Saturday, 02 February 2019 14:41

በድሬደዋ ተቃውሞና ግጭት ምክንያት አመራሮችን ጨምሮ ከ3 መቶ በላይ ሰዎች ታስረዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በጅግጅጋ ያለው አለመረጋጋት በነዋሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል


     በተቃውሞና ግጭት ውስጥ የሰነበተችው የድሬደዋ ከተማ ከማክሰኞ ጀምሮ ወደ መረጋጋት እየተመለሰች ሲሆን በጅግጅጋ በየጊዜው የሚያጋጥመው ግጭት በነዋሪዎች ላይ ስጋት መፍጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በድሬደዋ ከተማ ከጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና ግጭት ለማብረድ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ ሰራዊትና ከድሬደዋ ፖሊስ የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ጥረት ሲያደርግ መሰንበቱን ለአዲስ አድማስ የገለፁት ምንጮች፤ በሳምንቱ መጀመሪያም በግጭቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 10 ያህል የፀጥታ አባላትና የከተማዋ አመራሮችን ጨምሮ ከ300 በላይ ወጣቶች መታሰራቸውን ጠቁመዋል፡፡ “የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ” በሚል ካለፈው ረቡዕ ለ3 ቀናት የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ተጠርቶ እንደነበር የገለፁት ነዋሪዎች፤ አካባቢውን የተቆጣጠረው የምስራቅ እዝ የመከላከያ ሰራዊት የሚመራው ኮማንድ ፖስት አድማው እንዳይካሄድ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ በከተማዋ ለአድማ በታቀዱት ቀናት ከጥቂት የንግድ መደብሮች በቀር መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዋናነት አስተዳደር ስርአቱ ይቀየር የሚለው የተቃውሞ አጀንዳ ሲሆን አሁን በክልሉ ሁሉም መዋቅር በሚባል ደረጃ ስልጣንና የአመራር ቦታዎች የተያዙት 40 በመቶ በኦሮሞ፣ 40 በመቶ በሶማሌ እና 20 በመቶ በሌሎች ብሔሮች መሆኑን በመጥቀስ አሰራሩ ይቀየር የሚል ነው፡፡
ለዚህ የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞ በድሬደዋ ማስ ሚዲያ በኩል ምላሽ የሰጡት የከተማዋ አመራሮች በበኩላቸው፤ አሰራሩ በህግና ደንብ የታገዘ አይደለም፤ በቀጣይ ተገምግሞ ሊቀየር ይችላል ብለዋል። ለውጡ ፈፅሞ ድሬደዋ አልደረሰም የሚሉት የከተማዋ ወጣቶች፤ “ሳተናው የድሬደዋ ወጣቶች” በሚል አደረጃጀት ተቃውሟቸውን ሲያቀርቡና ላለፉት ጥቂት ወራት በተደጋጋሚ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጉዳዩ ላይ ሲወያዩ መቆየታቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶቹ ለሚያቀርቧቸው የለውጥ ጥያቄዎች ፈጣን ተግባራዊ ምላሽ አለመስጠቱ ሰሞኑን ለተፈጠረው ግጭትና ተቃውሞ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
በሌላ በኩል ማክሰኞ ጥር 21 ቀን የተከበረውን የአስተርዮ ማርያም የንግስ በዓል አክብረው ወደ ጅግጅጋ እየተመለሱ በነበሩ ምዕመናን ላይ ጥቃት መፈፀሙንና ሁለት ወጣቶች መገደላቸውን ተከትሎ ጅግጅጋ ከተማ በግጭት ስጋት ውስጥ መሰንበቷን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማው የፌደራል የጥበቃ አካላት ቢኖሩም ሰዎች በተለያየ መንገድ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ በመጥቀስ ሁኔታው በስጋት ውስጥ እንድንኖር አድርጎናል ብለዋል፡፡
ወጥቶ መግባት ስጋት እየሆነብን ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የፌደራል መንግስትና የክልሉ መንግስት በከተማው ያለውን የፀጥታ ስጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊቀርፉልን ይገባል ብለዋል፡፡  

Read 1058 times