Saturday, 02 February 2019 14:41

በደቡብ ክልል ግጭትና ጥቃት የ14 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በደቡብ ክልል በተፈጠረ በግጭትና የታጠቁ ሃይሎች በሰነዘሩት ጥቃት በዚህ ሣምንት ብቻ የ14 ሰዎች ህይወት መቀጠፉ ታውቋል፡፡
በደቡብ ክልል ቴፒ ከተማ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በተቀሰቀሰ ግጭት የ10 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ የኦነግ ታጣቂዎች በአማሮ ወረዳ በፈፀሙት ጥቃት ደግሞ የአራት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በቴፒ ከተማ የተፈጠረው ግጭት ከዚህ ቀደም ተቀስቅሶ የ13 ሰዎች ህይወት ከቀጠፈው ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ጋር የተገናኘ መሆኑ ታውቋል፡፡
በእለቱ ከአቅራቢያው የማሻ ከተማ ወደ ቴፒ በሁለት አውቶብሶች የተጫኑ ግለሰቦች መግባታቸውን ተከትሎ ግጭቱ መቀስቀሱን ለአሜሪካ ድምፅ የገለፁት የከተማዋ ነዋሪዎች፤ ግጭቱ በተደጋጋሚ እያጋጠመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ግጭት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በከተማዋና አካባቢው የሚገኙ 60 ያህል ቤቶች መቃጠላቸውንና በርካቶች ከቤት መፈናቀላቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከአራት ወር በፊት በከተማዋ በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት 13 ሰዎች ተገድለው ከ6 ሺህ በላይ  ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፤ ማክሰኞ ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም በዚያው በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ የኦነግ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ በአካባቢው ሰሞኑን የተገደሉትን ሰዎች ጨምሮ በዘንድሮ አመት ብቻ ከ80 በላይ ሰዎች በተመሳሳይ ጥቃት መገደላቸውም ተገልጿል፡፡
የክልሉ መንግስት በበኩሉ፤ በተለይ በአማሮና በቡርጂ ወረዳ በታጣቂ ኃይሎች በተደጋጋሚ የሚፈፀሙት ጥቃተ ከአቅሙ በላይ እየሆነ መምጣቱን አስታውቋል፡፡  

Read 6640 times