ግምት ውስጥ ከማስገባት አልፎ አይንህ ላፈር የሚያስብል ጥላቻን አትርፏል፡፡
ይህን ብልሃትና ብስለት አልቦ፣ በአመዛኙ ጫካ ቀመስ ኢህአዴግ፣ አጓጉል የፖለቲካ ጉዞ ሲያጤን የኖረው በለማ/ገዱ/ደመቀ/አብይ የሚመራው አዲሱ የለውጥ ሃይል፤ የጠላትን ስም በመቀየር አዋጭ ጉዞውን ጀምሯል፡፡ የአቶ መለስ/በረከት ኢህአዴግ፤ ጠላት የሚላቸውን አካላት፣ አዲሱ የለውጥ ሃይል ግን “ተፎካካሪ” በማለት በመሃከላቸው የነበረውን ውጥረት ስም በመቀየር ብቻ ማለዘብ ችለዋል፡፡ የስም ለውጡን በተግባር ለማስመስከር የፖለቲካ ምህዳሩን በመክፈት፣ ሚዲያዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል፡፡ ይህ ሁኔታ ለኢህአዴግ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ አንደኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስለ ድክመታቸው ኢህአዴግን ተወቃሽ የማድረግ አካሄዳቸውን ያስቀርና ለድክመታቸው ተጠያቂነቱ/ሃላፊነቱ የራሳቸው ብቻ ይሆናል። ይህ የተቃውሞ ፖለቲካውን መንደር ለስራ እንዲነሳ ያስገድደዋል፤ የእውነት ለሃገር የሚያስበውና ለስልጣን ብቻ የሚቋምጠው፣ በብቃት/በእውቀት የሚታገለውና ተቃራኒው፣ ምርትና ግርዱ ይለያል፡፡
እባብ ያየው ኦነግ ሼኔ
በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው የኢህአዴግ የለውጥ ቡድን ሆደ-ሰፊነት፣ መጋረጃቸውን ቀዶ ገበናቸውን  አደባባይ ካወጣባቸው ፓርቲዎች አንዱ፣ በምዕራብ ወለጋ እንቀሳቀሳለሁ የሚለው የኦነግ ሼኔ ቡድን ነው፡፡ በለውጡ ሃይል የበዛ ትዕግስት የተገለጠው የኦነግ ሼኔ አንዱ ገበና፣ እድሜውን በሚመጥን መንገድ በሃገሪቱ እያታዩ ያሉ ፖለቲካዊ ለውጦችን ተረድቶ፣ በዛው መንገድ ለመሄድ ያለመቻሉ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ኦነግ በሽግግሩ ወቅት በተራ ፖለቲካ ሻምፒዮኑ መለስ ዜናዊ መጥፎ በሆነ ሁኔታ የፖለቲካ ቁማር የተበላ ፓርቲ ነው፡፡
ይህ የፖለቲካ ቁማር ሽንፈት ምሬቱ፣ ለዳኦድ ኢብሳ ትናንት የተደረገ ያህል የሚያንገበግብ ቁጭት ውስጥ የከተታቸው ይመስላል፡፡ ዳኦድ ኢብሳ መለስ ብለው ሲያስቡት፣ የፖለቲካ ቁማሩ ሽንፈት የተጀመረውም የተጨረሰውም፣ ኦነግ ወታደሮቹን ካምፕ እንዲያስገባ የተስማማ ቀን እንደሆነ ገብቷቸዋል፡፡ ሊረዱ ያልቻሉት፤ ትናንት፣ ዛሬ አለመሆኑን፣ መለስ ዜናዊ የሚባል የተራ ፖለቲካ ቁማርተኛም፣ አሁን አለመኖሩን ነው፡፡ ዳኦድ፤ የሽግግር ዘመኑ ላይ ቆመው ከመቅረታቸው የተነሳ፣ ሌላው ቀርቶ አሁን በኢትዮጵያ መንበረ ስልጣን ላይ ያለው ኦሮሞ መራሹ ኦዴፓ መሆኑን እንኳን ያሰላሰሉት አይመስልም፡፡ ሌላው የዘነጉት ትልቅ ጉዳይ የአቶ መለስ ቁማር አሳዛኝ ተሸናፊ ያደረጋቸው፣ ወታደሮቻውን ካምፕ የማስገባት ያለማስገባት ጉዳይ በወቅቱ የሃገሪቱን ብሄራዊ ጦር ከማደራጀት ጋር የተያያዘ ግጥምጥሞሽ ዛሬ እንደሌለ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ህወሃት/ኢህአዴግ፤ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ለዘመናት የተገነባውን፣ በስብጥርነቱ ሃገራዊ መልክ የነበረውን የሃገር ብሄራዊ ጦር ሰራዊት፣ የደርግ ወታደር ነው በሚል ምክንያት  በትኗል፡፡ በተበተነው ጦር ምትክ ሃገራዊ ጦር ሰራዊት መገንባት፣ የሃገሪቱን የሽግግር መንግስት የሚመሩ ዋነኛ የፖለቲካ ሃይሎች ፋንታ ሆኖ ነበር፡፡ በሽግግር መንግስቱ አባልነት የተሰየሙ ቡድኖች  ብዙ ቢሆኑም፣ በጦር ታጅበው የመጡቱ ህወሃት/ኢህአዴግ እና ኦነግ ነበሩ፡፡ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ጦር ያነገበ በሚፈታት ሃገራችን፤ ህወሃት እና ኦነግ ባለ ጦር በመሆናቸው፣ ሁሉ በእጃቸው ሆኖ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ሃይሎች፤ የሃገሪቱን ብሄራዊ ጦር በማደራጀቱ ስራ ላይ ያላቸው ሚና፣ የሃገሪቱን መፃኢ ፖለቲካ ለመዘወር ላለመዘወር ዋናው የይለፍ ካርድ ነበር፡፡ ብልጣብልጡ አቶ መለስ፤ ኦነግን ያሸነፉትና ለቀጣዮቹ ረዥም ዘመናት የፖለቲካ ሜዳውን ብቻቸውን ሊፈነጩበት የሚችሉበትን መላ የመቱት፣ የህወሃት/ኢህአዴግ ጦር ላቅ ያለ ልምድና ብቃት ያለው በመሆኑ፣ የሃገሪቱ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት እንዲሆን፣ በአንፃሩ የኦነግ ወታደር ትጥቁን ፈቶ፣ ወደ ትንንሽ ወታደራዊ ካምፕ እንዲገባ ሲያደርጉ፣ ኦነግም በዚህ ሲስማማ ነው፡፡
አቶ መለስ ይህን ያደረጉት በቀጣዮቹ አመታት፣ ሃገሪቱን በሚያወሩለት ዲሞክራሲ ሳይሆን በጠመንጃ ጉልበት እንደሚመሯት አሳምረው ስለሚያውቁ ነው፡፡ ለዚሁ እንዲመች ወታደራዊ አመራሩን ከላይ እስከ  ታች በወንዛቸው ልጆች ሞሉት፡፡ ወታደሩ በለው ሲባል፣ ያገኘውን በጥይት የሚደፋው ከደደቢት ጀምሮ በተፈተለ ጥብቅ ገመድ፣ ከመለስ መንግስት ጋር ስለታሰረ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አስቀድሞ በአቶ መለስ አእምሮ የተፃፈው የኦነግ አገልግሎት ስላበቃ፣ የኦነግ አመራሮች በቦሌ እንዲሸኙ ተደረገ፡፡ ይህን አቶ መለስን ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰገነት ከፍታ፣ ኦነግን ወደ ስደት የዳረገ መበለጥ፣ የዳኦድ ኢብሳ ኦነግ በተለይ ሊረሳው አልቻለም፡፡ ሽግግር፣ ድርድር፣ ትጥቅ መፍታት የተባሉ ነገሮች በተከሰቱ ጊዜ ሁሉ፣ ይሄው ሽንፈቱ ውል እያለበት ሳይቸገር አልቀረም፡፡ ቁስሉ ያልዳነለት ሰው፣ ያየው ሰው ሁሉ አቁሳዩ ይመስለዋል፣ ማንም በተጠጋው ቁጥር ቁስሉ ይመረቅዛል፡፡ ኦነግ እየሆነ ያለው እንዲያ ነው፡፡ ስህተት ላለመድገም መጠንቀቄ ብሎት፣ ሞቱን የሚያፋጥን ትልቅ ስህተት ውስጥ እየወደቀ ያለው ለዚህ ነው፡፡
ያ ሌላ፣ ይሄ ሌላ
ከሃያ ሰባት አመት በፊት መለስ ዜናዊን ለመሰለ ሰው፣ ያሳየው ፖለቲካዊ  ገራምነቱ ያስበላው ኦነግ (ሼኔ)፤ ዛሬ በገራሙ ዶ/ር ዐቢይ/ አቶ ለማ መገርሳ ፊት፣ ያለ ወቅቱ የአቶ መለስን መሰሪነት ወርሶ፣ አጓጉል ብልጥ ለመሆን እየሞከረ ይገኛል፡፡ ብልጥነቴ ብሎ የተያያዘውን ጉዞ አንድ ብሎ የጀመረው፣ ኤርትራ ድረስ ሄዶ፣ ለተደራደራቸው የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን፣ ህወሃትን ለመውጋት፣ በምዕራብ ወለጋ የተሰማራውን ሸማቂ ቡድን ደብቆ ኤርትራ ባለው ጦሩ ብቻ ለመደራደር ሲሞክር ነው፡፡ ብረት አስቀምጬ በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብሎ ሲደራደር፣ ኤርትራ ያለውን ጦሩን ትጥቅ ለማስፈታት ተስማምቶ ነው፡፡
ሆኖም ኦነግ ከድሮም በወለጋ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ኖሯል፡፡ ይህ ሃይል ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ ለመጣል በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ራሱን በወታደራዊ ሃይልም ሆነ በፋይናንስ ለማሳደግ ችሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ (አማሮ፣ ቡርጅ፣ ጌዲኦ፣ ሰገን ዞኖች) አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሰላም የሚነሳው፣ በኦሮሚያ ባንክ የሚዘርፈው የኦነግ ሼኔ ቡድን፤ ይሄው በሃገር ቤት በተለይ ደግሞ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦነግ ሼኔ ቡድን አካል ነው፡፡ ኦነግ ሼኔ፤ ከእነ አቶ ለማ ጋር በኤርትራ ባደረገው የሰላም ስምምነት፣ በወለጋ ስለሚያንቀሳቅሰው ታጣቂ ቡድን ምንም እንዳላነሳ ነው የሚነገረው፡፡
ስለዚህ ድርድር ከአቶ ለማ መገርሳ መንግስት በኩል በግልፅ  ያልተነገረ መሆኑ፣ ነገሩን ይበልጥ እንቆቅልሽ ከማድረጉም በላይ ኦነግን ለብጥበጣ ሳይረዳው አልቀረም፡፡ የድርድሩ ሁኔታዎች ለህዝብ ግልፅ አለመደረጉ አቶ ለማን (በግሌ ለመጠርጠር ቢቸግረኝም) በኦነግ ወገንተኝነት ጭምር ያስጠረጠራቸው ጉዳይ ነበር፡፡ በእርግጥ ኦነግ (ሼኔ) ከመስመር ወጥቶ ሰው መግደል፣ ባንክ መዝረፍ የመሳሰሉ ተራ የውንብድና ተግባራት ላይ ጥልቅ ብሎ ከገባ በኋላ የአቶ ለማ ኦዴፓ፤ ከኦነግ ሼኔ ጋር ያደረገው ድርድር፣ ከሌሎች ብረት አንጋች ተቃዋሚዎች ጋር ከተደረገው የተለየ እንዳልሆነ ደጋግሞ እየተናገረ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ነገር የአቶ ለማ ኦዴፓ፤ ከኦነግ ጋር ሲደራደር ያደረገውንም ሆነ የፌደራል መንግስቱ ከታጠቁ ሃይሎች ሁሉ ጋር ሲደራደር ያደረገውን ግልፅነት የጎደለው አካሄድ ስህተትነት አይሸፍነውም፡፡
የታጠቁ ተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ሃገር ቤት ሲጋበዙ፣ የፌደራል መንግስቱ ጉዳዩን ለፓርላማ ውይይት አቅርቦ የድርድር ሁኔታዎችን ማስወሰን፣ እግረ-መንገዱንም ሁኔታዎቹን ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ነበረበት፡፡ ይህ ባለመሆኑ ሳቢያ  ነው በኦነግ ሼኔ በኩል ብዙ ችግሮች እየተከሰቱ ያሉት፡፡ ድርድሩ  ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ ኦብነግ እና አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ወደ ትክክለኛው መስመር ገብተው፣ የሃገር ማረጋጋቱን ስራ በማገዝ ላይ ሲሆኑ ኦነግ ሼኔ እንኳንስ አገር ሊያረጋጋ ቀርቶ መበጥበጡን በመተው ሊተባበር አልቻለም፡፡ ይህን የኦነግ ድርጊት ዝም ብሎ በማየት ላይ ያለው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት አዝማሚያ፤ ለሌላው ሰው ግራ አጋቢ ሲሆን ለኦነግ ሼኔ ደግሞ የሰፈሩ ሰዎች፣ የሃገሪቱን ስልጣን በመቆጣጠራቸው፣ ራሱን፣ የፈለገውን ለመሆን የተፈቀደለት፣ የንጉስ ልጅ አድርጎ  እንዲቆጥር ሳያደርገው አልቀረም፡፡
ኦነግ ሼኔ አሁን እየፈጸመ ያለውን ብጥበጣ የሚያደርገው፣ የሃገሪቱ መንግስት በህወኃት መኳንንት በሚዘወርበት ዘመን፣ እንደ ቂል ተሸናፊ ተቆጥሮ መናቁ ልክ እንዳልሆነ፣ ይልቅስ አስፈሪ፣ ጉልበታም፣ ጦረኛ መሆኑን ለማሳየትና ስም ለመቀየር ነው፡፡ ኦነግ ሼኔ የረሳው ነገር፣ የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ዘመን፤ ከተኳሽነት ይልቅ ታጋሽነት ጀግና የሚያስብልበት መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ኦነግ ሼኔ፤ ከዘመን ጋር የሚተላለፍ አሳዛኝ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም፡፡ ጦር ዋና በሆነበት ዘመን፣ ጦሩን ለመለስ ዜናዊ አስረክቦ፤ ዛሬ የሰላም ያለህ በሚባልበት ጊዜ፣ “ተኳሽ ነኝ” ማለት ከዘመን ጋር ክፉኛ መተላለፍ ነው፡፡
ማለባበስ ይቅር
የዳኦድ ኢብሳ ኦነግ (ሼኔ) በሰላም ለመታገል ተስማምቼ መጣሁ ብሎ፣ አዲስ አበባን ከረገጠበት ሰሞን ጀምሮ በችግር ፈጣሪነት ስሙ እየተነሳ ነው፡፡ ከቡራዩው አሰቃቂ፣ አስከፊና አሳዛኝ ግድያ እስከ ዛሬው የሰገን ግድያ ድረስ የኦነግ ስም ይነሳል፡፡ የኦነግ “መሳሪያዬን እንዳዘልኩ ለሰላማዊ ምርጫ ልወዳደር” እንደ ማለት የሚቃጣው ክርክር፣ ሰሚን ሁሉ ሲያስቅ የሰነበተ ነገር ነው፡፡ ዋል አደር ብሎ፣ በባንክ ዘረፋ ላይ እንደተሰማራም እየተዘገበ ይገኛል፡፡ “ኢሳት” እና “ዋዜማ” እንደዘገቡት፤ ኦነግ አስር ቀን ባልሞላ ጊዜ አስራ ሰባት ባንኮችን ዘርፏል፡፡
ሌላው የዳኦድ ኢብሳ ኦነግ አስቂኝ ነገር፣ “ከዛሬ ሃያ ምናምን አመት በፊት በሃገሪቱ ምርጫ ቦርድ  ባህር መዝገብ ውስጥ የታወቅኩ ፓርቲ ስለሆንኩ፣ ድጋሚ መመዝገብ አያስፈልገኝም” ያለው ነው፡፡ አንድ ፓርቲ በሃገሪቱ ምርጫዎች በተከታታይነት ካልተሳተፈ፣ እንደሌለ የሚቆጠር ሆኖ፣ እንደገና መመዝገብ እንዳለበት ማወቅ፣ የአንድ አዛውንት ዕድሜ ያህል በትግል ላይ ለኖረው ኦነግ ቀርቶ ለሌላውም ቀላል ነገር ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የዛሬ ሃያ ምናምን አመት የነበረው፤ በትንሹ ወደ አምስት ክፍልፋዮች ተቀይሯል፡፡ እንዲህ ግዙፍ ለውጥ በላዩ ላይ የተካሄደበት ኦነግ አንዱ ስንጣሪ ታዲያ፣ በድሮው ኦነግ ስም መመዝገቡ፣ ከእሩብ ምዕተ አመት በኋላ “ለብዙ ተሰነጣጥቄ ስመለስም የሚሰራ ነገር ነው” ብሎ ማሰቡ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡
የኦነግ መቅበጥበጥና የመንግስት የበዛ ትዕግስት፤ በተለይ ኦሮሞ ባልሆነው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ጥርጣሬ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በሃገሪቱ ዳርቻ ታጥቆ እየተንጎማለለ፣ ልቡ በል ባለው ሰዓት፣ የሚተኩሰውን ኦነግ ሼኔን እመራለሁ የሚሉትን አቶ ዳኦድ ኢብሳን አዲስ አበባ ላይ ቁጭ አድርጎ ማኖሩ፣ በተለይ ኦዴፓ መራሹን መንግስት ለትዝብትም ለጥርጣሬም ዳርጎታል፡፡ የሚብሰው ደግሞ ከሰሞኑ ፍሪዳ ተጥሎ ከኦነግ ሼኔ ጋር ኦዴፓ አደረገው የተባለው እርቅ ነገር ነው፡፡ አስታራቂዎቹ ኦነግ ባንክ ሲዘርፍ፣ እየተዟዟረ ሰው ሲገድል አንዳች ማለት ያልቻሉት አባገዳዎችና የኦሮሞ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ ሽማግሌዎቹ ኦነግ በብዙ ሲያጠፋ ዝም ብለው ከኦዴፓ ጋር እናስታርቅ ባሉበት መድረክ፤ ኦሮሞ ለኦሮሞ መጣላት እንደሌለበት ሲማፀኑ ተደምጠዋል፡፡ ኦነግ ሼኔ ከኦሮሚያ ክልል ወጥቶ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችን በጥይት መቁላቱ ለሸምጋዮቹ የሚሰጠውን ትርጉም ያወቀ የለም! ከሁሉም በላይ አሁን ኦነግ ሼኔ እያጠፋ ያለውን ጥፋት፣ አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ኦብነግ ቢያደርጉት ኖሮ፣ ከመንግስት ተመሳሳዩ ትዕግስት ይኖር ነበር? የሚለውን መጠየቅ እሻለሁ፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ያለ ጥፋታቸው እያፈሰ ያሰረው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት፤ በባለ ብዙ ጥፋቱ በኦነግ ላይ ተመሳሳዩን ለማድረግ ለምን እንደተቸገረ ግልፅ አይደለም፡፡   
አጥፊውን ኦነግ ሼኔን አርዶ ጋርዶ የታረቀው የአቶ ለማ ኦዴፓም ቢሆን፤ ከዚህ ቀደም ሲሸማገል የቆየና “አሁን ትዕግስቴ ስላለቀ የሃይል እርምጃ ወስጄ፣ የኦነግ ሼኔን የወለጋ አምባ እያፈራረስኩ ነው” ሲል የሰነበተ ነበር፡፡ “ትግስቴ ስላለቀ ወታደራዊ እርምጃ ጀምሬያለሁ” ያለው ኦዴፓ፤ በመሃል ደግሞ “ልታረቅ” ማለቱ ክፉ ነገር ባይሆንም፣ ለእርቅ ሲቀመጥ እርቁ የሚፈታው ነገር ምንድን ነው? የሚለውን ትልቅ ጥያቄ አለመመለሱ አጠያያቂ መሆኑ አይቀርም። እርቅ የሚጠላ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም ከኦነግ ጋር የሚደረግ እርቅ መልክ ሊያስይዛቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡
አንደኛው በምዕራብ ወለጋ ያሰማራቸው ታጣቂዎች በአነግ ሼኔ ሰላማዊ ትግል ላይ ያላቸው ሚና ምን እንደሆነ ቁርጥ አድርጎ ማሳወቅ አለበት፡፡ ከቁጥራቸው ጀምሮ፣ ትጥቅ አውርደው ካምፕ የሚገቡበትንም ሆነ ሌላ ሁኔታ ካለ፣ የዚህን የጊዜ ገደብ በውል ማሳወቅ አለበት፡፡ በተጨማሪም ከባንክ ዘረፈ የተባለው ገንዘብ መጠን ተገልፆ፣ በአስቸኳይ ይቅርታ ጠይቆ እንዲመልስ መደረግ አለበት። ካልሆነ ነገ ኦነግ ሼኔም፤ እንደ ህወሃት “ስታገል የቋጠርኩት የግል ጥሪቴ ነው” ብሎ ከሃገሪቱ ባንኮች በዘረፈው ገንዘብ ኦሮሟዊ ኢፈርት ልመስርት ሊል ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ መንግስት ሆኖ፣ ሃገር የሚመራ አካል፣ ባንክ ከዘረፈ ብድን ጋር በድፍኑ “ታርቄያለሁ” ማለቱ የሚያስተላልፈው መልዕክት፣ ሌብነትን ማውገዝ ሊሆን አይችልም። ይህ ነገር ተጨማሪ የባንክ ዘራፊዎችን ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የድሃን ሃገር ገንዘብ የወንበዴ ሲሳይ እያደረጉ፣ ከየምዕራብ ሃገሩ ምፅዋት ማምጣቱ  ምን ትርጉም አለው?   
ሁለተኛው ነገር ከኦነግ ጋር የተደረገው እርቅ፤ ፓርቲው ነውጠኝነቱን በሰላማዊነት ተክቶ፣ ከሃያ ሰባት አመት በኋላ በላዩ ላይ የተከሰተውን ለውጥ አጢኖ፣ በአዲስ መልክ  በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ “ማን ትጥቅ ፈቺ፣ ማን አስፈቺ ሊሆን ነው” ያለው ኦነግ ሼኔ፤ “እኔን ልመዝግብህ የሚል፣ ደፋር ምርጫ ቦርድ ማን ነው” እንደማይል እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ሌላውና ዋነኛው፣ የኦነግ ነገር፣ የኦሮሚያ ጉዳይ ብቻ ባለመሆኑ፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ተደራዳሪ፣ ኦዴፓ ብቻ መሆን የለበትም የሚለው ነው፡፡ ኦሮሞን ነፃ ለማውጣት እታገላለሁ የሚለው ኦነግ ሼኔ፤ ውጅግራውን አንግቦ የሚንቀሳቀሰው በኦሮሚያ ምድር ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ ኦሮሚያን በሚያጎራብቱ ክልሎች እየዘለቀ፣ የንፁሃንን ህይወት እያጠፋ ይገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት የአጎራባች ክልሎች መንግስታትም በኦነግ አደብ መግዛት ዙሪያ ሊነጋገሩ፣ እርቅ ካስፈለገም ሊታረቁ ይገባል፡፡ ኦነግ ከኦሮሚያ በተጨማሪ፣ የደቡብ ክልልንና ቤኒሻንጉል ክልሎችን እያመሰ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የፌደራል መንግስቱም በእርቅ ድርድሩ ውስጥ ሊወከል ያስፈልጋል ማለት ነው። ለእርቅ ሲቀመጡ እንዲህ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ሳይነካኩ፣ በየወሩ ፍሪዳ እያረዱ መታረቅ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ ለዚህ ምስክሩ  ኦነግ እና ኦዴፓ ታረቁ በተባለ ማግስት፣ ኦነግ ሼኔ፣ በደቡብ ክልል፣ ሰገን ዞን ዘልቆ፣ ሃገር ሰላም ብለው የሚጓዙ  አራት የኮሬና አማሮ  ወጣቶችን ከመኪና ላይ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን መቅጠፉ ነው፡፡   

Read 1483 times