Saturday, 02 February 2019 14:45

ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ በሽብር ታስረው የተፈቱ ዜጎችን ዛሬ እራት ይጋብዛሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

የአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ ዛሬ በካፒታል ሆቴል፣ በሽብር ምክንያት ታስረው ከተፈቱ ከ2 00 በላይ ዜጎች ጋር የውይይትና የእራት ፕሮግራም ማዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡
የፕሮግራሙ አስተባባሪ ከሆኑት አንዱ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ስለ ፕሮግራሙ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መረጃ፤ በሽብር ክስ ተፈርዶባቸው ታስረው የተፈቱ በከተማዋ የሚገኙ 2 መቶ ያህል ሰዎችና የህግ ጥብቅና ሲቆሙላቸው የነበሩ የህግ ባለሙያዎች በመርሃ ግብሩ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
መርሃ ግብሩንም ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረ/ፕ ነብዩ ባዬ ጋር በመሆን ይመሩታል ተብሏል፡፡
በሽብር ምክንያት ታስረው የተፈቱ ዜጎች በእስር ወቅት ለደረሰባቸው እንግልትና ጉዳት እውቅና ይሠጣል፤ በቀጣይም ከስነ ልቦናና ማህበራዊ ተግዳሮት የሚላቀቁበት መንገድ በመድረኩ ይመከርበታል ተብሏል፡፡
በእለቱም በሽብር ምክንያት ተከሰው የነበሩ ዜጎች መልሰው የሚቋቋሙበትንና የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲሁም መብትና ጥቅማቸውን በዘላቂነት የሚያስጠብቅላቸው ማህበር ይቋቋማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ዳንኤል አስረድተዋል፡፡

Read 7528 times