Monday, 28 January 2019 00:00

የቻይናን የህዝብ መዝሙር የማያከብሩ 6ሺህ ዶላርና 3 አመት እስር ይቀጣሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ህጻናት ተማሪዎች መዝሙሩን መማርና መዘመር ግዴታቸው ይሆናል


    ከፊል ልዑዋላዊቷና በቻይና ውስጥ የምትገኘው ሆንግ ኮንግ ለቻይና ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ተገቢውን ክብር የማይሰጡ ሰዎችን በ6 ሺህ ዶላር እና በሶስት አመት እስራት የሚቀጣና ህጻናት መዝሙሩን መማርና መዘመር እንዳለባቸው የሚያስገድድ አዲስ ህግ ልታወጣ መዘጋጀቷ ተዘግቧል፡፡
“ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ህግ” የሚል ስያሜ የተሰጠውና ባለፈው ረቡዕ ይፋ የተደረገው ይህ ህግ፣ የቻይናን ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር የሚያናንቅና ክብር የሚነሳ ድርጊት ሆን ብለውና በአደባባይ የሚፈጽሙ፤ በተጠቀሰው ገንዘብና እስራት እንደሚቀጡ የሚደነግግ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ህጉ መዝሙሩን የማያከብሩትን ከመቅጣት ባለፈ ሁሉም የአገሪቱ ህጻናት ተማሪዎች መዝሙሩን እንዲማሩና እንዲዘምሩ የሚያስገድድ ነው ብሏል፡፡
በሆንግ ኮንግ በእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮችና በሌሎች ዝግጅቶች ላይ የቻይና ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ሲዘመር የማጉረምረምና የማሾፍ ድርጊት በተለይ ሆንግ ኮንግ ከቻይና ተገንጥላ በመውጣት ራሷን የቻለች ሉአላዊት አገር መሆን አለባት የሚል ሃሳብ በሚያራምዱ ሰዎች ዘንድ እየተዘወተረ መምጣቱ ህጉን ለማውጣት ሰበብ እንደሆነ ነው ዘገባው የጠቆመው፡፡
በአመቱ መጨረሻ ላይ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀውንና ባለፈው ረቡዕ ለህግ መወሰኛ ምክር ቤት የቀረበውን ይህን ረቂቅ ህግ በሆንግ ኮንግ የሚገኙ የተለያዩ የዲሞክራሲና የነጻ ሃሳብ አራማጆች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን የሚጥስ ነው በሚል በአደባባይ እንደተቃወሙት የጠቆመው ዘገባው፣ የሆንግ ኮንግ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ግን ህጉን በከፍተኛ የአብላጫ ድምጽ ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

Read 1163 times