Monday, 28 January 2019 00:00

የታደሰ “ጥንቅሹ” ግጥሞችና የነጠፈው ሕልም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 እኔ ጦርነት ታክቶኛል፣ ደም ብዙ ነው ያጎደፈ
በጦር ብዕር ተፅፎ ነው፣ ዘመኔ የተለከፈ!
ከገጣሚ ነቢይ መኮንን “ስውር ስፌት” የግጥም መድበል ላይ እነዚህን ስንኞች የመዘዝኩት ለዛሬ ገበታዬ ያስፈተፍቱኛል ብዬ ስላሰብኩ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ታሪኳ በደም የተነከረ፣ ሕይወቷ በክፋት የተዘለዘለ ስለሆነ ያንን ማስታወሻ እየፈተሽኩ ነው፡፡ ዘመኗ አንዱ አንዱን በመጣል፣ አንዱ ሌላውን ዘልፎና ነቅፎ፣ እዚያው ጉድጓድ ውስጥ እየተገኘ፣ እዚያው ባህር ውስጥ እየዋኘ መቀጠሉ የሀገሩ ጉዳይ ግድ ለሚለው ሰው ሁሉ ትካዜን ያጭራል፤ ስሜትን ይረብሻል፡፡ እነ ኮሌኔል መንግሥቱ፤ ንጉሱ ላይ የደፈደፉትን ወንጀል መልሰው ሲያቦኩት ያየ፣ ቀጣዩ ታጋይም ያንን አንጓጦና አላግጦ ጠመንጃ ይዞ ሲነሳ፣ ልቡ ለፍትህና ለርትዕ እያለቀሰች ነበር፡፡ ውሎ አድሮ ግን ያው አዙሪት አጥምዶ፣ እዚያው ጉድጓድ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ … እንደዚህ እያለ ሀገር በየተራ ደም ሲዘንባት ኖራለች፡፡ ዛሬም ሰማይዋ የደም ደመና አርግዟል ….
በዚህ የተንደረደርኩት ሰሞኑን ወደ ማረሚያ ቤት የገቡት ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ)፣ በመጽሐፍ ያሰባሰቧቸውን ግጥሞች እያሰላሰልኩ ነበር። ሀሳባቸውና ትግላቸው - በፍልሚያው ሜዳ፣ በወጣትነት ጨቅላ ልብ --- ምን ይመስል እንደነበር በምናቤ ሳልኩት፡፡ በዚህ የቅኝት ጽሁፍ፤“የትግል ሜዳ ግጥሞች” በሚል በ2006 ዓ.ም ከታተመው መድበላቸው፣ ጥቂት ግጥሞችን አብረን እናይ ዘንድ ወደድኩ፡፡  
ሕብረተሰብ ሚቆመው
ስርዐት ‘ሚታነፀው
በጥቂት ቅቡዐን … ምርጥ የሰው ዘሮች
እኛ ነን አዋቂ … ሁሉን ሰሪ ባዮች
መቸ ሆነና … ዛሬስ ተረድቶናል
ዛሬስ ተምረናል፡፡
ራሱ ህዝቡ ነው … ዕድሉን ‘ሚወስን
ሰፊው ህዝብ ብቻ ነው … ባለ ሙሉ ስልጣን
(“ሌላ አያውቅልንም”፤ 1977 ዓ.ም)
እውን ይህን ህልም አቶ ታደሰ ካሳና ጓዶቻቸው፣ ስልጣን ላይ ወጥተው አድርገውታል? … ከሚበላው ቆርሶ፣ ከድህነቱ ቀንሶ ትግላቸውን ያገዘውን ገበሬ፣ ከደርግ ተናጥቀው ህይወቱን ለውጠዋል?... በተለይ እነርሱ እንታገልለታለን ያሉትን የአማራውን ሕዝብ፣ ለሃያ ሰባት ዓመታት የገቡለትን ቃል ፈፅመዋል? … ይህንን ለህሊናቸው ልተወው፡፡ የስልጣን ወንበር ላይ ያለውን በሽታ፣ በፍርሃትና በስጋት ነው የማየው፡፡ ምን ዓይነት ሰይጣን፣ ምን ዓይነት ምትሃት እንዳለው “ውስጡን ለቄስ” ብያለሁ!
አቶ ታደሰ ለደርግ የፃፉት ግጥም፣ ወደ ራሳቸው  ተመልሶ የመጣ ይመስላል፡፡ ጥቂት አስገራሚ ስንኞችን እነሆ፡-
የገዢ መደቦች … ሲያታሉን የኖሩት
እነ “ጌቶቻችን” … በኛው የከበሩት
መርዶ ይድረሳቸው … የዛሬውን ይስሙት፡፡
ሲሰብኩን የኖሩት … ሴራቸው ከሸፈ
ጊዜያቸው አበቃ … ከሰመ ረገፈ፡፡
አሁን የብአዴን/ኢህዴን ሰዎች ባብዛኛው ረግፈዋል፡፡ ሴራቸውም ከሽፏል፡፡ ዝርዝር ፖለቲካ ውስጥ አንገባም፡፡ ይሁን እንጂ በሰፈሩት ቁና የተሰፈሩ ይመስላል፡፡ እንደኔ ቢሆን ያንን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለው፣ ወጣትነታቸውን እንደ ችቦ ያነደዱለትን ትግል በወጉ ተጠቅመው፣ የሕዝብን ነፃነትና ፍትህ ለማስፈን ተግተው፣ የተሻለ የእረፍትና የጥሩ ታሪክ ባለቤት ቢሆኑ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በእሳት ተበጥሮ አልፎ፣ የዕድሜን መጨረሻ ውርደት ውስጥ ማሳለፍ ግን አለመታደል ነው፡፡ ያንን የወጣትነት ሕልም አዝረክርኮ፣ ያንን ደም የረጩለትን መቅደስ አርክሶ ታሪክን መቋጨት፣ በእነርሱ እግር ቆሞ ላየ ሰው ያሳዝናል፡፡
የኢህዴን ታሪክ የሚያሳዝነኝ “ሶረኔ” የሚለውን የግጥም መድበላቸውን ባየሁ ቁጥር ነው፡፡ ትግላቸው ምን ያህል መራራ፣ ሕይወታቸው የቱን ያህል አሳዛኝ እንደነበር ይጠቁማል፡፡ ያ ሁሉ ትግል ግን ግቡ ሕዝብ ጫንቃ ላይ መፈናጠጥ ከሆነና መልሶ አምባገነንነት ላይ ከሰቀለ ፋይዳው ምን ነበር? ያሰኛል፡፡ ወይስ እነርሱ ነገሮችን የሚያዩበት ዓይን ይለይ ይሆን?
ባልንጀራቸው አቶ በረከት ስምዖን በቅርቡ ባሳተሙት “ትንሳኤ ዘ - ኢትዮጵያ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ገፅ 222 ላይ እንዲህ ብለዋል፡-
“ኢትዮጵያ የፈጣን ዕድገት ዓለም አቀፍ ተምሳሌት መሆን ጀምራለች፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም የመሰከረለት ባለ ፈጣን ለውጥ አገር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በእርግጥም ማርሹን ወደፊት ካስገባችበት ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም በኋላ ያለው ሂደት፣ በሁሉም መስኮችና አካባቢዎች፣ የፈጣን ለውጥ አገር መሆኗን በገሐድ ያሳየ ነው፡፡--”
እኛ ግን ከዚህ በተቃራኒው ያለውን ሕይወት እያየን ኖረናል፡፡ ለመብታችን ታግለው፣ መብት አሳጥተውናል፡፡ ለሞታችን ሞተው፣ መልሰው ገድለውናል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ የተለመደ አዙሪት መሆኑ ያሳዝነኛል፡፡ ፖለቲካው አንዳች የሚያሳስት ነገር ያለው የሚመስለኝም ለዚህ ነው፡፡
እስቲ በወጣቱ ገጣሚ አሌክስ አብርሃም ግጥም ጥቂት ልበል፡-
ኧረ ፀሐይ በዛ … ኧረ ፀሐይ በዛ
የመጣው ወር ሁሉ ፀሐይ እያዘለ፣
የተሾመው ሁሉ “ፀሐይ ነን” እያለ፣
የአሥራ ሶስት ወር የእግዜር ፀሐይ፣
የአሥራ ሶስት ወር የሰው ጀንበር
ባቃጠላት ምድጃ አገር፣
ምን ታምር ይሆናል፣ ፀሐይ ሆኖ እንደመፈጠር!?
የሀገራችን ጉዞ ዱላ ቅብብሉ፣ እሾህ በእሾህ እየሆነ መምጣቱ ያሳዝናል፡፡ ለህዝብ የቆሙ ልቦች አበባቸው ረግፎ፣ አሜኬላ ሲያበቅሉ በእጅጉ ይቆጫል፡፡ አንዳቸውም እንደጀመሩ መጨረስ አልቻሉም፡፡ ንጉሡም የመካሪዎቻቸውን ሀሳብ አልሰማ ብለው አሟሟታቸው፣ ዘግናኝ ሆኖ አልፏል፡፡ ታሪካቸውም ጠልሽቷል። ለዘመናዊነት የዘረጉት ድንኳን የጥቂቶች መፈንጫ፣ የግፍ መዘከሪያ ሆኗል፡፡ ደርግም ለሰፊው ሕዝብ እኩልነትና ፍትህ ብሎ የደበደበው ከበሮ ተቀድዶ፣ የብዙዎች ደም ማቆሪያ ሆኗል፡፡
ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ስመጣ፣ የአቶ ታደሰ ካሳ ግጥሞች አሁንም ይህንን ምስል ያደምቁልናል፡፡ ያለፉት ሁሉ ከታሪክ እንዳልተማሩ፣ ከጉዟቸው ተሞክሮ እንዳላገኙ ሹክ ይሉናል - አንብበን እንጠይቅ፡-
“ከታሪክ አይማሩም”
ግፍ ሲበዛ ጭቆና ሲከር ….
በደል ሲበራከት ኑሮ ሲመር …
አልጠግብ ባይነት ተጠናውቷቸው
የስልጣን መብል ጥሟቸው
ምቾት ደስታቸውን ለማስፋት
ሰርክ የሚያደርጉት ጥረት
የ‘ነርሱ መቀበሪያ
ጉድድጓድ መቆፈሪያ …
መጥፊያቸው መሆኑን በጭራሽ አያውቁም
ያ‘ደሃሪያን ፀባይ ሆኖ ከታሪክ አይማሩም፡፡
ሀብታቸው ሲጨምር ኑሮ ሲመቻቸው
የማያልፍ ደስታ ገነት ሲመስላቸው
እነሱ ጠግበው ሲያድሩ … ጦሙን የሚያድር
እነሱ ሲፈነጥዙ … በችግር የሚያር
ሌት ተቀን እየማሰነ
ለነርሱ ደስታ ምንጭ የሆነ
ሰፊው ህዝብ መች እንዳለቀሰ ይኖራል?
መች የነሱን በደል ዘወትር ይጫናል?
ዳሩ አደሃሪያን ከታሪክ አይማሩም
ያለፉትን አይተው ነግ በኔ አይሉም፡፡
ይህን የታደሰ ጥንቅሹን ግጥም ያጤነ ሰው፣ ለራሳቸው ለኢህአዴግ ሰዎች የተፃፈ ነው የሚመስለው፡፡ የያኔዋ የደርግ ኢትዮጵያ፣ በነርሱ ጊዜ መልሳ መምጣቷን ያሳያል፡፡
የስልጣን በሽታ፣ የምኞት ቀውስ ---- የሚያሰኘን ይህ ነው፡፡ ራሳቸው እነ አቶ ታደሰ ከታሪክ መች ተማሩ? ያንን ሁሉ እሳት ያለፉለትንና ህይወታቸውን የገበሩለትን ትግል መልሰው አጠለሹት፡፡ ይህ የታሪካችን አሳዛኝ ገፅታዎች አካል ነው፡፡ ቀን በሰጠን ጊዜ ለወገኖቻችን የሚጠቅም ስራ እንዳንሰራ ማን አዚም እንዳደረገብን አላውቅም፡፡ ቀጣዩ ጊዜያችንም ምን እንደሚያመጣ እርግጠኛ መሆን አንችልም! … የዘመነ ኢህአዴግ ዓይነት እንባ እናነባለን ብዬ ግን አልሰጋም፡፡ በተዓምር!!
አቶ ታደሰ በትግል ዘመናቸው ለትውልዳቸው ተቆርቋሪ፣ ለወገናቸው አዛኝ እንደነበሩ፣ የግጥሞቻቸው ድምፆች ያስተጋባሉ፡፡ ዛሬ እኛ እያለቀስን የነበረውን ለቅሶ እርሳቸውም በስንኞቻቸው አልቅሰውታል፡፡ እንዲህ እያሉ፡-
ወንጀልን ሳያውቁት
ክስን ሳይሰሙት
በጅምላ እስር የበትር ደዌ ያተረፉ
በኢ-ሰብዐዊ ምርመራ የተሰቃዩ የተገረፉ
እግራቸው እንደምንጭ ደም ያፈለቀ
አካላቸው በፖሊስ ጫማ ርግጫ የደቀቀ ስንት ናቸው?
እስቲ በጥሞና አስታውሺያቸው?
ደግሞስ የታረዱት
የትም የተጣሉት
ለካድሬዎች መሸለሚያ ለፈተና የተረሸኑት
“ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ነኝ” የሚባል ተፅፎ
በሞተ በድናቸው ላይ ተለጥፎ
ግንባር ግንባራቸውን ተመትተው የተጣሉ
እንደአጎዛ ቁርበት ከፀሐይ ተሰጥተው የዋሉ
እንደ ወጣት ሁሉ … አፍላ ሞቅታን
እንደ ተማሪ ሁሉ … ስራ መያዝን
እንደ ባለደሞዝ ሁሉ … ወላጅ መርዳትን
አይተው ሳይቀሙስት
ጀምረው ሳይጠግቡት
ሕይወታቸው ባጭር የተቀጨ
ታሪካቸው በደም የተቋጨ
ሰው በላው ሰው የበላቸው
የአፈር ቀለብ ያረጋቸው
አትፍሪ ንገሪኝ እኮ ስንት ናቸው?
ገጣሚው (የጥንቱ ታጋይ) ታደሰ ጥንቅሹ የጻፉትና የሚጠይቁት ሰቆጣን ነው፡፡ የተመረሩት የተሰቀቁት በወታደራዊው መንግስት ነው። ይሁን እንጂ ከአርባ ዓመታት በኋላ፣ ያው ግፍ ስለተደገመ፣ በ1997 ዓ.ም አዲስ አበባን “ተናገሪ” የሚሏት የዘመኑ እልፍ ገጣሚዎች ፈልተዋል፡፡ እንቦቃቅላዎች ከእናታቸው ጉያ በሞት ተነጥቀዋል፡፡ የመላው ኦሮሚያ እስር ቤት ታጭቋል፤ በየጎዳናው ወድቀዋል፡፡ ጎንደር አልቅሳለች፡፡ ሁሉም መራራ ጽዋውን ጠጥቷል፡፡
ይህ ሁሉ የስልጣን አዙሪት ከታሪክ ያለመማር በሽታ ነው፡፡ ወጣትነትን የሰዉለትን ዓላማ ቀልብሶ፣ እንባን በእንባ መተካት … በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ሕይወትን ለህዝብ ከሰጡ በኋላ መልሶ ነጥቆ፣ በፍርድ እጅ መውደቅ! አሳዛኝ የጦቢያችን የአዙሪት ታሪክ!! ይህ ታሪካችን የሚያበቃበት ቀን መች ይሆን? ይህቺን ብቅ ያለችውን ፀሐይ የሚያደበዝዝ ጭጋግ፣ ዕድሜው አጭር ይሁን! በሀገራችን ሰማይ ላይ የተበተኑት የተስፋ ክዋክብት ድምቀታቸው አድማሳትን ይሙላ!!

Read 1074 times